ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ሮሜ. 8:3፣ ዮሐ. 1:29፣ ራእ. 5:12፣ ዕብ. 7:1–28፣ 9:11–15፣ ዘሌዋ. 16:13፣ ዕብ. 9:20–23፡፡
የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፤ ይኸውም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ ጉልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ” (ፊልጵ. 2፡9-10)፡፡
የዕብራውያን መጽሐፍ በሰማያዊው መቅደስ ስላለው የሱስ ሲናገር እንዲህ
ይላል፡ “ይህም ስፍራ ኢየሱስ ስለ እኛ ቀድሞ የገባበት ነው፡፡ እርሱም
እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ሊቀ ካህናት ሆኖአል፡፡” (ዕብ.
6፡20)፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ፤ በተለይም አዲስ ኪዳን ክርስቶስ በዚህ ምድር ስለ እኛ
መሥዋዕት ሆኖ ሥራውን ካጠናቀቀ በኋላ በሰማያዊው መቅደስ እንደ ሊቀ
ካህናችን ሆኖ የሚጫወተውን ሚና በግልጽ ያስቀምጥልናል (ዕብ. 10፡12)፡፡
በዚህ ሣምንት ክርስቶስ በሰማያዊው መቅደስ እየሰጠ በሚገኘው
አገልግሎት ዙሪያ ፍተሻ እናደርጋለን፡፡ የእርሱ የማማለድ ሥራ ሕዝቡን
ለመጨረሻው ጊዜ በማዘጋጀቱ ረገድ ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡ ስለዚህ ይህ እጅግ
ጠቃሚ የሆነ ምክር ተሰጥቶናል፡ “የቤተ መቅደሱና የፍርድ ምርመራው ርዕሰ
ጉዳይ በእግዚአብሔር ሕዝቦች ዘንድ በግልጽ ሊስተዋል ይገባል፡፡
ሁሉም--ታላቁ ሊቀ ካህን ስለሚገኝበት ሁናቴ ለየራሳቸው ዕውቀት ሊኖራቸው
ያስፈልጋል፡፡ ያለበለዚያ በዚህ ጊዜ አንገብጋቢ የሆነውን እምነት ለመለማመድ
ወይም በእግዚአብሔር የታቀደላቸውን ስፍራ ለመሙላት የማይቻል
ይሆንባቸዋል፡፡”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 488.
ክርስቶስ በሰማያዊው ቤተ መቅደስ ለእኛ ምን እያደረገ ይገኛል? ይህን ጉዳይ
በተለይ በመጨረሻዎቹ ጊዜያቶች ማስተዋላችን በጣም አስፈላጊ የሆነው
ለምንድን ነው?
ታላቁን የክርስቶስ መሥዋዕትነት ማጥናታችን አማኞችን ለመጨረሻው ጊዜ
በማዘጋጀቱ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ ብዙውን ጊዜ ሰዎች ከፊታቸው
ወዳስቀመጡት ግብ የሚመለከቱ ሲሆን ይህ ደግሞ ትክክል ነው፡፡ ሆኖም
ከዚህ በተጨማሪ ከኋላቸውም ዕቅድ መኖሩን መገንዘባቸው መልካም ነው፡፡
ስለ ቀራኒዮ እንናገራለን፡፡ በዚህ ቦታ የሱስ ስለ እኛ ያደረገው ነገር
የማይቀለበስና የመጨረሻ ከመሆኑ በተጨማሪ ከፊት ለፊት ላለው ግብ
እርግጠኞች የሚያደርገን ነው፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሮሜ 8:3፣ 1ጢሞቴ. 1:17፣ 6:16፣ 1ቆሮ. 15:53፡፡
እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው ለምንድን ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
እግዚአብሔር ኃጢአትን በሥጋ ለመኮነን ክርስቶስን የኃጢአት መሥዋዕት
አድርጎ ላከው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ክርስቶስ በባህሪው መለኮት እንደመሆኑ
ሊሞት አይችልም፡፡ ስለዚህ ጌታ በትክክል በእኛ ምትክ መሞት ይችል ዘንድ
እንደ እኛ ሰው ሆኖ ሟች የሆነውን ማንነት ለራሱ ወሰደ፡፡
ምንም እንኳ እርሱ መለኮት፣ በባህሪውም አምላክ ቢሆንም “በሰው
አምሳል ተገኝቶ… እስከ ሞት፣ ያውም በመስቀል ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ
ሆነ” (ፊልጵ. 2፡6-8)፡፡ የሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ መለኮትነቱ ግን
በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ በሚታወቅ መልኩ ሕያው ነበር፡፡ የሱስ ለዘጠኝ
ወራት በማኅጸን ውስጥ በነበረባቸው ጊዜያቶችና በመቃብር በቆየባቸው ቀናት
መለኮትነቱ ሰው ሊያስተውል ከሚችለው በላይ በጸጥታና በተረጋጋ ሁናቴ
ውስጥ የነበረ ሲሆን፤ ይህን መለኮትነቱን በምድራዊ ሕይወቱና አገልግሎቱ
ፈጽሞ አልተጠቀመም ነበር፡፡
ጥቅሱን ያንብቡ፡ ሉቃ. 9፡22፡፡ ጥቅሱ በዕቅድና ሆን ተብሎ ገቢራዊ
ስለሆነው የክርስቶስ ሞት ምን ይነግረናል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ክርስቶስ የተወለደው ለኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ ለመሞት ነበር፡፡ ክርስቶስ
ስለ ሚደርስበት--ፌዝ፣ እንግልት፣ ግርፋት፣ ድብደባና ልብ የሚሠብር ሥቅላት
ሳያስብ የኖረበት ዘመን ሊኖር እንደማይችል መገመት አያዳግትም፡፡ ይህ ፈጽሞ
ያልታየና ሙሉ ለሙሉ ያልተስተዋለ አቻ የሌለው ፍቅር ነው፡፡
እኛ ሰብዓዊ ፍጡራን በእንዲህ ዓይነቱ ፍቅር እግሮች ስር ወድቀን
በእምነትና በመታዘዝ አምልኮ ከማቅረብ ውጪ ምን ማድረግ እንችላለን?
የመስቀሉ እውነታ ስለ ሰው መልካም ሥራ ከንቱነት ምን ይነግረናል?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 1፡29፣ ራእ. 5፡12፣ 13፡18፡፡ ጥቅሶቹ በጋራ የያዙት
አንድ ምስል ምንድን ነው? የደኅንነትን እቅድ እንድናስተውል በመርዳቱ ረገድ
የምስሉ አስፈላጊነት ምን ይመስላል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
መጥምቁ ዮሐንስ የሱስን “የእግዚአብሔር በግ” ብሎ ሲጠራው ስለ ቤተ
መቅደሱ የማያሻማ ማስረጃ እያቀረበ ነበር፡፡ እንዲያውም ይበልጥ ቀጥተኛ
በሆነ መንገድ የክርስቶስን ለኃጢአት መሞት እንደ ብቸኛው ለኃጢአት
መሥዋዕት የታረዱ የሁሉም በጎች (እና በዕብራውያን ሜዳዊ ሥርዓት
የማንኛውም እንስሳ) መሥዋዕት ፍጻሜ አድርጎ ሲያቀርብ ይስተዋላል፡፡
በእርግጥ አራቱ ወንጌሎች የቱንም ዓይነት ተጨማሪ ትምህርት ቢኖራቸውም
የመልእክታቸው አንኳር ታሪክ የሱስ እንደ እግዚአብሔር በግ የዓለምን
ኃጢአት በማስወገድ ስለነበረው ሚና ነው፡፡
ሆኖም የየሱስ ታሪክ እና እርሱ ለደኅንነታችን የሠራው ሥራ ከሞቱና
ከትንሣዔውም በኋላ እንኳ በወንጌል መልእክቶች ብቻ አይጠናቀቅም፡፡
ክርስቶስ የመሥዋዕት በግ ሆኖ ሥራውን ካከናወነ በኋላ በሰማያዊው
መቅደስ ሊቀ ካህን ሆኖ የሚሰጠውን አገልግሎት የዕብራውያን መጽሐፍ ገና
ከመጀመሪያው የሚዳስሰው ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡ ከመስቀሉ በኋላ በሚኖረው
ሚና ዙሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ስፍራ ከተጠቀሰበት አንስቶ (ዕብ. 1፡3)
ባሉት ቀጣይ የመጽሐፉ ምዕራፎች የሱስ የሚወሳው እንደ ሊቀ ካህን ነው፡፡
በሰማያዊው መቅደስ የሚሠራው ሥራ ሙሉ ዝርዝር በዕብ. 7፡1-28
ተብራርቶአል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዕብ. 7፡1-28፡፡ ሐዋርያው ስለ የሱስ ምን እያለ ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ምንም እንኳ እነዚህ ቁጥሮች በጣም ጥልቀት ያላቸውና እጅግ የበለጸጉ
ቢሆኑም፤ ከአሮን መስመር ምድራዊ የቤተ መቅደስ አገልግሎት ካህናት ይልቅ
የሱስ ክርስቶስ የተሻለ ክህነት አለው የሚል ፍሬ ነገር ይዘዋል፡፡ አሁን ግን
በምድራዊው ካህንና ቤተ መቅደስ ፋንታ በሰማያዊው መቅደስ የሚያገለግል
ሰማያዊ ሊቀ ካህን አለን፡፡ ስለዚህ ዐይኖቻችንን በየሱስ ላይ ስናሳርፍ እርሱን
እንደ ሰማያዊ መቅደስ ሊቀ ካህናችን መመልከት እንችላለን፡፡
የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዕብ. 7፡24-27፣ 8፡6፡፡ በጥቅሶቹ
የተሰጠን ታላቅ ተስፋ ምንድን ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ሌላ ካህን ፈጽሞ ሊኖረው የማይችለውን ብቃት የተላበሰው ክርስቶስ ሙሉ
ለሙሉ የማዳን ኃይል አለው፡፡ እርሱ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን ያለው
አምላክ ነው፡፡ ቋሚ የክህነት ሥልጣን በእጁ ነው፡፡ ክርስቶስ በሽተኛውን
ሲፈውስና ብቸኝነት ያጠቃውን ሲያጽናና ይስተዋልበት በነበረው ተመሳሳይ
ፍቅር ለዘመናት ለሕዝበ ክርስቲያኑ ሲማልድ ኖሮአል፡፡ ክርስቶስ እንደ
ማናችንም ሰው ቢሆንም ነገር ግን ያለ ኃጢአት ተወለደ--ያለ ኃጢአትም ኖረ፡፡
ኃጢአት የሌለበት እርሱ የመላውን የሰው ዘር ኃጢአት ድምር ተሸክሞ ሞተ፡፡
ስለዚህ ሰው እና አምላክ የሆነው ክርስቶስ ብቻ በሰማያዊው መቅደስ
ለኃጢአተኞች የመማለድ ሥራ መሥራት ይችላል፡፡
የክርስቶስ መሥዋዕትነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገቢራዊ መሆኑን እነዚህ
ጥቅሶች ያሳዩናል፡፡ ለአንድ ጊዜ ብቻ መሆን የነበረበት የእርሱ መሥዋዕትነት
ለእያንዳንዱ ሰብዓዊ ፍጡር ደኅንነት ለማምጣት በቂ ነበር፡፡
በመስቀል ላይ መሥዋዕት የሆነው ማን እንደሆነ ማስተዋል እስከ ቻልን
ድረስ እንደዚያ ዓይነቱ መሥዋዕትነት ለመላው ሰብዓዊ ፍጡር በቂ መሆን
አይችልም?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዕብ. 9፡11-15፡፡ ክርስቶስ ቀደም ሲል በሞቱ እሁን ደግሞ
በሰማያዊ አገልግሎቱ ምን አስገኘልን?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ክርስቶስ “የዘላለም ቤዛነት” አስገኘልን ሲል ዕብ. 9፡12 ይነግረናል፡፡ ቤዛነት
በማለት የተተረጎመው የግሪክ ቃል በተጨማሪ “መዋጀት”፣ “ዋጋ ከፍሎ
ማስለቀቅ”፣ “ንብረትንና መብትን ማውረስ”፣ “ማዳን” የሚል ፍቺ አለው፡፡
ተመሳሳይ ቃል በሉቃ. 1፡68 ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን ይኸውም ጌታ “መጥቶ
ሕዝቡን ተቤዥቶአልና” በማለት ዘካርያስ በተናገረ ጊዜ ነበር፡፡ ዋጋ ከፍሎ
ያስለቀቀንና ቤዛ የሆነን፣ የዓለምን ኃጢአት ለማስተሰረይ ብቁ የሆነው
ብቸኛው የመሥዋዕት በግ ክርስቶስ ነው--የሚለው አገላለጽ የክርስቶስን ደም
ይወክላል፡፡ ክርስቶስ ይህን ያስገኘው ለራሱ ሳይሆን ነገር ግን ለእኛ መሆኑ
የወንጌልን የምስራች ታላቅ ያደርገዋል፡፡ የክርስቶስን መሥዋዕትነት ለግላቸው
ለሚቀበሉ ሁሉ ይህ ፍቱን ነው፡፡
ክርስቶስ “የዘላለም ቤዛነት” አስገኘልን በሚለው ጽንሰ ሃሳብ ዙሪያ ተወያዩ፡፡
እርሱ ይህን ዘላማዊ ቤዛነት ካስገኘልን በኋላ ነበር ስለ እኛ ወደ ሚያከናውነው
ሰማያዊ የመቅደስ ሥራው የገባው፡፡ ክርስቶስ በሰማያዊው መቅደስ ለእኛ
እያደረገ ስላለው ነገር ይህ ምን ዓይነት ተስፋ ይሰጠናል?
ምንም እንኳ ኃጢአት በእግዚአብሔርና በሰብዓዊው ዘር መሃል አስፈሪ
መለያየት ቢፈጥርም፤ በክርስቶስ የመሥዋዕትነት ሞት አማካይነት እኛ እንደ
ሰብዓዊነታችን ወደ እግዚአብሔር መቅረብና ከእርሱ ጋር የነበረንን ግንኙነት
መቀጠል ቻልን--ኤፌ. 2፡18፣ 1ጴጥ. 3፡18፡፡
“እኛም የነፍስ መልሕቅ የሆነ ጽኑና አስተማማኝ ተስፋ አለን፤ ይህም ተስፋ
ከመጋረጃው በስተ ጀርባ ወዳለው ውስጠኛ መቅደስ ይገባል፡፡ ይህም ስፍራ
ኢየሱስ ስለ እኛ ቀድሞ የገባበት ነው፡፡ እርሱም እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት
ለዘላለም ሊቀ ካህናት ሆኖአል” (ዕብ. 6፡19-20)፡፡ በጥቅሶቹ መሰረት የሱስ
ለእኛ ያደረገው ምንድን ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
የክርስቶስ ሥራ ስለሚያካትተው ነገር ዕብ፣ 9፡24 ምን ይላል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
የሱስ ስለ እኛ በአብ ፊት ሊታይ ወደ ሰማያዊው መቅደስ ገባ፡፡ ይህ ማለት
የሱስ በሥርየት አገልግሎቱ “የዘላለም ቤዛነት ሊያስገኝ” ስለ እኛ በአብ ፊት
ቆሞአል፡፡
አዎ--የሱስን የግል አዳኛችን አድርገን ስንቀበል ኃጢአታችን ተሰርዞ፣ ይቅር
ተብለንና ነጽተን በእግዚአብሔር ፊት እንቆማለን፡፡ ነገር ግን ክርስቲያን ከሆንና
እነዚያ ሁሉ የአሸናፊነት ድንቅ ተስፋዎች ከተሰጡን በኋላም እንኳ አሁንም
አልፎ አልፎ ራሳችንን በኃጢአት ወድቆ እናገኘዋለን፡፡ እንዲህ ያለው ሁናቴ
ሲከሰት በሰማይ ያለው የሱስ ሊቀ ካህናችን ይማልድልናል፡፡ ተነሳሂውን
ኃጢአተኛ የሚወክለው እርሱ የእኛን መልካም ሥራ ሳይሆን (ምንም መልካም
ሥራ ስለሌለን) ይልቁንም የራሱን የጽድቅ ሥራ ይዞ ስለ እኛ በአብ ፊት
ይማልዳል፡፡ “ስለዚህ ስለ እነርሱ እየማለደ ሁል ጊዜ በሕይወት ስለሚኖር፣
በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው
ይችላል፡፡” (ዕብ. 7፡25)፡፡
ምንም እንኳ በየሱስ የአዲስ ሕይወት ባለቤቶች ብንሆንም፣ በራሳችን ውስጥ
አስደናቂ ለውጦች መመልከት ብንችልም፤ ቋሚና ጽናት ያለው ምኅረትና
ይቅርታ እንደሚያስፈልገው የማይገነዘብ ማን ነው? ክርስቶስን እንደ ሊቀ
ካህናታችን ማወቃችንና መገንዘባችን ለእኛ የከበረ የሆነው ለምንድን ነው?
ምድራዊው የዕብራውያኑ የቤተ መቅደስ አገልግሎት ክርስቶስ ሊቀ ካህናችን
ሆኖ የከፈተውና የገባበት የሰማያዊው ምሳሌ መሆኑን የዕብራውያን መጽሐፍ
ያስተምራል፡፡ ሁለቱን ክፍሎች እንዲሁም የመሥዋዕት እና ከኃጢአት
የሚነጻበትን ሥርዓት የያዘው ምድራዊው አገልግሎት ይካሄድ የነበረው
“ምሳሌና ጥላ በሆነችው ውስጥ ነው፤ ሙሴ ድንኳኒቱን ለመሥራት በተነሣ
ጊዜ፣ ‘በተራራው ላይ በተገለጠልህ ምሳሌ መሠረት ሁሉን ነገር እንድታደርግ
ተጠንቀቅ’ የሚል ትእዛዝ የተሰጠው በዚህ ምክንያት ነበር” (ዕብ. 8፡5)፡፡
ምድራዊው የቤተ መቅደስ አገልግሎት ሁለቱን ክፍሎች ማለትም ቅዱሱንና
ቅድስተ ቅዱሳኑን እንዳካተተ ሁሉ፤ የክርስቶስም ሰማያዊ መቅደስ አገልግሎት
በተመሳሳይ ሁለቱንም ክፍሎች ያካትታል፡፡ በዘሌዋ. ምዕ. 16 የቤተ መቅደሱን
መንጻት ያስከተለው የምድራዊው ቤተ መቅደስ የፍርድ ጽንሰ ሃሳብ ከሥርየት
ቀን ጋር የተመላከተ ነበር፡፡ ይህ ሊቀ ክህኑ ስለ ሕዝቡ የማንጻትና የስርየት
ሥራ ለመሥራት በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ሁለተኛው ክፍል ማለትም ወደ
ቅድስተ ቅዱሳኑ (ዘሌዋ. 16፡12-14) የሚገባበት ነው፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዕብ. 9፡20-23፡፡ ሊነጻና ሊታጠብ የሚያስፈልገው ነገር
ምንድን ነው? ይህ ለክርስቶስ አገልግሎት የስርየት ቀን ግልጽ ማጣቀሻ የሆነው
ለምንድን ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ራሱ ሰማያዊው መቅደስ ሳይቀር “መንጻት” ይኖርበታል ወይስ አይኖርበትም
የሚለው አስተሳሰብ በነገረ መለኮት ምሑራን ዘንድ ግርምትን የፈጠረ ነበር፡፡
ሆኖም ጉዳዩ ከስርየት ቀን ማጣቀሻ አኳያ ከተስተዋለ በኋላ ግን ችግሩ መወገድ
ችሎአል፡፡ ክርስቶስ በሰማያዊው መቅደስ የሚሠራው ሥራ ምድራዊው ሊቀ
ካህን በእስራኤላውያኑ መቅደስ በዓመት አንድ ጊዜ ያከናውን ለነበረው የስርየት
አገልግሎት እውነተኛ ማሳያ እንደ ነበር በዕብ. 9፡23 እንመለከታለን፡፡
ምድራዊው ሊቀ ካህናት ይሠራ የነበረው ቤተ መቅደሱን የማንጻት ሥራ
ክርስቶስ አንድ ቀን በሰማያዊው መቅደስ ለሚሠራው ሥራ አመላካች ነበር፡፡
ይህ የሰማያዊው ነገር የማንጻት ተግባር ክርስቶስ እንዳረገ ገቢራዊ ይሆናል ብሎ
ጥቅሱ አይነግረንም፡፡ ይልቁንም በ1844 ይኼኛው የአገልግሎት ምዕራፍ እንደ
ጀመረ ከዳንኤል መጽሐፍ ጥናት መመልከት እንችላለን፡፡ ስለዚህ
የመጨረሻዎቹን ቀናት እንደሚጋፈጡ ክርስቲያኖች የምንገኝባቸውን ብርቱ
ቀናት እያስተዋልን ቀደም ባሉት ጊዜያቶች ክርስቶስ በሰጠን ዋስትናዎች እና
አሁን በቅድስተ ቅዱሳን እያደረገልን ባለው ነገር ላይ ማረፍ ይኖርብናል፡፡
የመጀመሪያው መልአክ እንዲህ ሲል በታላቅ ድምፅ ዐወጀ፡ “እግዚአብሔርን
ፍሩ፤ ክብርንም ስጡት፤ ምክንያቱም የፍርዱ ሰዓት ደርሶአል” (ራእ. 14፡7)፡፡
የአምላካዊው ፍርድ በተጨባጭ መኖር መጨረሻው የተቃረበ መሆኑን
ያመላክታል፡፡ እውነታው በዕለት ከዕለት አኗኗራችን ላይ ተጽእኖ ሊኖረው
የሚችለው እንዴት ነው?
ክርስቶስ በምድር መሥዋዕት በመሆን በሰማይ ደግሞ በሊቀ
ካህናትነት የሚሰጠውን አገልግሎት ለመግለጥ የዕብራውያን መጽሐፍ
በምሳሌነት ወደ ምድራዊው መቅደስ ያመላክተናል፡፡ የእስራኤላውያን ቤተ
መቅደስ ሁሌም ቢሆን የወንጌል ተጨባጭ ማስተማሪያ መሣሪያ ነው፡፡
ሥርዓቱ መሥዋዕትን፣ ፍርድንና የኃጢአትን መጨረሻ የሚያካትተውን
የደኅንነት እቅድ ለአይሁዳውያን ለማስተማር ታልሞ የተዘጋጀ ነበር፡፡ ይህ
በእንዲህ እንዳለ ክርስቶስ በፍጻሜው ጊዜ በሰማያዊው መቅደስ የሚሠራውን
የመጨረሻ ሥራ ገጽታ አንባቢው ማስተዋል እንዲችል የሚረዱ ተጨማሪ
ብርሃኖችን የዳንኤል መጽሐፍ ያክልልናል፡፡ “ለመንጻት፣ ለፍርድ እና ለጽድቅ
አጽንኦት የሚሰጡት የዳንኤል የመጨረሻው ጊዜ ራእዮች በምድር ታሪክ
መዝጊያ ላይ ገቢራዊ ወደሚሆነው የስርየት ቀን ገጽታ ያመላክታሉ፡፡ የማንጻት
ሥራው ከሰማያዊው መቅደስ እና ከንጉሡ መሲህ ሊቀካህን ጋር በቀጥታ
የተቆራኘ ነው፡፡ ራእዮቹ አንባቢውን ከጊዜ አላባ ጋር በማስተዋወቅ መሲሁ
በእግዚአብሔር ማደሪያ ሆኖ የመጨረሻውን የማንጻት፣ የፍርድ እና የጽድቅ
ሥራውን በሚጀምርበት ጊዜ በደህንነት ታሪክ ውስጥ ያሉትን ተወስነው
የተቀመጡ ጊዜያቶች ለይቶ እንዲገነዘብ ያስችላሉ፡፡”—Handbook of Seventhday Adventist Theology (Hagerstown, Md.: Review and Herald® Publishing
Association, 2000), p. 394.
ይህን ከኤለን ኋይት መልእክት የተወሰደ ጽሑፍ ይመልከቱ፡ “በጥንት ዘመን መሥዋዕት በሚሆነው እንስሳ ላይ በእምነት ይተላለፍ የነበረው የሕዝቡ ኃጢአት በታረደው የእንስሳ ደም ምሳሌ ወደ ምድራዊው መቅደስ ይተላለፍ ነበር፡፡ በተመሳሳይ በአዲሱ ኪዳን የተነሳሂው (ንስሐ የገባው ሰው) ኃጢአት በእምነት በክርስቶስ ላይ ያርፍና ወደ ሰማያዊው መቅደስ ይተላለፋል፡፡ የተለመደው ምድራዊው የማንጻት ሥራ የሚከወነው በኃጢአት የተበከለውን በማስወገድ አንደ ነበር ሁሉ፤ ሰማያዊው የማንጻት ሥራ ተግባራዊ የሚሆነው ደግሞ በዚያ የተጻፈውን በማስወገድ ወይም በመደምሰስ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይህ መተግበር ከመቻሉ አስቀድሞ የእርሱ ስርየት ተጠቃሚ ለመሆን ማን ለኃጢአቱ ንስሐ እንደገባና በክርስቶስ ላይ እምነት እንዳለው ለማየት መጻሕፍት መመርመራቸው የግድ ይሆናል፡፡ ”—The Great Controversy, pp. 421, 422. ኤለን ኋይት “የእርሱ ስርየት ተጠቃሚ” ስለሆኑት የምትናገራቸው ሁለት ነገሮች ምንድን ናቸው? በተለይ ከመጨረሻው ጊዜ ፈተናዎች አኳያ የእነዚህን ነገሮች ምንነት በእጅጉ ማስተዋል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘሌዋ. 16፡15-16፡፡ የደም ትርጉም ምንድን ነው? ደም ምን ይወክል ነበር? በጥንት ዘመን ደም ለስርየት ቀን ሥርዓታዊ አገልግሎት በእጅጉ አንገብጋቢ የነበረው ለምንድን ነው? ዛሬስ ለእኛ ያለው አንደምታ ምን ይመስላል?