ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ገላ. 3፡ 21-25፤ ዘሌ.18፡ 5፤ ሮሜ 3፡ 9-19፤ 1ቆሮ. 9፡ 20፤ ሮሜ 3፡ 1፣ 2፤ 8፡ 1-4፡፡
የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - ‹‹ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ከማመን የሆነው የተስፋ ቃል ለሚያምኑ ይሰጥ ዘንድ መጽሐፍ ከኃጢአት በታች ሁሉን ዘግቶታል›› (ገላ. 3፡22)፡፡
ከስደት ተመላሽ እርግቦች በቀን ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ማይሎችን በመብረር ወደ መዳረሻቸው በሚያስደንቅ ትክክለኛነት በመድረስ ችሎታቸው ይታወቃሉ፡፡ ሆኖም ከሁሉ የተሻሉ ከስደት ተመላሽ እርግቦች እንኳን አንዳንድ ጊዜ ግራ ይጋቡና (አቅጣጫው ይጠፋቸውና) ወደ መነሻቸው ሳይመለሱ ይቀራሉ፡፡ የዚህ አይነት አስከፊ ክስተት የተከሰተው በእንግሊዝ አገር ሲሆን ከስድስት መቶ ሺህ ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው ወደ ሃያ ሺህ የሚጠጉ ወፎች ወደ መስፈሪያቸው ሳይመለሱ መቅረታቸው ነበር፡፡
አብዛኞቻችን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ተለማምደን እንደምናውቀው ግራ መጋባት ወይም መጥፋት አስደሳች ነገር አይደለም፡፡ በፍርሃትና በስጋት እንድንሞላ ያደርገናል፤ በፍርሃት እንድንሸበር ሊያደርገንም ይችላል፡፡
በመንፈሳዊው ዓለምም ይህ እውነት ነው፡፡ ክርስቶስን ከተቀበልን በኋላ እንኳን ልንጠፋ፣ ወይም በፍጹም ወደ ጌታ መመለስ እስከማንችል ድረስ ግራ ልንጋባ እንችላለን፡፡
ነገር ግን መልካሙ ዜና እግዚአብሔር እኛን ለራሳችን አለመተዉ ነው፡፡ በወንጌል ውስጥ እንደተገለጠው እርሱ የእምነት መንገድን ካርታ ያዘጋጀ ሲሆን ካርታው ደግሞ ሕግንም ያካትታል፡፡ ብዙ ሰዎች ሕግን ከወንጌል ለመነጠል ይሞክራሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ እንደሆኑ አድርገው ያያሉ፡፡ ይህ አመለካከት ስህተት ብቻ ሳይሆን አሳዛኝ የሆኑ ውጤቶችም ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ ያለ ሕግ ወንጌል ሊኖር አይችልም፡፡ ወንጌልን ያለ ሕግ ማስተዋል ከባድ ነው፡፡
“እንግዲህ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ይቃወማልን?” (ገላ. 3፡ 21)፡፡ አስተያየቶቹ ተቃዋሚዎቹን ሕግን የማንኳሰስ አመለካከት አለው ብለው ወደ መደምደም ሊመሩአቸው እንደሚችሉ ስለተሰማው ወይም ስለ እግዚአብሔር ተስፋዎች ቀዳሚነት የሚሰጣቸው አስተያየቶች ሙሴንና ሕግን የመደምሰሻ ሰምለበስ ዘዴዎች ናቸው ብለው እንደሚያስቡ ስለተሰማው ጳውሎስ እነርሱ የሚያስቡትን ያንኑ ጥያቄ፡-‹‹ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ይቃወማል ትላላችሁን?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ለዚህ ጥያቄ ጳውሎስ በግልጽ አይደለም በማለት መልስ ይሰጣል፡፡ እግዚአብሔር ራሱን ስለማይቃወም የዚህ አይነት ድምዳሜ የማይቻል ነው፡፡ ሕግ ከተስፋ ቃል ጋር የሚቃረን አይደለም፡፡ በእግዚአብሔር አጠቃላይ የድነት እቅድ ውስጥ ሁለቱም የተለያዩ ሚናዎችና ተግባሮች አሉአቸው፡፡ የጳውሎስ ተቃዋሚዎች ስለ ሕግ ሚና ምን አይነት የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ነበሩአቸው? ገላ. 3፡ 21፣ ዘሌ. 18፡ 5ን ከዘዳ. 6፡ 24 ጋር ያነጻጽሩ፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ይህ ሕዝብ ሕግ መንፈሳዊ ሕይወት ሊሰጣቸው እንደሚችል አመኑ፡፡ ምናልባት የስህተታቸው መነሻ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን የሚኖሩ ሰዎች እንዴት መኖር እንዳለባቸው ለመምራት የተሰጡትን እንደ ዘሌዋውያን 18፡ 5 እና ዘዳግም 6፡ 24 ያሉትን የብሉይ ኪዳን ንባቦች በስህተት ከመተርጎማቸው የተነሳ ሊሆን ይችላል፡፡ ሕግ በቃል ኪዳኑ ውስጥ ሆኖ ሕይወትን መርቷል፣ ነገር ግን እነርሱ ሕግ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት ምንጭ ነው ብለው ደመደሙ፡፡ ነገር ግን ‹‹ሕያው የማድረግ›› ችሎታ በእግዚአብሔርና በእርሱ መንፈስ ብቻ ሥራ ላይ የሚውል ኃይል ስለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ያደርጋል (2 ነገ. 5፡ 7፣ ነህ. 9፡ 6፣ ዮሐ. 5፡ 21፣ ሮሜ 4፡ 17)፡፡ ሕግ ማንንም ቢሆን በመንፈሳዊነት ሕያው ሊያደርግ አይችልም፡፡ ይህ ማለት ግን ሕግ የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ተቃራኒ ነው ማለት አይደለም፡፡
ጳውሎስ ሕግ ሕይወት መስጠት እንደማይችል ለማረጋገጥ በመፈለግ በገላትያ 3፡ 22 ላይ እንዲህ በማለት ጽፏል፣ ‹‹መጽሐፍ ከኃጢአት በታች ሁሉን ዘግቶታል፡፡›› ጳውሎስ እኛ ምን ያህል መጥፎዎች እንደሆንን ለማሳየት ሲል በሮሜ 3፡ 9-19 ላይ ከብሉይ ኪዳን የተውጣጡ ጥቅሶችን ያመጣል፡፡ እነዚህ ጥቅሶች በዘፈቀደ የተያያዙ አይደሉም፡፡ የኃጢአት ችግር ማዕከል ከሆነው ሰብአዊ ልብን ከሚቀስፍ የራስ ወዳድነት አመለካከት ይጀምርና የኃጢአትን የመስፋፋት ባሕርይና በመጨረሻም ዓለም አቀፋዊነቱን ወደሚገልጹ ጥቅሶች ይሄዳል፡፡ ማብራራት የሚፈልገው ነጥብ ምንድር ነው? ከኃጢአት ስፋትና ከሕግ ውስንነቶች የተነሳ የዘላለም ሕይወት የተስፋ ቃል ወደ እኛ መምጣት የሚችለው ክርስቶስ በእኛ ፈንታ ሆኖ በፈጸመው ታማኝነት አማካይነት ብቻ ነው፡፡ በድጋሚ፣ የፕሮቴስታንት ተሃድሶን ወደ ፊት ያንቀሳቀሰው ታላቅ እውነት በዚህ ቦታ ይገኛል፡፡
ሕግ ማዳን ባይችልም ለሕግ መታዘዛችን ምን ታላላቅ ጥቅሞችን ያስገኝልናል? ለእግዚአብሔር ሕግ በመታዘዝዎ በሕይወትዎ ምን ተግባራዊ የሆነ መልካም ነገር ተለማምደዋል?
ጳውሎስ በገላትያ 3፡ 23 ላይ ‹‹እምነት ከመምጣቱ በፊት ከሕግ በታች ነበርን›› በማለት ይጽፋል፡፡ ጳውሎስ ‹‹እኛ›› ሲል በገላትያ ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ የነበሩ የአይሁድ አማኞችን እያመለከተ ነው፡፡ ከሕግ ጋር ትውውቅ የነበራቸው እነርሱ ስለነበሩ ከገላትያ 2፡ 15 ጀምሮ በተለየ ሁኔታ እየተናገራቸው ነበር፡፡ ይህ በገላትያ 3፡ 23 ላይ ባለው ‹‹እኛ›› እና በገላትያ 3፡ 26 ላይ ባለው ‹‹እናንተ›› በሚሉ ቃላት መካከል ባለው ንጽጽር ሊታይ ይችላል፡፡ ገላትያ 3፡ 23 ‹‹እምነት ከመምጣቱ በፊት›› ተብሎ ይነበባል፤ ጳውሎስ ሕግ ከክርስቶስ በፊት እና በኋላ ያለውን ቦታ እያነጻጸረ ስለሆነ ‹‹እምነት›› የሚለው ቃል እያመለከተ ያለው በአጠቃላይ የክርስቲያን እምነትን ሳይሆን ኢየሱስን ራሱን ሊሆን ይችላል፡፡
ጳውሎስ ከክርስቶስ መምጣት በፊት አይሁዶች ‹‹ከሕግ በታች›› ነበሩ ይላል፡፡ ‹‹ከሕግ በታች›› ሲል ምን ማለቱ ነው? ገላ. 3፡ 22፣ 23ን ከሮሜ 6፡ 14፣ 15፤ 1 ቆሮ. 9፡ 20፤ ገላ. 4፡ 4፣ 5፣ 21፤ 5፡ 18 ጋር ያነጻጽሩ፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጳውሎስ ‹‹ከሕግ በታች›› የሚለውን ሀረግ በደብዳቤዎቹ ውስጥ አሥራ ሁለት ጊዜ ይጠቀማል፡፡ ካለው ስፋት አንጻር የተለያዩ ዓይነት ትርጉሞች ሊኖሩት ይችላል፡፡
1. ‹‹ከሕግ በታች›› መሆን እንደ የድነት አማራጭ መንገድ (ገላ. 4፡ 21)፡፡ በገላትያ የነበሩ ተቃዋሚዎች ሕይወት ሰጭ የሆነውን ጽድቅ በመታዘዝ (በሥራ) ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ነበር፡፡ ነገር ግን ጳውሎስ አስቀድሞ ግልጽ እንዳደረገው ይህ የማይቻል ነገር ነው (ገላ. 3፡21፣ 22)፡፡ እንዲያውም የገላትያ ሰዎች ከሕግ በታች ለመሆን በመፈለግ ክርስቶስን መቀበል እምቢ እያሉ እንደነበር ጳውሎስ ኋላ ይጠቁማል፡፡
2. ‹‹ከሕግ በታች›› መሆን ከኩነኔው ሥር መሆን በሚል ስሜት (ሮሜ 6፡ 14፣ 15)፡፡ ሕግ የኃጢአት ስርየት መስጠት ስለማይችል የእርሱን ጥያቄ መጣስ በመጨረሻ ኩነኔን ያመጣል፡፡ ሰብዓዊ ፍጡራን በሙሉ ራሳቸውን የሚያገኙበት ሁኔታ ይህ ነው፡፡ ሕግ እርሱን በመጣስ በራሳቸው ላይ የሞት ፍርድን ያመጡትን በእስር ቤት በመዝጋት እንደ የእስር ቤት ጠባቂ ያገለግላል፡፡ በነገው ትምህርት እንደምንመለከተው መጠበቅ የሚለው ቃል (ገላ. 3፡ 23) በዚህ ንባብ ውስጥ ጳውሎስ ‹‹ከሕግ በታች›› የሚለውን ሀሳብ ያሳያል፡፡
ከዚህ ጋር ግንኙነት ያለው ‹‹ከሕግ በታች›› ተብሎ የተተረጎመው ኤኖሞስ የሚለው የግሪክ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም ‹‹በሕግ ውስጥ›› መሆን የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ከክርስቶስ ጋር ባለው አንድነት አማካይነት በሕግ መስፈርት ውስጥ መኖር ማለት ነው (1 ቆሮ. 9፡ 21)፡፡ በእምነት አማካይነት ጻድቅ የሆኑት ብቻ በሕይወት ስለሚኖሩ (ገላ. 3፡ 11) ‹‹በሕግ ሥራ››፣ ማለትም ያለ ክርስቶስ ሕግን ለመጠበቅ በመሞከር መጽደቅ አይቻልም፡፡ ይህ እውነት ሕግን አይሽርም፤ ሕግ የዘላለም ሕይወት መስጠት እንደማይችል ብቻ ያሳያል፡፡ ይህን ለማድረግ ጊዜው አልፎበታል፡፡
ጳውሎስ ስለ ሕግ ሁለት መሰረታዊ ድምዳሜዎችን ይሰጣል፡- (1) ሕግ ለአብርሃም የተሰጠውን የተስፋ ቃል አይሽርም ወይም አይደመስስም (ገላ. 3፡ 15-20)፤ ሕግ ከተስፋው ቃል ጋር አይቃረንም (ገላ. 3፡ 21፣ 22)፡፡
ታዲያ ሕግ የሚጫወተው ሚና ምንድር ነው? ጳውሎስ ሕግ የተጨመረው ‹‹ከመተላለፍ የተነሳ ነው›› ብሎ ከጻፈ በኋላ (ገላ. 3፡ 19) ከሕግ ጋር በተገናኘ ሁኔታ ሶስት የተለያዩ ቃላትን ወይም ሀረጎችን በመጠቀም አስፋፍቶ ያብራራል፡‹‹እንጠበቅ ነበር›› (ቁ. 23)፣ ‹‹ተዘግተን ነበር›› (ቁ. 23)፣ ‹‹ሞግዚት›› (ቁ. 24)፡፡ ገላትያ 3፡ 19-24ን በጸሎትና በጥንቃቄ ያንብቡ፡፡ ጳውሎስ ስለ ሕግ ምን እያለ ነው?
ጳውሎስ በገላትያ 3፡ 19 ላይ ስለ ሕግ የሰጣቸውን አስተያየቶች አብዛኞቹ ዘመናዊ ትርጉሞች የሚተረጉሙት ሙሉ በሙሉ አሉታዊ በሆኑ ቃላት ነው፡፡ ነገር ግን በግሪክ የተጻፈው የመጀመሪያው ጽሁፍ እንደዚህ ወደ አንድ ወገን ብቻ ያደላ አልነበረም፡፡ ‹‹መጠበቅ›› (ቁ. 23) ተብሎ የተተረጎመው የግሪክ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም ‹‹ዘብ መቆም›› ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን ‹‹በቁጥጥር ሥር ማዋል›› ወይም ‹‹ክትትል ማድረግ›› በሚል አሉታዊ መልኩ ጥቅም ላይ መዋል ቢችልም (2 ቆሮ. 11፡ 32)፣ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በአጠቃላይ ሲታይ ‹‹መከላከል›› ወይም ‹‹መጠበቅ›› የሚል አዎንታዊ ስሜት አለው (ፊል. 4፡ 7፣ 1 ጴጥ. 1፡ 5)፡፡ ‹‹መዘጋት›› ተብሎ ለተተረጎመው ቃልም ይህ ሁኔታ እውነት ነው (ገላ. 3፡ 23)፡፡ ‹‹መዝጋት›› (ዘፍ. 20፡ 18)፣ ‹‹መዝጋት›› (ዘጸ. 14፡ 3፣ ኢያሱ 6፡ 1፣ ኤር. 13፡ 19)፣ ‹‹መክበብ›› (ሉቃስ 5፡ 6)፣ ‹‹መዝጋት›› (ሮሜ 11፡ 32) ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡ እነዚህ ምሳሌዎች እንደሚያመለክቱት፣ በአገባቡ መሰረት፣ ይህ ቃል አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ትርጉም ሊኖረው ይችላል፡፡
ለእሥራኤል ልጆች ሕግ (የግብረገብና ሜዳዊ ሕግ) ምን ጥቅም ሰጣቸው? ሮሜ 3፡ 1፣ 2፤ ዘዳ. 7፡ 12-24፤ ዘሌ. 18፡ 20-30፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጳውሎስ ስለ ሕግ አሉታዊ የሆኑ ቃላትን መናገር ሲችል (ሮሜ 7፡ 6፣ ገላ. 2፡ 19)፣ ስለ እርሱ መናገር የሚችላቸው ብዙ አዎንታዊ ነገሮች ነበሩ (ሮሜ 7፡ 12፣ 14፤ 8፡ 3፣ 4፤ 13፤ 8)፡፡ ሕግ እግዚአብሔር በእሥራኤል ሕዝብ ላይ ያስቀመጠው እርግማን አልነበረም፤ ከዚህ በተቃራኒ በረከት እንዲሆን ታቅዶ ነበር፡፡ ምንም እንኳን የመስዋዕት ስርዓቱ በመጨረሻ ኃጢአትን ማስወገድ ባይችልም ወደሚችለው መሲህ አመልክቶ ነበር፣ የሰውን ባሕርይ የሚመሩ ሕጎቹ የጥንቱን ስልጣኔ ከቀሰፉ ብዙ ክፋቶች የእሥራኤልን ሕዝብ ጠበቁአቸው፡፡ ጳውሎስ በሌላ ቦታ ስለ ሕግ አዎንታዊ አስተያየቶችን በሰጠው መሰረት በዚህ ቦታ የሰጣቸውን አስተያየቶች ሙሉ በሙሉ አሉታዊ በሆነ ሁኔታ መረዳት ስህተት ሊሆን ይችላል፡፡ ያለ አግባብ ጥቅም ላይ ስለ ዋለ ጥሩ ነገር አስቡ፡፡ ለምሳሌ፣ በሽታን ለማከም የተሰራ መድኃኒት እንደ አደንዛዥ እጽ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፡፡ ይህን መርህ የተከተሉ ምን ምሳሌዎችን በራስዎ ሕይወት አዩ? ጥሩ የሆነ ነገር በመጥፎ ሁኔታ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል ማወቃችን ጳውሎስ በዚህ ቦታ እየተናገረ ያለውን ነገር ለማስተዋል ይረዳን ይሆን?
በገላትያ 3፡ 23 ውስጥ ጳውሎስ ሕግን እንደሚጠብቅና እንደሚከላከል ኃይል ይገልጸዋል፡፡ በቁጥር 24 ላይ በምን ይመስለዋል? ምንስ ማለት ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
‹‹ሞግዚት›› ተብሎ የተተረጎመው ቃል የመጣው ፓይዳጎጎስ ከሚል የግሪክ ቃል ነው፡፡ አንዳንድ ትርጉሞች ‹‹ሕግ አስከባሪ››(NRSV)፣ ‹‹አስተማሪ››(NKJV)፣ ወይም ‹‹ጠባቂ››(ESV) ተብለው ተተርጉመዋል፣ ነገር ግን ማንኛውም አንድ ቃል ብቻውን ሙሉ ትርጉሙን ሊያካትት አይችልም፡፡ ፓይዳጎጎስ በሮም ግዛት ውስጥ የጌታው ልጆች ዕድሜያቸው ስድስት ወይም ሰባት ዓመት ከሆነ ጀምሮ ወደ ብስለት ዕድሜ እስኪደርሱ ድረስ በእነርሱ ላይ ሙሉ ስልጣን የተሰጠው ባሪያ ነው፡፡
ፓይዳጎጎስ የጌታውን ልጆች ገላ እንደማጠብ፣ ምግባቸውን እንደመስጠት እና ከማንኛውም አደጋ እንደመከላከል ያሉ አካላዊ ፍላጎቶችን ከማሟላት በተጨማሪ ልጆቹ ወደ ትምህርት ቤት መሄዳቸውንና የቤት ሥራቸውን መሥራታቸውን የመቆጣጠር ኃላፊነት ነበረበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግብረገብን ማስተማርና ለራሱ መለማመድ ብቻ ሳይሆን እነዚህን መልካም ባሕርያት ልጆቹ መማራቸውንና ሥራ ላይ ማዋላቸውንም የማረጋገጥ ኃላፊነት ነበረበት፡፡
ምንም እንኳን አንዳንድ ፓይዳጎጎሶች ደጎችና በሥራቸው በሚተዳደሩት የሚወደዱ ቢሆኑም በአብዛኛው የጥንት ስነ-ጽሁፍ ጥብቅ የሆኑ ደንብ አስከባሪዎች አድርጎ ይገልጻቸዋል፡፡ ሰዎች እንዲታዘዙአቸው የሚያደርጉት በማስፈራራትና በተግሳጽ ብቻ ሳይሆን በመግረፍና በመደብደብም ነበር፡፡
ጳውሎስ ሕግን እንደ ፓይዳጎጎስ አድርጎ መግለጹ የህግን ሚና ለመረዳቱ ተጨማሪ ማብራሪያ ነው፡፡ ሕግ የተሰጠው ኃጢአትን ለማመልከትና ለትምህርት ነው፡፡ የዚህ ስራ ባሕርይ እንደሚያሳየው ሕግ እኛን እንደ ኃጢአተኞች ስለሚዘልፈንና ስለሚኮንነን አሉታዊ ገጽታ አለው፡፡ ነገር ግን ሕግ የሚያመጣው ኩነኔ ወደ ክርስቶስ ስለሚመራን እግዚአብሔር ይህን ‹‹አሉታዊ›› ሁኔታ እንኳን ለጥቅማችን ይጠቀመዋል፡፡ ስለዚህ ሕግና ወንጌል እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ አይደሉም፡፡ እግዚአብሔር ያዘጋጀው ሁለቱም ለድነታችን አብረው እንዲሰሩ ነበር፡፡ ‹‹በዚህ ጥቅስ ውስጥ (ገላ. 3፡ 24)፣ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያው ጳውሎስ አማካይነት እየተናገረ ያለው ስለ ግብረገብ ሕግ ነው፡፡ ሕግ ለእኛ ኃጢአትን በማሳየት ክርስቶስ እንደሚያስፈልገን እንዲሰማንና ለእግዚአብሔር መናዘዝንና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን በመለማመድ ይቅርታንና ሰላምን ለማግኘት ወደ እርሱ እንድንሸሽ ያደርገናል፡፡››—Ellen G. White, Selected Messages, book 1,p. 234.
የራስዎን ተግባሮች፣ ቃላቶችና ሀሳቦች ከሕግ ጋር ያወዳደሩት መቼ ነበር? ከሕግ ጽሕፈት ጋር ብቻ ሳይሆን ከመንፈስ ጋር በማወዳደር ንጽጽሩን አሁን ያድርጉ (ማቴ. 5፡ 28፣ ሮሜ 7፡ 6)፡፡ እርስዎ ምን ያህል ለውጥ አመጡ? ጳውሎስ በዚህ መልእክት ላይ ስላለው ነጥብ መልስዎ ምን ነገረዎት?
ጳውሎስ በገላትያ 3፡ 15 ላይ የሰጠውን አስተያየት ብዙዎች ሕግን ሙሉ በሙሉ እንደማይቀበል አድርገው ተርጉመውታል፡፡ ጳውሎስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሌላ ቦታ ስለ ሕግ ከሰጠው አዎንታዊ አስተያየት አንጻር ይህ አባባል ትርጉም አይሰጥም፡፡ ታዲያ ምን ማለቱ ነው?
በመጀመሪያ፣ በሕግ ኩነኔ ሥር አይደለንም ማለቱ ነው (ሮሜ 8፡ 3)፡፡ እንደ አማኝነታችን በክርስቶስ ስለሆንን በጸጋ ስር የመሆንን እድል አግኝተናል (ሮሜ 6፡ 14፣ 15)፡፡ ይህ በአገልግሎት ሂደት ውስጥ ለምንፈጽማቸው ስህተቶች ሳንፈራ ክርስቶስን በሙሉ ልባችን እንድናገለግለው ነጻነት ይሰጠናል፡፡ በወንጌል ያለው ነጻነት ማለት ይህ ነው፤ ይህ አንዳንድ ሰዎች በክርስቶስ የተገኘ ‹‹ነጻነት›› ብለው በመጥራት ሕግን መታዘዝ አያስፈልግም ከሚሉት የተለየ ነው፡፡ ነገር ግን ለሕግ አለመታዘዝ ኃጢአት ስለሆነ ኃጢአት ነጻነት ሳይሆን ባርነት ነው (ዮሐ. 8፡ 34)፡፡ ሮሜ 8፡ 1-3፡፡ በሕግ ኩነኔ ሥር አለመሆን ማለት ምን ማለት ነው? ይህ አስደናቂ እውነት በኑሮአችን ላይ ተጽእኖ የሚኖረው እንዴት ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
በክርስቶስ ይቅርታ ከማግኘታችን የተነሳ አሁን ከሕግ ጋር ያለን ግንኙነት የተለየ ነው፡፡ አሁን እርሱን ደስ የሚያሰኝ ሕይወት እንድንኖር ተጠርተናል (1 ተሰ. 4፡ 1)፤ ይህን ጳውሎስ በመንፈስ መራመድ ብሎ ይጠራዋል (ገላ. 5፡ 18)፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የግብረገብ ሕግ ተግባራዊ አይደለም ማለት አይደለም- ጉዳዩ ይህ አልነበረም፡፡ በህግ ኃጢአት እንደሚታወቅ እንደዚህ በግልጽ እስካየን ድረስ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ሕግ የእግዚአብሔር ባሕርይ መግለጫ ስለሆነ ሕግን በመታዘዝ የእርሱን ባሕርይ እናንጸባርቃለን፡፡ ከዚህም በላይ የደንቦችን ስብስብ ብቻ ሳይሆን ሕግ በፍጹም ሊያደርግልን ያልቻለውን ነገር ያደረገልንን የኢየሱስን ምሳሌ እንከተላለን፡፡ ሕግን በልባችን በመጻፍ (ዕብ. 8፡ 10) የሕግ ቅዱስ መስፈርት በሕይወታችን ተፈጻሚ እንዲሆን ያደርጋል (ሮሜ 8፡ 4)፡፡ ይህ ማለት ከኢየሱስ ጋር ባለን ግንኙነት ከዚህ በፊት አድርገን ከምናውቀው በላይ ሕግን የመታዘዝ ኃይል ይኖረናል፡፡
ሮሜ 8፡ 4ን ያንብቡ፡፡ በዚህ ቦታ ጳውሎስ ምን እያለ ነው? ይህ የተስፋ ቃል በሕይወትዎ እንዴት ተገልጦ አዩ? በተመሳሳይ ጊዜ፣ ምንም ዓይነት አዎንታዊ ለውጦችን ቢለማመዱም፣ ድነት ሁል ጊዜ በምንም ሳይሆን ክርስቶስ ለእኛ ባደረገልን ላይ መመስረት ያለበት ለምንድር ነው?
“በገላትያ ውስጥ ስላለው ሕግ ተጠይቄአለሁ፡፡ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣን ሞግዚት የትኛው ሕግ ነው? መልሴ ሜዳዊው ስርዓትና አስርቱ ትዕዛዛት ናቸው፡፡
‹‹ክርስቶስ የመላው አይሁድ ኢኮኖሚ መሰረት ነበር፡፡ አቤል ለመሞት ምክንያቱ ቃየል ለመዳን ወደ ክርስቶስ በሚያመለክት በመስዋዕቱ ስጦታ የተወከለውንና የኢየሱስ ክርስቶስን ደም የሚወክለውን መስዋዕት ባለማቅረብ በመታዘዝ ትምህርት ቤት ያለውን የእግዚአብሔርን እቅድ ለመቀበል እምቢ ማለቱ ነበር፡፡ ቃየል ለዓለም ሊፈስ ያለውን የክርስቶስን ደም የሚወክለውን ደም ማፍሰስ እምቢ አለ፡፡ መላው ስርዓት የተዘጋጀው በእግዚአብሔር ሲሆን ክርስቶስ የመላው ስርዓት መሰረት ሆነ፡፡ ይህ ሞግዚትነቱ ኃጢአተኛ ሰብአዊ ወኪሎችን የመላው አይሁድ ኢኮኖሚ መሰረት ወደሆነው ወደ ክርስቶስ የማምጣት ሥራው ጅምር ነበር፡፡
‹‹ከቤተ መቅደስ ጋር በተገናኘ ሁኔታ ያገለግሉ የነበሩ ሰዎች ክርስቶስ በሰብአዊ ዘር ፈንታ የሚያደርገውን ጣልቃ መግባት በተመለከተ ያለማቋረጥ ትምህርት እየተማሩ ነበር፡፡ ይህ አገልግሎት በእያንዳንዱ ልብ ውስጥ የመንግስቱ ሕግ ለሆነው ለእግዚአብሔር ሕግ ፍቅርን ለመፍጠር ታቅዶ የተዘጋጀ ነበር፡፡›› —Ellen G. White, Selected Messages, book 1, p. 233.
‹‹የአስርቱ ትዕዛዛት ሕግ ከምህረት አንጻር ከመታየት ይልቅ ነገሮችን ከመከልከል አንጻር መታየት የለበትም፡፡ አታድርጉዎቹ ስንታዘዛቸው ደስታ የምናገኝባቸው እርግጠኛ ዋስትናዎች ናቸው፡፡ በክርስቶስ ሆነን ስንቀበለው ለዘላለም ደስታ የሚያመጣ የባሕርይ ንጽህና እንዲኖረን ይሰራል፡፡ ለታዛዦች የመከላከያ አጥር ነው፡፡›› —Ellen G. White, Selected Messages, book 1, p. 235.
በሕይወታችን ኃጢአትን እንዴት ማሸነፍ እንችላለን ከሚል ጥያቄ ጋር ሁል ጊዜ እንታገላለን፡፡ ኃጢአትን ድል ስለማድረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን የተስፋ ቃሎች አሉ? እነዚህ ተስፋዎች እርግጠኛ እንዲሆኑ ራሳችንን በተሻለ ቦታ ማስቀመጥ የምንችለው እንዴት ነው? በተመሳሳይ ሁኔታ፣ የድነት ሙሉ ተስፋችንን በምናገኛቸው ድሎች ሳይሆን ክርስቶስ ለእኛ በፈጸመው ድል ላይ ማስቀመጣችንን እርግጠኞች ለመሆን መጠንቀቅ ያለብን ለምንድር ነው?
ብዙ ጊዜ ክርስቲያኞች ሕግ ተሽሮአል ሲሉ እንሰማቸዋለን፡፡ ነገር ግን እነዚሁ ክርስቲያኖች ኃጢአትን በመቃወም ይናገራሉ፣ ይህን ሲያደርጉ በእርግጥ ሕግ አለመሻሩን እየተናገሩ ናቸው፡፡ ታዲያ ሕግ ተሽሮአል ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? (ሀሳብ፡- ይህ አባባል በተለምዶ የሚነሳው ከየትኛው ትዕዛዝ አገባብ ነው?)
ማጠቃለያ፡- ሕግ የተሰጠው ኃጢአተኞችን ክርስቶስ እንደሚያስፈልጋቸው ለመጠቆም ነበር፡፡ እንደ ሞግዚት ስለ እግዚአብሔር ትምህርት እና ከክፉ ጥበቃ ይሰጠናል፡፡ ነገር ግን እንደ ሕግ አስከባሪ ኃጢአተኛነታችንን በመጠቆም ኩነኔን ያመጣል፡፡ ክርስቶስ ከሕግ ኩነኔ ነጻ በማውጣት ሕጉን በልባችን ይጽፋል፡፡