ወንጌል በገላትያ መጽሐፍ ውስጥ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2017

ከመስከረም 13-19

አስራ፡አረተኛ ትምህርት

Sept 23-29
 

በመስቀል መመካት

 

ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ገላ. 6፡ 11-18፣ ሮሜ 6፡ 1-6፣ 12፡ 1-8፣ 2 ቆሮ. 4፡ 10፣ 5፡ 17፣ 11፡ 23-29፡፡

 

የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - “ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልኩበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ” (ገላ. 6፡14)፡፡

በገላትያ መጽሐፍ ላይ የተደረገው ይህ ጥናት የጋለ ስሜት ያለው ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ደብዳቤው ራሱ ኃይለኛ ስለሆነ ነው፡፡ ጥሪውን ስላወቀ፣ የሰበከውን ነገር እውነት ስላወቀ (አስቀድሞ ብዙ ጊዜ እንደተባለው ሁሉ እውነቱ የመጣው ከጌታ ነው)፣ ጳውሎስ እንደ ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ እና ሆሴዕ ያሉ የብሉይ ኪዳን ነቢያት በነበራቸው የጋለ ስሜት ጻፈ፡፡ እነርሱ በዘመናቸው የነበሩት የእግዚአብሔር ሕዝብ ከስህተት እንዲመለሱ እንደተማጸኑ ሁሉ ጳውሎስም በጊዜው ከነበሩት ጋር ተመሳሳይ ነገር እያደረገ ነው፡፡ በጊዜው የነበሩ ሁኔታዎች ምንም ያህል የተለዩ ቢሆኑም የኤርምያስ ቃላት በእርሱ ዘመን ለነበሩት ሰዎች እንደሆኑ ሁሉ በገላትያ ላሉት ሰዎችም በቀላሉ ይሆናሉ፡‹‹እግዚአሰብሔር እንዲህ ይላል፡- ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፣ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፣ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ ነገር ግን የሚመካ፡- ምህረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና

በማስተዋሉ በዚህ ይመካ ደስ እግዚአብሔር›› (ኤር. 9፡23፣ 24)፡፡ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፣ ይላል ‹‹በግርማ የተሞላው›› የእኛ ሰብአዊ ጥበብ፣ ሐብታችን፣ እና ብርታታችን በከንቱነቱና በዋጋ ቢስነቱ ከክርስቶስ መስቀል ፊት በግልጽ ከቀረበው የበለጠ የቀረበበት ሌላ ቦታ የለም- በገላትያ ለነበሩ እየተሳሳቱ ለነበሩ መንጎቹ የጳውሎስ ትኩረቱ ይህ ነበር፡፡

*የዚህ ሳምንት ትምህርትን ለመስከረም 19 ሰንበት ለመዘጋጀት አጥኑ፡፡
 

መስከረም 14
Sept-24
 

የጳውሎስ የራሱ እጅ

 

ጳውሎስ በገላትያ 6፡11-18 ላይ ያስቀመጠውን የመዝጊያ አስተያየት በሌሎች ደብዳቤዎቹ መጨረሻ ላይ ካስቀመጠው አስተያየት ጋር ያነጻጽሩ፡፡ የገላትያን ደብዳቤ የደመደመበት ሁኔታ ከሌሎቹ ጋር የሚለያይበትና የሚመሳሰልበት በምን መንገድ ነው? (በሮሜ 1 እና 2፣ በቆሮንቶስ፣ በኤፌሶን፣ በፊልጵስዩስ፣ በቆላስያስ እና በ1ኛ እና በ2ኛ ተሰሎንቄ ላይ ያሉ የመጨረሻ አስተያየቶችን አነጻጽሩ፡፡)

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የጳውሎስ የመደምደሚያ አስተያየቶች ሁል ጊዜ አንድ ወጥ አይደሉም፣ ነገር ግን በርካታ የጋራ ነገሮች ይታዩባቸዋል፡- (1) ለተለዩ ግለሰቦች የቀረቡ ሰላምታዎች፣ (2) የመጨረሻ ማነሳሻዎች፣ (3) የግል ፊርማ እና (4) የመዝጊያ ቡራኬ፡፡ እነዚህ ልዩ ባሕርያት ጳውሎስ በገላትያ መልእክት ላይ ካቀረባቸው የመጨረሻ አስተያየቶች ጋር ሲነጻጸሩ ሁለት ወሳኝ ልዩነቶች ይታያሉ፡፡

መጀመሪያ፣ ከጳውሎስ ብዙ ደብዳቤዎች ጋር በማይመሳሰል ሁኔታ የገላትያ መጽሐፍ የግል ሰላምታ የለውም፡፡ ለምን? በደብዳቤው መጀመሪያ ላይ ባሕላዊ የሆነው ምስጋና አለመኖሩ በጳውሎስና በገላትያ ሰዎች መካከል ያለው ግንኙነት ለመዳከሙ ተጨማሪ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ጳውሎስ ትሁት ቢሆንም ደብዳቤው ለወዳጅ የሚጻፍ ዓይነት ደብዳቤ አልነበረም፡፡

ሁለተኛ፣ ጳውሎስ ለጸሐፊ በቃል እየተናገረ ደብዳቤዎቹን ማጻፍ ልማዱ እንደነበረ ማስታወስ አለብን (ሮሜ 16፡22)፡፡ ከጨረሰ በኋላ ብዙ ጊዜ ጳውሎስ ብዕሩን ይወስድና ደብዳቤውን ለመጨረስ ጥቂት ቃላትን በራሱ እጅ ይጽፍ ነበር (1 ቆሮ. 16፡21)፡፡ ነገር ግን ጳውሎስ በገላትያ ከዚህ በፊት ከሚያደርገው ልማድ ይዛነፋል፡፡ ብዕሩን ከጸሐፊው ሲወስድ በገላትያ ያለው ሁኔታ አሁንም ስላሳሰበው ተጨማሪ ነገሮችን በመጻፍ ደብዳቤውን ይጨርሳል፡፡ የገላትያ ሰዎችን በድጋሚ ከሞኝነት መንገዳቸው እንዲመለሱ ሳይማጸናቸው ብዕሩን ማስቀመጥ አልቻለም ነበር፡፡

በገላትያ 6፡11 ላይ ጳውሎስ ደብዳቤውን በትልልቅ ፊደላት መጻፉን አጽንኦት ሰጥቶ ይናገራል፡፡ ምክንያቱ ምን እንደሆነ አናውቅም፡፡ አንዳንዶች ጳውሎስ እያመለከተ ያለው የፊደላቱን መጠን ሳይሆን ቅርጸ-ቢስነታቸውን እንደሆነ ይገምታሉ፡፡ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ጳውሎስ ደብዳቤዎቹን በትክክል መጻፍ ያልቻለው ምናልባት እጆቹ ከስደት የተነሳ ሽባ ስለሆኑ ወይም ድንኳን ከመስራቱ የተነሳ ስለተጣመሙ ሊሆን ይችላል ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ እነዚህ አስተያየቶች የማየት ችግር እንደነበረበት ተጨማሪ ማስረጃ እንደሚሰጡ ያምናሉ፡፡ ሁለቱም አመለካከቶች ሊያሳምኑ የሚችሉ ቢሆኑም ጳውሎስ በትልልቅ ፊደሎች የጻፈበት ምክንያት ዛሬ እኛ በአንድ ሀሳብ ላይ አጽንኦት ለመስጠት ስንፈልግ ከቃሉ ስር እንደምናሰምር ወይም በትልልቅ ፊደላት እንደምንጽፍ ወይም ዘንበል አድርገን እንደምንጽፍ ይሆናል ብሎ ለመደምደም የሚያስችል አይደለም፡፡ ምክንያቱ ምንም ቢሆን ጳውሎስ አንባቢዎቹ ማስጠንቀቂያዎቹንና ተግሳጾቹን እንዲያዳምጡ በእርግጠኝነት ፈልጓል፡፡
 

መስከረም 15
Sept-25
 

በሥጋ መመካት

 

ገላትያ 6፡ 12፣ 13ን አንብቡ፡፡ በዚህ ቁጥር ውስጥ ጳውሎስ ምን እያለ ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ምንም እንኳን ጳውሎስ አስቀድሞ ስለ ተቃዋሚዎቹ አጀንዳና ተነሳሽነት ጥቆማ የሰጠ ቢሆንም (ገላ. 1፡7፣ 4፡17)፣ በገላትያ 6፡ 12፣ 13 ላይ ያቀረባቸው አስተያየቶች ስለ ተቃዋሚዎቹ ያቀረባቸው የመጀመሪያዎቹ ግልጽ አስተያየቶች ናቸው፡፡ እነርሱን ሲገልጽ ‹‹በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ የሚወዱ›› ይላል፡፡ ‹‹መልካም ሆነው መታየት›› የሚለው ሀረግ በግሪክ ቋንቋ ‹‹መልካም ፊት›› መላበስ ማለት ነው፡፡ በርግጥ ‹‹ፊት›› የሚለው ቃል በግሪክ ቋንቋ ተዋንያን ከሚለብሱት ጭንብል ጋር ተመሳሳይ ሲሆን በምሳሌያዊ ሁኔታ ተዋናዩ የሚጫወተውን ሚና ለመግለጽም ጥቅም ላይ ይውል ነበር፡፡ በሌላ አገላለጽ፣ ጳውሎስ እነዚህ ሰዎች የተመልካችን ጭብጨባ እንደሚፈልጉ ተዋንያን ናቸው እያለ ነው ያለው፡፡ በክብርና በውርደት በተመሰረተ ባህል ውስጥ መስማማት አስፈላጊ ስለሆነ እነዚያ ስህተትን ያስተምሩ የነበሩ ሰዎች በገላትያ በነበሩ መሰል አይሁዶችና ሌሎች በኢየሩሳሌም በነበሩ አይሁድ ክርስቲያኖች ፊት የክብር ደረጃቸውን ለማሻሻል የሚፈልጉ ይመስላሉ፡፡

ጳውሎስ ለዚህ ካነሳሳቸው ነገሮች መካከል ስለ አንዱ አስፈላጊ የሆነ ሀሳብ ይሰጣልከስደት ለማምለጥ መፈለግ፡፡ ምንም እንኳን ስደት በሚታይ መልኩ የአካል ድብደባን እንደሚያካትት የታወቀ ቢሆንም ‹‹ቀለል ያለ›› ጭንቀትንና መገለልን በማስከተል ጉዳት ያደርሳል፡፡ ጳውሎስና በይሁዳ የነበሩ ሌሎች ወግ አጥባቂ ቀናኢዎች አንድ ጊዜ የመጀመሪያውን ዓይነት ፈጽመዋል (ገላ. 1፡ 13)፣ ነገር ግን የኋለኛውም ቢሆን በክርስቲያኖች ላይ ተጽእኖ አለው፡፡

የአይሁድ ኃይማኖታዊ መሪዎች አሁንም በብዙ ስፍራዎች ወሳኝ የሆነ ፖለቲካዊ ተጽእኖ አላቸው፡፡ ሕጋዊ የሆነ የሮም እውቅና አላቸው፤ ከዚህ የተነሳ ብዙ የአይሁድ አማኞች ከእነርሱ ጋር ያላቸውን ጥሩ ግንኙነት ለመጠበቅ ጉጉት ነበራቸው፡፡ አሕዛቦችን በመግረዝና ሕግን እንዲጠብቁ በማስተማር በገላትያ የነበሩ ችግር ፈጣሪዎች በአገሬው ካሉ አይሁዶች ጋር አንድ የሚያስማማቸውን ነገር ማግኘት ይችላሉ፡፡ ይህ ከምኩራቦች ጋር የወዳጅነት ግንኙነት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን ከአህዛቦች ጋር እየተሰራ ባለው ሥራ እያደገ የመጣ ጥርጣሬ ከነበራቸው በኢየሩሳሌም ከነበሩ የአይሁድ አማኞች ጋርም ግንኙነታቸውን እንዲያጠነክሩ ያደርጋቸዋል (የሐዋ. 21፡20፣ 21)፡፡ በአንድ በኩል ሲታይ ተግባሮቻቸው ለአይሁዶች የሚሰጡትን ምስክርነት የበለጠ ውጤታማ ያደርግላቸው እንደነበር ምንም ጥርጥር አልነበረውም፡፡

በጳውሎስ አእምሮ ውስጥ ያለው ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢሆን ትርጉሙ ግን ግልጽ ነው፡- ‹‹በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ›› (2 ጢሞ. 3፡ 12)፡፡

እነዚህ ሰዎች ስህተቶቻቸውን ለማስተማር ምክንያታቸው ምን እንደሆነ ያስቡ፡፡ ሁሉም ነገር ከግምት ውስጥ ሲገባ ምክንያታዊ ይመስላል፡፡ ካልተጠነቀቅን በቀር ከሁሉ የተሻለ የሚባለው መንስኤም ቢሆን ወደ ስህተት ሊመራን እንደሚችል ይህ ምን ሊነግረን ይገባል? አንድን ነገር ለማድረግዎ መንስኤው ትክክል ሆኖ ግን የተሳሳቱ ነገሮችን ያደረጉበት የመጨረሻው ጊዜ መቼ ነበር?
 

መስከረም 16
Sept-26
 

በመስቀል መመካት (ገላ. 6:14)

 

“ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልኩበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ›› (ገላ. 6፡ 16)፡፡ ጳውሎስ አንዳንዶች ግዝረትን የግድ እንዲሉ ያነሳሳቸውን ምክንያት ካጋለጠ በኋላ በማጠቃለያ መልክ ብቻም ቢሆን ለገላትያ ሰዎች ለመጨረሻ ጊዜ የወንጌልን መልእክት ያቀርብላቸዋል፡፡ ለጳውሎስ ወንጌል በሁለት መሰረታዊ መመሪያዎች ላይ ተመስርቷል፡- (1) በመስቀል ማዕከላዊነት (ቁ. 14) እና (2) በጽድቅ አስተምህሮ (ቁ. 15)፡፡ የዛሬው ጥናታችን ትኩረት በመጀመሪያው ላይ ነው፡፡

በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እየኖርን ጳውሎስ ስለ መስቀል በመጀመሪያ ያስተላለፋቸው አስተያየቶች የፈጠሩትን ድንጋጤ ማስተዋል ይከብዳል (ገላ. 6፡14)፡፡ ዛሬ የክርስቶስ መስቀል በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ አዎንታዊ ስሜቶችን የሚፈጥር የተለመደ እና የተወደደ ምልክት ነው፡፡ ነገር ግን በጳውሎስ ዘመን መስቀል የሚመኩበት ነገር ሳይሆን የተናቀ ነገር ነበር፡፡ አይሁዶች የተሰቀለውን መሲህ ሀሳብ አስጸያፊ ሆኖ አገኙት፣ ሮማውያንም ስቅለትን እጅግ የሚያስጠላ ሆኖ ከማግኘታቸው የተነሳ የሮም ዜግነት ላለው ሰው ተገቢ የሆነ የቅጣት ዓይነት አድርገው እንኳን አይጠቅሱትም፡፡

የጥንቱ ዓለም የክርስቶስን መስቀል ያየበት ንቀት በግልጽ የታየው እጅግ ቀደምት በሆነ የስቅለት ስዕል ነው፡፡ በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የተሰራ የጥንት አስቂኝ ስዕል ሰው ከአህያ ራስ ጋር ተሰቅሎ ያሳያል፡፡ ከመስቀሉ በታች ለአምልኮ እጁን ወደ ላይ ባነሳ የሰው ስዕል አጠገብ ያለው ጽሁፍ እንዲህ ይነበባል፣ ‹‹አለክሳንደር አምላኩን ያመልካል፡፡›› ነጥቡ ግልጽ ነው፡- የክርስቶስ መስቀል ማሾፊያ ሆኗል፡፡ ጳውሎስ በድፍረት ከክርስቶስ መስቀል በቀር በምንም እንደማይመካ የተናገረው ከዚህ አገባብ በመነሳት ነው! ጳውሎስ ከዓለም ጋር በነበረው ግንኙነት የክርስቶስ መስቀል ምን ልዩነት አመጣ? ገላ. 6፡14፣ ሮሜ 6፡1-6፣ 12፡ 1-8፣ ፊል. 3፡ 8፡፡ የክርስቶስ መስቀል ለአማኙ ሁሉንም ነገር ይለውጣል፡፡ ራሳችንን እንዴት እንደምንመለከት ብቻ ሳይሆን ከዓለም ጋር እንዴት እንደምንገናኝም እንድንገመግም ይገዳደረናል፡፡ ዓለም-ይህ ክፉ ዘመንና በውስጡ ያለው ነገር ሁሉ (1 ዮሐ. 2፡ 16)እግዚአብሔርን ይቃወማል፡፡ ከክርስቶስ ጋር ስለሞትን ዓለም ከዚህ በፊት በእኛ ላይ እንደነበረው ባሪያዎች የማድረግ ኃይል አይኖረውም፣ ከዚህ በፊት ለዓለም የኖርንበት አሮጌ ሕይወት ከዚህ በኋላ አይኖርም፡፡ ጳውሎስ የተጠቀመውን ማመሳሰል በመከተል በአማኙና በዓለም መካከል ያለው መለያየት መሆን ያለበት ሁለቱም ለእርስ በርሳቸው እንደሞቱ ሆኖ ነው፡፡

ከዓለም ጋር ያለዎትን ግንኙነት ሊነካ በሚችልበት ሁኔታ መስቀል ምን አድርጓል? በሕይወትዎ ምን ልዩነት አመጣ? ለሞተልዎ ለጌታ ራስዎን ከመስጠትዎ በፊት ከነበረው አሁን እንዴት በተለየ ሁኔታ ይኖራሉ?
 

መስከረም 17
Sept-27
 

አዲስ ፍጥረት

 

ጳውሎስ ለክርስቲያን ሕይወት የክርስቶስን መስቀል ማዕከልነት አጽንኦት ሰጥቶ ከተናገረ በኋላ አሁን የወንጌል መልእክቱ ሁለተኛው መሰረታዊ መመሪያ በሆነው ጽድቅ በኃይማኖት ላይ አጽንኦት ይሰጣል፡፡

በሩብ ዓመቱ በሙሉ እንደተመለከትን ጳውሎስ በመሰረታዊነት ግዝረትን ከወንጌል በተቃራኒ አስቀምጧል፡፡ ሆኖም የግዝረት ልምምድን ራሱን አልተቃወመም ነበር፡፡ ጳውሎስ ግዝረትን በመቃወም በርካታ ጠንካራ አረፍተ ነገሮችን ተናግሯል (ገላ. 5፡ 2-4ን ይመልከቱ)፣ ነገር ግን የገላትያ ሰዎች አለመገረዝ ከመገረዝ ይልቅ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛል ከሚል ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ አልፈለገም፡፡ አንድ ሰው ለሚያደርገው ነገር ሕጋዊ እንደሚሆን ሁሉ ለማያደርገውም ነገር ሕጋዊ ሊሆን ስለሚችል ጳውሎስ መግለጽ የፈለገው ነጥብ ያ አይደለም፡፡ በመንፈሳዊ አነጋገር የግዝረት ጉዳይ ብቻውን የማይረባ ነው፡፡ እውነተኛ ኃይማኖት የተመሰረተው በውጫዊ ባሕርይ ላይ ሳይሆን በሰብአዊ ልብ ሁኔታ ነው፡፡ ኢየሱስ ራሱ እንዳለው ሰው በውጭ ሲታይ ድንቅ ሊመስል ይችላል፣ ነገር ግን በመንፈሳዊ ሁኔታ በውስጡ የበሰበሰ ሊሆን ይችላል (ማቴ. 23፡ 27)፡፡ አዲስ ፍጥረት መሆን ማለት ምን ማለት ነው? ገላ. 6፡ 15፣ 2 ቆሮ. 5፡ 17፡፡ ይህ ምን ማለት እንደሆነ እርስዎ ራስዎ እንዴት ተለማመዱት?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ክቲቲስ የሚለው ‹‹ፍጥረት›› ተብሎ የተተረጎመው የግሪክ ቃል ነው፡፡ ቃሉ ለአንድ ግለሰብ ‹‹ፍጡር›› (ዕብ. 4፡ 13) ወይም ለሁሉም ‹‹ለተፈጠሩ›› ነገሮች ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል (ሮሜ 8፡ 22)፡፡ በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን ቃሉ የፈጣሪን ተግባር ያመለክታል፡፡ ጳውሎስ መግለጽ የፈለገው ይህን ነው፡፡ ‹‹አዲስ ፍጥረት›› መሆን በግዝረት ወይም በማንኛውም ነገር ቢሆን በሰው ጥረት ሊሆን የሚችል ነገር አይደለም፡፡ ኢየሱስ ይህን ሂደት ‹‹አዲስ ልደት›› ይለዋል (ዮሐ. 3፡5-8)፡፡ እግዚአብሔር በመንፈሳዊነት የሞተን ሰው ወስዶ በውስጡ መንፈሳዊ ሕይወትን እፍ የሚልበት መለኮታዊ ተግባር ነው፡፡ ይህ ጳውሎስ ጽድቅ በኃይማኖት በማለት በተለየ ሁኔታ የሚገልጽበት ሌላኛው ዘይቤያዊ አነጋገር ነው፡፡

ጳውሎስ ይህን የአዲስ ልደት ልምምድ በጥልቀት የሚጠቅሰው በ2ኛ ቆሮንቶስ 5፡ 17 ላይ ነው፡፡ በዚህ ጥቅስ ውስጥ አዲስ ፍጥረት ማለት በሰማይ መጽሐፍት ውስጥ ቦታችንን ከመለወጥ የበለጠ መሆኑን ጳውሎስ ያብራራል፤ ዛሬ በሕይወታችን ለውጥ ያመጣል፡፡ ቲሞቲ ጆርጅ እንዳለው ‹‹መላውን የመለወጥ ሂደት ያካትታል፡ወደ ንስሃና ወደ እምነት የሚመራውን የመንፈስ ቅዱስን እንደገና የማሳደግ ሥራ፣ የሥጋ ፍላጎቶችን የማስገዛትን እና ሕይወት የማግኘትን ዕለታዊ ሂደት፣ በመጨረሻ ከክርስቶስ ምስል ጋር ወደ መስማማት በመምራት በቅድስና ያለማቋረጥ የማደግን ሂደት ያካትታል፡፡›› —Galatians, p.438፡፡ ነገር ግን የሚያጸድቀን አዲስ ፍጥረት መሆን አይደለም፡፡ ይልቁን ይህ መሰረታዊ ለውጥ መጽደቅ ምን ማለት እንደሆነ የማይሳሳት መገለጫ ነው፡፡
 

መስከረም 18
Sept-28
 

የመጨረሻ አስተያየቶች (ገላ. 6:16–18)

 

ጳውሎስ ‹‹በዚህ ሥርዓት በሚመላለሱ›› በሚላቸው ላይ በረከቱን ይሰጣል (ገላ. 6፡ 16)፡፡ በአገባቡ መሰረት ጳውሎስ ስለ የትኛው ‹‹ስርዓት›› የሚናገር ይመስሎታል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

‹‹ሥርዓት›› ተብሎ የተተረጎመው ቃል በቀጥታ የሚያመለክተው ግንበኞች ወይም አናጺዎች ለመለካት የሚጠቀሙበትን ቀጥ ያለ በትር ወይም የብረት ዘንግ ነው፡፡ ቃሉ በመጨረሻ ሰው አንድን ነገር የሚገመግምበትን ደንቦች ወይም መስፈርቶች በማመልከት ምሳሌያዊ ትርጉም ወስዷል፡፡ ለምሳሌ፣ ሰዎች ስለ አዲስ ኪዳን ደንብ ሲናገሩ የቤተ ክርስቲያንን እምነትና ልምምድ ለመወሰን ስልጣን እንዳላቸው ተደርገው የሚታዩትን በአዲስ ኪዳን ውስጥ ያሉትን ሃያ ሰባት መጻሕፍት እያመለከቱ ናቸው፡፡ ስለዚህ የሆነ አስተምህሮ በእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ ላለው ነገር ‹‹ብቁ ካልሆነ›› ተቀባይነት የለውም፡፡

ጳውሎስ በሰውነቱ ላይ የሚሸከማቸው ‹‹የጌታ ኢየሱስ ምልክቶች›› ምንድር ናቸው? ስለ እነርሱ ማንም ሰው ‹‹አያስቸግረኝ›› ብሎ ሲጽፍ ምን ማለቱ ነው? ገላትያ 6፡ 14 ይህን ጥያቄ ለመመለስ ይረዳ ይሆን? ገላ. 6፡ 17፣ 2 ቆሮ. 4፡ 10፣ 11፡ 23-29፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ምልክት የሚለው ቃል በግሪክ ቋንቋ እስቲግማታ ከሚል ቃል የመጣ ሲሆን እስቲግማ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የመጣው ከዚህ ነው፡፡ ጳውሎስ እየጠቆመ ያለው በዚያን ዘመን ጌታው ባሪያውን ለመለየት በጋለ ብረት በመተኮስ ምልክት የሚያደርግበትን ወይም እንደ መለያ እንዲሆን ወይም በአንዳንድ የምስጢር ኃይማኖቶች ለኃይማኖቱ ራሱን የሰጠ ሰው የመሰጠቱ ምልክት እንዲሆን በጋለ ብረት ሰውነትን በመተኮስ ምልክት የማድረግ ልምምድን ሊሆን ይችላል፡፡

በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን ‹‹የጌታ ኢየሱስ ምልክት›› ሲል ጳውሎስ እያመለከተ ያለው በስደትና ችግር ምክንያት በሰውነቱ ላይ ስለቀሩ ጠባሳዎች መሆኑ አያጠራጥርም (2. ቆሮ. 4፡10፣ 11፡24-27ን ይመልከቱ)፡፡ አሁን ተቃዋሚዎቹ እርሱ የለወጣቸውን አህዛብ ለአይሁዳዊነት ተገዥ የመሆናቸው ምልክት እንዲሆን የግዝረት ምልክትን እንዲቀበሉ ያስገድዱአቸዋል፡፡ ነገር ግን ጳውሎስ የማን ባሪያ እንደሆነ የሚያመለክቱ ምልክቶች አሉት፣ ስለዚህ ለእርሱ ከክርስቶስ በቀር ሌላ ታማኝነት የሚያስፈልገው ነገር የለም…፡፡ ጳውሎስ በጌታው አገልግሎት ላይ አያሌ ከጠላቶቹ የተቀበላቸው ጠባሳዎች እርሱ ለክርስቶስ የተሰጠ መሆኑን በአንደበተ ርቱዕነት ተናገሩ፡፡›› -Ellen G. White Comments, The SDA Bible Commentary, vol. 6,p. 989. በኢየሱስ ካለዎት እምነት የተነሳ አካላዊም ሆኑ ሌሎች ያለብዎት ‹‹ምልክቶች›› ምንድር ናቸው? በሌላ አነጋገር እምነትዎ ምን ያህል ዋጋ አስከፍሎታል?
 

መስከረም 19
Sept 29
 

ተጨማሪ ሀሳብ፡-

 

“የቀራንዮ መስቀል በመገዳደር እያንዳንዱን ምድራዊና ገሃነማዊ ኃይልን ያጠፋል፡፡ ተጽእኖ ሁሉ ማዕከል ያደረገው መስቀልን ሲሆን ሁሉም ከእርሱ እየወጣ ይሄዳል፡፡ በእርሱ ላይ ክርስቶስ ለሰብአዊ ዘር ሕይወቱን ስለ ሰጠ ታላቅ የስበት ማዕከል ነው፡፡ ይህ መስዋዕትነት የተከፈለው ሰውን ወደ መጀመሪያው ፍጽምና ለመመለስ ነው፡፡ አዎን፣ ከዚህም በተጨማሪ፣ መስዋዕትነቱ የተከፈለው ጠቅላላ የባሕርይ ለውጥ በመስጠት ሰውን ከአሸናፊዎች በላይ ለማድረግ ነው፡፡

“በክርስቶስ ብርታት የእግዚአብሔርንና የሰውን ታላቅ ጠላት የሚያሸንፉ ሰዎች በሰማይ ጉባኤ በፍጹም ካልወደቁ መላእክት በላይ የሆነ ቦታ ይይዛሉ፡፡ ክርስቶስ እንዲህ በማለት ያውጃል፣ ‹እኔ ከምድር ከፍ ከፍ ባልሁ ጊዜ ሰውን ሁሉ ወደ እኔ እስባለሁ፡፡› መስቀል እርሱን የሚደግፍ ተጽእኖ ባያገኝም ተጽእኖ መፍጠር ይችላል፡፡ ትውልድ ትውልድን ሲተካ ለአሁኑ ሰዓት የሚሆን እውነት እንደ ወቅቱ እውነት ተገልጦአል፡፡ በመስቀል ላይ የነበረው ክርስቶስ ምህረትና እውነት የተገናኘበት፣ ጽድቅና ሰላም የተሳሳሙበት ማዕከል ነው፡፡ ይህ ዓለምን የማንቀሳቀሻ መንገድ ነው (MS 56, 1899).” —Ellen G. White Comments, The SDA Bible Commentary, vol. 6, p. 1113.

 

የውይይት ጥያቄዎች፡

 

ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ በመጥቀስ ደብዳቤውን ከመጀመሩና ከመጨረሱ እውነታ ምን ቁም ነገር ያገኛሉ? ገላ. 1፡3 እና 6፡18ን ያወዳድሩ፡፡

‹‹እኔ ለዓለም ከተሰቀልኩበት. . . ›› (ገላ. 6፡ 14) ከሚለው የጳውሎስ አረፍተ ነገር አንጻር ክርስቲያኖች ከዓለም ጋር ምን ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል? ክርስቲያኖች ለዓለም ሞተው ከሆነ አካባቢን፣ ዘረኝነትን፣ ውርጃን፣ ወዘተ… ከሚመለከቱ ጉዳዮች ጋር እንዴት ግንኙነት መፍጠር አለባቸው?

አንድ ሰው ጳውሎስ በደብዳቤው ውስጥ የጻፈውን ‹‹አዲስ ፍጥረት›› መለማመዱን እንዴት ያውቃል?

በዚህ ሩብ ዓመት በተማሩት መሰረት በሚከተሉት እንደ ሕግ፣ የሕግ ሥራ፣ ጽድቅ በእምነት፣ አሮጌና አዲስ ኪዳን፣ የክርስቶስ ሥራ፣ እና የክርስቲያን ሕይወት ተፈጥሮ ባሉ ርዕሶች ላይ የጳውሎስን አመለካከቶች አንዴት ማጠቃለል ይችላሉ?

ማጠቃለያ:- እውነተኛ ኃይማኖት ውጫዊ ባሕርይን ብቻ ሳይሆን የልብን ሁኔታም ያካትታል፡፡ ልብ ለእግዚአብሔር አልፎ ሲሰጥና ግለሰቡ በእምነት ሲያድግ ሕይወቱ የበለጠውን የክርስቶስን ባሕርይ ያንጸባርቃል፡፡ ልብ ለክርስቶስ መገዛት አለበት፤ ይህ ሲሆን ሌላው ሁሉ ይከተላል፡፡
r>
የትንቢት መንፈስ መጻሕፍትን ተርጉሞና አሳትሞ ማሰራጨት ለሚፈልጉ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች የተሠጠ

ማሳሰቢያ

የትንቢት መንፈስ (Spirit of Prophecy - SOP) መጻሕፍት በሙሉ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት አለም አቀፍ ቤተክርስቲያን ንብረት ናቸው፡፡ እነዚህን ጽሁፎች በከፊልም ሆነ በሙሉ ወደ አማርኛም ሆነ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች በማስተርጎምና በማሳተም ለማዳረስ የሚፈልግ ግለስብም ሆነ ድርጅት፣ ሥራውን ከመጀመሩ በፊት ለኢትዮጵያ ዩኒየን ሚሽን የጽሁፍ ክፍል ጥያቄውን በጽሑፍ በማቅረብና በአካልም ቀርቦ በመወያየት ወደ ሰምምነት ከተደረሰ በኋላ ትርጉሙ፣ ህትመቱና ስርጭቱ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ተከናውኖ ሥራውን መፈፀም ይቻላል፡፡

በዚሁ መሠረት የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን በማሳተም ወንጌልን ለማዳረስ የሚጥሩ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች በእጅጉ ይበረታታሉ፡፡ ሆኖም ግን ይህንን በመተላለፍ ያለ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ፈቃድ በቤተክርስቲያኗ ስም የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን አሳትሞ ማስራጨት፣ በአገሪቱም ሆነ በዓለም ዓቀፍ የሥነ ጽሁፍ ህግ ያስጠይቃል፡፡ በተጨማሪም ድርጅቱ እያስተረጎመ ያለውን መጽሐፍ ሌላ አካል ተመሳሳዩን መጽሐፍ በመተርጎም ላልተፈለገ የጊዜ፣ የጉልበትና የገንዘብ ወጪም ይዳርጋል፡፡ ሰለሆነም የቤተክርስቲያኗ ህግና መተዳደሪያ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት ሁላችንም ጽሁፎችን በማሳተምም ሆነ በማሰራጨት የሶስቱን መላዕክት መልዕክት ለማዳረስ እንድንችል ጌታ ይርዳን፡፡

ድርጅቱ