ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 14:8፣ 16:19፣ ኢሳ. 52:9፣ ራእ. 18:1-10፣ 16:12-16፣ 1ነገሥ. 18:1-40፣ 1ቆሮ. 15:1-2፡፡
የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡- “በግምባሯም ላይ እንዲህ የሚል የምስጢር ጽሑፍ ተጽፎ ነበር፡ ታላቂቱ ባቢሎን፣ የአመንዝሮችና የምድር ርኩሰቶች እናት፡፡” (ራእ. 17፡5)፡፡
እስካሁን ባለን ግንዛቤ የራእይ መጽሐፍ ከብሉይ ኪዳን በቀጥታ
በተወሰዱ ቋንቋዎችና ምስሎች የተሞላ መሆኑን ተመልክተናል፡፡
ለምሳሌ ባቢሎን የሚለው ስያሜ በራእይ መጽሐፍ ለስድስት ጊዜ ያህል
ቢቀርብም፤ ከመቶዎች ዓመታት ቀደም ብሎ ከዓለም ታሪክነት ስላለፈው ልዕለ
ኃያል የናቡከደነፆር መንግሥት ግን አይናገርም፡፡ ይልቁንም ዮሐንስ እውነትን
ለማሳየት ሲል የብሉይ ኪዳን ተምሳሌታዊ አገላለጾችን ሲጠቀም ይታያል፡፡
የእግዚአብሔርን ሕዝቦች የጨቆነው ግዙፍ ፖለቲካዊና ኃይማኖታዊ ኃይል
የነበረው ባቢሎን--በመጨረሻዎቹም ጊዜያቶች ተመሳሳይ ሁናቴ በእግዚአብሔር
ሕዝቦች ላይ ለማድረስ ያስባል፡፡
በራእይ መጽሐፍ ብቻ የተጠቀሰ አንድ ቃል ያለ ሲሆን ይኸውም
አርማጌዶን ነው፡፡ የዚህ ቃል መሰረት የዕብራይስጥ ሀረግ ሲሆን የጥንቷን
እስራኤል አንድ ስፍራ በማያመላክት መልኩ “የጌዶ ተራራ” የሚል ፍቺ አለው፡፡
በዓለም ፍጻሜ ሲቃረብ በሜጌዶ ታላቅ ውጊያ ይካሄዳል ብለው ብዙዎች
ያምናሉ፡፡
በዚህ ሣምንት ጥናታችን በባቢሎንና አርማጌዶን ላይ ምልከታ በማድረግ
መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ምስሎች በመስጠት የሚናገረንን ለመማር
እንሞክራለን፡፡
የሚከተሉትን በባቢሎን ዙሪያ የተሰጡ ስድስት ማመሳከሪያዎች ይመልከቱ፡፡
ራእ. 14:8፣ 16:19፣ 17:5፣ 18:2፣ 10፣ 21፡፡ በብሉይ ኪዳን የቀረበውን የባቢሎን
ታሪክ በአእምሮአችን እንደያዝን--ከመጨረሻዎቹ ጊዜያቶች ዐውድ ጥቅሶቹ ስለ
ባቢሎን ምን ያስተምሩናል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
መጽሐፍ ቅዱስ የሁለት ከተሞች ወግ ነው የሚል አባባል አለ--የኢየሩሳሌምና
የባቢሎን፡፡ ኢየሩሳሌም የእግዚአብሔርን ከተማና እርሱ በመላው የመጽሐፍ
ቅዱስ ገጾች ለሕዝቡ የገባውን ኪዳን ስትወክል (መዝ. 102፡21፣ ኢሳ. 52፡9፣
65፡19፣ ራእ. 3፡12) ባቢሎን ደግሞ--ጭቆና፣ ሁከት፣ የሐሰት ኃይማኖት እና
በእግዚአብሔር ላይ የሚደረግን አመጻ ትወክላለች፡፡
ለምሳሌ ስለ ባቤል ግንብ ያስቡ (ዘፍ. 11፡9)፡፡ “ባቤል” የተሰኘው የዕብራይስጥ
ቃል “ባቢሎን” ከተሰኘው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ጴጥሮስ “ባቢሎን” ካለችው ቤተ
ክርስቲያን ሰላምታ መላኩ በ1ጴጥ. 5፡13 ተጠቅሶአል፡፡ ይህ ማለት የዛሬዋ ኢራቅ
ከምትገኝበት የጥንቷ ባቢሎን ፍርስራሽ ሳይሆን ብዙም ሳይቆይ የቤተ ክርስቲያን
ጨቋኝ ከምትሆነው ከራሷ ከሮም ነው፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 14፡8፣ 18፡3፡፡ ባቢሎን በዓለምና በእግዚአብሔር
ሕዝቦች ላይ ስላላት ክፉ ተጽእኖ ምን ይገልጻሉ?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
በራእይ መጽሐፍ እንደ ተገለጠው ባቢሎንን የሚወክለው ኃይል ክፉኛ
መበላሸቱና ይኸው ብልሹ ተጽእኖ ወይም እርክስና በተለያየ መጠንና ደረጃ
በመላው ዓለም መሰራጨቱ አያጠያይቅም፡፡ “የዝሙቷን ቁጣ ወይን ጠጅ” (ራእ.
14፡8) የሚለው ሀረግ ሐሰተኛ ኃይማኖታዊ አስተምህሮን፣ የረከሰ መንፈሳዊ
ሥርዓትንና እነዚህን ተከትሎ የሚመጣውን የመጨረሻ ውጤት የሚያሳይ ግልጽ
ማስረጃ ነው፡፡ ባቢሎን ወደ “ሕዝቦች ሁሉ” (ራእ. 18፡3) ለተሰራጨው የክፉው
ኃይል ጉልበት ናት፡፡ ሰለዚህ እያንዳንዱ ሰው ከዚህ እርክስና ለመጠበቅ ትኩረት
ሊያደርግ ይገባል፡፡
ብልሹ አሠራር፣ የተመሳቀለ ሁኔታና ጭቆና ወደ ሰፈነባት የዛሬዋ ዓለም
ለመመልከት ይሞክሩ፡፡ በየሱስ እና በቃሉ መልሕቅ መጠበቅ እንደሚያስፈልገን
አስመልክቶ ይህ ምን ሊያስተምረን ይገባል?
ባቢሎን በዓለም ዙሪያ ያላት ብልሹ ተጽእኖ የቱንም ያህል ግዙፍ ቢሆንም ነገር
ግን አንድ ቀን እንደሚያበቃላት የራእይ መጽሐፍ ይናገራል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 18፡1-10፡፡ ስለ “ታላቂቱ ባቢሎን” ምን ይነግሩናል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
በባቢሎን ውድቀት ዙሪያ የተነገረው የሁለተኛው መልአክ (ራእ. 14፡8)
መልእክት በድጋሚ በራእ. 18፡2 ቀርቦአል፡፡ ይህ ደግሞ ይህ አካል ምን ያህል
ብልሹ ሁናቴ ውስጥ እንደ ገባ ያሳያል፡፡
“ጌታ ዳግም ከመገለጡ አስቀድሞ ሰይጣን ‘በሐሰተኛ ታምራት
በምልክቶችና በድንቅ ነገሮች ሁሉ’ ይሠራል፡፡ ‘እንዲሁም ይድኑ ዘንድ እውነትን
ባለ መውደድ የሚጠፉትን ሰዎች በሚያታልል በተለያየ የክፋት ሥራ ይመጣል፡፡
በዚህም ምክንያት ‘በሐሰት እንዲያምኑ’ ለስሕተት አሠራር ይተዋሉ፡፡ (2ተሰ.
2፡9-11)፡፡ ይህ ሁናቴ ክንውን ሳያገኝና ቤተ ክርስቲያን ከዓለም ጋር ያላት
ሕብረት በመላው የክርስትና ተቋማት ገቢራዊ ሳይሆን የባቢሎን ውድቀት
የተሟላ አይሆንም፡፡ ለውጡ እየጨመረ የሚሄድ ዓይነት እንደ መሆኑ፤ ራእ.
14፡8 ፍጹም ክንዋኔ የሚያገኘው ገና ወደፊት ነው፡፡”—Ellen G. White, The
Great Controversy, pp. 389, 390.
የተጠቀሰው “ፍጹም ክንዋኔ” አሁን ደርሶ ይሁን ወይም አይሁን
የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ እኛ የምናውቀው ነገር ቢኖር በእነዚህ
ጥቅሶች መሰረት መንፈሳዊቷ ባቢሎን ለታላቁ ክፋቷ አንድ ቀን የእግዚአብሔርን
ፍርድ የምትቀበል መሆኑን ነው፡፡ “ኃጢአቷ እስከ ሰማይ ድረስ ተከምሮአልና፤
እግዚአብሔርም ዐመጻዋን አስታውሶአል” (ራእ. 18፡5)፡፡ እንደ ሌሎቹ ሁሉ
ይሄኛውም አገላለጽ ብሉይ ኪዳን በጥንታዊቷ ባቢሎን ዙሪያ ጥቅም ላይ
ያዋለውን አገላለጽ በማንጸባረቅ (ኤር. 51፡9) የፍርድ ጊዜን አይቀሬነት አንደምታ
ያሳያል፡፡
ሊመጣ ያለው ፍርድ ሊያስገርመን አይገባም፡፡ ደግሞስ የጥንቷ ባቢሎን
ፍርድ ተቀብላ የለ--(ዳን. 5)? ባቢሎንን ጨምሮ ሁሉም ሰው ለሠራው ምላሽ
መስጠት እንደሚኖርበት መጽሐፍ ቅዱስ በጣም ግልጽ አድርጎ ይናገራል፡፡
ሆኖም ክርስቲያኖች በዚያ የፍርድ ቀን ስለ እኛ የሚቆም አማላጅ እንዳለን
ማወቃችን እንዴት አጽናኝ ነው! (1ዮሐ. 2፡1፣ ዳን. 7፡22)፡፡ ያለበለዚያ የዕኛም
ዕጣ ፈንታ ከባቢሎን የተሻለ መሆን ባልቻለ ነበር፡፡
አሁን ቅጣት ያላገኙ የሚመስሉ አያሌ የፍትህ መጓደሎችና እርኩሰቶች--አንድ
ቀን የመጨረሻውን ዋጋ ከእግዚአብሔር እንደሚያገኙ በተሰጠው ተስፋ
መጽናናት የሚያገኙት እንዴት ነው?
ምንም እንኳ አያሌ ክርስቲያኖችን ጨምሮ ብዙዎች በራእይ መጽሐፍ ላይ
ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ ቢሆንም ነገር ግን አንዲት ቃል በስፋት ትታወቃለች፡
አርማጌዶን (ራእ. 16፡16)፡፡ ቃሉ በመንፈሳዊው ብቻ ሳይሆን በዓለማዊውም
ባህል ምድር በመጨረሻው ዕጣ ፈንታዋ የምታደርገውን መፍጨርጨር
ለማሳየት ጥቅም ላይ ውሎአል፡፡ ሆሊውድ አርማጌዶን የሚል ስያሜ የሰጠውን
ፊልም ሠርቶ ለተመልካች አቅርቦ ነበር፡፡ ፊልሙ ምድርን ሊያጠፋ ከሕዋው
ውስጥ ስለ ተምዘገዘገ ሰማያዊ ግዑዝ አካል ይተርካል፡፡ ምድር ፍጻሜ ሊኖራት
የመቻሉ ጽንሰ ሃሳብ በተወሰነ መልኩም ቢሆን በዓለማዊ ሰዎች አእምሮ
ውስጥም አለ፡፡
ከራእይ መጽሐፍ ጋር ትውውቅ ያላቸው በጣም ብዙ ክርስቲያኖች
አርማጌዶን የዓለም ታሪክ ፍጻሜ በተቃረበበት ወቅት የአሁኗ እስራኤል የጦር
ሠራዊት በመካከለኛው ምስራቅ የሚያደርገው ውጊያ እንደሆነ ያምናሉ፡፡
አንደኛው አባባል ከእስያ የሚነሱ 200 ሚሊዮን የሚደርሱ ተዋጊዎች ሰሜን
እስራኤልን ያጥለቀልቃሉ ሲል፤ ሌላኛው ደግሞ በዓለም የተለያዩ ክፍሎች
የሚነሱ የፖለቲካና ወታደራዊ ግጭቶች የመጨረሻውን የአርማጌዶን ፍልሚያ
የሚያደርጉት በሜጌዶን አካባቢ ነው ይላሉ፡፡
ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠን ትዕይንት ከዚህ ሙሉ በሙሉ የተለየ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ አርማጌዶንን በአገራት መካከል እንደሚነሳ ውዝግብ ሳይሆን
እንደ መጨረሻው የዩኒቨርስ አቀፍ ተቃርኖ ጡዘት ይስልልናል፡፡ ምንም እንኳ
አያሌ ኤኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የትዕይንቱ አካል ሆነው ብቅ ቢሉም፤
ፍልሚያው ኃይማኖታዊ እንጂ ኤኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ አይደለም፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 16፡12-16፡፡ እነዚህን ጥቅሶች ብቻ መሰረት በማድረግ
ስለ አርማጌዶን እንዴት መማር እንችላለን?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
በቅድሚያ ጥቅም ላይ የዋሉት ቃላት ምን ያህል ተምሳሌታዊ ባህሪ
እንዳላቸው ልብ ይበሉ፡፡ ከዘንዶው አፍ የሚወጡ እንቁራሪት መሰል መንፈሶች፣
ከሐሰተኛው ነቢይ አፍ፣ ከአውሬው አፍ…፡፡ “የአጋንንት መናፍስት” (ራእ.
16፡14) ሁሉን ከሚችል አምላክ ጋር ለውጊያ እንደሚወጡ መወሳቱ፤ የታላቁን
ተቃርኖ ትዕይንት ያሳየናል፡፡ በክርስቶስና በሰይጣን ኃይላት መካከል ያለው
ዓለማቀፋዊ ውዝግብ--አርማጌዶን በየትኛውም ዓይነት መንገድ ቢሆን ግልጽ
ሆኖ ይወጣል፡፡ ውጊያው ሜጊዶን አካባቢ የሚደረግ ተራ ውዝግብ አለመሆኑን
ልብ ይሏል፡፡
ጥቅሱን ያንብቡ፡ ራእ. 16፡15፡፡ በእነዚህ ትዕይንቶች መሃል የሱስ ስለ ዳግም
ምጽአቱና በጽድቁ ስለ መሸፈናችን አስፈላጊነት የሚሰጠን የማበረታቻ ቃል
በእጅጉ ማራኪ ነው፡፡ ይህ የምንገኝበትን ውጊያ መንፈሳዊ ተፈጥሮ ማስተዋል
እንድንችል እንዴት ይረዳናል?
ለመሆኑ ይህ የአርማጌዶን ታላቅ ጦርነት ምንድን ነው? በመጀመሪያ ከስያሜው
ስንነሳ “የሜጌዶ ተራራ” ለማለት የተፈለገ ይመስላል፡፡ ሆኖም ባካባቢው
ቀርሜሎስ ተራራ እንጂ ሜጌዶን በሚል ስያሜ የሚታወቅ ተራራ የለም፡፡
ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን የሜጌዶን ተራራ ለቀርሜሎስ ተራራ እንደ
ማመሳከሪያ ይመለከቱታል፡፡
ይበልጥ ወደ ዋናው ሃሳብ ስንመጣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የኤልያስንና
የበዓል ሐሰተኛ ነቢያትን የቀርሜሎስ ተራራ ታሪክ--በራእ. 13 ያለውን ትዕይንት
እንደሚገልጥ ተምሳሌት አድርገው ይመለከቱታል፡፡
በትናንቱ ጥናታችን እንደተመለከትነው ራእ. 16፡13 ስለ ዘንዶው፣ ስለ
አውሬው እና ሐሰተኛው ነቢይ የሚሰጠው ማስረጃ መልሶ ወደ ራእ. 13--
ማለትም በዘጠነኛው ትምህርት ወደ ተመለከትነው አስመሳዩ ስላሴ
ይወስደናል፡፡
ሁለተኛው አውሬ ከተፈጥሮ ውጪ የሆኑ ድርጊቶችን በመፈጸም “እሳት
ከሰማይ ወደ ምድር እስኪያወርድ ድረስ ታላላቅ ምልክቶችን” (ራእ13፡13)
ሲያደርግ፤ የራእ. 13 ክስተቶች በቁ. 13 እና 14 ወደ ከፍተኛ ደረጃ ይደርሳሉ፡፡
በዚህ ወቅት ክስተቶቹ በሰይጣንና በእግዚአብሔር ይኸውም እውነተኛውን
አምላክ በሚያመልኩና “ለአውሬው ምስል” (ራእ. 13፡14) በሚሰግዱ መሃል
ወደሚደረግ ቀጥተኛ ግጥሚያ ይሸጋገራሉ፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ነገሥ. 18፡1-18፡፡ በራእይ መጽሐፍ እንደ ታየው--ታሪኩ
በመጨረሻዎቹ ጊዜያቶች ይፋ የሚሆኑ አንዳንድ ክስተቶችን የሚያንጸባርቀው
እንዴት ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
የታላቁን ውዝግብ ትዕይንት በውልብታም ቢሆን ከብዙ አቅጣጫዎች በዚህ
ስፍራ እንመለከታለን፡፡ ኤልያስ፡ ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ሕግ በመተዉ የሐሰት
አማልክትን እያመለከ ይገኛል--በማለት ጉዳዩን ግልጽ አድርጎ ያቀርበዋል፡፡
ክፉው በዘመናት ራሱን ማለቂያ በሌላቸው ቅርጾችና መንገዶች ሲገልጽ
ቢኖርም፤ ሁሌም ቢሆን ጉዳዩ ይኸው አይደል? “ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንና
የውሃ ምንጮችን ለፈጠረው” (ራእ. 14፡7) እንሰግዳለን ወይም ሌላ የሆነ ነገር
እናመልካለን፡፡ ከራእ. 13 እና በዚያ ከተገለጡ ትዕይንቶች አንጻር ስንመለከት
ሰዎች ጌታን በማምለክ ፋንታ ለአውሬውና ለምስሉ ይሰግዳሉ፡፡ መሃል ሰፋሪ
የሚባል ቡድን የለም፡፡ ማንኛውም ሰው በእግዚአብሔር ወይም በሰይጣን በኩል
ይሰለፋል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ነገሥ. 18፡18-40፡፡ ምን ተከተሰተ? ታሪኩ ያለቀበት መንገድ
ምን ይመስላል? በመጨረሻ ላይ ታላቁ ውዝግብ ከፍ ያለ ደረጃ ከሚደርስበትና
ከግዙፉ ትዕይንት አኳያ--ወደ ፊት የሚሆነውን እንዴት ያንጸባርቃል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
በቀርሜሎስ ተራራ ላይ የተደረገው ውጊያ የእግዚአብሔር ነቢይ በነበረው
ኤልያስ እና በ450 የበኣል ካህናት መካከል ተካሄደ፡፡ (የክፉው ኃይል ምን ያህል
ከበጎው ይልቅ በቁጥር የበዛ እንደሆነ ልብ ይሏል)፡፡ ትዕይንቱ ማንኛው
እውነተኛ አምላክ እንደሆነ የሚያሳይ ነበር፡፡
ሰማይና ምድርን የፈጠረው እግዚአብሔር ወይስ ዓለምን ለማሳት የሚመኘውና
(ራእ. 12፡9) “ዘንዶው” በሌላ መንገድ የተገለጠበት በኣል?
እሳት ከሰማይ ወርዶ ለመሥዋዕት ያቀረቡትን ወይፈን እንዲበላው የበኣል
ነቢያት ጸሎት አደረጉ፡፡ ከጠኋት አንስተው ቀኑን ሙሉ ላደረጉት ልመና
“‘ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጩኹ እንጂ! ተኝቶም ከሆነ ቀስቅሱት’” (1ነገሥ.
18፡27) እያለ ኤልያስ አፌዘባቸው፡፡ ነቢያቱ በኃይለኛ ስሜት ውስጥ ተውጠው
ከአካላቸው ደም እስኪፈስ ገላቸውን በሠይፍና በጩቤ ያቆስሉ ነበር፡፡ ሆኖም
ሰውነታቸው በመዛሉና በመድከሙ ያለ አንዳች ውጤት አመሻሽ ላይ አቆሙ፡፡
የኤልያስ መሥዋዕት ሦስት ጊዜ ውሃ እንዲፈስበት በመደረጉ ውሃው
ጉድጓዱን ሞላው፡፡ ኤልያስ ለእግዚአብሔር ቀለል ያለ ጸሎት አቀረበ፡፡ ከዚያም
እሳት ወርዶ የመሥዋዕቱን እንጨት፣ ድንጋይና ዐፈር ጨምሮ ማንኛውንም ነገር
በቅጽበት በላው፡፡ የእውነተኛው አምላክ ኃይል ከበኣል ጋር ሲነጻጸር እውነተኛና
የማይሳሳት ሆኖ ተገኘ፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡና ከሐሰተኞቹ የበኣል ነቢያት ጋር ያስተያዩአቸው፡ ራእ. 16፡13፣
19፡20-21፡፡ እዚህ ላይ ምን ይመለከታሉ?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ምንም እንኳ ለጊዜው ስለ አርማጌዶን የምናውቃቸው ነገሮች ውሱን ሊሆኑ
ቢችሉም ነገር ግን ውጤቱን እናውቃለን፡--በእግዚአብሔር ጠላቶች ላይ
የሚደርሰውን ጥፋት እና የእግዚአብሔርንና የቅዱሳኑን እውነተኝነት፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ቆሮ. 15፡1-2፡፡ ምንም እንኳ ጥቅሶቹ ከአርማጌዶን ዐውድ
የተለዩ ቢሆኑም ጳውሎስ እየጠቆመ ያለው ነገር ምንድን ነው? በተለይ የወደፊቱ
ከያዘው ብርሃን አኳያ ይህን ማስታወሳችን አግባብ የሆነው ለምንድን ነው?
በተጨማሪ የአርማጌዶንን ዐውድ የያዘውን ራእ. 16፡15 ያንብቡ፡፡ ጥቅሶቹ
በአንድነት ምን ይነግሩናል?
“ብዙ ጸሐፊዎች ስለ አርማጌዶን ውጊያ በጻፏቸው ታሪኮች
አሰቃቂ ፍጡራንን እና አስቀያሚ ክስተቶችን ቢያካትቱም፤ ከእውነታው ጋር
ቅርበት ያላቸው የሚመስሉ ሀሳቦች ሲያንጻረቁባቸው ይታያሉ፡፡ ‘እነሆ፤ እንደ
ሌባ እመጣለሁ፤ ዕራቁቱን እንዳይሆን ኀፍረቱም እንዳይታይ ነቅቶ ልብሱን
የሚጠብቅ ሰው ብፁዕ ነው’ (ራእ. 16፡15)--ይህ አርማጌዶን የሚለውን ቃል
ከማግኘታችን አስቀድሞ የሚመጣ ጥቅስ፤ ለየሱስ ዳግም ምጽአት እና
ለመጨረሻው ጊዜ ክስተቶች እንድንዘጋጅ የሚነግሩንን አያሌ የአዲስ ኪዳን
መልእክቶች ያስተጋባል፡፡
“ሌላው በራእ. 17፡14 የምናገኘው ጥቅስ እንዲህ ይላል፡ ‘እነዚህ በጉን
ይዋጋሉ፤ በጉ ግን ድል ይነሳቸዋል፤ ምክንያቱም እርሱ የጌቶች ጌታና የነገሥታት
ንጉሥ ነው፤ ከእርሱ ጋር ያሉ የተጠሩት፣ የተመረጡትና የታመኑትም አብረው
ድል ይነሳሉ፡፡’ እዚህ ላይ በመጨረሻ እውን በሚሆነው ታላቁ ጦርነት ተቀዳሚ
ዓላማቸው ሌሎችን በመሣሪያ ማጥፋት ሳይሆን ለቀረበላቸው መለኮታዊው
ጥሪና መመረጥ ታማኝ የሆኑ ተዋጊ ሕዝቦችን እናገኛለን፡፡ ይህ ዛሬም
መንግሥታትና የነፃነት ተዋጊዎች እያደረጉ ካለው ውጊያ ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ
የተለየ ነው፡፡ በተደጋጋሚ እንደ ተናገርኩት የአርማጌዶን ውጊያ የአእምሮ
ፍልሚያ ነው፡፡ በተጨማሪ ለታረደው በግ ከልብ የመነጨ ታማኝነት እንድናሳይ
የቀረበ የልብ ተግዳሮት ነው፡፡ (Rev. 5:9, 10, 12; 13:8).”—Jon Paulien, Ar-
mageddon at the Door (Hagerstown, Md.: Autumn House Publishing,
a division of Review and Herald Publishing Association, 2008), p. 193.
1.በራእይ መጽሐፍ የተጠቀሱት አብዛኞቹ ክስተቶች በራሱ በተጠቀሰው ስፍራ
ገቢራዊ ይሆናሉ ብሎ የሚያምነውን ሰው ሊረዱት የሚችሉት እንዴት ነው? ይህ
ጥቅሶችን ለመፍታት አስቸጋሪ አካሄድ መሆኑን መመልከት እንዲችሉ እንዴት
ልናግባባቸው እንችላለን?
2.የባቢሎን ተጽእኖ መላውን ዓለም ያካተተ መሆኑን ቀደም ባለው ትምህርታችን
ተመልክተናል፡፡ አንዳንዶቹ የባቢሎን አስተምህሮዎች የትኞቹ ናቸው? እነዚህን
አስተምህሮዎች ለይተን በመገንዘብ ማስወገድ የምንችለው እንዴት ነው?
3.በሰኞው ትምህርት የሚከተለው የኤለን ኋይት ጽሑፍ ቀርቦ ነበር፡ “ይህ ሁናቴ
ክንውን ሳያገኝና ቤተ ክርስቲያን ከዓለም ጋር ያላት ሕብረት በመላው የክርስትና
ተቋማት ገቢራዊ ሳይሆን የባቢሎን ውድቀት የተሟላ አይሆንም” እዚህ ላይ
“ቤተ ክርስቲያን ከዓለም ጋር ያላት ሕብረት” ስለሚለው ሀረግ አሰብ ያድርጉ፡፡
ለመሆኑ ይህ የተሰጠን ብርቱ ማስጠንቀቂያ ምን ይመስላል?