መዳን በእምነት ብቻ:ሮሜ መጽሐፍ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2017

ከመስከረም 27-ጥቅምት 3

ሁለተኛ ትምህርት

October 7–October 13
 

ተጋድሎው

 

ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት:- ዕብ. 8:6, ማቴ. 19:17, ራዕይ 12:17, ዘሌ. 23, ሐዋ. 15:1– 29, ገላ. 1:1–12ን ያንብቡ

 

የመታሰቢያ ጥቅስ፦ ‹‹“ህግ በሙሴ ተሰጠ፣ ነገር ግን ጸጋና እውነት በክርስቶስ መጣ፡፡” ›› (ዮሐ. 1:17)፡፡

 

የጥንቷ ቤተክርስትያን ላፍታ እኳን የአይሁድ መሲህ የሆነውን ክርስቶስን በመቀበል ድነት ይሆናል ብለው አስበው የማያውቁ አይሁዶች ቅልቅል ስትሆን፣ እንዲያውም ይህንን መቀበል እግዚአብሔር ለአባቶቻቸው የሰጠውን የኪዳን ተስፋ ችላ ማለት እንደሆነ የሚቆጥሩ ሰዎች ነበሩባት ፡፡ በሌላ መልኩ ሲታሰብ እነርሱ ትክክል ነበሩ፡፡ ለጥንቱ አይሁዶች ትልቁ ጥያቄያቸው የነበረው ክርስቶስን ለመቀበል አህዛቦች ክርስትያን መሆን አለባቸው የሚለው ነበር፡፡ ለብዙዎቻቸው አሳሳቢ የነበረው ጉዳይ አህዛብ ክርስቶስን ከመቀበላቸው በፊት አይሁድ መሆን አለባቸው ወይስ የለባቸውም የሚለው ነበር፡፡

አህዛብ ክርስቶስን ለመቀበል አይሁድ መሆንና እጅግ ብዙ የሆኑ የአይሁድ ህጎች ሊጫንባቸው እንደማይገባ ውሳኔ የተሰጠው በኢየሩሳሌም በነበረው የምክክር ጉባኤ ከብዙ ጊዜ ቆይታ በኋላ ነበር ፡፡

ከውሳኔው በተቃራኒ አንዳንድ መምህራን ወደ ክርስትና የመጡ አህዛብ የኪዳኑን ተስፋ ወራሾች ለመሆን መገረዝን ጨምሮ ሌሎቹንም የአይሁድ ህጎች መጠበቅ እንደሚገባቸውና ይህም የእስራኤል የሆነውን ታላቅ ሀብት ለመካፈል አስፈላጊ የሆነ ቅድመ- ሁኔታ እንደሆነ ያስተምሩ ነበር፡፡

*ለጥቅምት 4 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ፡፡
 

መስከረም 28
Oct 8
 

የተሻለው ኪዳን

 

ዕብ. 8:6ን ያንብቡ፡፡ በዚህ ያለው መልዕክት ምንድነው? ይህንን ‹‹የተሻለ ተስፋ›› እንዴት እናስተውለዋለን?

ምናልባትም የአዲስ ኪዳንና የብለይ ኪዳን ክርስትና ትልቁ ልዩነት የአዲስ ኪዳን ዘመን የተጀመረው መሲህ በሆነው በናዝሬቱ በክርስቶስ መምጣት መሆኑ ሊሆን ይችላል፡፡ እርሱ አዳኝ እንዲሆን በእግዚአብሔር የተላከ ነበር፡፡ ሰዎች እርሱን ችላ ብለው መዳንን መጠበቅ አይችሉም፡፡ እርሱ በከፈለው መስዋዕትነት ብቻ ኃጢአታቸው ይቅርታ ያገኛል፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ያለ ኩነኔ ሊቆሙ የሚችሉት ፍጹም በሆነው በእርሱ ተግባር ብቻ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር መዳን በክርስቶስ ጽድቅ ብቻ እንጂ ሌላ በምንም አይደለም፡፡

የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን የመዳንን ተስፋና የመሲሁን ዘመን በረከት ወደ ፊት እንደሚሆን ተጠባብቀው ነበር፡፡ የአዲስ ኪዳን ዘመን ሰዎች ደግሞ እግዚአብሄር የላከውን መሲሁን የናዝሬቱን ኢየሱስን፣ አዳኙን ይቀበሉት ይሆን በሚል ጥያቄ ተገዳድሯቸዋል፡፡ በእርሱ አምነውና እርሱ በእውነት እንደመጣላቸው ተቀብለውት ቢሆንና ራሳቸውን ቢሰጡ ለእነርሱ ሲል በነጻ በከፈለው መስዋዕትነቱ በዳኑ ነበር፡፡


በተመሳሳይ ሁኔታ በአዲስ ኪዳንም ቢሆን የግብረገብ ለውጥ ባላስፈለገ ነበር፣ ምክንያቱም እነዚህ ሁኔታዎች የተመሰረቱት በእግዚአብሄርና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ባህርይ ላይ ነበር፡፡ የእግዚአብሄርን ትዕዛዛት መጠበቅ በብሉይ ኪዳን አስፈላጊ እንደነበር እንዲሁ በአዲስ ኪዳንም አስፈላጊ ነበር፡፡

ማቴ. 19:17; ራዕይ 12:17; 14:12; እና ያዕ. 2:10, 11ያንብቡ፡፡ እነዚህ ጥቅሶች በአዲስ ኪዳን ስለሚገኙ አስርቱ ትዕዛዛት ምን ይነግሩናል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

እስራኤላውያን ያከናውኗቸው የነበሩ በተለየ ሁኔታ ከብሉይ ኪዳን ጋር ቁርኝት ያላቸው ሜዳዊ ሥርዓቶች እና ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የሊቀ ካህንነት ተግባርና ወደ ሞቱ የሚያመላክቱ የነበሩ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል ምክንያቱም ‹‹የተሻለውን ተስፋ›› በሚመለከት አዲስ ሥርአት የተጀመረ በመሆኑ ነበር፡፡

በሮሜ መጽሐፍ ላይ ጳውሎስ የተከተለው አስተምህሮ ዋና ዓላማው አይሁዶችንና አህዛብን ከአይሁድነት ወደ ክርስትና በሚደረግ የሽግግር ወቅት ላይ ያለውን ሁኔታ በትክክል እንዲረዱ ማድረግ ነበር፡፡ ሽግግሩን ለማድረግ ጊዜ ይጠይቅ ይሆናል፡፡ ብዙዎች ክርስቶስን የተቀበሉ አይሁዶች ለሚፈለግባቸው ለውጥ ዝግጁ አልነበሩም፡፡

እርስዎ የሚወዱዋቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች የትኞቹ ናቸው? ምን ያህል ጊዜ የኔ ብለው ይጠብቋቸዋል? እነዚህ ተስፋዎች በህይወትዎ እንዳይሟሉ መሰናክል በሚሆኑ ነገሮች ላይ ምን ዓይነት ምርጫ እያደረጉ ነው?



 
መስከረም 29
Oct 9
 

የአይሁድ ህጎችና ደንቦች

 
ጊዜ በፈቀደ መጠን የዘሌዋውያንን መጽሐፍ በፍጥነት ያንብቡት፡፡ ለምሳሌ ዘሌዋውያን 12፣16፣23ን ይዩ፡፡

እነዚህን ህጎችና ሥርዓቶች ሲያነቧቸው ወደ አእምሮዎ የሚመጣው ምንድነው? እነዚህን ሁሉ በብሉይ ኪዳን ዘመን እንጂ በአዲስ ኪዳን ዘመን ለመከተል አስቸጋሪ የሚሆነው ለምንድነው?

የብሉይ ኪዳንን ህጎች በአምስት ክፍሎች ለመመደብ ይቻላል፡፡ 1ኛ ግብረገባዊ ህጎች፣ 2ኛ አንድን ህጎች፣ 2ኛ አንድን ያለፈ ነገር ለማስታወስ የምናደርጋቸውስርዓቶች፣ 3ኛ ማህበረሰባዊ፣ 4ኛ የፍርድ እና የጤና ህጎች በመባል ሊመደቡ ይችላሉ፡፡

ይህ አመዳደብ በከፊል ሰው ሰራሽ ነው፡፡ በትክክል ሲታይ አንዳንዶቹ ክፍሎች ከሌሎቹ ጋር ይነካካሉ፣ ከዚህም የተነሳ አንዳንዶቹ ይመሳሳላሉ እናም በድሮው አመለካካት ልዩነት እንዳላቸው ተደርገው አይታዩም ነበር፡፡

ግብረ-ገባዊ ህጎች በአሥርቱ ትዕዛዛት የተዋጡ ነበሩ ዘጸ (20:1–17):: ይህ ህግ ከሰው የሚጠበቀውን ግብረ-ገባዊ ህጎችን በሙሉ በውስጡ ያጠቃልላል፡፡ እነዚህ አስርቱ ትዕዛዛት የሚገለጹትና የሚተገበሩት በመጀመሪያዎቹ አምስት በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ እንደተጻፉት የተለያዩ ህጎችና የፍርድ ሁኔታዎች ነበር፡፡ ይህ አገላላጽ የሚያሳየው የእግዚብሄርን ህግ በተለያየ ሁኔታ ማክበርን ወይም መጠበቅን ነው፡፡ ማህበረ-ሰባዊ ህጎችም ከዚህ የተለዩ አይደሉም፡፡ እነርሱም ጭምር በአሥርቱ ትዕዛዛት ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ ይህ የአንድን ሰው ከማህበረሰቡ ባለስልጣናትና ከሌሎቹ የማህበረሰቡ አባላት ጋር ያለውን ግኑኝነት ያመለክታል፡፡ እነርሱም ለጥቃቅን ጥፋቶች የተለያዩ ቅጣቶችን ሰይመዋል፡፡

አንድን ነገር ለማስታወስ የሚደረጉ ሥርአቶች የቤተ-መቅደስ ሥርዓቶች ሲሆኑ፣ እነዚህም የመስዋዕትና ተያያዥ ሥርዓቶች የአንድን የማህበረሰቡን አባል ኃላፊነት ለማሳወቅ የሚደረጉ ሥርዓቶች ናቸው፡፡ የግብዣ ቀናትና አከባበራቸውም ተዘርዝረው ተቀምጠዋል፡፡

የጤና ህጎችም ከሌሎቹ ህጎች ጋር ይመሳሰላሉ ፡፡ የንጽህናን ጉድለት ለመከላከል የተሰጡ ህጎች የሚገልጹት አንድን ነገር ለማስታወስ በተደጋጋሚ የሚደረጉ ሥርዓቶችን የንጽህና ጉድለት ያመለክታሉ፡፡ንጹህና ንጹህ ያልሆነውን ሥጋ በሚመለከት የተሰጡ ህጎች በውጫዊ እይታ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡

አይሁዳውያን ስለእነዚህ ሁሉ ህጎች በሚያስቡበት ጊዜ ሁሉም ከእግዚአብሔር የተሰጡ በመሆናችው በአእምሮአችው የተወሰኑ ልዩነቶችን ማስቀመጣቸው አይቀሬ ነው፡፡ አሥርቱ ትዕዛዛት ከእግዚአብሄር አፍ ለህዝቡ በቀጥታ የተነገሩ ናቸው፡፡ ከሌሎቹ ህጎች በተለየ እንዲታዩ የሚያደርጋቸው ይህ ነው፡፡ ሌሎቹ ህጎች በሙሴ የተጻፉ ናቸው፡፡ የቤተ መቅደስ ህጎችም ሊኖሩ የሚችሉት መቅደሱ እስካለ ብቻ ነው፡፡

የማህበረሰብ ህጎችም በአብዛኛው የአይሁድ ህዝቦች ህሊና እንደ ሃገር ጠፍቶ በሌሎች ህዝቦች ቁጥጥር እስከሆኑ ድረስ በማንም ላይ ሊተገበሩ አይችሉም፡፡ የቤተ መቅደስ አገልግሎት ሥርዓቶችም ቤተ መቅደሱ እስከተደመሰሰ ድረስ ቦታ አይኖራቸውም፡፡ እንዲሁም ጥላ የነበሩ ሥርዓቶችም (ማለትም ክርስቶስን የሚያመለክቱ የነበሩ) ቢሆኑም ዋናው እስከመጣ ድረስ ዋጋ አይኖራቸውም፡፡

 

መስከረም 30
Oct 10
 

እንደ ሙሴ ሥርዓቶች

 

ሐዋ. 15፡ 1ን ያንብቡ፡፡ ትልቅ አለመግባባትን የፈጠረው ምን ነበር? አንዳንድ ሰዎች ይህ ለአይሁድ ህዝብ አይደለም ብለው የሚያምኑት ለምንድነው? ዘፍ. 17:10

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ሃዋርያት በአንጾኪያ ከሚገኙ አገልጋዮችና ፈቃደኛ ወንጌላውያን ጋር በመሆን ነፍሳትን ለመማረክ በሚያደርጉት ጥረት ከይሁድ ወገን የሆኑ የተወሰኑ ‹‹የፈሪሳውያን እምነት›› ተከታይ የሆኑ ጥቂት አማኖች በጥቂት ጊዜ ውስጥ ወደ ሰፊ ክርክር የሚያመራ ጥያቄ ለአማኞች በማስተዋወቅ ተሳካላቸው፡፡ አማኝ ለሆኑ አህዛቦች ጥርጣሬን ፈጠሩ፡፡ እነዚህ መምህራን አንድ ሰው ለመዳን መገረዝና ከክርስቶስ መሰቀል በፊት እርሱን እንዲያመለክቱ ይደረጉ የነበሩ ሥርዓቶችን ሁሉ መጠበቅ አለበት ብለው በታላቅ ድፍረት ማስተማር ጀመሩ፡፡ አይሁዳውያን ሁልጊዜ በመለኮት ስለተሰጣቸው የአገልግሎት ስያሜ በራሳቸው እጅግ የሚኩራሩ በመሆናቸው ወደ ኢየሱስ እምነት የተለወጡት ብዙዎች ሳይቀሩ እግዚአብሔር የዕብራውያንን አምልኮ ቀድሞ የተቀበለው እስከሆነ ድረስ እግዚአብሔር ምንም አይነት ለውጥ እንዲደረግ ይፈቅዳል ብለው አያምኑም ነበር፡፡ ከዚህም የተነሳ የአይሁዳውያን ህግና በዓላት በክርስትና በዓላትና በክርስትና መመሪያ ውስጥ መካተት ይኖርበታል ብለው ግፊት አደረጉ፡፡ በቤተመቅደስ ይደረጉ የነበሩ የመስዋዕት ሥርዓቶች ሁሉ እውነተኛ ለሆነው ለእየሱስ ክርስቶስ ሞት ጥላ ወይም ምሳሌ በመሆናቸው እውነተኛው በመገለጡ ሙሴ ያስተማራቸው ሥርዓት ከዚያ በኋላ ሊደረግ እንደማያስፈልግ ለማስተዋል ዝንጉ ነበሩ፡፡

ሐዋ. 15፡ 2- 12 ያለውን ያንብቡ፡፡ ይህ ክርክር የሚረግበው እንዴት ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

“ጳውሎስ ቀጥተኛ የሆነውን የእግዚአብሔርን መመሪያ የሚጠባበቅ ሲሆን ሁልጊዜ ግን የኃይማኖት ባለስልጣናት በአማኞች ህብረት ውስጥ የሚያመጡትን ማንኛውንም ነገር የመለየት ብቃት ነበረው፡፡ እርሱ የምክክርን አስፈላጊነት ጠንቅቆ የሚያውቅ በመሆኑ በጣም አስፈላጊ ጉዳዮች ሲፈጠሩ ወንድሞችንና የቤተክርስትያን አባላትን አንድ ለማድረግና ትክክለኛውን ውሳኔ ለመወሰን የእግዚአብሔር ጥበብ እንደሚያስፈልግ ያውቅ ነበር፡፡” —Ellen G. White, The Acts of the Apostles, p. 200.

ለነብይነቱ ጥሪ እና ክርስቶስ እንዴት ጠርቶ ለመልዕክቱ እንደ ሾመው የሚናገረው ጳውሎስ ከሰፊው የቤተክርስትያን አካል ጋር ለመስራት ምን ያህል ፈቃደኛ እንደሆነ ማወቅ በጣም ደስ የሚያሰኝ ነው፡፡ ይህ ማለት ጥሪው ምንም ይሁን ምን እርሱ የቤተክርስትያን አካል መሆኑንና ከእነርሱም ጋር በተቻለ መጠን አብሮ መስራት እንዳለበት በትክክል ተረድቷል ማለት ነው፡፡

ስለ ቤተክርስትያን አመራር እርስዎ ያለዎት አመለካከት ምን ይመስላል? ተባባሪ ነዎት? መተባባር በጣም አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? እያንዳንዱ ሰው ከቤተክርስትያን ውጪ በራሱ እንደሚያስበውና መስራት እንደሚፈልገው ብቻ የሚሄድ ከሆነ እንዴት ተግባራትን ማከናወን ይቻላል?

 

ጥቅምት 1
Oct 11
 

ከአህዛብ የሆኑ አማኞች

 

ሐዋ. 15:5–29ን ያንብቡ፡፡ የጉባኤው ውሳኔና ወደዚህ ውሳኔ እንዲመጡ ያደረጋቸው ምክንያት ምን ነበር?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ውሳኔው ከአይሁዳውያን ክርክር በተቃራኒ ነበር፡፡ ይህ ተረት ወደ ክርስትና የመጡ አህዛቦች መገረዝና የአይሁድን ወግ መጠበቅ አለባቸው እንዲሁም የአይሁድ ወግና ደንብ በክርስትና መመሪያ ውስጥ መካተት አለበት የሚል ነበር፡፡ ” Ellen G. White, The Acts of the Apostles, p. 189.

በሐዋ. ሥራ 15፡10 ላይ ጴጥሮስ እነዚህን አሮጌ ህጎች ለመሸከም የሚከብድ ‹‹ቀንበር›› ብሎ መግለጹ ደስ የሚል ነው፡፡ እነዚህን ህጎች የፈጠረው ጌታ ቀንበር እንዲሆኑ ነውን? በፍጹም አይመስልም፡፡ በምትኩ ግን አንዳንድ መሪዎች ብዙዎቹን ህጎች ወደራሳቸው ባህል በመለወጥ ከበረከት ወደ ሸክም እንዲለወጡ አድርገዋቸዋል፡፡ ጉባኤው ያሰበው የአህዛብን አማኞች ከዚህ ለመታደግ ነበር፡፡

ቅዱሳን ልትሆኑ ለተጠራችሁ፡፡ በአንዳንድ ትርጉሞች ‹‹ልትሆኑ›› የተጠራችሁ የሚለው በተለየ አይነት አጻጻፍ እናገኘዋለን፡፡ ይህ ማለት ቃሉ የተርጓሚዎቹ አጠቃቀም መሆኑን ያሳያል፡፡ ነገር ግን እነዚህን ቃላት ትርጉማቸው ሳይበላሽ መጠቀም ይቻላል፡፡ ከዚያም የምናገኘው ትርጉም ‹‹ የተጠራችሁ ቅዱሳን ›› የሚል ይሆናል፡፡ ይህም ማለት ‹‹የተሰየማችሁ›› ቅዱሳን የሚለውን ትርጉም ይሰጣል፡፡

ከአህዛብ የመጡ አማኞች አሥርቱን ትዕዛዛት ላለመታዘዝ ያቀረቡት ምንም አይነት ጥያቄ እንደሌለ ያስተውሉ፡፡ እስቲ አስቡት አትግደል ወይም አታመንዝር በሚለው ትዕዛዝ ፋንታ ጉባኤው ደም አትብላ ቢላቸው ምን ይመስል እንደሆነ አይታችኋል?

ከአህዛብ ለሆኑ አማኞች የተሰጠው መመሪያ ምንድነው? (ሐዋ. 15:20, 29) እነዚህ የተለዩ ሥርዓቶች ለምን አስፈለጉ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------


ምንም እንኳ የአይሁድ አማኞች የራሳቸውን ደንብና ባህል በአህዛብ ላይ የመጫን ሀሳብ ባይኖራቸውም ፣ ጉባኤው አረማውያን በክርስቶስ አንድ ከሆኗቸው አይሁዳውያን የሚያሳዝን አንዳችም ነገር አለማድረጋቸውን እርግጠኛ መሆን ፈለጉ፡፡ ስለዚህም ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ከአህዛብ ወገን የሆኑ አማኞችን በደብዳቤ ለጣኦት ከታረደ ሥጋ ፣ከምንዝርና ከሙት ነገሮች እና ከደም እንዲርቁ መመሪያ ለመስጠት ተስማሙ፡፡ አንዳንዶች ሰንበት በተለየ ሁኔታ ስላልተጠቀሰ ፣ እርሱ ለአህዛብ አማኞች አልተሰጠም ይሉ ነበር፡፡ (በእርግጥ ላለመዋሸት ወይም ላለመግደልም በተመሳሳይ ሁኔታሥፍራ የለውም ማለት ነው፡፡

በአንዳንድ መንገዶች ከእግዚአብሄር ቃል ሳይሆን ከባህሎቻችን በመነሳት በሰዎች ላይ ጭነት እያሸከምን ይሆን? እንዲህ ከሆነ እንዴት መሆን አለበት? ሀሳብዎትን ወደ ሰንበት ትምህርት ክፍል ይዘው ይምጡ፡፡
 

ጥቅምት 2
Oct 12
 

ጰውሎስና የገላትያ ሰዎች

 

ምክሩ ምንም ያህል ግልጽ ቢሆንም ፣ አይሁድ ያልሆኑ አማኞች የአይሁድን ህግና ወግ መጠበቅ አለባቸው በማለት የራሳቸውን አመለካከት የሙጥኝ ያሉና በማስተማርም የገፉበት አልጠፉም፡፡ ይህ ነገር ለጳውሎስ በእምነት ጉዳይ ላይ ምንም ችግር እንደማያመጣ ዋጋ እንደሌለው ተራ ወሬ ሳይሆን ጠንከር ያለ አሳሳቢ ጉዳይ ነበር፡፡ ለእርሱ ይህ የክርስቶስን ወንጌል ከመካድ እኩል ነበር፡፡(ሮሜ 1:8).

ገላ. 1:1–12ን ያንብቡ፡፡ ጰውሎስ በገላትያ ያለውን ክርክር እንዴት ባለ ትኩረት ይመለከተዋል? ይህ ስለ ጥያቄው አስፈላጊነት ምን ይነግረናል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ከዚህ በፊት እንደተገለጸው የሮሜ ደብዳቤ ዋነኛ ትኩረት ሆኖ በስፋት የሚታየው የገላትያን ሁኔታ የሚመለከት ነበር፡፡ ጳውሎስ በሮሜ መልዕክት ላይ በመሆን የገላትያን መልዕክት ዋና ሐሳብ አዳብሯል፡፡ አንዳንድ የአይሁድ አማኞች እግዚአብሄር በሙሴ አማካይነት የሰጣቸው ህግ በጣም አስፈላጊ በመሆኑ ከአህዛብ ወገን የሆኑ አማኖች ሊያከብሩት እንደሚገባ አጥብቀው ይከራከሩ ነበር፡፡ ጳውሎስ እየሞከረ ያለው የዚህን ትክክለኛ ቦታና ጥቅም ነበር፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች በገላትያ ያገኙትን ዓይነት ሥፍራ በሮሜ እንዳያገኙ እየጣረ ነው፡፡

ጳውሎስ በገላትያና በሮሜ እየተናገረ ያለው ስለ አስርቱ ትዕዛዛት ነው ወይስ ስለ ሜዳዊ ሥርዓት ነው? ብሎ ጥያቄ ማንሳት ነገሩን በጣም ማቅለል ነው፡፡ በታሪክ እንደሚታወቀው ክርክሩ ከአህዛብ ወገን የሆኑ አማኞች መገረዝና የሙሴን ህግ መጠበቅ አለባቸው ወይስ የለባቸውም የሚል ነበር፡፡ በእየሩሳሌም የነበረው የመማክርት ጉባኤ ይህንን ክርክር መመሪያ አውጥቶ የቋጨ ቢሆንም አንዳንዶች ውሳኔውን ለመቀበል እምቢ ብለው ነበር፡፡

የሰንበት ትዕዛዝ በክርስትያኖች ላይ አይሰራም ለሚሉ ወገኖች መልስዎ ምንድን ነው? የወንጌልን እውነት ድርድር ውስጥ በማያስገባ ሁኔታ የሰንበትን እውነት እንዴት አድርገው ያሳያሉ?
 

ጥቅምት 3
Oct 13
 

ለተጨማሪ ጥናት:-

 

የሚከተሉትን መጸህፍት ያንብቡ፡፡ “Jew and Gentile,” pp. 188–192, 194–197; “Apostasy in Galatia,” pp. 383–388, in The Acts of the Apostles; “The Law Given to Israel,” pp. 310– 312; “The Law and the Covenants,” pp. 370–373, in Patri-archs and Prophets; “The Chosen People,” pp. 27–30, in The Desire of Ages.

ቤተክርስትያናችን የተጋድሎና የክርክር ጊዜያት እንደሚገጥማት ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን ይህ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ሰይጣን ሁልጊዜ ከቤተክርስትያን ጋር በውጊያ ላይ ነው፡፡ በጥንት ዘመን እንኳ ክርክር በቤተክርስትያን ውስጥ በአማኞች መካካል ይታይ ነበር፡፡ በቤተክርስትያን ውስጥ አንድ እንኳ መፍትሄ ያላገኘ ክርክር ካለ ቤተክርስያንን በአንጭጯ ይቀጫታል፡፡

“በተጨማሪም በአማኞች መካካል የተነሳው የውሸት መምህራን አስተሳሰብ፣ ክፍፍል፣ የስህተት ትምህርት እና ስሜታዊነት በተደጋጋሚ በገላትያ አማኞች ዘንድ ሥፍራ አግኝተዋል፡፡ እነዚህ የውሸት መምህራን የአይሁድን ባህል ከወንጌል እውነት ጋር ይቀላቅሉ ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም የነበረውን የመማክርት ጉባኤ ውሳኔን ችላ በማለት ከአህዛብ ወገን የሆኑ አማኞችን የሜዳዊውን ሥርዓት እንዲጠብቁ ይጎተጉቷቸው ነበር፡፡” —Ellen G. White, The Acts of the Apostles, p. 383.

 

የመወያያ ጥያቄዎች:

 

· በክፍላችሁ ውስጥ ረቡዕ መጨረሻ ባለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፡፡ እርስዎ በቤተክርስትያንዎ ውስጥ ወይም በቤትዎ ውስጥ ወይም በራስዎ ውስጥ በሌሎች ላይ ሸክም አድርገው የሚጭኗቸው አስፈላጊ ያልሆኑ ምን ዓይነት ነገሮች አሉ? እነዚህን ነገሮች በእርግጥ ማድረጋችንን የምናውቀው እንዴት ነው? ወይም በተቃራኒው መንገድ ርቆ በመሄድ ችግር ውስጥ እንገኛለን?

· ክርክር ምንድነው? ለእነዚህ አስተሳሳቦች ምላሸ የምንሰጠው እንዴት ነው? በትክክል ፊት ለፊት ስናያቸው እነዚህ ክርክሮች ስህተት የሚሆኑትና ይህንን አስተሳሳብ የሚደግፉ ሰዎች አስርቱ ትዕዛዛት አስፈላጊ አይደሉም በሚሉት አይነት ሲኖሩ የማይታዩት ለምንድን ነው?

· ገላ. 1:1-12ን ያንብቡ፡፡ ጳውሎስ በወንጌል ማስተዋሉ በፍጹም የማይደራደርና፣ በእምነት አስተምህሮዎች ላይ ምን ያህል ጽኑ እና ትጉህ መሆኑን አጥኑ፡፡ እኛም በዚህ የብዙሃን ድምጽ በሚሰማበት እንዲሁም ነገሮች አንጻራዊ ናቸው ብለው ሰዎች በሚያምኑበት ዘመን በአንዳንድ መሰረታዊ እምነቶች ላይ ሳንንሸራተት ጸንተን ልንቆም የሚንችለው እንዴት ነው? ይህ አንዳንድ አስተምህሮዎች ድርድር እንደማያስፈልጋችው ምን ይነግረናል?

· የፕሮቴስታንትን ተሓድሶ ስላመጣው ጉዳይ ተነጋገሩ፡፡ ሳይፈቱ የቀሩ ልዩነቶች ምንድናችው?