ወንጌል በገላትያ መጽሐፍ ውስጥ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2017

ከመስከረም 6-12

አስራ ሶስተኛ ትምህርት

Sept 16-22
 

ወንጌልና ቤተ ክርስቲያን

 

ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምነት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ገላ.6፡ 1-10፣ ማቴ.18፡ 15- 17፣ 1 ቆሮ.10፡ 12፣ ሮሜ.15፡ 1፣ ዮሐ. 13፡ 34፣ ሉቃስ 22፡ 3፡፡

 

የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - “እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለኃይማኖት ሰዎች መልካም እናድርግ” (ገላ. 6፡ 10)፡፡

አንዳንድ ገበሬዎች በጣም ትልልቆቹን አትክልቶች ለራሳቸው ለማቆየትና ትንንሾቹን እንደ ዘር አድርገው ለመትከል ወሰኑ፡፡ ከጥቂት ተስፋ አስቆራጭ መከሮች በኋላ ተፈጥሮ ምርቶቻቸውን የብይ መጠን ያላቸው እስኪሆኑ ድረስ እንዳሳነሳቸው አገኙ፡፡ በዚህ ጥፋት አማካይነት ገበሬዎቹ ጠቃሚ የሆነ የሕይወትን ሕግ ተማሩ፡፡ “በሕይወት ውስጥ ከሁሉ የተሻሉ ነገሮችን ለራሳቸው በማድረግ ትራፊዎችን ለዘር መጠቀም አይችሉም፡፡ የሕይወት ሕግ መከር የተከልነውን ነገር ያንጸባርቃል” በማለት አወጀ፡፡

“በሌላ መልኩ፣ ትንንሽ አትክልቶችን መትከል የተለመደ ልምምድ ነው፡፡ የሕይወትን ትልልቅ ነገሮች ለራሳችን በመውሰድ ትርፍራፊዎችን እንተክላለን፡፡ ከተለመደው ውጭ በሆኑ መንፈሳዊ ሕጎች በመጠምዘዝ ራስ ወዳድነታችን ራሰን ባለመውደድ እንዲሸለም እንጠብቃለን፡፡” —International StudentFellowship Newsletter, March 2007. ጳውሎስ ይህን መርህ በገላትያ 6፡ 1-10 ላይ ሥራ ላይ ያውላል፡፡ አባላት ‹‹እርስ በርሳቸው ከመናከስና ከመባላት›› ፈንታ ቤተ ክርስቲያን መንፈስ ሌሎችን ከራሳችን እንድናስቀድም የሚመራን ቦታ መሆን አለባት፡፡ በጸጋ መዳናችንን መረዳት ሌሎችን በምንይዝበት ሁኔታ ትሁታን፣ ታጋሾችና ርኅሩኆች ሊያደርገን ይገባል፡፡
 

መስከረም 7
Sept-17
 

የወደቁትን ወደ ቀድሞ ሁኔታ መመለስ

 

ስለ ክርስቲያን ሕይወት ተፈጥሮ ጳውሎስ በጣም ከፍተኛ የሆኑ ግምቶች ቢኖሩትም (ገላ. 5፡16) በገላትያ 6፡1 ላይ ለአማኞች የሰጠው ምክር በሚያድስ ሁኔታ እርግጠኛ ነው፡፡ ሰብአዊ ፍጡራን ፍጹም አይደሉም፣ እጅግ በጣም ራሳቸውን የሰጡ ክርስቲያኖችም ቢሆኑ ከስህተት ነጻ አይደሉም፡፡ በግሪክ ቋንቋ ጳውሎስ በገላትያ 5፡ 16 ላይ የተናገራቸው ቃላት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሆነ ጊዜ ሊሆን የሚችለውን ነገር እያየ እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲነሱ እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ተግባራዊ ምክር ሰጠ፡፡ ክርስቲያኖች እንደ እነርሱ ያለ አማኝ ወደ ኃጢአት ባሕርይ ሲወድቅ እንዴት ምላሽ መስጠጥ አለባቸው? ገላ. 6፡ 1፣ ማቴ. 18፡ 15-17፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጳውሎስ በገላትያ 6፡ 1 ላይ ከሰጠው ምክር ጥቅም ለማግኘት እርሱ በአእምሮው ውስጥ ያለውን ትክክለኛ ሁኔታ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ይህ በዓረፍተ ነገሩ የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ጥቅም ላይ በዋሉት ሁለት ቃላት ዙሪያ ይሽከረከራል፡፡ የመጀመሪያው ቃል ቢገኝ የሚል ነው፡፡ ቃል በቃል ሲተረጎም ‹‹ቢታወቅ፣ ቢወሰድ ወይም ቢደነቅ›› የሚል ትርጉም አለው፡፡ አገባቡና ከቃሉ ጋር ግንኙነት ያላቸው የተለያዩ በቀላሉ የማይታዩ ነገሮች ጳውሎስ በአእምሮው ሁለት ሁኔታዎች እንዳሉት ያሳያል፡፡ ሌላኛው አማኝ የሆነ ስህተት ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ‹‹ስለሚይዘው›› አማኝ ብቻ የሚናገር ሳይሆን ግለሰቡ ሁኔታዎች ጥሩ ቢሆኑለት ኖሮ ላለመያዝ በሚመርጥበት ባሕርይ ራሱን ‹‹ተወስዶ›› ስለሚያገኝበት ሂደትም ይናገራል (ምሳሌ 5፡ 22ን ይመልከቱ)፡፡

ጳውሎስ እየገለጸ ያለው ስህተት ሆን ተብሎ የተፈጸመ አለመሆኑን የሚጠቀማቸው ቃላቶች ግልጽ ያደርጋሉ፡፡ ፓራፕቶማ ከሚባለው የግሪክ ቃል የመጣው ‹‹ስህተት›› ወይም ‹‹ኃጢአት›› ተብሎ የተተረጎመው ቃል የሚያመለክተው ሆን ተብሎ የተፈጸመ ኃጢአትን ሳይሆን ስህተትን፣ መሰናከልን ወይም የተሳሳተ እርምጃን ነው፡፡ ጳውሎስ አስቀድሞ በመንፈስ ‹‹ስለ መራመድ›› በተናገራቸው አስተያየቶች ብርሃን ሲታይ የኋለኛው ልዩ ትርጉም ይሰጣል፡፡ ምንም እንኳን ይህ የግለሰቡን ስህተት በምንም መንገድ ይቅር የሚል ባይሆንም ጳውሎስ እየተናገረ ያለው በእምቢተኝነት ስለሚፈጸም ኃጢአት አለመሆኑን ግልጽ ያደርጋል (1 ቆሮ. 5፡1-5)፡፡ ይህን በመሰሉ ሁኔታዎች ተገቢ የሆነው ምላሽ ግለሰቡን ወደ ቀድሞ ሁኔታ መመለስ እንጂ ቅጣት ወይም ከአባልነት መሰረዝ መሆን የለበትም፡፡ ‹‹መመለስ›› ተብሎ የተተረጎመው የግሪኩ ካታርቲዞ ማለት ‹‹መጠገን›› ወይም ‹‹በሥርዓት ማስቀመጥ›› ማለት ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የአሳ መረቦችን ‹‹ስለ መጠገን›› ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን (ማቴ. 4፡ 21) በግሪክ ስነ-ጽሁፍ ውስጥ እንደ ሕክምና ቃል የተሰበረ አጥንትን የማስተካከልን ሂደት ይገልጻል፡፡ ወድቆ እግሩ የተሰበረ አማኝን ጥለነው እንደማንሄድ ሁሉ እንደ ክርስቶስ አካል አባላት በእግዚአብሔር መንግስት መንገድ ላይ አብረን ስንጓዝ ተደናቅፈው ስለሚወድቁት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በርጋታ መጠንቀቅ አለብን፡፡

ማቴዎስ 18፡15-17ን ከመተግበር ይልቅ ብዙ ጊዜ ስላናደደን ሰው መጥፎ ነገር የምንናገረው፣ ቁጣችን በዚያ ሰው ላይ እንዲነድ የምንፈቅደው፣ ወይም ለመበቀል እንኳን የምናቅደው ለምንድር ነው?
 

መስከረም 8
Sept-18
 

ከፈተና ተጠንቀቁ

 

“ናታንም ዳዊትን አለው፡- ያ ሰው አንተ ነህ” (2 ሳሙ. 12፡ 7)፡፡ ጳውሎስ በገላትያ 6፡1 ላይ እኛም ደግሞ እንዳንፈተን ራሳችንን እንድንጠብቅ የተናገራቸው ቃላት አሳሳቢነት ችላ መባል የለበትም፡፡ ጳውሎስ ከሰጠው ምክር በስተጀርባ ያለው አንገብጋቢነትና የግል ጭንቀት እርሱ ተማጽኖውን በሚያቀርብበት ሁኔታ ሊታይ ይችላል፡፡ ‹‹ተጠንቀቁ›› ተብሎ የተተረጎመው ቃል ቀጥተኛ ትርጉሙ ‹‹በጥንቃቄ መመልከት›› ወይም ‹‹በጥንቃቄ የተሞላ ትኩረት መስጠት›› የሚል ነው (ከሮሜ 16፡ 17፣ ፊል. 2፡ 4 ጋር አነጻጽሩ)፡፡ ስለዚህ ጳውሎስ በቀጥታ እያለ ያለው ኃጢአት በድንገት እንዳያገኛችሁ ‹‹ራሳችሁን በጥንቃቄ ተመልከቱ›› ነው፡፡ ይህንን ማስጠንቀቂያ ለማጉላት በገላትያ 6፡ 1 የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ከተጠቀመው ከሁለተኛ መደብ ብዙ ቁጥር (‹‹ሁላችሁም››) በቁጥሩ የመጨረሻ አጋማሽ ላይ ወደ ሁለተኛ መደብ ነጠላ (አንተ) ይቀይራል፡፡ ይህ ለመላው ጉባኤ የሚሆን አጠቃላይ ማስጠንቀቂያ አይደለም፤ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላለ እያንዳንዱ ግለሰብ የተሰጠ የግል ማስጠንቀቂያ ነው፡፡

ጳውሎስ የገላትያ ሰዎችን እንደዚህ አጠንክሮ የሚያስጠነቅቀውን ኃጢአት ባሕርይ በግልጽ አይገልጽም፡፡ ምናልባት በአእምሮው ውስጥ ያለ አንድ መተላለፍ ብቻ አልነበረም ይሆናል፣ ነገር ግን ምንም ዓይነት ኃጢአት ቢሆን ሌላውን ሰው ከዚያ ኃጢአት ለመመለስ ጥረት እያደረጉ ያሉትን ያንኑ ኃጢአት የመፈጸም አደጋን እያመለከተ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በገላትያ 5፡ 26 ላይ ‹‹ስለ መመካት›› የሰጠው ማስጠንቀቂያ የሚያመለክተው እነርሱ ለመመለስ ጥረት እያደረጉ ካሉት ሰዎች በሆነ መንገድ በመንፈሳዊነት የተሻሉ እንደሆኑ እንዳይሰማቸው ነው፡፡ ጳውሎስ የገላትያ ሰዎችን ስለ መንፈሳዊ ኩራት ማስጠንቀቅ ለምን አስፈለገው? 1 ቆሮ. 10፡ 12፣ ማቴ. 26፡ 34፣ 2 ሳሙ. 12፡ 1-7፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የክርስቲያን ጉዞ ከሚገጥሙት ታላላቅ አደጋዎች መካከል አንዱ እኛ አንዳንድ ዓይነት ኃጢአቶችን ከመስራት ነጻ እንደሆንን የሚሰማን መንፈሳዊ ኩራት ነው፡፡ አሳዛኙ እውነታ ግን ሁላችንም ተመሳሳይ የሆነ ኃጢአተኛ ተፈጥሮ ያለን መሆኑ ነው-እግዚአብሔርን የሚቃወም ተፈጥሮ፡፡ ስለዚህ ያለ የእግዚአብሔር መንፈስ የመግታት ኃይል ሁኔታዎች ምቹ ሲሆኑ ወደ ማንኛውም ኃጢአት ልናጎነብስ እንችላለን፡፡ ከክርስቶስ ውጭ የሆነውን ትክክለኛ ማንነታችንን ማወቅ በራስ ጽድቅ ኃጢአት ውስጥ እንዳንወድቅ ሊከለክለን ከመቻሉም በላይ ስህተት ለሚፈጽሙ ለሌሎች ሰዎች ትልቅ ርኅራኄ እንዲኖረን ያደርጋል፡፡

በሆነ ጊዜ እርስዎ ራስዎ በደለኛ ሆነው የነበሩባቸውን ኃጢአቶች የፈጸሙትን ሌሎች ሰዎችን እየኮነኑ ራስዎን ያገኙት ስንት ጊዜ ነው (ምናልባትም በልብዎ ውስጥ ብቻ)?
 

መስከረም 9
Sept-19
 

ሸክምን መሸከም (ገላ. 6፡ 2-5)

 

የወደቀውን ሰው ወደ ቀድሞ ሁኔታ ከመመለስ በተጨማሪ ጳውሎስ በገላትያ ላሉ አማኞች ምን ሌሎች ማስጠንቀቂያዎችን ይሰጣል? (ገላ. 6፡ 2-5፤ ደግሞ ሮሜ 15፡ 1፣ ማቴ. 7፡ 12ን ይመልከቱ)፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

በገላትያ 6፡ 5 ላይ ‹‹ሸክም›› ተብሎ የተተረጎመው የግሪኩ ቃል ባሮስ የሚል ነው፡፡ በቀጥታ የሚያመለክተው አንድ ሰው ከባድ ሸክምን ወይም ጭነትን ተሸክሞ ረዥም ርቀትን መጓዝን ነው፡፡ በጊዜ ብዛት ግን በሞቃት ቀን ለረዥም ሰዓታት እንደሚሰራ ሥራ ያለውን (ማቴ. 20፡ 12) ማንኛውንም ዓይነት ችግር ለመግለጽ ዘይቤያዊ አነጋገር ሆኗል፡፡ ‹‹አንዱ የሌላውን ሸክም ይሸከም›› የሚለው የጳውሎስ ትዕዛዝ አገባብ የሚያካትተው አስቀድሞ በተጠቀሰው ቁጥር ውስጥ ያለውን የመሰል አማኞች የግብረ ገብ መዛባትንም በእርግጠኝነት የሚያካትት ሲሆን በአእምሮው ውስጥ የነበረው ሸክምን መሸከም በጣም ሰፊ ነው፡፡ የጳውሎስ መመሪያዎች ችላ መባል ስለሌለበት ስለ ክርስቲያን ሕይወት በርካታ መንፈሳዊ ግንዛቤዎችን ያሳያሉ፡፡ በመጀመሪያ፣ ቲሞቲ ጆርጅ እንዳለው ‹‹ ሁሉም ክርስቲያኖች ሸክም አለባቸው፡፡ በሕይወታችን በሚኖረው የእግዚአብሔር ፈቃድ ቅደም ተከተል በመደገፍ ሸክሞቻችን በመጠን፣ በቅርጽና በዓይነት ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ ለአንዳንዶች በቁጥር 1 ላይ እንደተገለጸው የፈተና ሸክምና የግብረ ገብ መዛባት ውጤቶች ናቸው፡፡ ለሌሎች ደግሞ አካላዊ ሕመም ወይም የአእምሮ መዛባት፣ ወይም የቤተ ሰብ ችግር ወይም የሥራ ማጣት፣ ወይም የአጋንንት ጭቆና ወይም ሌሎች በርካታ ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን ከሸከም ነጻ የሆነ አንድም ክርስቲያን የለም፡፡›› — Galatians, p. 413.

ሁለተኛ፣ እኛ ሸክማችንን ሁሉ ብቻችንን እንድንሸከም የእግዚአብሔር እቅድ አይደለም፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ብዙ ጊዜ ሌሎች ሰዎች የእኛን ሸክም እንድንሸከም እንዲረዱን ከምንፈቅድ ይልቅ ሌሎች ሸክማቸውን እንዲሸከሙ ለመርዳት የበለጠ ፈቃደኞች ነን፡፡ ጳውሎስ እኛም የሚያስፈልጉን ነገሮችና ድክመቶች እንዳሉብን ለመቀበል እምቢ የማለትን ሰብአዊ ኩራት የሚያመለክተውን ይህን በራስ ብቃት የመታመንን አመለካከት ይነቅፋል (ገላ. 6፡ 3)፡፡ እንደዚህ ያለ ኩራት ስለ ሌሎች ያለንን ምቾት የሚቀማ ብቻ ሳይሆን ሌሎች እግዚአብሔር እንዲፈጽሙት የጠራቸውን አገልግሎት እንዳይፈጽሙም ይከለክላቸዋል፡፡ በመጨረሻ፣ የእግዚአብሔር ምቾት የሚገለጠው በእኛ ተግባሮች አማካይነት ስለሆነ እግዚአብሔር የሌሎችን ሸከም እንድንሸከም ይጠራናል፡፡ ይህ ሀሳብ የተገነባው ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል በመሆኗ እውነታ ላይ ነው፡፡ የዚህ መግለጫ በሚከተሉት የጳውሎስ ቃላት ውስጥ ተገልጾአል፣ ‹‹ነገር ግን ሀዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን›› (2 ቆሮ. 7፡ 6)፡፡ ‹‹ለጳውሎስ የእግዚአብሔር መጽናናት የተሰጠው በግል ጸሎቱና እግዚአብሔርን በመጠበቁ ሳይሆን በጓደኛው አብሮ መሆንና እርሱ ባመጣለት የምስራች›› መሆኑን ልብ ይበሉ፡፡

“የእርስ በርሳችንን ሸክም የምንሸከምበት ሰብአዊ ጓደኝነት እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለው ዓላማ ክፍል ነው፡፡” John R. W. Stott, The Message of Galatians, p. 158.

እርዳታ ከመፈለግ የሚያግድዎት ነገር ምንድር ነው—ኩራት፣ እፍረት፣ የእምነት እጦት፣ የራስ ብቃት ስሜት? ችግር ከገጠመዎት የሚተማመኑበትን ሰው በመፈለግ ያ ሰው ሸክምዎን እንዲጋራ ለምን አይጠይቁትም?
 

መስከረም 10
Sept-20
 

የክርስቶስ ሕግ (ገላ. 6፡ 2-5)

 

ጳውሎስ ሸክምን መሸከምን የክርስቶስን ሕግ ከመፈጸም ጋር ያገናኛል፡፡ ‹‹የክርስቶስ ሕግ›› ሲል ምን ማለቱ ነው? ገላ. 5፡ 14፣ 6፡ 2፣ ዮሐ. 13፡ 34፣ ማቴ. 22፡ 34-40፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጳውሎስ ‹‹የክርስቶስ ሕግ›› (ኖሞን ቶ ክሪስቶ) ብሎ ጥቅም ላይ ያዋለው ሀረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሌላ ቦታ አይገኝም፣ ነገር ግን በ1ኛ ቆሮንቶስ 9፡ 21 ላይ ተመሳሳይ የሆነ አባባልን ተጠቅሟል (ኤኖሞስ ክሪስቶ)፡ የዚህ ሀረግ የተለየ መሆን የተለያዩ ዓይነት በርካታ ትርጉሞች እንዲሰጡት አድርጎታል፡፡ አንዳንዶች በስህተት በሲና የተሰጠው የእግዚአብሔር ሕግ በተለየ ሕግ፣ በክርስቶስ ሕግ ለመተካቱ ማስረጃ ነው ብለው ይከራከራሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ሕግ የሚለው ቃል ዝም ብሎ አጠቃላይ ‹‹መርህ›› ነው (ሮሜ 7፡ 21ን ይመልከቱ) ይላሉ፣ ይህ ማለት የሌሎችን ሸክም በመሸከም የኢየሱስን ምሳሌ እየተከተልን ነው ይላሉ፡፡ የኋለኛው ትርጉም የሆነ ጥሩ ነገር ሲኖረው አገባቡና ከገላትያ 5፡ 14 ጋር ተመሳሳይነት ያለው አባባል እንደሚያመለክተው ‹‹የክርስቶስን ሕግ መፈጸም›› የግብረ ገብ ሕግን በፍቅር የመፈጸም ሌላኛው መግለጫ ነው፡፡ ጳውሎስ ቀደም ብሎ በደብዳቤው ውስጥ የክርስቶስ መምጣት የግብረ ገብ ሕግን እንዳልደመሰሰው አሳይቷል፡፡ ከዚያ ይልቅ በፍቅር የተተረጎመ የግብረ ገብ ሕግ በክርስቲያን ሕይወት አስፈላጊ የሆነ ሚና መጫወቱን ይቀጥላል፡፡ ይህ ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ያስተማረውና በሕይወቱ ዘመን ሁሉ፣ በሞቱም ጭምር የተለማመደው ምሳሌ መሆን የሚችል ነገር ነው፡፡ የሌሎችን ሸክም በመሸከማችን የኢየሱስን ዱካ እየተከተልን ብቻ ሳይሆን ሕግንም እየፈጸምን ነን፡፡ በእነዚህ ጥቅሶች ውሰጥ የሚነሳው ሌላኛው ተቃርኖ በገላትያ 6፡ 2 እና ፡ 5 መካከል ያለው ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ችግር በቀላሉ የሚፈታው ጳውሎስ ሁለት የተለያዩ ሁኔታዎችን ለመግለጽ ሁለት የተለያዩ ቃላትን እየተጠቀመ መሆኑን ግለሰቡ ሲገነዘብ ነው፡፡ አስቀድመን እንደተመለከትነው በቁጥር 2 ላይ ለሸክም (ባሮስ) ጥቅም ላይ የዋለው ቃል የሚያመለክተው ረዥም ርቀትን ተሸክመው የሚሄዱትን ከባድ ሸክም ነው፡፡ በቁጥር 5 ላይ ያለው ፖርቲኦን የሚለው ቃል ግን የሚያመለክተው የመርከብን ጭነት፣ ወታደር በጀርባው የሚሸከመውን ሸክም ወይም በእናት ማህጸን ውስጥ ያለውን ሕጻን ነው፡፡

የመጀመሪያዎቹ ሸክሞች ማራገፍ የሚቻሉ ሲሆኑ የኋለኞቹ ግን የማይቻሉ ናቸው፡፡ እርጉዝ እናት ልጇን መሸከም አለባት፡፡ ይህ ምሳሌ እንደሚያመለክተው ሌሎች ሰዎች ሊረዱን የሚችሉአቸው አንዳንድ ሸክሞች አሉ፣ ነገር ግን ሌሎች እንደ በደለኛ ህሊና፣ ስቃይ፣ ወይም ሞት ያሉ ማንም ሊረዳን የማይችላቸው ሸክሞች አሉ፡፡ እነዚህን ሸክሞች ለመሸከም በእግዚአብሔር እርዳታ ብቻ መደገፍ አለብን (ማቴ. 11፡ 28-30)፡ ፡

አንዳንድ ሸክሞችን በተመለከተ ከሌሎች ሰዎች እርዳታን ማግኘት ሲችሉ ሌሎቹን ግን ወደ ጌታ ብቻ መውሰድ ይኖርቦታል፡፡ እርስዎ መሸከም የማይችሉአቸውን ነገሮች ለጌታ መስጠትን እንዴት መማር ይችላሉ?
 

መስከረም 11
Sept-21
 

መዝራትና ማጨድ (ገላ. 6፡ 6-10)

 

በገላትያ 6፡ 7 ላይ ‹‹አይዘበትበትም›› ተብሎ የተተረጎመው ቃል (ሙክቴሪዞ) በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኘው በዚህ ቦታ ብቻ ሲሆን በብሉይ ኪዳን የግሪክ ትርጉም ላይ ብዙ ጊዜ ይታያል፡፡ ቃል በቃል ሲተረጎም ‹‹በንቀት ማሾፍ›› ማለት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን በተለየ ሁኔታ የሚያመለክተው የእግዚአብሔርን ነቢያት መናቅ ነው (2 ዜና 36፡ 16፣ ኤር. 20፡7)፡፡ በአንድ ቦታ ደግሞ በእግዚአብሔር ላይ የማመጽን አመለካከት ሥዕላዊ በሆነ ሁኔታ ለመግለጽ ጥቅም ላይ ውሏል (ሕዝ. 8፡ 17)፡፡ ጳውሎስ ለመግለጽ የፈለገው ሰዎች እግዚአብሔርን ችላ ሊሉ ወይም ትዕዛዛቱን ላይታዘዙ እንደሚችሉ ነው፣ ነገር ግን እግዚአብሔርን ማሞኘት አይችሉም፡፡ እርሱ የመጨረሻው ፈራጅ ነው፣ በመጨረሻ ለድርጊቶቻቸው ዋጋ ይከፍላሉ፡፡ ገላትያ 6፡ 8ን ያንብቡ፡፡ በዚህ ቦታ ጳውሎስ ምን እያለ ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ገጸ-ባሕርያት ውስጥ በመንፈስ ስለ መዝራትና በሥጋ ስለ መዝራት ምን ምሳሌዎችን ያገኛሉ? (ለምሳሌ የሐዋ. 5፡1-5፣ ሉቃስ 22፡3፣ ዳን. 1፡8፣ ማቴ. 4፡1ን ይመልከቱ፡፡)

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጳውሎስ ስለ መዝራትና ስለ ማጨድ የተጠቀመው ዘይቤያዊ አነጋገር ልዩ አይደለም፡፡ በብዙ የጥንት ምሳሌያዊ አነጋገሮች ላይ የሚታይ የሕይወት እውነታ ነው፡፡ ነገር ግን ወሳኙ ነገር ጳውሎስ አስቀድሞ ስለ ሥጋ እና ስለ መንፈስ የሰጣቸውን አስተያየቶች ለማጉላት የተጠቀመበት ሁኔታ ነው፡፡ ጄምስ ዲ ጂ ዱን እንዲህ ብሏል፣ ‹‹የዘመኑ አቻ ቃል ለመምረጥ ነጻ ነን፣ ነገር ግን የምርጫችንን ውጤቶች ለመምረጥ ነጻ አይደለንም›› የሚል ነው፡፡ —Galatians, p. 330.

ምንም እንኳን እግዚአብሔር ኃጢአታችን ከሚያስከትላቸው ምድራዊ ውጤቶች ሁል ጊዜ ነጻ ባያወጣንም ስለፈጸምናቸው መጥፎ ምርጫዎች ተስፋ መቁረጥ የለብንም፡፡ እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ይቅር ስላለን እና እንደ ልጆቹ አድርጎ ስለተቀበለን ልንደሰት እንችላለን፡፡ አሁን ትኩረት ማድረግ ያለብን ሰማያዊ መከርን ሊያስገኙ በሚችሉ አሁን ልንሰራባቸው በምንችላቸው መልካም አጋጣሚዎች ላይ ነው፡፡

ገላትያ 6፡10 ‹‹የክርስቲያን ስነ ምግባር መንታ ትኩረት እንዳለው ያሳያል፡አንደኛው‹‹ለሁሉም ሰዎች መልካም እናድርግ›› የሚል ዓለም አቀፋዊና ሁሉንም የሚያቅፍ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ‹‹በተለይ ለአማኞች ቤተሰብ›› የሚል ውስንና የተለየ ነው፡፡ ጳውሎስ ያቀረበው ዓለም አቀፋዊ ተማጽኖ የተመሰረተው በሁሉም ቦታ ያሉ ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ ስለሆኑ በእርሱ እይታ ለዘላለም ክቡር ናቸው በሚለው ሀሳብ ላይ ነው፡፡ ክርስቲያኖች ይህን ቀዳሚ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መገለጥ በራሱ ጊዜ ሁሉን በሚያሳውር የዘረኝነት፣ የወሲብ፣የጎሰኝነት፣ የመደብ እና ከአዳምና ሄዋን ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሰብአዊ ማህበረሰብን እየቀሰፉ ላሉ በሺሆች ለሚቆጠሩ አክራሪነቶች ሰለባ ሆነዋል፡፡”—Timothy George, Galatians, pp. 427, 428፡፡ ለክፉ ወይም ለመልካም እየዘራችሁ ናችሁ፡፡ የምታጭዱት መከር ምን ዓይነት ነው?
 

መስከረም 12
Sept-22
 

ተጨማሪ ሀሳብ፡-

 

“የእግዚአብሔር መንፈስ ክፉን በህሊና ቁጥጥር ሥር ያደርጋል፡፡ ሰው ራሱን ከመንፈስ ተጽእኖ በላይ ከፍ ሲያደርግ የኃጢአትን መከር ይሰበስባል፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ሰው የአለመታዘዝን ዘር እንዳይዘራ ለመግታት መንፈስ በእርሱ ላይ የሚኖረው ተጽእኖ አነስተኛ ነው፡፡ የሚሰጡ ማስጠንቀቂያዎች በእንደዚህ ዓይነት ሰው ላይ የሚኖራቸው ኃይል አነስተኛ ነው፡፡ ቀስ በቀስ ለእግዚአብሔር ያለው ፍርሃት እየጠፋ ይሄዳል፡፡ በሥጋ ይዘራል፤ ጥፋትን ያጭዳል፡፡ ራሱ የዘራው ዘር መከር እየበሰለ ነው፡፡ የተቀደሱ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ንቆአል፡፡ የሥጋ ልቡ የድንጋይ ልብ ይሆናል፡ እውነትን መቋቋሙ በደለኛነቱን ያጸናል፡፡ ከውኃ ጥፋት በፊት በነበረው ዓለም ሕገ-ወጥነት፣ ወንጀል፣ እና ጠብ የነገሰው ሰዎች የክፉ ዘርን ስለዘሩ ነበር፡፡

‹‹ነፍስን የሚያጠፉ ወኪሎችን በተመለከተ ሁሉም እውቀት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ሰውን ለመቃወም እግዚአብሔር የላከው ከማንኛውም ትዕዛዝ የተነሳ አይደለም፡፡ ሰውን በመንፈሳዊነት እውር አያደርግም፡፡ ሰው እውነትን ከሀሰት መለየት እንዲችል እግዚአብሔር በቂ ብርሃንና ማስረጃ ይሰጣል፡፡ ነገር ግን ሰው እውነትን እንዲቀበል አያስገድድም፡፡ መልካምን ወይም መጥፎን እንዲመርጥ ነጻነት ይሰጠዋል፡፡ ሰው ውሳኔውን በትክክለኛ አቅጣጫ ለመምራት የሚያስችለውን በቂ ማስረጃ ሲቃወምና ክፉውን ሲመርጥ ይህን ድርጊት ለሁለተኛ ጊዜ ያለ አንዳች ችግር ያደርገዋል፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ በታላቅ ጉጉት ራሱን ከእግዚአብሔር ይለይና በሰይጣን ወገን ለመቆም ይመርጣል፡፡ በክፉ እስኪጸና ድረስ እና እንደ እውነት አድርጎ እየተንከባከበ ያለውን ውሸት እስከሚያምን ድረስ በዚህ መንገድ መጓዙን ይቀጥላል፡፡ ተቃውሞው መከሩን አፍርቷል፡፡ (MS 126, 1901).” —Ellen G. WhiteComments, The SDA Bible Commentary, vol. 6, p. 1112.

 

የውይይት ጥያቄዎች፡

 

ተግባራዊ በሆነ መልኩ ወደ ኃጢአት የወደቀውን እንደ እኛ ያለ አማኝ ‹‹መመለስ›› ማለት ምን ማለት ነው?

የተፈጸመው የኃጢአት ዓይነት ወደ ቀድሞ ሁኔታ የመመለስን ሂደት የሚወስነው በምን መንገዶች ነው? ወደ ቀድሞ ሁኔታ መመለስ ማለት ሁሉም ነገር ከዚህ በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ይሆናል ማለት ነውን? ተወያዩ፡፡

ሰዎች በራሳቸው መሸከም ያለባቸው ሸክሞች ስላሉ (ገላ. 6፡ 5) አንድ አማኝ ሌላ ሰውን ለመርዳት መሞከር እንዳለበት ወይም እንደሌለበት እንዴት መወሰን ይችላል?

የእርስዎ ቤተ ክርስቲያን በገላትያ 6 ውስጥ ባለው መመሪያ የምትለካው እንዴት ነው? በግልዎ ልዩነትን ለማምጣት ምን ማድረግ ይችላሉ?

ማጠቃለያ፡- እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል የመገኘቱ ማሳያው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክርስቶስን የመሰለ መንፈስ መታየቱ ነው፡፡ ስህተት ለሚሰሩ ሰዎች ይቅርታና መታደስ በሚሰጥበት ሁኔታ፣ በፈተና ጊዜ አንዱ ሌላውን በሚረዳበት ሁኔታ፣ እና በራሳቸው መካከል ብቻ ሳይሆን ከማያምኑት ሰዎችም ጋር በሚፈጽሙት የደግነት ሥራዎች መታየት ይችላል፡፡