ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ገላ 3:1-14 ሮሜ 1:2 ; 4:3 ዘፍ 15:6; 12: 1-3 ዘሌ 17:11 2ቆሮ 5:21
የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - ‹‹በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፏልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን›› (ገላ. 3፡ 13)፡፡
አንድ ትንሽ ልጅ ሁለመናዋ ቀለም የተቀባች እና ባማረ ሁኔታ የተገጣጠመች ትንሽ ጀልባ ሰራ፡፡ አንድ ቀን የሆነ ሰው ጀልባውን ሰረቀበትና እጅግ አዘነ፡፡ አንድ ቀን በገንዘብ አበዳሪ ሱቅ አጠገብ ሲያልፍ ጀልባውን ተመለከተ፡፡ ደስ ብሎት ወደ ገንዘብ አበዳሪው ሮጠና እንዲህ አለው፣ ‹ያቺ የእኔ ትንሽ ጀልባ ነች፡፡› ገንዘብ አበዳሪው ‹አይደለም፣ ስለገዘኋት የእኔ ነች› አለው፡፡ ልጁ ‹ልክ ነህ፣ ነገር ግን እኔ ስለ ሰራኋት የእኔ ነች› አለው፡፡ ገንዘብ አበዳሪው መልሶ ‹እኔ ምን ቸገረኝ፣ ሁለት ዶላር መክፈል ከቻልክ መልሰህ የራስህ ልታደርጋት ትችላለህ› አለው፡፡ አንድ ሳንቲም እንኳን ለሌለው ልጅ ያ እጅግ ብዙ ገንዘብ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጀልባዋን የራሱ ሊያደርጋት ወሰነ፤ ከዚህ የተነሳ ሳር የማጨድ ሥራ እና ሁሉንም የተለመዱ ዕለታዊ ሥራዎች ሰራና የተፈለገውን ገንዘብ አገኘ፡፡
‹‹ወደ ሱቅ ሮጠና ‹ጀልባዬን እፈልጋታለሁ› አለ፡፡ ገንዘቡን ከፈለና ጀልባዋን ተቀበለ፡፡ ጀልባዋን በክንዶቹ ተሸከሞ አቅፎ ከሳማት በኋላ እንዲህ አለ፣ ‹አንቺ ውዷ ትንሽ ጀልባ፣ እወድሻለሁ፡፡ የእኔ ነሽ፡፡ ሁለት ጊዜ የእኔ ነሽ፡፡ መጀመሪያ ሰራሁሽ፣ አሁን ደግሞ ገዛሁሽ፡፡›
‹‹የእኛም ሁኔታ እንደዚህ ነው፡፡ እኛም ሁለት ጊዜ የጌታ ነን፡፡ እርሱ ፈጠረን፣ እኛ ግን ወደ ሰይጣን የአበዳሪ ሱቅ ገባን፡፡ ከዚያ በኋላ ኢየሱስ መጥቶ እጅግ ትልቅ በሆነ ዋጋ ገዛን፣ በብርና በወርቅ ሳይሆን በራሱ ክቡር ደም ገዛን፡፡ በፍጥረትም ሆነ በድነት የጌታ ነን፡፡›› —William Moses Tidwell, Pointed Illustrations (Kansas Press, 1951) p. 97. City, Mo.: Beacon Hill
ገላትያ 3፡ 1-5ን ያንብቡ፡፡ ከዚህ በታች ጳውሎስ እያላቸው ያለውን ነገር አሳጥረው ይጻፉ፡፡ እኛም ትክክል በሆነ ነገር ጀምረን ኋላ በሕጋዊነት ውስጥ በመውደቅ ተመሳሳይ በሆነ መንፈሳዊ ወጥመድ ውስጥ ልንወድቅ የምንችለው እንዴት ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጳውሎስ በቁጥር አንድ ላይ ስለ ‹‹ሞኝ›› የገላትያ ሰዎች የተናገራቸውን ቃላት ስሜት ለማግኘት በርካታ ዘመናዊ ትርጉሞች ጥረት አድርገዋል፡፡ ጳውሎስ በግሪክ የተጠቀመው ቃል ከዚያም የበለጠ ጠንካራ ነው፡፡ ቃሉ አኖኢቶይ የሚል ሲሆን ለአእምሮ ጥቅም ላይ ከሚውለው ኖስ (nous) ከሚል ቃል የመጣ ነው፡፡ ቃል በቃል ሲተረጎም ‹‹አእምሮ ቢስ›› ማለት ነው፡፡ የገላትያ ሰዎች እያሰቡ አይደሉም፡፡ ጳውሎስ በዚህ አያቆምም፤ የሚያደርጉትን ነገር በሞኝነት እያደረጉ ስለሆነ የሆነ ጠንቋይ አስማት አድርጎባቸው ይሆን በማለት በመገረም ይናገራል፡፡ ‹‹አዚም ያደረገባችሁ ማነው?›› እዚህ ላይ ለመጠቀም የመረጣቸው ቃላት የሚጠቁሙት አሁን ባሉበት ሁኔታ እንዲገኙ ያደረጋቸው የመጨረሻው ምንጭ ሰይጣን መሆኑን ነው (2ቆሮ. 4፡ 4)፡፡
የገላትያ ሰዎች በወንጌል ላይ ባደረጉት ክህደት ጳውሎስን እጅግ ግራ ያጋባው ነገር ቢኖር ድነት በክርስቶስ መስቀል ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነው፡፡ ማጣት የማይገባቸው ነገር ነበር፡፡ በገላትያ 3፡ 1 ላይ ‹‹ተስሎ ነበር›› ተብሎ የተተረጎመው ቃል በቀጥታ ሲተረጎም እንደ ‹‹ማስታወቂያ ተለጥፎ ነበር›› ወይም እንደ ‹‹ስዕል ተስሎ ነበር›› የሚል ትርጉም አለው፡፡ ሁሉንም የሕዝብ አዋጆች ለመግለጽ ጥቅም ላይ ውሎ ነበር፡፡ ጳውሎስ እያለ ያለው መስቀል የስብከቱ ማዕከላዊ ክፍል ስለነበር የገላትያ ሰዎች በዓይነ ህሊናቸው ክርስቶስ ተሰቅሎ ተመልክተዋል ነው፡፡ ሆኖም በተግባራቸው ከመስቀሉ እየራቁ ናቸው እያላቸው ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ጳውሎስ አሁን የገላትያ ሰዎች ያላቸውን ልምምድ መጀመሪያ ወደ ክርስቶስ እምነት ከመጡበት ሁኔታ ጋር እያነጻጸረ ነው፡፡ ይህን የሚያደርገው ጥቂት የመከራከሪያ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ነው፡፡ መጀመሪያ መንፈስን የተቀበሉት እንዴት ነው? መጀመሪያ ክርስቲያኖች የሆኑት እንዴት ነው? ከዚህ ትንሽ በተለየ አቅጣጫ እግዚአብሔር ለምን መንፈስን ሰጣቸው? መንፈስን ለማግኘት የሚያስችላቸውን የሆነ ነገር ስላደረጉ ነበርን? በፍጹም አይደለም! በዚህ ፈንታ ክርስቶስ ለእነርሱ ያደረገላቸውን መልካም የምስራች ስላመኑ ነበር፡፡ እንደዚህ በጥሩ ሁኔታ ከጀመሩ በኋላ አሁን በራሳቸው ባሕርይ መደገፍ እንደሚችሉ እንዲያስቡ ምን አደረጋቸው? እኔ በደንብ ተግባሬን እያከናወንኩ ነኝ፣ እኔ ጽኑ ክርስቲያን ነኝ፣ ይህን ወይም ያንን አላደርግም…እና ለመዳን የሚያበቃኝን ያህል ጥሩ ነኝ፣ ብለው እያሰቡ ራስዎን የሚያገኙት ስንት ጊዜ ነው? የዚህ እይታ ስህተቱ ምንድን ነው?
ጳውሎስ ከሐዋርያት ጋር በኢየሩሳሌም የተደረሰውን ስምምነት (ገላ. 2፡ 1-10) እና የገላትያ ሰዎችን የግል ልምምድ (ገላ. 3፡1-5) በመጠቀም እስካሁን ድረስ የጽድቅ በኃይማኖት ወንጌሉን ከጥቃት ተከላክሏል፡፡ በገላትያ 3፡ 6 ላይ በመጀመር ለወንጌሉ የመጨረሻ ማረጋገጫ ለመስጠት ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት ይመለሳል፡፡ እንዲያውም ከገላትያ 3፡ 6-4፡ 31 ያለው ሀሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተመሰረቱ ቀጣይነት ካላቸው መከራከሪያዎች የተሰራ ነው፡፡
በገላትያ 3፡ 6-8 ላይ ጳውሎስ ስለ ‹‹ቅዱስ መጽሐፍ›› ሲጽፍ ምን ማለቱ ነው? ሮሜ 1፡ 2፣ 4፡3፣ 9፡17ን ልብ ይበሉ፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጳውሎስ ደብዳቤውን ለገላትያ ሰዎች በጻፈ ጊዜ ‹‹አዲስ ኪዳን›› እንዳልነበረ ማስታወስ አስፈላጊ ነው፡፡ ጳውሎስ ቀዳሚው የአዲስ ኪዳን ጸሐፊ ነው፡፡ ምናልባት የማርቆስ ወንጌል ከአራቱ ወንጌላት ቀዳሚው ሳይሆን አይቀርም፣ ነገር ግን ጳውሎስ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ (65 ዓ.ም) አልተጻፈም፤ ያ ማለት ደግሞ ጳውሎስ ደብዳቤውን ለገላትያ ሰዎች ከጻፈ ከአሥራ አምስት አመት በኋላ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ጳውሎስ ቅዱሳት መጻሕፍትን ሲጠቅስ በአእምሮው ያለው ብሉይ ኪዳን ብቻ ነው፡፡
ጳውሎስ ባስተማረው ትምህርት ውስጥ ብሉይ ኪዳን ወሳኝ የሆነ ሚና ተጫውቷል፡፡ የብሉይ ኪዳንን ትምህርቶች እንደ ሙት ጥቅሶች ሳይሆን ስልጣን እንዳለውና እንደ ሕያው የእግዚአብሔር ቃል ይመለከት ነበር፡፡ በ2ጢሞ. 3፡ 16 ላይ ‹‹መጻሕፍት ሁሉ በእግዚአብሔር መንፈስ ተጻፉ›› ብሎ ጽፏል፡፡ ‹‹በእግዚአብሔር መንፈስ›› ተብሎ የተተረጎመው ቃል ቲኦፕኔስቶስ (theopneustos) ከሚል ቃል የመጣ ነው፡፡ ቲኦ (theo) የሚለው የቃሉ የመጀመሪያው ክፍል ‹‹እግዚአብሔር›› የሚል ሲሆን ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ‹‹ተነፈሰ›› የሚል ትርጉም አለው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ‹‹እግዚአብሔር የተነፈሳቸው›› ናቸው፡፡ ክርስቶስ ቃል የተገባው መሲህ መሆኑን ለማሳየት (ሮሜ 1፡ 2)፣ ስለ ክርስቲያን አኗኗር ትምህርት ለመስጠት (ሮሜ 13፡ 8-10) እና ትምህርቱ ተአማኒነት ያለው መሆኑን ለማረጋገጥ (ገላ. 3፡ 8-9) ጳውሎስ ቅዱሳት መጻሕፍትን ይጠቀማል፡፡ ጳውሎስ ምን ያህል ጊዜ ከብሉይ ኪዳን እንደ ጠቀሰ በትክክል ለመወሰን ይከብዳል፣ ነገር ግን አጭር በሆኑት የቲቶ እና የፊልሞና ደብዳቤዎች ውስጥ ካልሆነ በስተቀር በሌሎች ደብዳቤዎቹ ሁሉ ውስጥ ተጠቅሶ እናገኛለን፡፡
ገላትያ 3፡ 6-14ን በጥንቃቄ ያንብቡ፡፡ በእነዚያ ቁጥሮች ውስጥ ጳውሎስ ከብሉይ ኪዳን የሚጠቅሳቸውን ንባቦች ይመልከቱ፡፡ ይህ ንባብ ብሉይ ኪዳን ምን ያህል ስልጣን እንዳለው ምን ይነግረናል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
አንዳንድ ጊዜ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ አንዱ ክፍል ከሌላኛው ክፍል የበለጠ የእግዚአብሔር መንፈስ ምሪት ያለበት አድርገው ይገምታሉን? ጳውሎስ በ2ጢሞ. 3፡16 ላይ በጻፈው መሰረት በዚያ አቅጣጫ የመሄድ አደጋው ምንድን ነው?
ጳውሎስ የወንጌል መልእክቱን ተአማኒነት ለማረጋገጥ ቅዱሳት መጻሕፍትን ሲመለከት አብርሃምን የጠቀሰው ለምንድን ነው? (ገላ. 3፡ 6)፡፡ በአይሁዳዊነት ውስጥ አብርሃም ማዕከላዊ ቦታ የያዘ ሰው ነበር፡፡ የአይሁድ ዘር አባት ብቻ ሳይሆን በጳውሎስ ዘመን የነበሩ አይሁዶች እውነተኛ የሆነ አይሁድ መምሰል ያለበት ምሳሌ አድርገውም የሚያቀርቡት ሰው ነበር፡፡ ብዙዎች የእርሱ መታዘዝ ባሕርዩን እንደሚገልጽ አድርገው የሚያዩት ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር አብርሃምን ጻድቅ ሰው ነው ያለው ከመታዘዙ የተነሳ ነው ብለውም ያምኑ ነበር፡፡ አብርሃም አገሩንና ቤተሰቡን ተወ፣ ግዝረትን ተቀበለ፣ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ ልጁን እንኳን ለመሰዋት ፈቃደኛ ነበር፡፡ መታዘዝ ይህ ነው! የጳውሎስ ተቃዋሚዎች ግዝረት የግድ አስፈላጊ ነው ሲሉ መከራከሪያቸው ይህን መሰረት በማድረግ ነበር፡፡
ነገር ግን ጳውሎስ በገላትያ መጽሐፍ ውስጥ አብርሃምን በሕግ ጠባቂነቱ ሳይሆን በእምነት ምሳሌነቱ ዘጠኝ ጊዜ በመጥቀስ ክርክሩን ወደ ራሳቸው ይመልሳል፡፡
ጳውሎስ ከዘፍጥረት 15፡ 6 ላይ የጠቀሰውን ልብ ይበሉ፡፡ የአብርሃም እምነቱ ‹‹ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት›› ማለት ምን ማለት ነው? (ሮሜ 4፡ 36፣ 8-11፣ 22-24)፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
መጽደቅ የሚለው ቃል ከሕግ ዓለም የተወሰደ ሲሆን ተቆጠረለት የሚለው ቃል ደግሞ ከንግድ ዓለም የተወሰደ ነው፡፡ ‹‹በግለሰቡ ተቀማጭ ሂሳብ ላይ የሆነ ነገር ማስቀመጥ›› ወይም ‹‹ክሬዲት መስጠት›› ማለት ሊሆን ይችላል፡፡ በገላትያ 3፡ 6 ላይ ለአብርሃም ብቻ ጥቅም ላይ የዋለ ሳይሆን ከአበው ጋር በተገናኘ ሁኔታ ሌላ አሥራ አንድ ጊዜ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ተቆጠረለት፣ እንደሆነ ተደርጎ ተቆጠረለት፣ ወይም ተሰጠው በማለት ትርጉም ሰጥተውታል፡፡ እንደ ጳውሎስ ዘይቤያዊ አነጋገር በተቀማጭ ሂሳባችን ላይ የተቀመጠው ነገር ጽድቅ ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር እኛን ጻድቅ አድርጎ የሚቆጥረን በምን መሰረት ነው? ምንም እንኳን የጳውሎስ ተቃዋሚዎች ይሆናል ቢሉም በእርግጠኝነት በመታዘዝ ላይ ተመስርቶ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለ አብርሃም መታዘዝ የፈለጉትን ቢሉ እንኳን እግዚአብሔር አብርሃምን እንደ ጻድቅ የቆጠረው በእምነቱ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ነው፡- የአብርሃም መታዘዝ ለመጽደቁ መሰረት አይደለም፤ እርሱ ያደረጋቸውን ነገሮች ያደረገው ለመጽደቅ አይደለም፤ እነዚያን ነገሮች ያደረገው አስቀድሞ ስለ ጸደቀ ነው፡፡ ጽድቅ ወደ መታዘዝ የሚመራ ሲሆን መታዘዝ ግን ወደ ጽድቅ አይመራም፡፡
እርስዎ ባደረጉት ነገር ሳይሆን ክርስቶስ ለእርስዎ ባደረገው ነገር ብቻ ጸድቀዋል ማለት ምን ማለት እንደሆነ ያስቡ፡፡ ይህ የምስራች የሆነበት ምክንያንት ምንድን ነው? ይህን እውነት የራስዎ ማድረግን፣ ማለትም ከዚህ በፊት የገጠመዎትም ሆነ አሁን እየገጠመዎት ያለው ትግል ምንም ቢሆን፣ ይህ ነገር በግልዎ ለእርስዎ እንደሚሆን እንዴት መማር ይችላሉ?
መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንደሚያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ፡በአንተ አህዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ›› (ገላ. 3፡ 8)፡፡ ጳውሎስ ወንጌል ለአብርሃም ተሰበከ ብሎ የጻፈ ብቻ ሳይሆን ሰባኪው እግዚአብሔር መሆኑንም ጽፏል፤ ስለዚህ እውነተኛ ወንጌል መሆን ነበረበት፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ወንጌልን ለአብርሃም የሰበከው መቼ ነበር? ጳውሎስ ዘፍጥረት 12፡ 3ን መጥቀሱ የሚያመለክተው እግዚአብሔር አብርሃምን በዘፍጥረት 12፡ 1-3 በጠራው ጊዜ የገባለት ቃል ኪዳን በአእምሮው ውስጥ መኖሩን ነው፡፡
ዘፍጥረት 12፡ 1-3ን ያንብቡ፡፡ እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ስለ ፈጸመው የቃል ኪዳን ባሕርይ ይህ ምን ይነግረናል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር የፈጸመው ቃል ኪዳን መሰረቱ ማዕከል ያደረገው እግዚአብሔር ለእርሱ በሰጠው ተስፋ ላይ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለአብርሃም አራት ጊዜ ‹‹አደርጋለሁ›› አለ፡፡ እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጣቸው ተስፋዎች ሙሉ በሙሉ ከአንድ ወገን የሆኑ መሆናቸው የሚያስደንቅ ነው፡፡ ሁሉንም ቃል የገባው እግዚአብሔር ሲሆን አብርሃም ግን አንድም ቃል አልገባም፡፡ ይህ ደግሞ አብዛኞቹ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ጥረት ከሚያደርጉት መንገድ ተቃራኒ ነው፡፡ በተለምዶ እርሱ የሆነ ነገር የሚያደርግልን ከሆነ እኛም ልናገለግለው ቃል እንገባለን፡፡ በርግጥ አብርሃም በራሱ መተማመንን ትቶ ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር መተማመንን መማር ስለነበረበት ቀላል ነገር አልነበረም (ዘፍ. 22ን ይመልከቱ)፡፡
ስለዚህ የአብርሃም ጥሪ የወንጌልን ፍሬ ነገር፣ ድነት በእምነትን ያሳያል፡፡ አንዳንዶች በስህተት መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት የተለያዩ የድነት መንገዶችን ያስተምራል ብለው ይደመድማሉ፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን ድነት ትዕዛዛቱን በመጠበቅ ላይ የተመሰረተ ነበር ይላሉ፤ ከዚያም ያ መንገድ በደንብ ስላልሰራ እግዚአብሔር ሕግን በማጥፋት ድነት በእምነት እንዲሆን አደረገ ይላሉ፡፡ ይህ ከእውነት የራቀ አባባል ነው፡፡ ጳውሎስ በገላትያ 1፡ 7 ላይ እንደጻፈው አንድ ወንጌል ብቻ አለ፡፡
በብሉይ ኪዳን ውስጥ ድነት በእምነት ብቻ መሆኑን የሚገልጹ ሌሎች ምሳሌዎችን ማግኘት ይችላሉን? ለምሳሌ ዘሌ. 17፡ 11፣ መዝ. 32፡ 1-5፣ 2ሳሙ. 12፡ 1-13፣ ዘካ. 3፡ 1-4ን ይመልከቱ፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ብዙ ጊዜ ‹‹ርካሽ ጸጋ›› የሚለውን ሀረግ እንሰማለን፡፡ ይህ የማይመጥን ስያሜ ነው፡፡ ጸጋ ርካሽ ሳይሆን ነጻ ነው (ቢያንስ ለእኛ)፡፡ ነገር ግን በመልካም ሥራችን በእርሱ ላይ እንጨምራለን ወይም ኃጢአት ለመስራት እንደ ማሳበቢያ እንጠቀማለን ብለን ስናስብ እናበላሸዋለን፡፡ በራስዎ ልምምድ ከእነዚህ ሁለቱ መንገዶች ወደ የትኛው ያጋድላሉ? ይህን ማቆም የሚችሉት እንዴት ነው?
የጳውሎስ ተቃዋሚዎች በገላትያ 3፡ 10 ላይ በተናገራቸው የድፍረት ቃላት በጣም መደነቃቸው አያጠራጥርም፡፡ ከእርግማን ሥር ስለመሆናቸው አስበው አያውቁም ነበር፤ አስበውት ቢሆን እንኳን በመታዘዛቸው ምክንያት በረከት እንደሚያገኙ መጠበቅ ነበር፡፡ ሆኖም የጳውሎስ ንግግር የማያሻማ ነበር፡- ‹‹‹‹ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ ከእርግማን በታች ናቸውና በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፏልና፡፡››
ጳውሎስ ሁለት ሙሉ በሙሉ የተለያዩ አማራጮችን እያነጻጸረ ነው፡- ድነት በእምነት እና ድነት በሥራ፡፡ በዘዳግም ምዕራፍ 28 እና 29 ላይ የተዘረዘሩት የቃል ኪዳን በረከቶችና እርግማኖች ግልጽ ናቸው፡፡ የታዘዙት ተባርከዋል፣ ያልታዘዙት ደግሞ ተረግመዋል፡፡ አንድ ግለሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት በመታዘዝ ላይ መደገፍ ከፈለገ ሕግን በሙሉ መጠበቅ አለበት፡፡ ለመከተል የምንፈልገውን አንስተን ለመምረጥ ነጻነት አልተሰጠንም፤ እዚህና እዚያ የምንፈጽማቸውን ጥቂት ስህተቶች እግዚአብሔር ያልፋቸዋል ብለን ማሰብም የለብንም፡፡ መርሁ ሁሉም ወይም ምንም የሚለው ነው፡፡
‹‹ሁሉም በድለዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎሎአቸዋል›› (ሮሜ. 3፡ 23) ስለሚል በእርግጥ ይህ ነገር መጥፎ ዜና የሆነው ለአህዛብ ብቻ ሳይሆን ሕጋውያን ለሆኑት የጳውሎስ ተቃዋሚዎችም ነው፡፡ ጥሩ ለመሆን የፈለገውን ያህል ጠንክረን ብንሞክርም ሕግ እንደ ሕግ ተላላፊዎች ይኮንነናል፡፡
ክርስቶስ ከሕግ እርግማን ነጻ ያወጣን እንዴት ነበር? ገላ. 3፡ 13፣ 2ቆሮ. 5፡ 21ን ይመልከቱ፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጳውሎስ እግዚአብሔር በክርስቶስ ያደረገልንን ነገር ለማሳወቅ ሌላ ዘይቤያዊ አነጋገርን ይጠቀማል፡፡ መዋጀት የሚለው ቃል ‹‹መልሶ መግዛት›› ማለት ነው፡፡ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ወይም ባሪያን ነጻ ለማውጣት እንደሚያገለግል የመቤዤት ዋጋ ጥቅም ላይ ውሎ ነበር፡፡ የኃጢአት ዋጋ ሞት ስለሆነ ሕግን ለመጠበቅ ካለመቻል የተነሳ የሚመጣው እርግማንም ብዙ ጊዜ የሞት ፍርድ ነው፡፡ ለድነታችን የተከፈለው የመቤዤት ዋጋ ትንሽ አልነበረም፤ እግዚአብሔር የልጁን ሕይወት እንዲሰጥ አድርጎታል (ዮሐ. 3፡ 16)፡፡ ኢየሱስ ከእርግማን የተቤዤን የእኛ ኃጢአት ተሸካሚ በመሆን ነው (1ቆሮ. 6፡ 20፣ 7፡ 23)፡፡ እርሱ በፈቃደኝነት የእኛን እርግማን በራሱ ላይ በመውሰድ በእኛ ፈንታ የኃጢአትን ሙሉ ቅጣት ተቀበለ (2ቆሮ. 5፡ 21)፡
ጳውሎስ እንደ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማረጋገጫ ዘዳግም 21፡ 23ን ይጠቅሳል፡፡ እንደ አይሁዶች ወግ አንድ ሰው ከተገደለ በኋላ ሥጋው በእንጨት ላይ ከተሰቀለ በእግዚአብሔር እርግማን ሥር ነው፡፡ የኢየሱስ በመስቀል ላይ መሞት የዚህ እርግማን ምሳሌ እንደሆነ ተደርጎ ታይቷል (የሐዋ. 5፡ 30፣ 1ጴጥ. 2፡ 24)፡፡
ስለዚህ መሲህ በእግዚአብሔር እርግማን ሆነ የሚለውን ሀሳብ መረዳት ለማይችሉት ለአንዳንድ አይሁዶች መስቀል የመሰናከያ ዓለት መሆኑ አያስደንቅም፡፡ ነገር ግን ይህ በትክክል የእግዚአብሔር ዕቅድ ነበር፡፡ አዎን፣ መሲህ እርግማንን ተሸከመ፣ ነገር ግን የራሱን ሳይሆን የእኛን እርግማን ነው የተሸከመው!
የእኛ ምትክና ዋስትና በሆነው ክርስቶስ ላይ የሁላችን በደል ተጫነበት፡፡ እኛን ከሕግ ኩነኔ እንዲያድነን እንደ ሕግ ተላላፊ ተቆጠረ፡፡ የእያንዳንዱ የአዳም ዘር በደል የእርሱን ልብ እየተጫነው ነበር፡፡ እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ ያለው ቁጣ፣ ከኃጢአት የተነሳ የተገለጠው አሰቃቂ የሆነ አለመደሰት፣ የልጁን ልብ በድንጋጤ ሞላው፡፡ ክርስቶስ በሕይወቱ ዘመን በሙሉ ለወደቀው ዓለም የአባቱን ምህረትና ይቅርታ የምስራች ሲያሰራጭ ነበር፡፡ የእርሱ ዋና ሀሳብ የኃጢአተኞች ዋና ለሆነው ድነትን መስጠት ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን ከተሸከመው አስፈሪ ከሆነ የኃጢአት ሸክም የተነሳ የአባቱን የእርቅ ፊት ማየት አይችልም ነበር፡፡ አዳኙ እጅግ ከፍተኛ በሆነ ስቃይ ውስጥ በነበረበት ወቅት መለኮታዊ ፊት ከእርሱ መሰወር በፍጹም ሰው ሊያስተውለው በማይችል ሀዘን ልቡን ወጋው፡፡ ይህ ሀዘን እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ አካላዊ ስቃይ እምብዛም አልተሰማውም ነበር፡፡›› Ellen G. White, The Desire of Ages, p. 753.
‹‹አሁን ሉተር እንደ የእውነት ተጋዳይ በመሆን በድፍረት ወደ ሥራው ገባ፡፡ ድምጹ ከመድረክ ላይ ልባዊ የሆኑና ከበድ ያሉ ማስጠንቀቂያዎችን በማስተላለፍ ተሰማ፡፡ በሕዝብ ፊት የኃጢአትን አስጸያፊ የሆነ ባሕርይ አስቀመጠና ሰው በራሱ ሥራ ኃጢአቱን ማሳነስ ወይም ከቅጣቱ ማምለጥ እንደማይችል አስተማረ፡፡ ለእግዚአብሔር ከመናዘዝና በክርስቶስ ከማመን ሌላ ምንም ነገር ኃጢአተኛን ሊያድን አይችልም፡፡ የክርስቶስ ጸጋ ሊገዛ አይችልም፤ ነጻ ስጦታ ነው፡፡ ሰዎች ከቅጣት ማምለጫ እንዳይገዙ፣ ነገር ግን ወደ ተሰቀለው አዳኝ በእምነት እንዲመለከቱ መከራቸው፡፡ ” —Ellen G. White, The Great Controversy, p. 129.
ዛሬ እንኳን በራሳችን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ድነት በእምነት ብቻ፣ ያለ እኛ ሥራ የእግዚአብሔር ጸጋ በክርስቶስ አማካይነት ያድነናል የሚለውን ትምህርት መቀበል የሚከብዳቸው ሰዎች አሉ፡፡ አንዳንዶች ይህን እጅግ አስፈላጊ የሆነ እውነት ላለመቀበል እንዲያመነቱ የሚያደርግ ነገር ምንድን ነው?
ጳውሎስ ስለ ድነት በሥራ ስነ-መለኮታዊ ስህተት አጠንክሮ ተናገረ፡፡ ያ ጥሩ ስለሆነ የስነ-መለኮት ትምህርት አስፈላጊነት ምን ይነግረናል? እኛ እንደ ቤተ ክርስቲያን በመካከላችን ስህተት ሲስተማር አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በኃይል መቆም ያለብን ለምንድን ነው?
ማጠቃለያ፡- በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ከጅምር እስከ መጨረሻ የድነታችን መሰረቱ በክርስቶስ ማመን ብቻ ነው፡፡ አብርሃም ጻድቅ ሆኖ የተቆጠረው በእግዚአብሔር ተስፋዎች ስላመነ ነበር፤ ያው የጽድቅ ስጦታ የአብርሃምን እምነት ለሚጋራ ለማንኛውም ሰው ይሰጠዋል፡፡ ስለ ስህተቶቻችን ያልተኮነንንበት ብቸኛው ምክንያት ኢየሱስ በእኛ ቦታ በመሞት ዋጋውን ስለከፈለ ነው፡፡