ወንጌል በገላትያ መጽሐፍ ውስጥ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2017

ከሐምሌ 22-28

ስድስተኛ ትምህርት

Jul 29 - Aug 4
 

የተስፋው ተቀዳሚነት

 

ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ገላ. 3፡15-20፣ ዘፍ. 9፡11- 17፣ ማቴ. 5፡17-20፣ ዘጸ. 16፡22-26፣ ዘፍ. 15፡1-6፡፡

 

የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - “ርስቱ በሕግ ቢሆንስ እንግዲያስ በተስፋ ቃል አይሆንም፤ በተስፋ ቃል ግን እግዚአብሔር ለአብርሃም ሰጥቷል›› (ገላ. 3፡18)፡፡

የሆነ ሰው አንድ ፖለቲከኛን እንዲህ በማለት ጠየቀው፣ ‹‹የምረጡኝ ዘመቻ ስታደርግ የገባሃቸውን ቃሎች በሙሉ ጠብቀሃልን?›› እርሱም መልሶ ‹‹አዎን፣…ቢያንስ እጠብቃለሁ ብዬ ያቀድኳቸውን በሙሉ ጠብቄያለሁ›› አለ፡፡

በዚህም ሆነ በዚያ በሆነ ጊዜ የገባውን ቃል ያልጣሰ ሰው ማን ነው? የገባውን ቃል ያልፈጸመ ወይም የተገባለት ቃል ሳይፈጸምለት ያልቀረ ሰው ማን ነው? አንዳንድ ሰዎች ቃላቸውን ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም አቅደው ቃል ይገባሉ፣ ነገር ግን ኋላ ቃላቸውን ሳይፈጽሙ ይቀራሉ፤ ሌሎች ደግሞ ድምጽ ከአፋቸው ሲወጣ ወይም ቃላቶች ከጣቶቻቸው ሲወጡ ሙሉ በሙሉ ውሸት እንደሆነ እያወቁ ቃል ይገባሉ፡፡

ለእኛ የተገቡልን የእግዚአብሔር ተስፋዎች ሙሉ በሙሉ ከዚህ የተለዩ በመሆናቸው ታድለናል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እርግጠኛና የማይለወጥ ነው፡፡ ጌታ ‹‹እኔ ተናግሬያለሁ እፈጽምማለሁ፣ አስቤአለሁ አደርግማለሁ›› ይላል (ኢሳ. 46፡11)፡፡ በዚህ ሳምንት ትምህርት ጳውሎስ ትኩረታችንን የሚስበው እግዚአብሔር ለአብርሃም በገባው ቃል ኪዳንና ከ430 ዓመት በኋላ ለእሥራኤል በተሰጠው ሕግ መካከል ወዳለው ግንኙነት ነው፡፡ በሁለቱ መካከል ያለውን ግንኙነት እንዴት ማስተዋል እንችላለን? ይህ ወንጌልን ለመስበክ ምን እንደምታ አለው?
 

ሐምሌ 23
Jul-30
 

ሕግና እምነት (ገላ. 3፡ 15-18)

 

ምንም እንኳን የአብርሃም ሕይወት በመጀመሪያ በእምነት የሚታወቅ መሆኑን ተቃዋሚዎቹ ቢያምኑም ከአራት ምዕተ አመት በኋላ እግዚአብሔር ሕጉን ለእሥራኤል ለምን ሰጠ? የሚል ጥያቄ እንደሚኖራቸው ጳውሎስ አወቀ፡፡ የህግ መሰጠት ከዚያ በፊት የነበረውን ስምምነት ዋጋ አያሳጣውምን? ጳውሎስ በሰው የመጨረሻ ኑዛዜና ኪዳን እና እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር በፈጸመው ቃል ኪዳን መካከል ያለውን መመሳሰል ያሳየበት ነጥብ ምንድን ነው? ገላ. 3፡ 15-18፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ቃል ኪዳንና ኑዛዜ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ቃል ኪዳን በሁለት ወይም ከሁለት በላይ በሆኑ ሰዎች መካከል የሚፈጸም የጋራ ስምምነት ነው፤ ይህ ብዙ ጊዜ ‹‹ኮንትራት›› ወይም ‹‹ውል›› ይባላል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ኑዛዜ የአንድ ሰው መግለጫ ነው፡፡ ሴፕቱጀንት የሚባለው የግሪኩ የብሉይ ኪዳን ትርጉም እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ለጋራ ስምምነቶች ወይም ኮንትራቶች ጥቅም ላይ በሚውል በግሪኩ ሲንቴኬ (syntheke) በሚል ቃል በፍጹም አይተረጉመውም፡፡ በዚህ ፈንታ ለኪዳን ወይም ለኑዛዜ የሚያገለግለውን ዲያቴኬ (diatheke)የሚለውን ቃል ይጠቀማል፡፡ ለምን? ምናልባት ይህ የሆነበት ምክንያት ተርጓሚዎቹ እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር የፈጸመው ቃል ኪዳን በሁለት ግለሰቦች መካከል የተፈጸመ ስምምነት እንዳልሆነ ስለተገነዘቡ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ከራሱ ፈቃድ ሌላ በምንም ላይ ያልተመሰረተ ነበር፡፡ ‹‹ቢሆን ኖሮ›› እና ‹‹ነገር ግን›› የሚሉ ሁኔታዎች አልተያያዙበትም፡፡ አብርሃም ዝም ብሎ እግዚአብሔርን በቃሉ ሊይዘው ነው፡፡

እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ልዩ ባሕርያት ለማጉላት ጳውሎስ የ‹‹ኑዛዜን›› እና የ‹‹ቃል ኪዳንን›› ጥንድ ትርጉም ይወስዳል፡፡ እንደ ሰው ኑዛዜ ሁሉ የእግዚአብሔር ተስፋም የተወሰኑ ተጠቃሚዎች አሉት፤ እነርሱም አብርሃምና ልጆቹ ናቸው (ዘፍ. 12፡1-5፣ ገላ. 3፡16)፤ ውርስንም ያካትታል (ዘፍ. 13፡15፣ 17፡8፣ ሮሜ 4፡13፣ ገላ. 3፡29)፡፡ ለጳውሎስ እጅግ አስፈላጊው ነገር የእግዚአብሔር ተስፋ የማይለወጥ ባሕርይ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የሰው ኑዛዜም ተግባራዊ ከሆነ በኋላ አይለወጥም፡፡ ስለዚህ በሙሴ አማካይነት ሕግን መስጠት እግዚአብሔር አስቀድሞ ከአብርሃም ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ዋጋ ቢስ አያደርገውም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተስፋ ስለሆነ (ገላ. 3፡16) በምንም መንገድ ቢሆን እግዚአብሔር ቃሉን የሚያጥፍ አይደለም (ኢሳ. 46፡11፣ ዕብ. 6፡18)፡፡

በሚከተሉት ንባቦች ውስጥ ተስፋ በሚለው ቃል ቦታ ቃል ኪዳን የሚለውን ተኩ፡፡ በእያንዳንዱ ንባብ ውስጥ ‹‹የቃል ኪዳን›› ባሕርይ ምንድን ነው? የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን እንደ ተስፋ አድርጎ መረዳት የንባቡን ትርጉም እንዴት ግልጽ ያደርገዋል? ቃል ኪዳን ምን እንደሆነ በተሻለ ሁኔታ ለመረዳትስ እንዴት ይረዳል? (ዘፍ. 9፡ 11-17፣ 15፡ 18፣ 17፡ 1-21)፡፡ ይህ ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ እና እንዴት ልንታመንበት እንደምንችል ምን ያስተምረናል?
 

ሐምሌ 24
Jul-31
 

እምነትና ሕግ (ሮሜ 3፡ 31)

 

ጳውሎስ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ባለው ግንኙነት ስለ እምነት የበላይነት አጠንክሮ ተከራክሯል፡፡ ‹‹በህግ ሥራ ማንም መጽደቅ ስለማይችል›› (ገላ. 2፡16) ግዝረትም ሆነ ማንኛውም ‹‹የሕግ ሥራ›› ለድነት ቅድመ ሁኔታ አለመሆኑን በተደጋጋሚ ተናግሯል፡፡ ከዚህም በላይ የአንድን አማኝ ማንነት የሚገልጸው የሕግ ሥራ ሳይሆን እምነት ነው (ገላ. 3፡7)፡፡ ይህ ተደጋጋሚ የሆነ የሕግ ሥራን መቃወም የሚከተለውን ጥያቄ ያስነሳል፡- ‹‹ታዲያ ሕግ በፍጹም ዋጋ የለውምን? እግዚአብሔር ሕግን ሽሮታልን?››

ድነት በሕግ ሥራ ሳይሆን በእምነት ስለሆነ ጳውሎስ እምነት ሕግን ይሽራል ማለቱ ነው ወይ? የሚከተሉት ጥቅሶች ምን ይነግሩናል? ሮሜ 3፡31ን ከ ሮሜ 7፡ 7፣ 12፤ 8፡ 3 እና ማቴ 5፡ 17-20 ጋር ያነጻጽሩ፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጳውሎስ በሮሜ 3 ላይ ያቀረበው ሙግት በገላትያ መጽሐፍ ውስጥ ስለ እምነትና ሕግ ካቀረበው ውይይት ጋር ይመሳሰላል፡፡ እርሱ የሚሰጣቸው አስተያየቶች አንዳንዶች ከሕግ በላይ እምነትን ከፍ ከፍ እያደረገ ነው ወደሚል ድምዳሜ ሊመራቸው እንደሚችል ስለተሰማው ጳውሎስ መልስ እንዲመልሱለት የማይፈልገውን ጥያቄ ይጠይቃል፣ ‹‹ሕግን በእምነት እንሽራለንን?›› (ሮሜ 3፡ 31)፡፡

በሮሜ 3፡ 31 ላይ ‹‹መሻር›› ተብሎ የተተረጎመው ቃል ካታርጌኦ (katargeo) ነው፡፡ ጳውሎስ ይህን ቃል በተደጋጋሚ የሚጠቀመው ሲሆን ሲተረጎም ‹‹ዋጋ ቢስ ማድረግ›› (“to nullify”) (ሮሜ 3፡ 3)፣ ‹‹ማጥፋት›› (‹‹to abolish”) (ኤፌ. 2፡ 15)፣ ወይም ‹‹መደምሰስ›› (to destroy) (1ቆሮ. 6፡13) ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡ ዛሬ አንዳንድ ሰዎች ጳውሎስ አስተምሮአል ብለው እንደሚናገሩት እርሱ በሆነ መንገድ ሕግ በክርስቶስ መስቀል ላይ ተሸሮአል የሚለውን ሀሳብ ማጽደቅ ፈልጎ ቢሆን ኖሮ ይህ ጊዜው ነበር፡፡ ነገር ግን ጳውሎስ ይህንን አስተሳሰብ በአጽንዖት የሚቃወመው ብቻ ሳይሆን የእርሱ ወንጌል ሕግን ‹‹ያጸናል›› ይላል፡፡

‹‹ጽድቅ በእምነት እቅድ የስርየት መስዋዕትን በመጠየቅና በመስጠት›› እግዚአብሔር ለሕግ ያለውን አክብሮት ያሳያል፡፡ ጽድቅ በእምነት ሕግን ከሻረ ኃጢአተኛውን ከኃጢአቱ ነጻ ለማድረግና ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም ወደ መፍጠር ለመመለስ የክርስቶስ የስርየት ሞት አያስፈልግም ነበር፡፡

‹‹ከዚህም በላይ ትክክለኛ የሆነ እምነት ለእግዚአብሔር ሕግ በመታዘዝ በሚኖር ሕይወት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም ያልተቆጠበ ፈቃደኛነትን ያሳያል፡፡ . . . ትክክለኛ የሆነ እምነት፣ ከሙሉ ልብ ለአዳኝ ባለው ፍቅር ተመስርቶ፣ ወደ መታዘዝ ብቻ ይመራል፡፡›› —The SDA Bible Commentary, vol. 6, p. 510.

በርግጥ ጳውሎስ እምነት ሕግን ዋጋ ቢስ ያደርገዋል ማለቱ ቢሆን ኖሮ ምን ውጤትን እንደሚያስከትል ያስቡ፡፡ እንደዚህ ቢሆን ኖሮ ዝሙት ወይም መስረቅ ወይም መግደል ኃጢአት መሆናቸው ይቀራል ማለት ነው? እርስዎ ዝም ብለው የእግዚአብሔርን ሕግ ቢታዘዙ ኖሮ ራስዎን ከስንት ሀዘን፣ ስቃይና ሕመም ነጻ እንደሚያደርጉ ያስቡ፡፡ ለእግዚአብሔር ሕግ ካለመታዘዝ የተነሳ እርስዎም ሆኑ ሌሎች ምን አይነት መከራ ደረሰባችሁ?
 

ሐምሌ 25
Aug-1
 

የህግ አላማ

 

በገላትያ 3፡19-29 ላይ ጳውሎስ ብዙ ጊዜ ‹‹ሕግን›› ጠቅሷል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ጳውሎስ በዋነኛነት እየተናገራ ያለው ሕግ የትኛው ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

አንዳንዶች በቁጥር 19 ላይ እስከ የሚለው ቃል ሕግ ጊዜያዊ መሆኑን ያሳያል ብለው በማመን የህግ ዓላማው በመስቀል ላይ ተፈጽሞ ከፍጻሜ ላይ ስለደረሰ ንባቡ የሚያመለክተው ሜዳዊ ሕግን ነው ብለው አስበዋል፡፡ ምንም እንኳን ይህ አባባል በራሱ የሆነ ትርጉም የሚሰጥ ቢሆንም ጳውሎስ በገላትያ መጽሐፍ ውስጥ ሊገልጽ የሚፈልገው ነጥብ አይመስልም፡፡ ሜዳዊውና የሞራል ሕግ ከመተላለፍ የተነሳ በሲና ‹‹የተጨመሩ›› ቢሆንም ጳውሎስ በመጀመሪያ ደረጃ በአእምሮው ውስጥ የያዘው የሞራል ሕግን መሆኑን የሚከተለውን ጥያቄ ከግምት ውስጥ በማስገባት እናያለን፡፡

ጳውሎስ ሕግ ተጨማሪ ተደርጎአል ይላል ወይ? ከምን ላይ ነው የተጨመረው? ለምንድን ነው የተጨመረው? ገላ. 3፡19ን ከሮሜ 5፡13፣ 20 ጋር ያነጻጽሩ፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጳውሎስ ቀድሞ በተፈጸመው ኑዛዜ ላይ የተደረገ የሆነ ተጨማሪ ነገር በመሆን መጀመሪያ የተቀመጠውን ስምምነት እንደቀየረው ዓይነት ሕግ እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር በፈጸመው ቃል ኪዳን ላይ ተጨምሯል አይልም፡፡ ሕግ ከሲና በፊት ለረዥም ጊዜ ኖሯል (የነገን ትምህርት ይመልከቱ)፡፡ በዚህ ፈንታ ጳውሎስ እያለ ያለው ሕግ ለእሥራኤል የተሰጠው ሙሉ በሙሉ ለተለየ ዓላማ ነው፡፡ ወደ እርሱ በእምነት የሚመጡትን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር እና እርሱ ወደሚሰጠው ጸጋ ለማመልከት ነበር፡፡ ሕግ ኃጢአተኛነታችንን እና የእግዚአብሔር ጸጋ እንደሚያስፈልገን ያሳየናል፡፡ ሕግ ድነትን ‹‹ለማግኘት›› የሚያገለግል የሆነ ዓይነት ፕሮግራም እንዲሆን አልታሰበም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ፣ ጳውሎስ እንዳለው፣ ሕግ የተሰጠው ‹‹ኃጢአትን ለማብዛት›› ነው (ሮሜ 5፡ 20)፤ ይህ ማለት በሕይወታችን ውስጥ ያለውን ኃጢአት በግልጽ ሊያሳየን ነው (ሮሜ 7፡ 13)፡፡

ሜዳዊ ሕጎች ወደ መሲሁ ያመለከቱ እና በቅድስናና በአዳኙ አስፈላጊነት ላይ አጽንዖት የሰጡ ሲሆን የግብረገብ ሕግ ደግሞ ኃጢአትን በሚያሳዩት በአታድርጉዎቹ አማካይነት ኃጢአት የተፈጥሮ ሁኔታችን አካል መሆኑን ብቻ ሳይሆን በርግጥም የእግዚአብሔርን ሕግ መጣስ መሆኑንም ያሳያል (ሮሜ 3፡ 20፤ 5፡ 13፣ 20፤ 7፡ 7፣ 8፣ 13)፡፡ ጳውሎስ ‹‹ሕግ በሌለበት መተላለፍ የለም›› (ሮሜ 4፡ 15) ያለበት ምክንያት ይህ ነው፡፡ ሕግ እንደ አጉሊ መነጽር ያገለግላል፡፡ መሳሪያው ልብስን የሚያቆሽሹ ቆሻሻ ነጥቦችን አይጨምርም፣ ነገር ግን በደንብ እንዲታዩ ያደርጋቸዋል፣ አንድ ሰው በእርቃነ-ዓይኑ ሊያያቸው የማይችላቸውን ብዙ ቦታዎች ያሳያል፡፡›› —William Hendriksen, New Testament Commentary,Exposition on Galatians (Grand Rapids, Mich.: Baker BookHouse, 1968), p. 141.
 

ሐምሌ 26
Aug-2
 

የእግዚአብሔር ሕግ የሚቆይበት ጊዜ

 

ሕግ በሲና ተራራ ላይ ስለመጨመሩ ጳውሎስ የተናገረው አረፍተ ነገር ሕግ አስቀድሞ አልነበረም ማለት ነው ወይ? ካልሆነ ከሲና በፊትና በኋላ የነበረው ልዩነት ምን ነበር? ዘፍ. 9፡ 5፣ 6፤ 18፡ 19፤ 26፡ 5፤ 39፡ 7-10፤ ዘጸ. 16፡ 22-26፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

እግዚአብሔር ሕጉን ለአብርሃም በመብረቅ፣ በነጎድጓድና በሞት ቅጣት ማሳየት አላስፈለገውም (ዘጸ. 19፡ 10-23)፡፡ ታዲያ እግዚአብሔር ለምን ለእሥራኤላውያን በዚህ ሁኔታ ሕጉን ሰጠ? የእሥራኤል ልጆች በግብፅ በባርነት በቆዩበት ጊዜ የእግዚአብሔር ታላቅነትና የግብረገብ መስፈርቶቹ ከእይታቸው ጠፍቶ ስለነበረ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ የራሳቸውን የኃጢአተኛነት መጠንና የእግዚአብሔርን ሕግ ቅድስና እንዲያውቁ መደረግ ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ የሲናው መገለጥ በርግጠኝነት ይህንን አድርጓል፡፡

ጳውሎስ ‹‹ተስፋ የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ›› ሕጉ ተጨምሯል ሲል ምን ማለቱ ነው? ገላ. 3:16–19፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ብዙዎች ይህ ጥቅስ የተረዱት በሲና ተራራ ላይ የተሰጠው ሕግ ጊዜያዊ ነው እንደሚል አድርገው ነው፡፡ ከአብርሃም በኋላ በ430 ዓመት ገደማ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ከፍጻሜ ላይ ደረሰ፡፡ ነገር ግን ይህ ትርጉም ጳውሎስ ስለ ሕግ በሮሜ መጽሐፍ እና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ ማቴዎስ 5፡ 17-19 ባሉ ንባቦች ውስጥ ከሚለው ጋር ይጋጫል፡፡

ይህን ንባብ የሚያነቡ ሰዎች ብዙ ጊዜ የሚፈጽሙት ስህተት እስከ የሚለው ቃል የተወሰነ ጊዜን ያመለክታል ማለታቸው ነው፡፡ ነጥቡ ይህ አይደለም፡፡ መዝ. 112፡ 8 እግዚአብሔርን የሚፈራን ሰው ሲገልጽ ‹‹በጠላቶቹ ላይ ድልን እስኪያገኝ ድረስ ልቡ ጽኑ ነው፣ አይፈራም›› ይላል፡፡ ይህ ማለት ድልን ሲያገኝ ይፈራል ማለት ነውን? በራዕይ 2፡ 25 ላይ ኢየሱስ እንዲህ ይላል፣ ‹‹እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ፡፡›› ኢየሱስ እርሱ ከመጣ በኋላ ታማኝ መሆን አያስፈልገንም ማለቱ ነውን?

የህግ ሚና በክርስቶስ መምጣት አላበቃም፡፡ ሕግ እስካለ ድረስ ኃጢአትን ማሳየቱን ይቀጥላል፡፡ ጳውሎስ እያለ ያለው የክርስቶስ መምጣት በሰብአዊ ታሪክ ውስጥ ነገሮች አዲስ መልክ የሚይዙበት ወሳኝ ነጥብ ይሆናል ነው፡፡ ሕግ ማድረግ ያልቻለውን ክርስቶስ ማድረግ ይችላል፤ ለኃጢአት እውነተኛ ፈውስ ይሰጣል፣ ማለትም ኃጢአተኞችን በማጽደቅ በመንፈሱ በውስጣቸው ሕጉን ይፈጽማል (ሮሜ 8፡ 3፣ 4)፡፡

እግዚአብሔር ይህን ወይም ያን ወይም ሌላ አድርጎልኝ ቢሆን ኖሮ ዳግመኛ አልጠራጠረውም ወይም በእርሱ ላይ ጥያቄ አላነሳም ነበር ብለው ለራስዎ አስበው ያውቃሉ? በሲና ስለሆነው ነገር፣ እሥራኤላውያን እንዴት ኃይለኛ የሆነውን የእግዚአብሔርን ኃይል መገለጥ እንዳዩ ያስቡ፡፡ ነገር ግን ያደረጉት ነገር ምን ነበር? ይህ ስለ እውነተኛ እምነትና እንዴት እንደምናገኘውና እንደምንጠብቀው ምን ሊነግረን ይገባል? (ቆላ. 2፡ 6ን ይመልከቱ)፡፡
 

ሐምሌ 27
Aug-3
 

የተስፋው የበላይነት

 

‹‹ይህ ሰው በሲና ተራራ ከተናገረው መልአክና ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ በማህበሩ ውስጥ የነበረው ነው፤ ይሰጠንም ዘንድ ሕይወት ያላቸውን ቃላት ተቀበለ›› (የሐዋ. 7፡ 38)፡፡

በገላትያ 3፡ 19፣ 20 ላይ ሕግ የጸጋ ቃል ኪዳንን ዋጋ ቢስ አለማድረጉን የሚገልጹ ሀሳቦችን ማቅረቡን ይቀጥላል፤ የተቃዋሚዎቹ የስነ-መለኮት ትምህርት ትክክል ቢሆን ኖሮ ሕግ ሊያደርግ የሚችለው ያንን ብቻ ስለነበር ይህ አስፈላጊ ነበር፡፡ ስለዚህ ለመዳን ከእግዚአብሔር ጸጋ በተቃራኒ በራሳችን ሕግ ጥበቃ መደገፍ ከነበረብን እንደ ኃጢአተኞች መቆም የምንችለው የት እንደነበር ያስቡ፡፡ በመጨረሻ ያለ ተስፋ እንሆናለን፡፡

ምንም እንኳን ጳውሎስ በገላትያ 3፡ 19፣ 20 ላይ የሚሰጣቸው አስተያየቶች ዝርዝሮች ከባድ ቢሆኑም መሰረታዊ ነጥቡ ግን ግልጽ ነው፡- ሕግ በመላእክትና በሙሴ በኩል ስለተሰጠ የተስፋው ቅርንጫፍ ነው፡፡ ሕግን ከመስጠት ጋር የመላእክት ግንኙነት በዘጸአት መጽሐፍ ውስጥ አልተጠቀሰም፣ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ በሌሎች በርካታ ቦታዎች ውስጥ ይገኛል (ዘዳ. 33፡ 2፤ የሐዋ. 7፡ 38፣ 53፤ ዕብ. 2፡2)፡፡ ጳውሎስ በ1ጢሞ. 2፡5 ላይ ክርስቶስን ሲያመለክት አማላጅ የሚለውን ቃል ይጠቀማል፣ ነገር ግን በዚህ ቦታ የሰጣቸው አስተያየቶች ሙሴ ‹‹የእግዚአብሔርን ቃል እነግራችሁ ዘንድ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔርና በእናንተ መካከል ቆምሁ›› ያለው ዘዳግም 5፡5 በአእምሮው ውስጥ ለመኖሩ ጠንካራ ሀሳብ ይሰጣሉ፡፡

ቁጥር የሌላቸው መላእክት በተገኙበት በሲና ሕግን መስጠት በግርማ የተሞላ እንደነበረ እና እንደ ሕግ ሰጭ ሙሴ አስፈላጊ እንደመሆኑ ሁሉ ሕግን የመስጠት ሂደት በእጅ አዙር ነበር፡፡ ግልጽ የሆነ ንጽጽር ሲደረግ እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባው ቃል አማላጅ ስለማያስፈልግ ቀጥታ ነበር (በተመሳሳይ ሁኔታ ለአማኞች ሁሉ እንደዚሁ ነው)፡፡

ቁጥር የለሽ መላእክት በተገኙበት በሲና ሕግን የመስጠት ሂደት በግርማ የተሞላ እንደነበረና ሙሴ እንደ ሕግ ሰጭ ሆኖ እንደቀረበ ሁሉ ሕግን የመስጠት ሂደት በእጅ አዙር ነበር፡፡ ግልጽ በሆነ ንጽጽር አማላጅ አስፈላጊ ስላልነበረ የእግዚአብሔር ተስፋ ለአብርሃም በቀጥታ ተሰጠ (በተመሳሳይ ሁኔታ ለአማኞች ሁሉ ይሰጣል)፡፡ በመጨረሻም ሕግ የፈለገውን ያህል ጠቃሚ ቢሆንም ለመዳን ጸጋው በእምነት እንዳሚያድነን ለተሰጠው ተስፋ ምትክ አይደለም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ሕግ ተስፋው እንዴት አስደናቂ እንደሆነ በተሻለ ሁኔታ እንድናስተውል ይረዳናል፡፡

አብርሃም ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ የተገናኘባቸውን ሁኔታዎች ይግለጹ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲህ ዓይነት ቅርበት ምን ጥቅም ነበረው ? ዘፍ. 15፡ 1-6፣ 18፡ 1-33፣ 22፡ 1-18ን ይመልከቱ

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስላሉ አንዳንድ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ያደረጉ ሰዎች ያስቡ፡- አዳምና ሔዋን በኤደን (ዘፍ. 3)፤ የያዕቆብ መሰላል (ዘፍ. 28)፤ ጳውሎስ በደማስቆ መንገድ ላይ (የሐዋ. 9)፡፡ ምናልባት ትዕይንታዊ የሆነ ልምምድ አላጋጠመዎትም ይሆናል፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ለእርስዎ ራሱን የገለጠው በምን መንገዶች ነው? አብርሃም ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ዓይነት ቅርበት እንዳይለማመዱ በግል ሕይወትዎ የሚከለክል ምን ነገር እንዳለ ራስዎን ይጠይቁ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ነገር ካለ ለመለወጥ ምን እርምጃዎችን መውሰድ ይችላሉ?
 

ሐምሌ 28
Aug-4
 

ተጨማሪ ሀሳብ፡-

 

“ሕዝቡ በባርነት ውስጥ እያሉ የእግዚአብሔርንና የአብርሃማዊውን ቃል ኪዳን መርሆዎች እውቀት በከፍተኛ ደረጃ አጥተው ነበር፡፡ እግዚአብሔር እነርሱን ከግብፅ ነጻ በማውጣት እርሱን ወደ መውደድና በእርሱ ወደ መታመን ለመምራት ኃይሉንና ምህረቱን ሊያሳያቸው ፈለገ፡፡ ግብጻውያን ያሳድዷቸው ስለነበር ማምለጥ የማይቻል ወደ መሰለበት ወደ ቀይ ባሕር አመጣቸው፡፡ ይህን ያደረገው የራሳቸውን ደካማነት እንዲረዱና መለኮታዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው እንዲገነዘቡ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ነጻ አወጣቸው፡፡ ከዚህ የተነሳ ለእግዚአብሔር ፍቅር ያላቸውና በምስጋና የተሞሉ፣ በሚረዳቸው በእርሱ ኃይልም የሚተማመኑ ሆኑ፡፡ ከአካላዊ ባርነት ነጻ አውጪአቸው በመሆን ከራሱ ጋር አቆራኝቷቸው ነበር፡፡

‹‹ነገር ግን በአእምሮዎቻቸው ውስጥ መቀረጽ የነበረበት ትልቅ እውነት ነበር፡፡ በጣዖት አምልኮና በክፋት ውስጥ ከመኖራቸው የተነሳ ስለ እግዚአብሔር ቅድስና፣ ስለ ራሳቸው ልብ እጅግ ኃጢአተኛነት፣ ስለ አቅመ-ቢስነታቸው፣ በራሳቸው የእግዚአብሔርን ሕግ መታዘዝና መማር እንደማይችሉ እውነተኛ የሆነ ግንዛቤ አልነበራቸውም፡፡” —Ellen G. White, Patriarchs and Prophets, p. 371.

‹‹የእግዚአብሔር ሕግ በሲና ተራራ በሚያስፈራ ታላቅነት መነገሩ ለኃጢአተኛ የኩነኔ ንግግር ነበር፡፡ መኮነን የህግ ተግባሩ ነው፣ ነገር ግን በእርሱ ውስጥ ይቅርታ ለመስጠትም ሆነ ለማዳን ኃይል የለውም፡፡›› Comments, The p. 1094. SDA Bible Commentary, vol. 6,

 

የውይይት ጥያቄዎች፡

 

- ስለ ሁሉም የተስፋዎች ሀሳብ፣ በተለይም ስለተጣሱት ተስፋዎች ያስቡ፡፡ ለእርስዎ የገቡትን ተስፋ ስለ ጣሱ ሰዎች ምን ይሰማዎታል? አንድ ሰው የገባውን ቃል ለመጠበቅ አቅዶ ማድረግ ባይችል ወይም ሀሳቡን ቢለውጥ ወይም መጀመሪያውኑ ያለውን ነገር ከልቡ አለማለቱን ቢገነዘቡ ምን ያህል ልዩነት ያመጣል? ምክንያቱ ምንም ቢሆን የተገባው ቃል ከተጣሰ በኋላ በግለሰቡ ላይ የነበረዎት የመታመን ደረጃ ምን ሆነ? በእግዚአብሔር ተስፋዎች መታመን እንደሚችሉ ማወቅ ለእርስዎ ምን ማለት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ በእግዚአብሔር ተስፋዎች መታመንን እንዴት መማር ይችላሉ?

እግዚአብሔር የሰጠንን አስፈላጊ እውነቶች ማየት እስከማንችልበት ጊዜ ድረስ በአካባቢያችን ተጽእኖ ምክንያት ልንበላሽ በምንችልበት አደጋ ውስጥ የሆንነው በምን መንገዶች ነው? እነዚያ ሊያበላሹን የሚችሉ ተጽእኖች ምን እንደሆኑ እንዴት ማወቅ እንችላለን? እንዴትስ ልንከላከል እንችላለን?

ማጠቃለያ፡- በሲና ላይ ሕግን መስጠት እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠውን ተስፋ ዋጋ ቢስ አላደረገውም፣ ሕጉም በተስፋው የሚሰጣቸውን ነገሮች አልቀየረም፡፡ ሕግ የተሰጠው ሰዎች ምን ያህል ኃጢአተኞች እንደሆኑ ትክክለኛ የሆነ መረዳት እንዲኖራቸውና ለአብርሃምና ለዘሩ የተሰጠው የእግዚአብሔር ተስፋ እንደሚያስፈልጋቸው እንዲገነዘቡ ነበር፡፡