ለመጨረሻው ጊዜ መዘጋጀት
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2018

ከግንቦት 25 - ሰኔ 1

አስረኛ ትምህርት

June 2 – 8


አሜሪካ እና ባቢሎን



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 13:1–12፣ 14:9–11፣ 16:2፣ 19:20፣ 20:4፣ ኤር. 51:6-7፣ 53፣ 57፣ ራእ. 18:1–4፡፡


የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡- “ ‘በዚያን ዘመን ስለ ሕዝብህ የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሳል፡፡ መንግሥታት ከተመሠረቱበት ጊዜ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ የመከራ ጊዜ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በዚያን ጊዜ ስማቸው በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ ይድናሉ፡፡” (ዳን. 12፡1)፡፡

ባለፈው ሣምንት ጥናታችን ስለ አስመሳዩ ስላሴ ማለትም ሰይጣን (ዘንዶው) እና ሁለቱ የምድር ኃይላት የተመለከትን ሲሆን እነዚህ በአንድነት በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ስደት ያደርሳሉ፡፡ ከእነዚህ ኃይላት አንዱ የሆነው ከባሕር የወጣው አውሬ (ራእ. 13፡1-10) ከነብር፣ ከድብ እና ከአንበሳ የተውጣጣ አካል የነበረው ሲሆን (ራእ. 13፡2) እነዚህ ምስሎች በቀጥታ የተወሰዱት ከዳን 7፡4-6 ነው፡፡ በስድስተኛው ሣምንት ጥናታችን--ከባቢሎን (አንበሳ)፣ ሜዶንና ፋርስ (ድብ) እና ግሪክ (ነብር)--በኋላ ሮም የመጨረሻው የምድር ልዕለ ኃያል ሆኖ እንደሚወጣ ተመልክተናል፡፡ ከአረማዊው ሮም ማለትም ከዚህ አራተኛው አውሬ ላይ የሚነሳው ትንሹ ቀንድ ኃይል በቀጥታ ወደ ሮም ጳጳሳዊ ሥርዓትነት ይለወጣል በዳን. 7፡7-8፣ 19-21፣ 23-25፡፡ እንዲሁም በዳን. 7 የተገለጸው አብዛኛው የጳጳሳዊው ሥርዓት ጸባይ ከባሕር በወጣው አውሬ (ራእ. 13፡1-10) ውስጥ እንደሚታይ ተመልክተናል፡፡ የሆነው ሆኖ ሮም ብቻውን ሳይሆን ሌላም ኃይል እንዳለ ተገልጾአል፡፡ በዚህ ሣምንት አብዛኛው ትኩረታችን በራእ. 13 በተገለጹ ኃይላትና ጉዳዮች ዙሪያ ይሆናል፡፡ እንደ ተለመደው እንዲህ በማለት እንጠይቃለን፡ ለመሆኑ የእነዚህ ሁኔታዎች ፍቺ ምንድን ነው? መዘጋጀት የምንችለውስ እንዴት ነው?

ግንቦት 26
Jun 03

ለሞት የሚያደርሰው ቁስሉ መዳን


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 13፡1-10፡፡ እነዚህ ጥቅሶች ጳጳሳዊው ሥርዓት ቀደም ባሉት ጊዜያትም ሆነ ወደፊት ስለሚኖረው ሚና ለምን እንደሚጠቅሱ ምክንያቶቹን ለመመልከት ይሞክሩ፡፡ በተለይ ምን ያህል በግልጽ የሚታይ ሚና እንዳለው ልብ ይበሉ፡፡ ይህ ከመጨረሻዎቹ ቀናት ክስተቶች አኳያ ምን ማለት ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ምንም እንኳ እግዚአብሔር በተለያዩ ቤተ ክርስቲያኖች የሚያመልኩ ታማኝ ሕዝቦች ቢኖሩትም ነገር ግን ይህ ኃይማኖታዊ ተቋም ቀደም ባለው ታሪክ የተጫወታቸውና ወደፊትም በመጨረሻዎቹ ቀናት በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ ሚናዎች እንደሚኖሩት መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 13፡3፡፡ እዚህ ላይ እየሆነ ያለው ነገር ምንድን ነው? ስለ ሮም ታዋቂነትና ዝና ምን ያስተምረናል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የእምነት ማዕከልና በብዙ መንገድ የምዕራቡ ዓለም የፖለቲካ እምብርት ሆና ለምዕተ ዓመታት ዘልቃለች፡፡ ሰላም ለመፍጠር ሲል ወደ ተቆጣው ጳጳስ ግሪጎሪ 7ኛ የመኖሪያ ቅጥር አምባ መጥቶ የነበረው የሮም ንጉሥ ቅዱስ ሔነሪ 4ኛ ታሪክ የቤተ ክርስቲያኗን ኃይልና ሥልጣን ማሳየት ከቻሉ ምሳሌዎች መሃል የሚጠቀስ ነው፡፡ የሚገርመው ይህ የሮማ ንጉሥ የጳጳሱን የመግቢያ ፈቃድ አግኝቶ ወደ ውስጥ እስኪዘልቅ ለሦስት ቀናት የአውሮፓን ክረምት ቁር እና ብርድ ተቋቁሞ በቅጥሩ ደጃፍ እንዲቆይ ተደርጎ ነበር፡፡ ባገኘው ድል ልቡ የታበየው ጆርጅ 7ኛ የነገሥታትን ኩራት ድባቅ መትቶ ልክ ማግባት የእርሱ ተግባር መሆኑን በኩራት ሲናገር ተደምጦ ነበር፡፡ ሆኖም ቤተ ክርስቲያኒቱ በገጠማት ተሐድሶ፣ ወጣ ያለ አስተምህሮ እንዲሁም በፈረንሳይ አብዬት የተነሳ የሮም ፖለቲካዊ እና ኃይማኖታዊ የበላይነት በአሥራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ አከተመለት፡፡ ከጳጳሳቱ አንዱ የነበረው ፒየስ 6ኛ በ1798 በፈረንሳይ ሠራዊት በምርኮ ከተወሰደ በኋላ በ1799 በግዞት እያለ ሞቶአል፡፡
ሆኖም ራእ. 13 “ለሞት የሚያደርሰው ቁስሉ ዳነ” በማለት ስለ ማንሰራራቱ ይናገራል፡፡ ምንም እንኳ ዛሬ ሮም በንጉሥ ግሪጎሪ 7ኛ ዘመን እንደ ነበረው ሥልጣኑን በሙሉ ኃይሉ የሚጠቀምበት ሁኔታ ላይ ባይሆንም ነገር ግን ለዘመኑ ጳጳሳት ክብርና ዝና ምስጋና ይግባውና በኃይማኖትም ሆነ በፖለቲካ ተጽእኖ ፈጣሪ ኃይል ለመሆን በቅቶአል፡፡ (ለአብነት ያህል ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ በአውሮፓውያኑ ቀመር 2015 ላይ በሁለቱም የአሜሪካ ምክር ቤቶች ተገኝተው ያደረጉት ንግግር በዓይነቱ የመጀመሪያ እና ታሪካዊ ነበር፡፡) በመጽሐፍ ቅዱሳዊው ትንቢት መሰረት ይህ ተጽእኖ እያደገና እየተመነደገ የሚሄድ ነው፡፡ በተቻለን መጠን የሰዎችን ስሜት ሳንጎዳ እንድንሰብክ ለተጠራንበት መልእክት ታማኝ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

ግንቦት 27
Jun 04

ዩኤስ አሜሪካ በትንቢት


ሮም በራእ. 13 የተገለጸው ዓይነት ተጽእኖ ዛሬም ሆነ ወደፊት ሊኖራት የሚችለው እንዴት ነው? በማለት ብዙዎች ይጠይቃሉ፡፡ ሮም የጦር ሠራዊት ታዝ የነበረበት ጊዜ ካከተመ አያሌ ዘመናት ቢቆጠሩም ምላሹ በዚያው ራእ. 13 ላይ ይገኛል፡፡ ጠቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 13፡11-12፡፡ የዚህን ኃይል ማንነት ለይተን እንድንገነዘብ የሚረዱን ምልክቶች ምንድን ናቸው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ይህኛውን አውሬ ተከትሎ ወደ ሥልጣን የሚመጣውና ለአርባ ሁለት ወራት ሥልጣን የተሰጠው ኃይል (ራእ. 13፡5) ሮም እንደሆነ ተደርጎ ለረጅም ዘመናት በፕሮቴስታንቶች ታምኖአል፡፡ ጳጳሳዊው ኃይል ተቃዋሚዎቹን የጨቆነባቸው ጊዜያቶች አርባ ሁለቱ ወራት በዳን. 12፡6 “ለዘመን፣ ለዘመናት፣ ለዘመን እኩሌታም” በሚል ከተጠቀሰው ወይም ከሦስት ዓመት ተኩል (ራእ. 12፡44) ወይም ደግሞ ከ1260 ትንቢታዊ ቀናት (ራእ. 12፡6) ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ ትንቢታዊ ጊዜ (አንድ ቀን እንደ አንድ ዓመት በሚለው የትንቢት ፍቺ መርኅ መሰረት) የጀመረው ጳጳሳዊው ሥርዓት ገናና በሆነበት 538 ዓ.ም. ሲሆን፤ ያበቃው ደግሞ ጳጳሱ በምርኮ በተወሰደበት ዓመት--1798 ዓ.ም. ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ጳጳሳዊው ኃይል ለሞት የሚያደርሰውን ቁስል በመቀበሉ ትንቢቱ ፍጻሜ አገኘ፡፡
በዚህ ጊዜ አካባቢ ማለትም “አርባ ሁለቱ ወራት” (1798) መገባደጃ ላይ ሌላ ኃይል ብቅ ይላል (ራእ. 13፡11፣ 13፡1)፡፡ ይህ ኃይል የወጣው ከምድር ሲሆን ቀደም ብሎ ከባሕር (ከብዙ ሕዝብ መሃል) ከወጣው (ዳን. 7፡2-3) እና ቀደም ካሉት ከአብዛኞቹ ኃይላት ጋር ሲነጻጸር ልዩነት ነበረው፡፡ “‘ያየኸቸው ውሆች፡ ወገኖች፣ ብዙ ሰዎች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች ናቸው’” (ራእ. 17፡15)፡፡ ይህ ኃይል ሰው ችምችም ብሎ ከማይኖርበት የምድር ክፍል የወጣ እንደመሆኑ፤ እንደ ሌሎቹ ሁሉ የትኛውንም ኃይል ገርስሶ መውጣት አላስፈለገውም፡፡ በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ይህ ኃይል ዬኤስ አሜሪካ መሆኑን አፍ ሞልቶ መናገር ይቻላል፡፡
“በ1798 የዓለም ልዕለ ኃያል የመሆን ግስጋሴ በመጀመር ገናና የመሆን ተስፋ ሰንቆ የተነሳውና የዓለምን መንግሥታት ትኩረት የሳበው ማን ነበር? የዚህን ኃይል ማንነት ለመግለጽ ጥቅም ላይ የዋሉት ምሳሌያዊ አገላለጾችና አንደምታዎች የሚያጠያይቁ ዓይነት አይደሉም፡፡ የትንቢቱን ዝርዝር መመሪያ በትክክል የሚያሟላው አንድ እና አንድ ብቻ አገር ሲሆን ይኸውም ዩኤስ አሜሪካ ነው፡፡”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 440. ምንም እንኳ መጀመሪያ ላይ ይህ ኃይል የጨዋነት ተምሳሌት በሆነው ሁለት ቀንዶች ባሉት በግ የተገለጸ ቢሆንም፤ ነገር ግን ውሎ አድሮ እንደ “ዘንዶ” (ራእ. 13፡11) ይናገራል፡፡ ይህ ደግሞ ቀደም ባለው ኃይል የሥልጣን ዘመን ገቢራዊ የሆነው ዓይነት የስደት ጊዜ መኖሩን ይጠቁማል፡፡ ሮም አስቀድሞ የተተነበየው ፍጻሜ ያገኝ ዘንድ እንዴት ተጽእኖ ማድረግ ትችላለች? ለሚለው ጥያቄ-- ከጀርባዋ የዩኤስ አሜሪካ ኃያል ድጋፍ ስላላት በቀላሉ ገቢራዊ መሆን ይችላል ሲል ራእ. 13፡11-17 መልስ ይሰጣል፡፡

ግንቦት 28
Jun 05

ፈታኙ የአምልኮ ጉዳይ


ጌታ በዘመናት በጣኦት እና በሌሎች የሐሰት አምልኮዎች ይወድቁ የነበሩትን ሕዝቦች ያለማቋረጥ መምራትና መታደግ ነበረበት (ማቴ. 4፡8-10)፡፡ በራእ. 13 እንደ ተገለጸው በመጨረሻው ቀውስ ወቅት የአምልኮ ጉዳይ ገንኖ ይወጣል፡፡ እዚህ ላይ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ማንን ማምለክና ማገልገል እንደሚኖርባቸው ምርጫ ማድረጋቸው የግድ ይሆናል (ኢያ. 24፡15)፡፡
ቀደም ብለን “ዳንኤልና የመጨረሻው ጊዜ” በሚል ርዕስ ባጠናነው ሁለተኛው ሰንበት ትምህርታችን “ለወርቁ ምስል” (ዳን. 3፡5) እንዲሰግዱ የታዘዙትን ዕብራውያን ወጣቶች ታሪክ ተመልክተን ነበር፡፡ እንዲሁም ራእ. 13 በመጨረሻው ጊዜ የእግዚአብሔር ሕዝቦች የሚደርስባቸውን ስደት ለመግለጽ ከዚያኛው ምዕራፍ እንዴት ቃላቶችን እንደ ተጠቀመ ተመልክተናል፡፡ ይህ ማለት ዳን. 3 በግምባር ቀደም ያስቀመጠውን መመልከታችን፤ በራእ. 13--መጨረሻዎቹ ቀናት የሚሆነውን ለማወቅ ያስችለናል፡፡ ቀደም ባለው ዘመን ሁሉም ሰው ከወርቅ ለተሠራው ምስል እንዲሰግድ ያለበለዚያ ግን በሚነደው እቶን እሳት ውስጥ እንደሚጣል ብርቱ ትእዛዝ ተሰጥቶ እንደ ነበር ሁሉ በተመሳሳይ ወደ ፊት “ለዚህ ምስል የማይሰግዱ ሁሉ እንዲገደሉ” (ራእ. 13፡15) የሚያዝ ትእዛዝ ይወጣል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 14:9–11፣ 16:2፣ 19:20፣ 20:4፡፡ የአምልኮ ጉዳይ እጅግ ወሳኝ እንደሚሆን አስመልክቶ ጥቅሶቹ ምን ይነግሩናል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ባቢሎን ሁሌም የምትወሳው በሐሰት አምልኮ ርዕሰ መዲና ተምሳሌትነት ነው፡፡ የባቤል ግንብ ሉሲፈር “ከደመናዎችም ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ” (ኢሳ. 14፡14) እንዳለው ዓይነት የገንቢዎቹን ብርቱ ምኞት ያንጸባረቀ እንደ መሆኑ፤ እግዚአብሔር ከዚህ በኋላ ምድርን በውሃ እንደማያጠፋ (ዘፍ. 9፡8-11) የገባውን ቃል ለመቀበል በመቃወም ራሳቸውን ለማዳን ያደረጉትን ጥረት የሚያሳይ ነበር፡፡ የባቢሎን መንግሥት ከቀድሞው በተመሳሳይ ለሰብዓዊው የእጅ ሥራ ውጤት ከፍ ያለ አክብሮት የሰጠ ነበር፡፡ ናቡከደነፆር “ያሠራኋት ታላቂቷ ባቢሎን ይህች አይደለችምን?” (ዳን. 4፡30) በማለት ራሱን በማወደስ ተመጻደቀ፡፡ ከዚያም በእርሱ እግር የተተካው ልጁ ንጉሥ ቤልሻዛር ሰሎሞን ከሠራው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የወርቅ መጠጫዎችን በማስመጣት “ንጉሡና መኳንንቱ፣ ሚስቶቹና ቁባቶቹም ጠጡባቸው፡፡ የወይን ጠጁንም እየጠጡ የወርቅና የብር፣ የናስ፣ የብረት፣ የእንጨትና የድንጋይ አማልክት አመለኩ” (ዳን. 5፡3-4)፡፡ እዚህ ላይ የቤተ መቅደሱ እውነተኛ መጠጫዎች በሚያሰክር የወይን ጠጅ መሞላታቸውንና ከዚያ የጠጡ ሁሉ ምን ያህል እንደ ደነዘዙና የማገናዘብ አቅማቸውን እንዳጡ ልብ ማለቱ ተገቢ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ ባቢሎን ስትወድቅ በከተማዋ ከነበሩት መሃል ብዙዎቹ ጠፉ፡፡ ውጪያዊው የታይታ እውነት ጭምብል በገዳዩ “የባቢሎን ወይን ጠጅ” ሊያስተን ይችላል፡፡ ሐሰተኛ አምልኮ እና ሐሰተኛ ጽንሰ ሀሳቦች ለሰይጣናዊው መንግሥት ገንዘቡ ናቸው፡፡
ዛሬ የማንኛውም ሐሰት አምልኮ ተካፋይ ላለመሆናችን ምን ያህል እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

ግንቦት 29
Jun 06

“ታላቂቱ ባቢሎን”


የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡፡ ጥቅሶቹ ስለ ባቢሎን ምን ያስተምሩናል? ኤር. 51:6-7፣ 53፣ 57፣ ዘካ. 2:7፣ ራእ. 17:5-6፣ 18:2-3፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ባቢሎን በሐሰት አምልኮ ርዕሰ መዲናነት ረጅም ታሪክ እንዳላት በትናንቱ ጥናታችን ተመልክተናል፡፡ ይህ ደግሞ ሕዝቦችን ለሚያስተው ለመጨረሻው ጊዜ ኃይል ገጣሚ ያደርጋታል፡፡ ዘንዶውን፣ ከባሕር የወጣውን አውሬ እና ቀዩን አውሬ ያስተያዩ (ራእ. 12፡3፣ 13፡1-3፣ 17፡3)፡፡ በመሃላቸው የሚስተዋሉት ተመሳሳይነትና ልዩነቶች ምንድን ናቸው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ሰባት ራሶችና አስር ቀንዶች ያሏቸው ሦስቱ አውሬዎች በዳን. 7 የቀረቡትን ራሶች እና ቀንዶች አጠቃላይ ድምር ይወክላሉ፡፡ እያንዳንዱ በሌላው እግር የተተካ ሥርዓት አዲሱን አገዛዝ የሚያጸናው በቀደመው ላይ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ቀዩ አውሬ የዘንዶውን፣ ከባሕር የወጣውን አውሬ እና (በአረማዊውና ጳጳሳዊው ሮም ቅደም ተከተል ምሳሌ መሰረት) ከምድር የወጣውን አውሬ (ራእ. 13፡11-14) መሰረታዊ ባህርያት አጣምሮ መያዙ “ሦስቱንም የእግዚአብሔር ጠላት ኃይሎች በእውነተኛ ግንባርነት ይመድባቸዋል”—Jacques B. Doukhan, Secrets of Revelation, The Apocalypse Through Hebrew Eyes (Hagerstown, Md.: Review and Herald® Publishing Association, 2002), p. 162. በተጨማሪ በራእ. 17 በቀዩ አውሬ ላይ የተቀመጠችው ሴት በኃይማኖትና በፖለቲካ ኃይሎች መካከል የተከለከለውን የአንድነት መሰረታዊ ባህሪ በምሳሌ ያቀርባል፡፡ ይህች ሴት በራእ. 12 ከተገለጸችው ንጹህዋ ጋር ፍጹም ተቃራኒ ናት፡፡
ንጹህዋ ሴት (ራእ. 12) በሰማይ ፀሐይን የለበሰች ዐሥራ ሁለት ከዋክብት ያሉት አክሊል የደፋች በዘንዶው ጥቃት ይደርስባታል የትሩፋን እናት አመንዝራዋ ሴት (ራእ. 17) በውሆች ላይ ሐምራዊና ቀይ ልብስ የተጎናጸፈች በወርቅ፣ በከበሩ ድንጋዮችና በዕንቆች ያጌጠች በዘንዶው ትደገፋለች የአመንዝራዎች እናት የአመንዝራዎች እናት የሆነችው ባቢሎን ራስዋን በማባዛት ሥራ ተጠምዳለች፡፡ ክህደት የፈጸመችው ይህች እናት ቤተ ክርስቲያን አያሌ ክህደት የፈጸሙ ልጆች አሏት፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በክርስትና ላይ ክህደት ስትፈጽም፣ ስህተት ስታውጅና ግፍ ስትሠራ የኖረችውን ተቋም የእኔ ሊላት አይችልም፡፡ ምንም እንኳ ሰይጣን እውነተኞቹ የእርሱ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ቢፈጽምም፤ ለብዙ መቶ ዓመታት ተቋቁመው ማለፍ ችለዋል፡፡
ራእ. 14፡8 ስለ ባቢሎን ውድቀት ወይም በእውነት ላይ ስለሚፈጸም ክህደት ሕዝቡን በማጠንቀቅ፤ ውሎ አድሮ የአውሬውን ምልክት ወደ መቀበል ከሚወስደው የመጨረሻ ማሳቻ (ራእ. 14፡9-11) እንድንጠበቅ ያሳስበናል፡፡ ዛሬም በባቢሎን የሚገኙ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ከእርሷ ወጥተው ከመጨረሻው ጊዜ የእግዚአብሔር ትሩፋን ቤተ ክርስቲያን ጋር በአንድነት ይቆሙ ዘንድ (ራእ. 18፡4) ይህ ማስጠንቀቂያ እጅግ ብርቱ በሆነ ኃይል ለመጨረሻ ጊዜ ለሕዝቡ ይቀርባል፡፡

ግንቦት 30
Jun 07

ሕዝቤ ሆይ፤ ከእርሷ ውጡ


የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ተማሪዎች የዓለምን ሁኔታ በተለይ ከመጨረሻው ጊዜ ጋር እያስተያዩ በታላቅ ፍላጎትና ጉጉት ለዓመታት ሲፈትሹና ሲመረምሩ ቆይተዋል፡፡ ለምሳሌ ዩኤስ አሜሪካ በዚህ ዙሪያ ስለሚኖራት ሚና አሰብ ያድርጉ፡፡ አንዳንድ አድቬንቲስቶች ወደ ኋላ በ1851 አስገራሚ በሆነ መልኩ የአሜሪካንን ሁናቴ እንደ ሁለተኛው አውሬ ኃይል (ራእ. 13፡11-15) ለይተው መመልከት ችለው ነበር፡፡ በዚያን ዘመን ማለትም በ1800 አጋማሽ የዓለም ልዕለ ኃያላን ይባሉ የነበሩት የድሮዎቹ፡ ፐርሽያ፣ ፈረንሳይ፣ ኦስትሪያ-ሐንጋሪ እና እንግሊዝ ነበሩ፡፡ በዚያን ወቅት አሜሪካ የነበራት የወታደር ብዛት 20 ሺ ሲሆን ይህ አሃዝ በዋተርሉ ውጊያ (በ1815) ተሰልፈው ከነበሩት ወታደሮች ጋር ሲነጻጸር አንድ አሥረኛው ብቻ ነበር፡፡ አርባ ዓመት ቀደም ብሎ ማለትም በ1814 እንግሊዝ ወረራ አካሂዳ ዋሽንግቶን ዲሲን አቃጥላ ነበር፡፡ በ1867 ሲቲንግ ቡልስ በሚባል ይታወቅ የነበረ የአሜሪካ ጎሳ መሪና ተከታዮቹ በዩኤስ አሜሪካ ሰራዊት ላይ ውጊያ ከፍተው ሰባተኛውን የአሜሪካ ፈረሰኛ ሬጅመንት አዛዥ ጀነራል ከስተርን ጦር ከጥቅም ውጪ ማድረግ ችለው ነበር፡፡ ምንም እንኳ አንዳንዶች ዩኤስ አሜሪካ አንድ ቀን “የአውሬውን ምስል” በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያጠናክር ኃይል ይሆናል ብለው ገና በጠዋቱ ለይተው በመመልከት አስተያየታቸውን መስጠት ቢችሉም፤ ነገር ግን በዚያን ወቅት ይህ አገር ገና ከምድሪቱ ነባር ቀይ ሕንዶች ጋር ይዋጋ የነበረና ሁሌም ድል የማይቀናው ዓይነት መንግሥት ነበረ፡፡ የዓለም ክስተቶች ይሆናሉ ብለን ባመንበት አቅጣጫ መጓዛቸውን መቀጠላቸው አጠያያቂ ባይሆንም ነገር ግን ወደ መጨረሻው ከመድረሳችን አስቀድሞ ገና ብዙ ነገሮች መገለጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ለምሳሌ ስለ “አውሬው ምልክት” ስናወራ ዛሬ ሰዎች አራተኛውን ትእዛዝ እየጠበቁ ቢሆኑ ወይም ባይሆኑ--ይህን ምልክት የተቀበለ ማንም ስለ አለመኖሩ አጽንኦት መስጠታችን በእጅጉ አስፈላጊ የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ገና ተጨማሪ መገለጥ የሚኖርባቸው ነገሮች አሉ፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 18፡1-4፡፡ በጥቅሱ እየሆነ ያለው ነገር ምንድን ነው? ይህን ነገር አሁን ማስታወሳችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ለዓለም ስላለን ተልዕኮ ጥቅሶቹ ምን ያስተምሩናል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

እነዚህ ጥቅሶች በፖለቲካ፣ በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊነት አብልጦ የዘቀጠውን ዓለም አስቀያሚ ምስል ይሰጡናል፡፡ የሐሰት ኃይማኖታዊ አስተምህሮ በዓለም ላይ የሚያስከትለውን ክፉ ተጽእኖ ይገልጹልናል፡፡ ሆኖም በዚህ መሃል ታላቅ ተስፋ የሚሰጥ ትዕይንት የሚስተዋል ሲሆን ይኸውም ከክብሩ ነጸብራቅ የተነሳ ምድር እንድትበራ ያደረገው ከሰማይ የመጣው ሌላ መልአክ ክስተት ነው፡፡ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ገና ያልተገነዘቡ ታማኝ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ከባቢሎን እንዲወጡ መጠራታቸው ሌላው እንዲያውቁ የተፈለገው ተጨማሪ ነጥብ ነው፡፡ ይህ ማለት ከባቢሎን የወጡት የእግዚአብሔር ሕዝቦች ገና ላልወጡት እስከ መጨረሻው የሚሠሩት ሥራ መኖሩን ያመላክታል፡፡
ጌታ አሁንም በባቢሎን የሚገኙትን ጥቂት ወገኖች “ሕዝቦቼ” ብሎ መጥራቱ ለእኛ የሚሰጠው ትርጉም ምንድን ነው? ራሳችንን ከሌሎች ጋር ለማዛመድ በምናደርገው ሂደት ይህን ማስታወስ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ሰኔ 1
Jun 08

ተጨማሪ ሀሳብ፡


ሰይጣን በእግዚአብሔር ሕግ ላይ የፈጸመው ጥቃት-በራሱ በእግዚአብሔር፣ በሥልጣኑና በመንግሥቱ ላይ የተደረገ ጥቃት ነው፡፡ ዓለም በከባድ ቀውስ ውስጥ በምትወድቅባቸው በመጨረሻዎቹ ቀናት ሰይጣን “የእግዚአብሔርን ትእዛዛት” (ራእ. 12፡17፣ 14፡12) የሚጠብቁ ወገኖች ላይ ጥቃት ይከፍታል፡፡ ለዚህ መንስኤው በምድር ላይ በወኪሎቹ አማካይነት ለእርሱ ክብር ለመስጠት የሚቃወሙ ሕዝቦች እነርሱ ብቻ በመሆናቸው ነው፡፡ ቀደም ሲል በእግዚአብሔር ላይ በሰማይ ከፍቶት የነበረው ዘመቻ በዚህም ምድር የቀጠለ ቢሆንም ነገር ግን በሰማይ እንደ ተሸነፈ በዚህም ምድርም ድል ይሆናል፡፡ “በሰማይ ከተጀመረው ታላቁ ተቃርኖ አንስቶ የሰይጣን ዓላማ የእግዚአብሔርን ሕግ መገርሰስ ነው፡፡ በፈጣሪ ላይ ዐመጻ ያደረገው ይህን ዕኩይ ዓላማውን ተግባራዊ ለማድረግ ሲል ነበር፡፡ ምንም እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር ቢጣልም ያንኑ የውጊያ ስልት እንደገፋበት ይገኛል፡፡ ሰዎችን ማሳትና የእግዚአብሔርን ሕግ እንዲጥሱ መምራት ጽኑና የማያወላውል ዓላማው አድርጎ ገፍቶበታል፡፡ ሁሉም የሕጉ ክፍል እንዲወገድ ማድረግ ወይም አንዱን ብቻ ነጥሎ ማስወገድ-ውሎ አድሮ የሁሉም ውጤቱ አንድና ተመሳሳይ ነው፡፡ ‘ምክንያቱም ሕግን ሁሉ የሚፈጽም ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ቢኖር፣ ሁሉን እንደ ተላለፈ ይቆጠራል’ ያዕ. 2:10”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 582.


የውይይት ጥያቄዎች፡




1.በሰንበት ትምህርት ጥናት ክፍለ ጊዜ በዓለም ሁናቴዎች ዙሪያ በመነጋገር እነዚህ ሁናቴዎች በምን መልኩ ይሆናሉ ብለን የምናምንባቸውን አቅጣጫዎች እንደሚያመለክቱ ተነጋገሩ፡፡ ገና ያልተገለጡት ክስተቶች የትኞቹ ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የኤለን ኋይት ጽሑፎች በግልጽ የማያስተምሩትን ጊዜ የመወሰን፣ የድፍረት ትንበያዎችንና አክራሪ አመለካከቶችን እያስወገድን-የጊዜውን ምልክቶች ሁሌም በንቃት መጠባበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
2.በአምልኮ ጥያቄ ዙሪያ ጊዜ ወስዳችሁ ተነጋገሩ፡፡ አንድን ነገር ማምለክ ሲባል ምን ማለት ነው? የምናመልከው ምንም ይሁን ምን--አምልኮአችን መሆን ያለበት እንዴት ነው?
3.እግዚአብሔር ዛሬም በባቢሎን ሕዝቦች አሉት በሚለው ጽንሰ ሃሳብ ዙሪያ በደንብ ተወያዩ፡፡ “ባቢሎን” የሚለውን (ተምሳሌታዊ) ቃል ፍቺ የምናስተውለው እንዴት ነው? ሰዎች የቱንም ዓይነት ፖለቲካዊ አመለካከት ቢያራምዱ ወይም ኃይማኖታዊ አቋም ቢይዙ--የተሰጠንን መልእክት ለእነርሱ የመስበክ ግዴታችንን መቀጠል እንዳለብን አስመልክቶ ይህ ምን ያስተምረናል?