ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡1ኛ ቆሮ. 1፡ 10-13፣ ዘፍ. 17፡ 1-21፣ ዮሐ. 8፡ 31-36፣ ቆላ. 3፡ 11፡፡ ገላትያ 2፡1-14፣
የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - “በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ” ፊል. 2፡2
የፕሮቴስታንት ተሃድሶ አንቀሳቃሽ የነበረው ጆን ካልቪን አንድነት መጥፋትና መከፋፈል ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት የሚጠቀምባቸው ዋና መሳሪያዎቹ መሆናቸውን በማመን ክርስቲያኖች መከፋፈልን እንደ ወረርሽኝ መከላከል አለባቸው አለ፡፡
ነገር ግን አንድነትን ለመጠበቅ ሲባል እውነት መተው አለበት ወይ? የፕሮቴስታንት ተሃድሶ አባት የነበረው ማርቲን ሉተር በወርምስ በተሰየመው የምክር ቤት ስብሰባ ላይ ክስ ተመስርቶበት በቀረበ ጊዜ በአንድነት ስም መዳን በእምነት ብቻ የሚለውን አመለካከት ለማጠፍ ቢመርጥ ኖሮ ምን ሊሆን እንደሚችል ያስቡ፡፡
‹‹ተሃድሶ አንቀሳቃሹ በአንዲት ነጥብ እንኳን ቢሸነፍ ኖሮ ሰይጣንና ሰራዊቱ ድልን በተቀዳጁ ነበር፡፡ ነገር ግን የእርሱ የማይናወጥ ጽናት ቤተ ክርስቲያንን ነጻ ለማውጣትና አዲስ እና የተሻለ ዘመን ለመጀመር ምክንያት ነበር፡፡›› ” —Ellen G. White, The GreatControversy, p. 166.
በገላቲያ 2፡1-14 ላይ አንዳንድ አማኞች አንድነትን ለማጥፋት ጥረት እያደረጉ በነበሩበት ሰዓት ሐዋርያው በሐዋርያት ክበብ ውስጥ አንድነትን ለማቆየት ሊያደርገው የሚችለውን ሁሉ ሲያደርግ እናገኛለን፡፡ ነገር ግን ለጳውሎስ አንድነት አስፈላጊ ቢሆንም ያን አንድነት ለማግኘት ሲባል የወንጌል እውነትን ለድርድር ማቅረብን እምቢ አለ፡፡ በአንድነት ውስጥ ልዩነትን ለማስተናገድ እድል ቢኖርም በዚህ ሂደት ውስጥ ወንጌል በፍጹም ለድርድር መቅረብ የለበትም፡፡
1ቆሮ. 1፡ 10-13ን ያንብቡ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድነት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ጳውሎስ ስለነበረው እምነት ይህ ንባብ ምን ይነግረናል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
የእርሱ ወንጌል ከእግዚአብሔር የተሰጠው አይደለም የሚለውን መሰረተ ቢስ ውንጀላ በማስተባበል ጳውሎስ በገላትያ 2፡ 1፣ 2 ላይ ትኩረቱን እየቀረበበት ባለ በሌላ ክስ ላይ ያደርጋል፡፡ በገላትያ የነበሩ ሀሰተኛ መምህራን የጳውሎስ ወንጌል ጴጥሮስና ሌሎች ሐዋርያት ካስተማሩት ጋር አይጣጣምም አሉ፡፡ ጳውሎስ ከዳተኛ ነው ይሉት ነበር፡፡
ለዚህ ክስ ምላሽ እንዲሆን ጳውሎስ ከተለወጠ ከአሥራ አራት አመት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ስላደረገው ጉዞ ማውራት ይጀምራል፡፡ ጳውሎስ ያንን ጉዞ ያደረገው መቼ እንደ ነበረ ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ባንሆንም በጥንት ዘመን ይደረግ የነበረ ማንኛውም ጉዞ ቢሆን ቀላል እንዳልነበረ ይታወቃል፡፡ ከአንጾኪያ ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዘው በመሬት ከሆነ የሶስት መቶ ማይል ጉዞ ቢያንስ ሶስት ሳምንት የሚወስድበት ሲሆን በርካታ ችግሮችና አደጋዎች ያሉበት ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ ችግሮች ቢኖሩም ጳውሎስ ይህንን ጎዞ ያደረገው ሐዋርያት ስለጠሩት ሳይሆን መንፈስ ስለጠራው ነበር፡፡ እዚያ እያለ ወንጌሉን በሐዋርያት ፊት አቀረበ፡፡
ያንን ያደረገው ለምንድን ነው? ይህንን ያደረገው ያስተምር ስለነበረው ነገር አንዳች ጥርጣሬ ስለነበረው አልነበረም፡፡ ከእነርሱ ምንም አይነት ማረጋገጫ አያስፈልገውም ነበር፡፡ በዚህ ሰዓት ይህንን ወንጌል ለአሥራ አራት አመታት ሲሰብክ ቆይቷል፡፡ ምንም እንኳን የእነርሱ ፈቃድ ወይም ማረጋገጫ ባያስፈልገውም ለሐዋርያት ድጋፍና ማበረታቻ ከፍተኛ ዋጋ ሰጠ፡፡
ስለዚህ የእርሱ መልእክት የተለየ ነው የሚለው ውንጀላ በጳውሎስ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ጥቃት ሳይሆን በሐዋርያት አንድነትና በቤተ ክርስቲያን በራሷ ላይ ያነጣጠረ ነበር፡፡ ጳውሎስ ለአህዛብ በነበረው ተልዕኮና በኢየሩሳሌም በነበረችው እናት ቤተ ክርስቲያን መካከል የሚኖር መከፋፈል አጥፊ የሆኑ ውጤቶች ስለሚያስከትል የሐዋርያትን አንድነት መጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ነበር፡፡ በአህዛብ ክርስቲያኖችና በአይሁድ ክርስቲያኖች መካከል ሕብረት ከሌለ ‹‹ክርስቶስ ይከፋፈልና ጳውሎስ ወንጌልን ለአህዛብ ለማድረስ ያደረገው ጥረትና አሁንም እያደረገ ያለው ጥረት በተስፋ መቁረጥ ያበቃል፡፡›› —F. F. Bruce, TheEpistle to the Galatians (Grand Rapids, Mich.: William B.Eerdmans Publishing Company, 1982), p. 111.
ዛሬ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ስጋት ላይ እየጣሉ ያሉ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? እነዚህን ስጋቶች ከለየን በኋላ እንዴት ነው የምንይዛቸው? ከአንድነት ከራሱ የበለጠ አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
ግዝረት በጳውሎስና በአንዳንድ የአይሁድ ክርስቲያኖች መካከል በነበረው አለመግባባት ማዕከላዊ ቦታ የያዘበት ምክንያት ምንድን ነው? ዘፍ. 17፡ 1-22፣ ገላ. 2፡ 3-5፤ 5፡ 2፣ 6፤ የሐዋ. 15፡ 1፣ 5ን ይመልከቱ፡፡ አንዳንዶች ከአህዛብ የተመለሱ ክርሰቲያኖች እንኳን መገረዝ አለባቸው ብለው ማመናቸው ለመረዳት ይህን ያህል ከባድ የማይሆነው ለምንድን ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ግዝረት እግዚአብሔር ከአይሁድ ሕዝብ አባት ከነበረው ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን ምልክት ነበር፡፡ ምንም እንኳን ግዝረት ወንድ ለሆኑ የአብርሃም ዝሪያዎች ቢሆንም ሁሉም ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ወዳለው የቃል ኪዳን ግንኙነት ተጋብዘዋል፡፡ የግዝረት ምልክት ለአብርሃም የተሰጠው በዘፍጥረት 17 ላይ ነው፡፡ ይህ የሆነው እግዚአብሔር ልጅ እሰጥሃለሁ ያለውን ቃል ኪዳን እንዲፈጽም ለመርዳት ሲል አብርሃም ከግብጻዊቷ የባለቤቱ ባሪያ ልጅ ለማግኘት አጥፊ የሆነ ጥረት ካደረገ በኋላ ነበር፡፡
ግዝረት ለቃል ኪዳኑ ገጣሚ የሆነ ምልክት ነበር፡፡ ይህ ሰዎች በደንብ አስበው ያዘጋጇቸው እቅዶች እግዚአብሔር ቃል የገባውን ነገር በፍጹም ተግባራዊ እንደማያደርጉ የሚያሳስበን ነገር ነው፡፡ ውጫዊው ግዝረት የተሰጠው የውስጥ ግዝረት ምልክት እንዲሆን ነበር (ዘዳ. 10፡16፤ 30፡6፤ ኤር. 4፡4፤ ሮሜ. 2፡29)፡፡ በራስ ከመተማመን ተለይተን ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር መደገፋችንን ይወክላል፡፡
ነገር ግን በጳውሎስ ዘመን ግዝረት መጀመሪያ ምልክት እንዲሆን የታቀደለትን አላማ በመሳት ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ብሔራዊና ኃይማኖታዊ መታወቂያ ሆኖ ነበር፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት ወደ አንድ መቶ ሃምሳ አመታት ገደማ አንዳንድ ለእምነታቸው እጅግ ቀናኢ የነበሩ ሰዎች በፓሊስታይን የነበሩ ያልተገረዙ አይሁዶች ብቻ ሳይሆኑ በእነርሱ ግዛት ሥር ያሉ በዙሪያቸው ያሉ የአህዛብ ወንዶች ሁሉ እንዲገረዙ አስገደዱ፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ግዝረት ወደ ድነት የሚያደርስ መታወቂያ እንደሆነ አድረገው ያምኑ ነበር፡፡ ይህ ‹‹ ‹የተገረዙ ወንዶች ወደ ገሃነም አይወርዱም› ›› በማለት ሙሉ በሙሉ በመታመን በተነገሩ በጥንት አስደናቂ አባባሎች ውስጥ ሊታይ ይችላል፡፡ —C. E. B. Cranfield, ACritical and Exegetical Commentary on the Epistle to theRomans (Edinburgh: T. & T. Clark Ltd., 1975), p. 172.
ጳውሎስ ግዝረትን ይቃወም ነበር ብሎ መገመት ስህተት ነው፡፡ ጳውሎስ ይቃወም የነበረው አህዛብ የግድ መገረዝ አለባቸው የሚለውን ሀሳብ ነበር፡፡ ሀሰተኛ መምህራን ‹‹እንደ ሙሴ ወግ ካልተገረዛችሁ በስተቀር መዳን አትችሉም›› ይሉ ነበር (የሐዋ. 15፡1)፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ የግዝረት ሳይሆን የድነት ጉዳይ ነው፡፡ ድነት በክርስቶስ በማመን ብቻ የሚገኝ ወይም በሰብአዊ መታዘዝ የሚገኝ ነገር ነው፡፡ ምናልባት ዛሬ ግዝረት አጨቃጫቂ ነገር ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ጋር ተነጻጻሪ የሆነ እንደ ቤተ ክርስቲያን እየታገልን ያለ ችግር ምንድን ነው?
ገላትያ 2፡1-10ን ያንብቡ፡፡ ጳውሎስ ሀሰተኛ ወንድሞች ‹‹ባሪያዎች ሊያደርጉን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን አርነታችንን ይሰልሉ ዘንድ ሾልከው በስውር ገብተዋል›› (ገላ. 2፡4) ይላል፡፡ ክርስቲያኖች ነጻ የወጡት ከምንድን ነው? ዮሐ. 8፡ 31-36፤ ሮሜ 6፡6፣ 7፤ 8፡ 2፣ 3፤ ገላ. 3፡ 23-25፤ 4፡ 7፣ 8፤ ዕብ. 2፡ 14፣ 15ን ያንብቡ፡፡ የዚህን ነጻነት እውነታ ለራሳችን የምንለማመደው እንዴት ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ነጻነት፣ እንደ ክርስቲያን ልምምድ መግለጫ፣ ለጳውሎስ አስፈላጊ የሆነ ጽንሰ ሀሳብ ነበር፡፡ ይህን ቃል ማንኛውም በአዲስ ኪዳን ውስጥ ያለ ሰው ከተጠቀመበት የበለጠ ጳውሎስ የተጠቀመበት ሲሆን በገላትያ መጽሐፍ ውስጥ ነጻ እና ነጻነት የሚሉት ቃላት ብዙ ጊዜ ቀርበዋል፡፡ ነገር ግን ለክርስቲያን ነጻነት ማለት በክርስቶስ የሚገኝ ነጻነት ነው፡፡ ያለ አንዳች ገደብ ለእግዚአብሔር ራስን በመስጠት የመኖር ዕድል ነው፡፡ ለኃጢአተኛ ተፈጥሮአችን ፍላጎቶች ባሪያ ከመሆን ነጻ መሆንን (ሮሜ 6)፣ ከሕግ ኩነኔ ነጻ መሆንን (ሮሜ 8፡ 1፣ 2)፣ እና ከሞት ኃይል ነጻ መሆንን (1 ቆሮ. 15፡ 55) ያካትታል፡፡
‹‹ጴጥሮስ ለተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደተሰጠው እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደተሰጠኝ እዩ›› (ገላ. 2፡ 7) ሲል ጳውሎስ ጥሪውን ተገንዝቦታል፡፡ ይህ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በልዩነት ውስጥ ስለሚኖረው አንድነት ባሕርይ ምን ሀሳብ ይሰጣል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
እግዚአብሔር ጴጥሮስን ለአይሁድ ወንጌልን እንዲሰብክ እንደ ጠራው ሁሉ ጳውሎስንም ለአህዛብ እንዲሰብክ እንደ ጠራው ሐዋርያት አምነው ተቀበሉ፡፡ በሁለቱም በኩል ወንጌሉ ተመሳሳይ ቢሆንም አቀራረቡ ግን ሐዋርያት ሊደርሷቸው ጥረት በሚያደርጉላቸው ሰዎች ሁኔታ ይደገፍ ነበር፡፡ በዚህ ጥቅስ ላይ በግልጽ የተቀመጠው ነገር ቢኖር ‹‹አንድና ተመሳሳይ የሆነው ዘዴ በተለያየ መንገድ እንደሚሰማና በተለያዩ ማህበራዊና ባሕላዊ አውዶች ውስጥ የተለያየ ኃይል እንደሚኖረው መገንዘቡ ነው፡፡…በትክክል በልዩነት አንድነት እንዳለ ሁሉ ለክርስቲያን አንድነት መሰረቱ ይህ አንድነት ነው፡›› —James D.G. Dunn, The Epistle to Mass.:Hendrickson p. 106. the Galatians (Peabody, Publishers, Inc., 1993),
‹‹ከምቾት ክበባችን›› እንድንወጣ በሚያደርጉን የወንጌል ስርጭትና የመመስከር ዘዴዎች ላይ የሌሎችን አመለካከት ለማስተናገድ ክፍት መሆን ያለብን እንዴት ነው? አንዳንድ የሚረብሹአችሁ ወንጌልን የማሰራጨት ዘዴዎች አሉን? ካሉ ምንድን ናቸው? ለምንድን ነው የሚረብሹአችሁ? ስለ እነዚህ ነገሮች የበለጠ አእምሮዎ የተከፈተ መሆን ያስፈልግ ይሆን?
ከጳውሎስ ጋር በኢየሩሳሌም ምክክር ከተደረገ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጴጥሮስ በሶሪያ ውስጥ የነበረችውን የመጀመሪያዋ የአህዛብ ቤተ ክርስቲያን የነበረባትንና የጳውሎስ ሚስዮናዊ እንቅስቃሴ መነሻ የሆነችውን አንጾኪያን ጎበኘ፡፡ እዚያ እያለ ጴጥሮስ ከአህዛብ ክርስቲያኖች ጋር በነጻነት በላ፣ ነገር ግን ከያዕቆብ የተላኩ የአይሁድ ክርስቲያኖች ቡድን እዚያ በደረሱ ጊዜ እነርሱ ምን ይሉኛል ብሎ በመፍራት ባሕርዩን ሙሉ በሙሉ ለወጠ፡፡
ጴጥሮስ የተሻለ ማወቅ የነበረበት ለምን ነበር? ገላ. 2፡ 11- 13ን ከሐዋር. 10፡ 28 ጋር ያነጻጽሩ፡፡ ባህላችንና በኃይል ሥር የሰደደ ወግና ባሕል በህይወታችን ውስጥ ምን ያህል ማድረግ እንደሚችል የእርሱ ድርጊት ምን ይነግረናል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
አንዳንዶች በስህተት ጴጥሮስና ከእርሱ ጋር የነበሩ አይሁድ ብሉይ ኪዳን ስለ ንጹህና እርኩስ ምግብ ያስቀመጠውን ሕግ መከተል ትተዋል ብለው አስበዋል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ይህ አይደለም፡፡ ጴጥሮስና ሁሉም የአይሁድ ክርስቲያኖች የአይሁድን የምግብ ሕጎች ትተው ቢሆን ኖሮ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለ ጥርጥር ከፍተኛ የሆነ ሁከት ይከተል ነበር፡፡ እንደዚያ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ተጽፎ የተቀመጠ ነገር ይኖር ነበር፣ ነገር ግን የለም፡፡ ስለዚህ ሊሆን የሚችለው ነገር ቢኖር ከአህዛብ ጋር በአንድ ጠረጴዛ ላይ ተቀምጦ አብሮ መብላት ነው፡፡ ብዙ አይሁዶች አህዛብን እንደ እርኩስ ይመለከቱ ስለነበር ጥያቄው በአንዳንዶች ዘንድ በተቻለ መጠን ከእነርሱ ጋር ማህበራዊ ግንኙነት ከመፍጠር የመራቅ ጉዳይ ነው፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ጴጥሮስ ከራሱ ጋር ብዙ የታገለ ሲሆን ጉዳዩን አጥርቶ እንዲመለከት የረዳው ከእግዚአብሔር የመጣለት ራዕይ ነበር፡፡ ጴጥሮስ የሮም ወታደሮች መቶ አለቃ ወደነበረው ወደ ቆርኔሊዮስ ቤት ከገባ በኋላ እንዲህ አለ፡‹‹አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ፣ ለእኔ ግን እግዚአብሔር ማንንም ሰው ርኩስና የሚያስጸይፍ ነው እንዳልል አሳየኝ›› (የሐዋ. 10፡ 28)፡፡ ጴጥሮስ በጉዳዩ ላይ የተሻለ እውቀት ቢኖረውም ከአገሩ የመጡ ሰዎችን ማስከፋት ስለፈራ ወደ ቀድሞ ተግባሩ ተመለሰ፡፡ ይህ ባሕልና ወግ ጴጥሮስን እንዴት በኃይል ይስበው እንደነበር ያሳያል፡፡
ቢሆንም የጴጥሮስ ተግባር ምን እንደሆነ ጳውሎስ በትክክል አስቀምጦታል፡በገላትያ 2፡ 13 ላይ የተጠቀመው የግሪክ ቃል ግብዝነት የሚል ነው፡፡ ባርናባስ እንኳን ‹‹በእነርሱ ግብዝነት እስኪወሰድ ድረስ›› ብሎ ገልጾታል፡፡ እነዚህ ከአንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ ሌላኛው የእግዚአብሔር ሰው የተሰነዘሩ ጠንካራ ቃላት ናቸው፡፡
ግብዝ መሆን እንደዚህ ቀላል የሚሆነው ለምንድን ነው? (ምናልባት የሌሎችን ስህተት ለመፈለግ ካለን ከፍተኛ ጉጉት የተነሳ ለራሳችን ስህተቶች ዓይኖቻችንን ወደ መጨፈን ስለምናዘነብል ይሆን ይሆን?) በራስዎ ሕይወት ምን ዓይነት ግብዘነት አለብዎት? ከዚህ የበለጠ ጠቃሚ የሆነው ጥያቄ ቢኖር ይህንን ግብዝነት እንዴት ሊገነዘቡትና ከሕይወትዎ ሊነቅሉት ይችላሉ? የሚለው ነው፡፡
በአንጾኪያ የነበረው ሁኔታ በእርግጥ ውጥረት የነገሰበት ነበር፡- ሁለት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሆኑ ጳውሎስና ጴጥሮስ ፊት ለፊት ግጭት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ጴጥሮስ ላሳየው ባሕርይ ምክንያት እንዲሰጥ ከመጠየቅ ጳውሎስ ወደ ኋላ አላለም፡፡
ጳውሎስ በሕዝብ ፊት ጴጥሮስን ስለተጋፈጠበት ሁኔታ ምን ምክንያቶችን ነው የሚሰጠው? ገላ. 2፡ 11-14፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
እንደ ጳውሎስ አመለካከት ችግሩ ጴጥሮስ ከኢየሩሳሌም ከመጡት እንግዶች ጋር ለመብላት መወሰኑ አይደለም፡፡ የጥንት ወጎች በርግጠኝነት እንደዚህ ማድረግን ይሹ ነበር፡፡ ጉዳዩ ‹‹የወንጌል እውነት›› ጉዳይ ነበር፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ ሕብረት የመፍጠር ወይም አብሮ የመብላት ልምምዶች ጉዳይ ብቻ አልነበረም፡፡ በትክክለኛ እይታ ሲታይ የጴጥሮስ ድርጊት መላውን የወንጌል መልእክት ወደ ድርድር ያመጣ ጉዳይ ነበር፡፡ ገላትያ 3፡ 28ን እና ቆላስያስ 3፡ 11ን ያንብቡ፡፡ በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ያለው እውነት ጳውሎስ የሰጠውን ጠንካራ ምላሽ እንድናስተውል የሚረዳን እንዴት ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ከጴጥሮስና ከሌሎች ሐዋርያት ጋር በተሰበሰበ ጊዜ አህዛብ ለግዝረት ሥርዓት እንዲገዙ ሳይገደዱ በክርስቶስ የተሰጡትን በረከቶች በሙሉ መቀበል ይችላሉ ከሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰው ነበር፡፡ የጴጥሮስ ድርጊት ያንን ስምምነት አደጋ ውስጥ ጣለው፡፡ ከዚህ በፊት የአይሁድና የአህዛብ ክርስቲያኖች በግልጽ ሕብረት የሚፈጥሩበት ምቹ ሁኔታ በተፈጠረበት ቦታ አሁን ጉባኤው ተከፋፍሏል፣ ይህ ደግሞ ወደ ፊት የተከፋፈለች ቤተ ክርስቲያን የምትኖርበትን ዕድል ፈጠረ፡፡
በጳውሎስ አመለካከት የጴጥሮስ ድርጊት ከአህዛብ የተመለሱ ክርስቲያኖች ቢበዛ ሁለተኛ ደረጃ የሚሰጣቸው ክርስቲያኖች እንደሆኑ የሚያመለክት ሲሆን የእርሱ እርምጃዎች አህዛቦች ሙሉ የሆነ ሕብረትን መፍጠር ከፈለጉ ለግዝረት ሕግ እንዲገዙ ጠንከር ያለ ጫና እንደሚያደርግባቸው አመነ፡፡ ከዚህ የተነሳ እንዲህ አለ፡ - ‹‹አንተ አይሁዳዊ ሆነህ ሳለህ እንደ አይሁዳዊ ሳይሆን እንደ አህዛብ እየኖርክ አህዛቦች እንደ አይሁዶች እንዲኖሩ እንዴት ታስገድዳለህ?›› (ገላ. 2፡ 14)፡፡ ‹‹እንደ አይሁዶች›› እንዲኖሩ የሚለው አባባል ቃል በቃል ሲተረጎም ‹‹ወደ አይሁድነት መቀየር›› ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ‹‹የአይሁዶችን የአኗኗር ዘዴ እንዳለ መቀበል›› ማለት ነው፡፡ ምኩራብን የሚከታተሉና በአይሁድ ባህሎች ይሳተፉ የነበሩ አህዛቦች ይህንን ያደርጉ ነበር፡፡ ጳውሎስ ሀሰተኛ ወንድሞች ብሎ የሚጠራቸው በገላትያ የነበሩ የእርሱ ተቃዋሚዎች ‹‹የአይሁዳዊነት አቀንቃኞች›› ተብለው የተጠሩበት ምክንያትም ይህ ነው፡፡
የጴጥሮስ ተግባራት ትክክል የሆኑ ይመስል ባርናባስና ሌሎችም በደንብ ማወቅ የሚገባቸው ሰዎች በዚህ ባሕርይ ተጠመዱ፡፡ ይህ እንዴት ያለ ‹‹የአቻ ተጽእኖ›› ግልጽ ምሳሌ ነው! በዙሪያችን ያሉ ሰዎች ወደ ስህተት አቅጣጫ እንዳይመሩን ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለ አንድነትና ልዩነት ተጨማሪ ጥናት ለማድረግ ኤለን ጂ ኋይት ምክር ለጻሐፉትና ለመጻሕፍት አዘጋጆች በሚለው መጽሐፏ ‹‹አዲስ ብርሃንን መመርመር›› (“Investigation of New Light”) በሚል ርዕስ የጻፈችውን ሀሳብ በገጽ 45 እና 47 ላይ ፣ እንዲሁም ምርጥ መልእክቶች በሚለው አንደኛ መጽሐፏ ውስጥ ‹‹ለቀደምት ንባቦች የተሰጠ ማብራሪያ›› (“An Explanation of Early Statements”) በሚል ርዕስ ስር ገጽ 75 ላይ፣ የወንጌል ሰራተኞች በሚል መጽሐፍ ውስጥ ‹‹ዘዴኛ መሆን›› (“Tactfulness,”) በሚል ርዕስ ስር ገጽ 117-119 ላይ፣ እንዲሁም ‹‹ማኑስክርፕት ሪሊዝ›› (“Manuscript Release 898,”) ገጽ 1092, 1093, in 1888 Materials, vol. 3.ያሉ ሀሳቦችን ያንብቡ፡፡
‹‹ከሁሉ የተሻሉ ሰዎች እንኳን ለራሳቸው ከተተው አሰቃቂ ስህተቶችን ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ ለሰብአዊ ወኪል ብዙ ሀላፊነቶች በተሰጡት መጠን፣ የማዘዝና የመቆጣጠር ሥልጣኑ ከፍተኛ ስለሆነ፣ የጌታን መንገድ በጥንቃቄ ካልተከተለ በስተቀር፣ አእምሮንና ልብን ከትክክለኛ መንገድ ማራቁ የማያጠራጥር ነው፡፡ ጴጥሮስ በአንጾኪያ በታማኝነት መርሆዎች ፈተና ወደቀ፡፡ ጳውሎስ የእርሱን የተዛባ ተጽእኖ ፊት ለፊት መቋቋም ነበረበት፡፡ ይህ ተጽፎ የተቀመጠው ሌሎች ጥቅም እንዲያገኙበትና በከፍተኛ ቦታ የተቀመጡ ሰዎች በታማኝነት ነጥብ ላይ እንዳይወድቁና ከመርህ እንዳይርቁ ከባድ ማስጠንቀቂያ እንዲሆናቸው ነው፡፡”— Ellen G. White Comments, The SDA Bible Commentary, vol. 6, p. 1108.
ፊት ለፊት መጋፈጥ ደስ የሚላቸው ሰዎች በጣም ጥቂት ናቸው፣ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ አስፈላጊ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስህተትን ማውገዝ ያለባትና የሚሰጠውን እርምት ለመቀበል እምቢተኛ የሚሆኑ ሰዎችን መቅጣት ያለባት በምን ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ነው?
የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን በዓለም ዙሪያ እያደገች ሳለ ብዙ ልዩነቶች ያላት እየሆነች ትሄዳለች፡፡ በእንደ እነዚህ ዓይነት ልዩነቶች መካከል አንድነት እንዳይጠፋ ቤተ ክርስቲያን ምን ዓይነት እርምጃዎችን መውሰድ ትችላለች? አንድነታችንን እንደጠበቅን በመካከላችን ያሉትን የባህልና የወግ ልዩነቶችን መቀበልንና ብሎም መደሰትን ልንማር የምንችለው እንዴት ነው?
የተለየ ባህል ላለው ሕዝብ ወንጌልን ስናካፍል ሳለ መለወጥ የሌለባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? መለወጥ ያለባቸው ነገሮችስ ምንድን ናቸው? መለወጥ በሌለበትና አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ደግሞ እንዲለወጥ በምንፈቅደው ነገር መካከል ያለውን ልዩነት የምናውቀው እንዴት ነው?
ማጠቃለያ፡-
አንዳንድ የአይሁድ ክርስቲያኖች አህዛብ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች ለመሆን መገረዝ አለባቸው ብለው ግፊት ማድረጋቸው ለቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮ ነበር፡፡ ምንም እንኳን በሐዋርያት መካከል አለመግባባቶች ቢኖሩም፣ የክርስቶስ አካል አንድ ሆና እንድትቆይና ለወንጌል እውነት ታማኝ ሆና እንድትቀጥል ይህ ጉዳይ ቤተ ክርስቲያንን ወደ ሁለት የተለያዩ ዓይነት እንቅስቃሴዎች እንዳይከፍላት ለማድረግ በአንድነት ሰሩ፡፡