ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 2ኛ ጴጥ.3፡ 15፣ 16፤ ገላ.1፤ ፊል.1፡ 1፤ ገላ. 5፡ 12፡፡
የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - ‹‹ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሽ አሰኛለሁን? ወይስ ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም›› (ገላ. 1፡10)፡፡
በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያሉ ተማሪዎች በግቢያቸው ውስጥ የዘር፣ የፆታ፣ የኑሮ ደረጃ፣ ወይም የእምነት ልዩነት ሳይደረግ ሁሉም ሰው ተቀባይነት የሚያገኝበትን ማዕከል ገነቡ፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ከአመታት በኋላ ወደ ግቢው ሲመለሱ ሌሎች ተማሪዎች ማዕከሉን በአዲስ መልክ ንድፍ ሰርተውለት እንዳገኙ አድርገው ያስቡ፡፡ ሁሉም ሰው የአንድነት ስሜት እንዲኖረው ታስቦ ንድፍ በተሰራለት ለማህበራዊ ግንኙት በሚያገለግለውና ብዙ ክፍት ቦታ በነበረው ትልቅ ክፍል ፋንታ ሰዎች በዘር፣ በፆታ እና በመሳሰሉ ሁኔታዎች እንዲገቡባቸው ገደብ የተዘጋጀላቸው በሮች ወዳሉአቸው ወደ በርካታ ትንንሽ ክፍሎች ተከፋፍሏል፡፡ ይህን ንድፍ የሰሩ ተማሪዎች እነዚህን ለውጦች የማድረግ ሥልጣን የመጣላቸው ለምዕተ አመታት ፀንቶ ከኖረው ልምምድ ነው ብለው ሊሞግቱ ይችሉ ይሆናል፡፡ ይህ ሁኔታ ጳውሎስ በገላትያ ለነበሩ ቤተ ክርስቲያናት ደብዳቤውን በጻፈ ጊዜ ወንጌል በገላትያ መጽሐፍ ውስጥ ከገጠመው ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል፡፡ አህዛቦች በእምነት ብቻ ቤተ ክርስቲያንን እንዲቀላቀሉ የነበረው እቅድ አህዛቦች የቤተ ክርስቲያን አባል ከመሆናቸው በፊት መገረዝ አለባቸው ብለው በሚያስተምሩ ሀሰተኛ መምህራን ግድድሮሽ እየገጠመው ነበር፡፡
ጳውሎስ ይህ አቋም በወንጌል በራሱ ላይ የተፈጸመ ጥቃት እንደሆነ አድርጎ ተመለከተው፤ ከዚህ የተነሳ ምላሽ መስጠት ነበረበት፡፡ ምላሹም ለገላትያ ሰዎች የተጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡
2ጴጥ. 3፡ 15፣ 16ን ያንብቡ፡፡ እነዚህ ጥቅሶች የቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን የጳውሎስን ጽሁፎች እንዴት ታያቸው እንደ ነበር ምን ይነግሩናል? መገለጥ እንዴት እንደሚሰራ ይህ ምን ያስተምረናል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በጻፈ ጊዜ የስነ-ጽሁፍ ድንቅ የፈጠራ ሥራ ለማዘጋጀት እየሞከረ አልነበረም፡፡ ይልቁንም በመንፈስ ቅዱስ ምሪት እርሱንና በገላትያ የነበሩ አማኞችን የሚያካትቱ የተወሰኑ ሁኔታዎችን እያሳወቀ ነበር፡፡ እንደ ገላትያ መልእክት ያሉ ደብዳቤዎች በጳውሎስ የሐዋርያነት አገልግሎት ላይ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ለአህዛብ ሚስዮናዊ እንደመሆኑ በሜደትራኒያን ባሕር አከባቢ ተበታትነው ያሉ በርካታ ቤተ ክርስቲያናትን መሰረተ፡፡ ምንም እንኳን መጎብኘት በቻለ ጊዜ ሁሉ ቢጎበኛቸውም በአንድ ቦታ ለረዥም ጊዜ መቆየት አልቻለም ነበር፡፡ ጳውሎስ በአካል መገኘት ያልቻለባቸውን ጊዜያቶች ለማካካስ ለቤተ ክርስትያናቱ ምሪት ለመስጠት ደብዳቤዎችን ጻፈ፡፡ በጊዜ ብዛት የደብዳቤዎቹን ቅጂዎች ከሌሎች ቤተ ክርስቲያናት ጋር ይጋሩ ነበር (ቆላ. 4፡ 16)፡፡
ምንም እንኳን ከጳውሎስ ደብዳቤዎች አንዳንዶቹ ቢጠፉም በአዲስ ኪዳን ውስጥ ቢያንስ አስራ ሶስት መጻሕፍት ስሙን ይዘዋል፡፡ ከዚህ በላይ በጴጥሮስ የተነገሩ ቃላት እንደሚያመለክቱት በሆነ ጊዜ የጳውሎስ ጽሁፎች እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ታይተው ነበር፡፡ ይህ የእርሱ አገልግሎት በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጅምር ላይ ምን ያህል ሥልጣን እንዳገኘ ያሳያል፡፡
በአንድ ወቅት አንዳንድ ክርስቲያኖች የጳውሎስ ደብዳቤዎች ይዞታና አቀራረብ የተለየና በእግዚአብሔር መገለጥ የተሰጠውን ቃል እንዲይዝ በመንፈስ ቅዱስ የተፈጠረ ነው ብለው አምነው ነበር፡፡ ከኦክስፎርድ የሆኑ ቤርናርድ ግሬንፌል እና አርተር ሀንት የተባሉ ሁለት ምሁራን በግብጽ አገር ወደ አምስት መቶ ሺህ የሚቆጠሩ የጥንት በፓፒራስ ላይ የተጻፉ ጽሁፎችን ቁርጥራጮች ባገኙ ጊዜ ይህ አመለካከት ተለወጠ (ከበርካታ መቶ ሺህ አመታት በፊት እና ከክርስቶስ ልደት በኋላ ለጽሁፍ ሥራ ጥቅም ላይ ይውል በነበረው በጣም ዝነኛ በሆነው በፓፒራስ ላይ የተጻፉ ዶኩመንቶች ናቸው)፡፡ አንዳንድ የጥንት የአዲስ ኪዳን ቅጂዎችን ከማግኘት በተጨማሪ ፋክቱሮችን፣ የግብር ደረሰኞችን፣ እና የግል ደብዳቤዎችንም አግኝተው ነበር፡፡
ሁሉንም እጅግ ያስደነቀው ደግሞ የጳውሎስ ደብዳቤዎች ይዞታና አቀራረብ በእርሱ ዘመን የነበሩ ደብዳቤ ጸሐፊዎች የሚጠቀሙት የተለመደ ፎርማት መሆኑ ነበር፡፡ የደብዳቤው ፎርማት ወይም ይዞታ (1) ላኪውንና ተቀባዩን ከጠቀሰ በኋላ ሰላምታ ያካተተ መክፈቻ የነበረው፤ (2) የምስጋና ቃል የነበረው፤ (3) የደብዳቤውን ዋና ክፍል የያዘ እና በመጨረሻም (4) መዝጊያ የነበረው ነበር፡፡ በአጭሩ፣ ጳውሎስ እርሱ በነበረበት ዘመን ለነበሩ ሰዎች ለመናገር እነርሱ የሚያውቁትን መንገድና ዘዴ በመጠቀም በዘመኑ የነበረውን መሰረታዊ ፎርማት ይከተል ነበር፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ዛሬ የሚጻፍ ቢሆን ኖሮ ጌታ እኛን ለመድረስ ምን አይነት ቋንቋ፣ ፎርማትና ዘዴ የሚጠቀም ይመስልዎታል?
ምንም እንኳን የጳውሎስ መልእክቶች በአጠቃላይ የጥንት ደብዳቤዎችን መሰረታዊ ይዘት ቢከተሉም የጳውሎስ መልእክት ወደ ገላትያ ሰዎች እርሱ በጻፋቸው በሌሎች መልእክቶች ውስጥ የሌሉ በርካታ ልዩ ባሕርያት አሉት፡፡ መረዳት ሲቻል እነዚህ ልዩነቶች ጳውሎስ እየገለጸ ያለውን ሁኔታ በደንብ እንድንረዳ ይረዱናል፡፡ ጳውሎስ በገላትያ 1፡ 1ና 2 ላይ ያስቀመጠውን የመክፈቻ ሰላምታ በኤፌሶን 1፡ 1፣ በፊልጵስዩስ 1፡ 1 እና በ2ኛ ተሰ. 1፡ 1 ላይ ከጻፈው ጋር አወዳድሩ፡፡ ጳውሎስ በገላትያ ላይ የጻፈው ሰላምታ ከሌሎች ጋር የሚመሳሰለውና የሚለየው በምን መንገዶች ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጳውሎስ በገላትያ ውስጥ ያቀረበው የመክፈቻ ሰላምታ በሌሎች ቦታዎች ካቀረበው ሰላምታ ጥቂት የሚረዝም ብቻ ሳይሆን የሐዋርያነት ስልጣኑን መሰረት ለመግለጽ ከመንገዱ ወጣ ይላል፡፡ ሐዋርያ የሚለው ቃል በቀጥታ ሲተረጎም ‹‹የተላከ›› ወይም ‹‹መልእክተኛ›› ማለት ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ፣ ጠበቅ ባለ መልኩ፣ የመጀመሪያዎቹን አሥራ ሁለት የኢየሱስ ተከታዮችና ከሙታን የተነሣው ክርስቶስ ተገልጦላቸው ምስክሮቹ እንዲሆኑ የሾማቸውን ሌሎችን ያመለክታል (ገላ. 1፡ 19፣ 1ኛ ቆሮ. 15፡ 7)፡፡ ጳውሎስ ከዚህ የተመረጠ ቡድን ውስጥ ራሱን ይመድባል፡፡ ጳውሎስ የእርሱ ሐዋርያነት ከማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር ላይ የማያርፍ መሆኑን አጥብቆ መናገሩ የሚያሳየው አንዳንድ በገላትያ ያሉ ሰዎች የእርሱን የሐዋርያነት ሥልጣን ለመናቅ ሙከራ እንደሚያደርጉ ነው፡፡ ለምን? አስቀድመን እንደተመለከትን በቤተ ክርስቲያን ውሰጥ ካሉ ሰዎች መካከል አንዳንዶች ጳውሎስ ድነት በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ በማመን ብቻ ነው የሚለው መልእክት አላስደሰታቸውም ነበር፡፡ የጳውሎስ ወንጌል ለመታዘዝ ዝቅተኛ ቦታ እየሰጠ እንደሆነ ተሰማቸው፡፡ እነዚህ ችግር ፈጣሪዎች ብልጥ ናቸው፡፡ የጳውሎስ የወንጌል መልእክት መሰረቱ ከሐዋርያነቱ ሥልጣን ምንጭ ጋር በቀጥታ የተሳሰረ መሆኑን ስላወቁ (ዮሐ. 3፡ 34) በዚያ ስልጣን ላይ ኃይለኛ የሆነ ጥቃት ለመሰንዘር ቁርጥ ሀሳብ አደረጉ፡፡ ሆኖም የጳውሎስን ሐዋርያነት በቀጥታ አንቀበልም አላሉም፤ ነገር ግን ይህን ያህል ትርጉም ያለው ነገር አይደለም ብለው ሞገቱ፡፡
ጳውሎስ ከኢየሱስ የመጀመሪያዎቹ ተከታዮች መካከል አንዱ አይደለም አሉ፤ ስለዚህ የእርሱ ስልጣን ከእግዚአብሔር ሳይሆን ከሰዎች- ምናልባትም ጳውሎስንና ሲላስን ሚስዮናውን አድርገው ከላኩ በአንጾኪያ ካሉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ነው አሉ (የሐዋ. 13፡ 1-3)፡፡ ምናልባትም ሥልጣኑ የመጣው በመጀመሪያ ጳውሎስን ካጠመቀው ከአናንያ ሊሆን ይችላል አሉ (የሐዋ. 9፡ 10-18)፡፡ በእነርሱ አመለካከት ጳውሎስ ከአንጾኪያ ወይም ከደማስቆ የተላከ መልእክተኛ ነው- ከዚያ ያለፈ ነገር የለም! ከዚህ የተነሳ የእርሱ መልእክት የእግዚአብሔር ቃል ሳይሆን የራሱ አመለካከት ነው ብለው ሞገቱ፡፡
ጳውሎስ እነዚህ ውንጀላዎች ሊያስከትሉ ያሉትን አደጋ ተገነዘበና ጊዜ ሳያጠፋ እግዚአብሔር የሰጠውን ሐዋርያነት ይከላከላል፡፡
ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ስልጣን ብልጠት ባለበት መንገድ ግድድሮሽ እየገጠመው ያለው በምን መንገዶች ነው? እነዚህን ግድድሮሾች ልንገነዘባቸው የምንችለው እንዴት ነው? ከዚህ የበለጠ ጠቃሚ ጥያቄ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን በተመለከተ በአስተሳሰብዎ ላይ ተጽእኖ ያሳደሩት እንዴት ነው?
ጳውሎስ ሐዋርያነቱን ከመከላከል በተጨማሪ ለገላትያ ሰዎች በጻፈው መልእክት መግቢያ ሰላምታ ላይ ሌላ አጽንዖት የሰጠው ነገር ምንድን ነው? ገላትያ 1፡ 3-5ን ከፊልጵስዩስ 1፡ 2 እና ከቆላስያስ 1፡ 2 ጋር ያነጻጽሩ፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ከጳውሎስ ደብዳቤዎች ልዩ ባሕርያት አንዱ በሰላምታዎቹ ውስጥ ፀጋና ሰላም የሚሉ ቃላትን የሚያገናኝበት መንገድ ነው፡፡ የእነዚህ ሁለት ቃላት ጥምረት በግሪክ እና በአይሁድ ዓለም ውስጥ ከሚደረጉ ልዩ ባሕርይ ካላቸው አብዛኞቹ ሰላምታዎች ተሻሽሎ የመጣ ነው፡፡ የግሪክ ጸሐፊ ‹‹ሰላም›› (chairein) ብሎ በሚጽፍበት ጳውሎስ በግሪክ ቻሪስ (charis) ከሚለው ቃል ጋር ተመሳሳይ ትርጉም ያለውን ‹‹ፀጋ›› የሚል ቃል ይጽፋል፡፡ በዚህ ላይ ‹‹ሰላም›› የሚል የተለመደ የአይሁድ የሰላምታ ቃል ይጨምራል፡፡
የእነዚህ ሁለት ቃላት ጥምረት ዝም ብሎ የቀልድ አነጋገር አይደለም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ቃላቶቹ በመሰረታዊነት የእርሱን የወንጌል መልእክት የሚገልጹ ናቸው፡፡ (እንዲያውም ጳውሎስ እነዚህን ቃላት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከማንኛውም ጸሐፊ የበለጠ ይጠቀምባቸዋል)፡፡ ፀጋና ሰላም ከጳውሎስ ሳይሆን ከእግዚአብሔር አብ እና ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ናቸው፡፡
ጳውሎስ በገላትያ 1፡ 1-6 ውስጥ የትኞቹን የወንጌል ገጽታዎች ነው ያካተተው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ምንም እንኳን ጳውሎስ በመልእክቶቹ መክፈቻ ላይ የወንጌልን ባሕርይ ለማጎልበት ያለው ቦታ ትንሽ ቢሆንም የወንጌልን ፍሬ ነገር በብልሃት በጥቂት አጭር ቁጥሮች ውስጥ ይገልጻል፡፡ ወንጌል የሚሽከረከርበት ማዕከላዊው እውነት ምንድን ነው? እንደ ጳውሎስ ከሆነ ተቃዋሚዎች ያስተጋቡ እንደነበሩት ከሕግ ጋር ስምምነት መፍጠራችን አይደለም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ወንጌል ሙሉ በሙሉ የሚያርፈው ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞቱና በትንሳኤው ለእኛ ባደረገልን ነገር ላይ ነው፡፡ የክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ እኛ ለራሳችን በፍጹም ማድረግ የማንችለውን አንድ ነገር አድርገውልናል፡፡ ብዙዎችን በፍርሃትና በባርነት ከሚይዘው ከክፉ ኃይል ተከታዮቹን ነጻ በማውጣት የኃጢአትንና የሞትን ኃይል ሰብረዋል፡፡ ጳውሎስ እግዚአብሔር በክርስቶስ አማካይነት ለእኛ የፈጠረልንን ፀጋና ሰላም እየገለጸ ሳለ በቁጥር አምስት ላይ ወደሚታየው ድንገተኛ ወደሆነ ምስጋና ይገባል፡፡
ጳውሎስ በገላትያ 1፡ 1-5 ውስጥ የተጠቀማቸውን ቃላት በሚያህሉ በራስዎ ቃላት ወንጌል ማለት ምን ማለት እንደሆነ ያለዎትን የራስዎን መረዳት ይጻፉ፡፡ እርስዎ የጻፉአቸውን ቃላት ወደ ሰንበት ትምህርት ክፍሎ ያምጡ፡፡
በተለምዶ በጳውሎስ ደብዳቤዎች ውስጥ የመክፈቻ ሰላምታን ተከትሎ የሚመጣው ምንድን ነው? ገላትያ የሚለየው እንዴት ነው? ገላትያ 1፡ 6ን ከሮሜ 1፡ 8፣ 1ቆሮ. 1፡ 4፣ ፊል. 1፡ 3 እና 1ተሰ. 1፡ 2 ጋር ያነጻጽሩ፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ምንም እንኳን ጳውሎስ ለአብያተ ክርስቲያናት በጻፋቸው ደብዳቤዎቹ ውስጥ በአከባቢው የሚያጋጥሙትን ግድድሮሾች ሁሉ ቢገልጽም ከመክፈቻ ሰላምታው አስከትሎ የጸሎት ቃል ወይም ለአንባቢዎቹ እምነት እግዚአብሔርን ማመስገንን ልማዱ አድርጎ ነበር፡፡ ጥያቄ ሊያስነሱ በሚችሉ ባሕርያት እየታገሉ ለነበሩ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፋቸው ደብዳቤዎች ውስጥ እንኳን ይህንን አድርጓል (1ቆሮ. 1፡ 4ን እና 5፡ 1ን ያነጻጽሩ)፡፡ በገላትያ የነበረው ሁኔታ ግን እጅግ የሚያበሳጭ ስለነበረ ጳውሎስ ምስጋናን ሙሉ በሙሉ ትቶ ቀጥታ ወደ ነጥቡ ይገባል፡፡
ጳውሎስ በገላትያ እየሆነ ያለው ነገር ምን ያህል እንዳሳሰበው የሚገልጹ ምን ዓይነት ጠንካራ ቃላትን ነበር የተጠቀመው? ገላትያ 1፡ 6-9፣ 5፡12ን ያንብቡ፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጳውሎስ የገላትያ ሰዎችን ለመክሰስ ቃላትን አይቆጥብም፡፡ በቀላሉ ሲገለጽ፣ እንደ ክርስቲያኖች የተጠሩበትን መጠራታቸውን በመካድ ይወነጅላቸዋል፡፡ በአዲሱ ኪንግ ጄምስ እትም መመለስ ተብሎ በቁጥር ስድስት ላይ የተተረጎመው ቃል ብዙ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው ከጦር ሰራዊት በመለየት ለአገራቸው ያላቸውን ታማኝነት የካዱ ወታደሮችን ለመግለጽ ነው፡፡ በመንፈሳዊ አነጋገር፣ ጳውሎስ እያለ ያለው የገላትያ ሰዎች ለእግዚአብሔር ጀርባቸውን እየሰጡ ያሉ ከዳተኞች ናቸው ነው፡፡
የገላትያ ሰዎች እግዚአብሔርን እየተው ያሉት እንዴት ነው? ወደ ሌላ ወንጌል በመመለስ ነው፡፡ ጳውሎስ ከአንድ በላይ የሆነ ወንጌል አለ እያለ ሳይሆን በክርስቶስ ማመን በቂ አይደለም በማለት የሚያስተምሩ አንዳንድ ሰዎች ሌላ ወንጌል እንዳለ አድርገው እያቀረቡ መሆናቸውን እየገለጸ ነው (የሐዋ. 15፡ 1-5)፡፡ ጳውሎስ በዚህ ወንጌልን በማዛባታቸው እጅግ ከመበሳጨቱ የተነሳ ማንም ሌላ ወንጌል የሚሰብክ ቢኖር በእግዚአብሔር እርግማን ሥር እንዲሆን ይፈልጋል (ገላ. 1፡ 8)፡፡ ስለዚህ ነጥብ ጳውሎስ እጅግ ግልጽ ከመሆኑ የተነሳ በመሰረታዊነት ያንኑ ነገር ሁለት ጊዜ ይለዋል (ገላ. 1፡ 9)፡፡
ዛሬ በእኛ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንኳን (በአንዳንድ ቦታዎች) ከአስተምህሮ በላይ በልምምድ ላይ አጽንዖት የመስጠት ዝንባሌ አለ፡፡ እጅግ አስፈላጊው ነገር ልምምዳችን፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ነው ተብሎ ተነግሮናል፡፡ ልምምድ ምንም ያህል አስፈላጊ ቢሆንም በዚህ ቦታ የቀረበው የጳውሎስ ጽሁፍ ስለ ትክክለኛው አስተምህሮ አስፈላጊነት ምን ያስተምረናል?
በገላትያ የነበሩ ችግር ፈጣሪዎች የጳውሎስ ወንጌል የሌሎችን ተቀባይነት ለማግኘት ካለው ፍላጎት የመነጨ ነው እያሉ ነበር፡፡ ጳውሎስ የሰዎችን ተቀባይነት ለማግኘት እየፈለገ ቢሆን ኖሮ በደብዳቤው ውስጥ በተለየ ሁኔታ ምን ማድረግ ይችል ነበር? ገላትያ 1፡ 6-9፣ 11-24ን ልብ ይበሉ፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጳውሎስ ከአህዛብ የተመለሱ ሰዎች እንዲገረዙ ያልጠየቃቸው ለምንድን ነው? የጳውሎስ ተቃዋሚዎች ይህንን ያደረገበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን የሚለወጡ ሰዎች እንዲኖሩ ስለፈለገ ነው አሉ፡፡ ጳውሎስ ከአህዛብ የተመለሱት እንዲገረዙ ያልጠየቀበት ምክንያት አህዛቦች ግዝረትን በተመለከተ የራሳቸው ታአቅቦዎች ስላሉአቸው ነው ብለው ሳያስቡ አልቀሩም፡፡ እርሱ ሰውን ለማስደሰት የሚፈልግ ነው አሉት፡፡ እንደ እነዚህ ላሉ ውንጀላዎች መልስ ሲሰጥ ተቃዋሚዎቹ በቁጥር 8 እና 9 ላይ የጻፋቸውን ጠንካራ ቃላት እንዲመለከቱ ያመለክታቸዋል፡፡ እርሱ ይፈልግ የነበረው ተቀባይነትን ማግኘት ብቻ ቢሆን ኖሮ በእርግጠኝነት ከዚህ በተለየ ሁኔታ መልስ ይሰጥ ነበር፡፡
ጳውሎስ ሰዎችን ለማስደሰት እየሞከሩ የክርስቶስ ተከታይ መሆን አይቻልም ያለው ለምንድን ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጳውሎስ በቁጥር 11 እና 12 ላይ ወንጌሉንና ስልጣኑን የተቀበለው በቀጥታ ከእግዚአብሔር እንደሆነ ከሚገልጸው አባባል በኋላ በቁጥር 13-24 ላይ ያሉ ቃላት ነጥቡን የሚያጸኑት እንዴት ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ቁጥር 13-24 ጳውሎስ ከመለወጡ በፊት የነበረውን ሁኔታ (ቁ. 13፡ 14)፣ በመለወጡ ጊዜ የነበረውን ሁኔታ (ቁ. 15፣ 16) እና ከተለወጠ በኋላ የነበረውን ሁኔታ(ቁ. 16-24) እንደ ራሱ የሕይወት ታሪክ አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ ጳውሎስ በእነዚህ በእያንዳንዱ ክስተቶች ዙሪያ ያሉ ነገሮች እርሱ ወንጌልን ከእግዚአብሔር እንጂ ከማንም መቀበል እንደማይችል ያረጋግጣሉ ይላል፡፡ ጳውሎስ ማንም ሰው ቢሆን ስለ እርሱ መጠራት ጥያቄ በማንሳት መልእክቱን እንዲያንኳስስበት ዝም ብሎ አይፈቅድም፡፡ ምን እንደሆነለት ያውቃል፣ ምን እንዲያስተምር እንደተጠራም ያውቃል፣ የሚያስከፍለው ዋጋ ምንም ቢሆን ያን የተጠራበትን ሥራ ሊሰራው ነው፡፡
በክርስቶስ ስላለዎት መጠራት ምን ያህል እርግጠኛ ነዎት? እግዚአብሔር ምን እንዲያደርጉ እንደጠራዎት እንዴት እርግጠኛ መሆን ይችላሉ? ስለ መጠራትዎ እርግጠኛ ቢሆኑም የሌሎችን ምክር መስማትን ለምን መማር አለብዎት?
‹‹በሁሉም ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ በልደት አይሁድ የነበሩ አንዳንድ አባላት ነበሩ፡፡ እነዚህን ወደ ክርስትና የተለወጡትን አይሁዶች የአይሁድ መምህራን በቀላሉ ስለሚያገኟቸው በእነርሱ አማካይነት በቤተ ክርስቲያናት ውስጥ መቆናጠጫ ቦታ አገኙ፡፡ ከቅዱሳት መጻሕፍት ክርክር የተነሳ ጳውሎስ ያስተማራቸውን አስተምህሮዎች መገርሰስ የማይቻል ነበር፤ ከዚህ የተነሳ የእርሱን ተጽእኖ ለመቃወምና ስልጣኑን ለማዳከም እጅግ ይሉኝታ ቢስ የሆኑ እርምጃዎችን መውሰድን እንደ የመጨረሻ አማራጭ አድርገው ወሰዱ፡፡ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር እንዳልነበረና ከእርሱም ምንም ሥራ እንዳልተቀበለ ተናገሩ፤ ነገር ግን ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ሌሎች ሐዋርያት ካላቸው አመለካከት ተቃራኒ የሆነ ነገርን ያስተምራል አሉት፡፡
“እነዚህን ቤተ ክርስቲያናት ለማጥፋት በፍጥነት ስጋት እየፈጠሩ ያሉ ክፋቶችን ባዬ ጊዜ የጳውሎስ ነፍስ ታወከች፡፡ ከዚያ በኋላ ወዲያውኑ የሀሰት ጽንሰሀሳባቸውን እያጋለጠ እና ከእምነት የተለዩትን በጽኑ እየገሰጻቸው ለገላትያ ሰዎች ጻፈላቸው፡፡›› -Ellen G. White,Sketches From the Life of Paul, pp. 188, 189.
በክፍል ውስጥ ወንጌል ምን እንደሆነ ስላለዎት መረዳት የጻፉትን ማብራሪያዎች ያንብቡ፡፡ አንዳችን ከሌላችን ጽሁፎች ምን እንማራለን?
ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በጻፈው ሰላምታ የክርስቶስ ሞት የተፈጸመው ለተለየ ምክንያት እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ያ ምክንያት ምንድን ነው? ያ ዛሬ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?
በገላትያ 1፡14 ላይ ጳውሎስ ለአባቶች ወግ እጅግ ቀናተኛ እንደነበረ ይናገራል፡፡ ‹‹ወግ›› ሲል ፈሪሳውያን በቃል ያስተላለፏቸው ወጎች እና ራሱ ብሉይ ኪዳን ማለቱ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ወግ በእምነታችን ውስጥ (ቦታ ካለው) ምን ቦታ ነው ያለው? መላውን የወግ ጥያቄ በተመለከተ የጳውሎስ ልምምድ ዛሬ ላለን ለእኛ ምን ማስጠንቀቂያ ሊሰጠን ይችል ይሆን?
ጳውሎስ እርሱ ከሚያምነው በተለየ መንገድ ለሚያምኑት ‹‹ትዕግስት የለሽ›› የሆነ የሚመስለው ለምንድን ነው? የተለየ የወንጌል አመለካከት ስለነበራቸው ሰዎች የጻፋቸውን አንዳንድ ነገሮች እንደ ገና ያንብቡአቸው፡፡ እንደዚህ አይነት ጠንካራና የማይደራደር አቋም ያለው ሰው ዛሬ በእኛ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታየው እንዴት ነው?
ማጠቃለያ፡- በገላትያ የነበሩ ሀሰተኛ መምህራን የጳውሎስ ሐዋርያነት እና የወንጌል መልእክት ከእግዚአብሔር የተሰጡ አይደሉም በማለት አገልግሎቱን ለመሸርሸር እየሞከሩ ነበር፡፡ ጳውሎስ እነዚህን ሁለቱንም ውንጀላዎች ለገላትያ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ የመክፈቻ ቁጥሮች ላይ ይጋፈጣቸዋል፡፡ የድነት መንገድ አንድ ብቻ መሆኑን በድፍረት ያውጅና በእርሱ መለወጥ ዙሪያ የነበሩ ክስተቶች የእርሱ መጠራትና ወንጌል ከእግዚአብሔር ብቻ መሆን እንደሚችሉ ያሳያሉ ይላል፡፡