ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡-ገላ. 5፡ 16-25፤ አዳ. 13፡ 4፣ 5፤ ሮሜ 7፡ 14-24፤ ኤር. 7፡ 9፤ ሆሴዕ 4፡ 2፤ ማቴ. 22፤ 35-40፡፡
የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - "ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ"።(ገላ.5:16)
እጅግ በጣም ተወዳጅ ከሆኑ የክርስቲያን መዝሙሮች መካከል አንዱ በሮቤርት ሮቢንሰን የተደረሰው ‹‹ና አንተ የበረከት ምንጭ›› የሚል መዝሙር ነው፡፡ ነገር ግን ሮቢንሰን ሁል ጊዜ የእምነት ሰው አልነበረም፡፡ የአባቱ መሞት ስላስቆጣው ወደ ወራዳነትና ወደ ጠጪነት ሕይወት ገባ፡፡ ዝነኛ የሆነውን ጆርጅ ዋይት ፊልድን ከሰማ በኋላ ሮቢንሰን ህይወቱን በመስጠት የሜቶድስት ቤተ ክርስቲያን ፓስተር ሆነና ያንን የውዳሴ መዝሙር ዘመረ፡፡ መዝሙሩ በመጀመሪያ የሚከተሉትን መስመሮች ያካተተ ነበር፡‹‹እኔ ባለ ብዙ ዕዳ በጸጋህ እኖራለሁ፤ ደግነትህ እንደ ኃብል ወደ አንተ ይሳበኝ፣ ልቤን ግዛው አትመውም ለሰማያዊ ቤቴ፣ ተቅበዝባዡን ልቤን ከአንተ ጋር እሰረው፡፡››
የሆነ ሰው ተቅበዝባዥ ስለሆነው የክርስቲያን ልብ ምቾት ስላልተሰማው ቃላቱን እንደሚከተለው ለወጣቸው፡‹‹ጌታ ሆይ፣ የአምልኮ ዝንባሌ እንዳለኝ ይሰማኛል፤ እንዲሁም የማገለገለውን አምላክ የመውደድ ዝንባሌ አለኝ:: ምንም እንኳን የመጽሐፉ አርታኢ ሀሳብ መልካም ቢሆንም የክርስቲያንን ትግል በትክክል የሚያሳዩት የመጀመሪያዎቹ ቃላት ናቸው፡፡ አማኞች እንደመሆናችን ሁለት ተፈጥሮዎች አሉን፤ እነርሱም ሥጋና መንፈስ ሲሆኑ እነርሱ ደግሞ በግጭት ውስጥ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ኃጢአተኛ ተፈጥሮአችን ከእግዚአብሔር ለመራቅ ‹‹ተጋላጭ›› ቢሆንም ለመንፈሱ ራሳችንን አሳልፈን ለመስጠት ፈቃደኞች ከሆንን ለሥጋ ፍላጎቶች ባሪያዎች መሆን የለብንም፡፡ በዚህ ሳምንት ጥቅሶች ውስጥ የጳውሎስ መልእክት ዋና ግፊት ይህ ነው፡፡
ገላትያ 5፡ 16ን አንብቡ፡፡ ‹‹መራመድ›› የሚለው ሀሳብ ከእምነት ሕይወት ጋር ምን ግንኙነት አለው? ዘዳ. 13፡ 4፣ 5፤ ሮሜ 13፡ 13 ኤፌ. 4፡ 1፣ 17፤ ቆላ. 1፡ 10፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
“መራመድ”የሚለው ቃል ከብሉይ ኪዳን የተወሰደ ዘይቤያዊ አነጋገር ሲሆን ሰው ሊኖረው የሚገባውን ባሕርይ የሚያመለክት ነው፡፡ ጳውሎስ፣ ራሱ አይሁዳዊ የሆነ፣ ብዙ ጊዜ የክርስቲያን ሕይወትን የሚያመለክት ባሕርይን ለመግለጽ ይህን ዘይቤያዊ አነጋገር ይጠቀማል፡፡ ይህን ዘይቤያዊ አነጋገር የተጠቀመበት ሁኔታ ከቀደምት ቤተ ክርስቲያን ጋር ግንኙነት ካለው የመጀመሪያ ስም ጋርም ግንኙነት ሊኖረው ይችላል፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች ክርስቲያን ተብለው ከመጠራታቸው በፊት (የሐዋ. 11፡ 26)፣ ‹‹የመንገዱ›› ተከታዮች በመባል ብቻ ይታወቁ ነበር (ዮሐ. 14፡6፣ የሐዋ. 22፡ 4፣ 24፡ 14)፡፡ ይህ የሚያመለክተው በቀደምት ጊዜያቶች ክርስትና ኢየሱስን ማዕከል ያደረገ የስነ-መለኮት ትምህርት እምነቶች ስብስብ ብቻ ሳይሆን ‹‹ሊኬድበት›› የሚገባ የህይወት ‹‹መንገድ›› ነበር፡፡ ጳውሎስ ስለ መራመድ የተናገረው ዘይቤያዊ አነጋገር በብሉይ ኪዳን ውስጥ ካለው በምን መንገድ ይለያል? ዘጸ. 16፡ 4፤ ዘሌ. 18፡ 4፤ ኤር. 44፡ 23ን ከገላ. 5፡ 16፣ 25፤ ሮሜ 8፡ 4 ጋር አነጻጽሩ፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጠባይ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተተረጎመው እንደ ‹‹መራመድ›› ሳይሆን ልዩ በሆነ ሁኔታ ‹‹በሕግ እንደ መራመድ›› ነበር፡፡ አይሁዶች በሕግ እና በቅድመ አያቶቻቸው ወጎች ውስጥ ያሉትን ሕጎችና ደንቦች ለማመልከት የተጠቀሙት ቃል ሃላክሃህ ነበር፡፡ ሃላክሃህ በተለምዶ ‹‹የአይሁድ ሕግ›› ተብሎ ቢተረጎምም ቃሉ በትክክል ‹‹መራመድ›› በሚለው የዕብራይስጥ ቃል ላይ የተመሰረተ እና ቃል በቃል ሲተረጎም ‹‹የመሄድ መንገድ›› የሚል ትርጉም ያለው ነው፡፡
ጳውሎስ ‹‹በመንፈስ ስለመራመድ›› የሰጣቸው አስተያየቶች ለሕግ የመታዘዝ ተቃራኒዎች አልነበሩም፡፡ ክርስቲያኖች ሕግን በሚጥስ መልኩ እንዲኖሩ ሀሳብ እየሰጠ አይደለም፡፡ ጳውሎስ ሕግንም ሆነ ለሕግ መታዘዝን እየተቃወመ አልነበረም፡፡ እርሱ የተቃወመው ሕግ ያለ አግባብ ጥቅም ላይ እየዋለ የነበረበትን የሕጋዊነት መንገድ ነበር፡፡ እግዚአብሔር የሚፈልገው ትክክለኛ መታዘዝ ሊደረስበት የሚችለው በውጫዊ ግዴታ ሳይሆን መንፈስ በፈጠረው ውስጣዊ መነሳሳት ብቻ ነው (ገላ. 5፡ 18)፡፡
‹‹በመንፈስ ስለ መራመድ›› የራስዎ ልምምድ ምን ነበር? ያንን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነበር? የዚህ ዓይነቱን ጉዞ በሕይወትዎ የበለጠ ከባድ የሚያደርጉ ልምምዶች ምንድር ናቸው?
“ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፣ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም” (ገላ. 5፡ 17፤ ሮሜ 4፡ 14-24ን ደግሞ ይመልከቱ)፡፡
እንደ አማኝ በሕይወትዎ የእነዚህ ቃላትን ከባድና አስቸጋሪ እውነታ እንዴት ተለማመዱ?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጳውሎስ የሚገልጸው ትግል የእያንዳንዱ ሰብአዊ ፍጡር ትግል አይደለም፤ በተለየ ሁኔታ የሚያመለክተው በክርስቲያን ውስጥ ያለውን ውስጣዊ የገመድ ጉተታ ውድድር ነው፡፡ ሰብአዊ ፍጡራን ከሥጋ ፍላጎት ጋር በሚጣጣም ሁኔታ ስለተወለዱ (ሮሜ 8፡ 7)፣ እርግጠኛ የሆነ መንፈሳዊ ጦርነት የሚጀምረው በመንፈስ አዲስ ስንወለድ ብቻ ነው (ዮሐ. 3፡ 6)፡፡ ይህ ማለት ግን ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች የሞራል ጦርነትን አይለማመዱም ማለት አይደለም፤ እነርሱም የሞራል ጦርነት ያጋጥማቸዋል፡፡ ያ ጦርነትም ቢሆን በመጨረሻ የመንፈስ ውጤት ነው፡፡ ነገር ግን አማኝ እርስ በርሳቸው በጦርነት ላይ ያሉ ሁለት ተፈጥሮዎች ስላሉት የክርስቲያን ትግል አዲስ መልክ ይይዛል፡፡
በታሪክ ዘመን ሁሉ ክርስቲያኖች ከዚህ ዓይነት ትግል እፎይታ ለማግኘት ተመኝተዋል፡፡ አንዳንዶች ግጭቱን ወደ ፍጻሜ ለማምጣት የፈለጉት ከማህበረሰቡ በመለየት ሲሆን ሌሎች ደግሞ ኃጢአተኛ ተፈጥሮ ሊወገድ የሚችለው በሆነ መለኮታዊ የጸጋ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ ሁለቱም ጥረቶች የተሳሳቱ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን በመንፈስ ኃይል በእርግጠኝነት የሥጋ ፍላጎቶችን ማሸነፍ ብንችልም በዳግም ምጻት አዲስ አካል እስክንቀበል ድረስ ጦርነቱ በተለያዩ መንገዶች ይቀጥላል፡፡ የትም ብንሄድ ትግሉን ይዘን ስለምንሄድና እስክንሞት ወይም ዳግም ምጻት እስከሚሆን ድረስ ይህን ማድረጋችንን ስለምንቀጥል ከማህበረሰብ መሸሽ ምንም አይጠቅምም፡፡
ጳውሎስ በሮሜ 7 ላይ በክርስቲያኖች ውስጥ ያለው ውስጣዊ ጦርነት የሚፈልጉትን ነገር እንዳያደርጉ እንደሚከለክላቸው ሲጽፍ የጦርነቱን ሙሉ መጠን እያሰመረበት ነው፡፡ ሁለት ተፈጥሮዎች ስላሉን በአንድ ጊዜ በጦርነቱ በሁለቱም ወገን ነን፡፡ መንፈሳዊ ክፍላችን መንፈሳዊውን በመፈለግ ሥጋን ይጠላል፡፡ ነገር ግን ሥጋዊ ክፍላችን ሥጋዊ ነገሮችን በመናፈቅ መንፈሳዊ የሆነውን ነገር ይቃወማል፡፡ የተለወጠ አእምሮ በራሱ ሥጋን ለመቃወም እጅግ ደካማ ስለሆነ ሥጋን ለማሸነፍ ያለን ብቸኛው ተስፋችን ኃጢአተኛ እኛነታችንን በመቃወም ከመንፈስ ጋር ለመወገን በየቀኑ ውሳኔ ማድረግ ነው፡፡ ጳውሎስ በመንፈስ ለመጓዝ እንድንመርጥ የሚገፋፋን ከዚህ የተነሳ ነው፡፡
በእነዚህ ሁለት ተፈጥሮዎች መካከል ስላለው ጦርነት ካለዎት የራስዎ ልምምድ በመነሳት በፍጹም ማብቂያ ከሌለው ከራስ ጋር ከሚደረግ ጦርነት ጋር ለመስማማት ጥረት እያደረገ ላለ ክርስቲያን ምን ምክር ይሰጣሉ?
በሥጋና በመንፈስ መካከል ያሉ ግጭቶችን ካስተዋወቀ በኋላ የሥነ-ምግባርን መጥፎና መልካም ነገሮች በመዘርዘር የዚህ ልዩነትን ተፈጥሮ ጳውሎስ በገላትያ 5፡ 18-26 ላይ ያብራራል፡፡ የመጥፎ ነገሮችና የመልካም ነገሮች ዝርዝር በአይሁድም ሆነ በግሪክና ሮም ስነ-ጽሁፍ ውስጥ ያለ በደንብ የተመሰረተ የስነ-ጽሁፍ ጠባይ ነው፡፡ ይህ ዝርዝር መተው ያለባቸውን መጥፎ ባህሪያትንና መወሰድ ያለባቸውን መልካም ባሕርያትን ለይቶ አስቀምጦአል፡፡
ከዚህ በታች ባለው ንባብ ውስጥ የተዘረዘሩትን የመጥፎና የመልካም ነገሮችን ዝርዝር በጥንቃቄ ይመርምሩ፡፡ ጳውሎስ በገላትያ 5፡ 19-24 ላይ ያስቀመጣቸው ዝርዝሮች በምን መንገዶች ከእነዚህ ዝርዝሮች ጋር ተመሳሳይና ልዩ ናቸው? ኤር. 7፡9፤ ሆሴዕ 4፡2፤ ማር. 7፡21፣ 22፤ 1 ጢሞ. 3፡2፣ 3፤ 1 ጴጥ. 4፡3፤ ራዕይ 21፡8፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጳውሎስ የመጥፎና የመልካም ዝርዝሮችን በደንብ ቢያውቃቸውም በገላትያ መጽሐፍ ውስጥ ሁለቱን ዝርዝሮች በሚጠቀምበት መንገድ ጉልህ ልዩነቶች አሉ፡፡ በመጀመሪያ፣ ጳውሎስ ሁለቱንም ዝርዝሮች ቢያነጻጽራቸውም በተመሳሳይ ሁኔታ አያመለክታቸውም፡፡ ለክፉው ዝርዝር ‹‹የሥጋ ሥራዎች›› የሚል ስም ሲሰጣቸው ለመልካሙ ዝርዝር ደግሞ ‹‹የመንፈስ ፍሬ›› የሚል ስም ይሰጣል፡፡ ይህ አስፈላጊ የሆነ ልዩነት ነው፡፡ ጄምስ ዲ ጂ ዱን እንደጻፈው ‹‹ሥጋ ይጠይቃል፣ ነገር ግን መንፈስ ያቀርባል፡፡ አንዱ ዝርዝር ፍላጎትንና ችሎታን ለማስከበር የመጓጓት እና በጣም አስደሳች የሆነ የራስን ፍላጎት የመፈጸም አየር ሲተነፍስ ሌላኛው ደግሞ ለሌሎች ግድ እንደሚለው፣ ስለ የመንፈስ እርጋታ፣ ስለ ጥንካሬ፣ ስለ ተአማኒነት ይናገራል፡፡ አንዱ ሰብአዊ ማምታታትን የሚያሳይ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የውስጥ ለውጥ ኃላፊነት ያለው ባሕርይ ምንጭ መሆኑን የሚያሳየውን ነጥብ በማጠናከር መለኮታዊ ማስቻልንና ጸጋ ሰጭነትን ያመለክታል፡፡›› —The Epistle to the Galatians, p. 308.
በጳውሎስ ሁለቱ ዝርዝሮች መካከል ያለው ሁለተኛው ማራኪ ልዩነት የክፉ ዝርዝር ‹‹የሥጋ ሥራዎች›› በመባል ሆነ ተብሎ በብዙ ቁጥር መገለጹ ነው፡፡ ነገር ግን ‹‹የመንፈስ ፍሬ›› ነጠላ ነው፡፡ ይህ ልዩነት የሚያመለክተው በሥጋ የሚኖር ሕይወት ከመለያየት፣ ከሕውከት፣ ከመከፋፈልና አንድነትን ከማጥፋት የተሻለ ምንም ነገር አያስተዋውቅም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በመንፈስ ቁጥጥር ስር የሚኖር ሕይወት አንድነትን በሚያጠናክሩ ዘጠኝ ባሕርያት ራሱን የሚገልጽ አንድ የመንፈስ ፍሬን ያፈራል፡፡
በዚህ አውድ አንዳንድ ሰዎች ግለሰቡ/ቧ ቅን እስከሆነ/ች ድረስ ስለ እግዚአብሔር የሚያምነው/የምታምነው ነገር ልዩነት አያመጣም ይላሉ፡፡ ምንም ነገር ቢሆን ከእውነት መራቅ አይችልም፡፡ ጳውሎስ ስለ ክፉ ነገሮች የሰጠው ዝርዝር የዚህን ተቃራኒ ያመለክታል፡- ስለ እግዚአብሔር የተበላሸ አመለካከቶችን መያዝ ስለ ወሲብ ባሕርይና ስለ ኃይማኖት፣ እና ስለ ስነ-ምግባር ሰዎች የተዛቡ ሀሳቦች እንዲኖሩአቸው ይመራል፡፡ እነዚህ ነገሮች የሰብአዊ ግንኙነትን መበላሸት ያስከትላሉ፡፡ ከዚህም በላይ የዘላለም ሕይወትን ወደማጣትም ይመራሉ (ገላ. 5፡ 21)፡፡
“የሥጋ ሥራዎችን” ዝርዝር ይመልከቱ፡፡ እያንዳንዱን መተላለፍ ከአስርቱ ትዕዛዛት መካከል አንዱን ወይም ሁሉንም መተላለፍ እንደሆነ አድርገው በምን መንገዶች መመልከት ይችላሉ?
“የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግስት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው፡፡ እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም›› (ገላ. 5፡ 22-23)፡፡ ለአስርቱ ትዕዛዛት መታዘዝ በእነዚህ ቁጥሮች ላይ እንደተገለጸው የመንፈስን ፍሬ የሚያንጸባርቀው በምን መንገዶች ነው? (ማቴ. 5፡ 21፣ 22፣ 27፣ 28፤ 22፡ 35-40ን ደግሞ ይመልከቱ፡፡)
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
አስርቱ ትዕዛዛት የፍቅር አማራጮች አይደሉም፤ ለእግዚአብሔርና ለሰው እንዴት ፍቅርን ማሳየት እንዳለብን ለመምራት ይረዱናል፡፡ ከሕግ ቃል ምንም ያህል ብልጫ ቢኖረውም ፍቅር ከሕግ ጋር አይጋጭም፡፡ እግዚአብሔርን መውደድና ባልንጀራችንን መውደድ አስርቱን ትዕዛዛት ዋጋ ቢስ ያደርጋል የሚለው ሀሳብ የተፈጥሮ ፍቅር የመሬት ስበትን ሕግ ከንቱ ያደርጋል እንደማለት ነው፡፡
የሥጋ ሥራዎች አንድ ቃል ባላቸው አስራ አምስት ቃላት ከተገለጹበት በተቃራኒ የመንፈስ ፍሬ በዘጠኝ ማራኪ በሆኑ መልካም ተግባራት ተገልጾአል፡፡ ምሁራን እነዚህ ዘጠኙ መልካም ተግባራት ሶስት ሶስት በመሆን በሶስት ማዕቀፍ እንደተዘጋጁ ያምናሉ፣ ነገር ግን በቅደም ተከተላቸው ወሳኝነት ላይ ብዙ መስማማት የለም፡፡ አንዳንዶች በሶስት ቁጥር ውስጥ ስለ መለኮት ውስጣዊ (ያልተገለጸ) መግለጫ እንዳለ ያያሉ፤ ሌሎች ደግሞ ሶስቱ የተዛመዱ ነገሮች ከእግዚአብሔር፣ ከባልንጀራችንና በመጨረሻም ከራሳችን ጋር ግንኙነት መፍጠር ያለብንን መንገዶች ያንጸባርቃሉ ብለው ያምናሉ፤ ሌሎች ደግሞ ዝርዝሩን በዋንኛነት የኢየሱስ መግለጫ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ምንም እንኳን ከእነዚህ ሀሳቦች ውስጥ እያንዳንዱ የራሱ የሆነ ጥሩ ነገር ቢኖረውም ችላ መባል የሌለበት እጅግ ወሳኝ የሆነው ነጥብ ጳውሎስ በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ለፍቅር የሚሰጠው ከሁሉ የበለጠ አስፈላጊነት ነው፡፡
ጳውሎስ ከዘጠኙ መልካም ባሕርያት ውስጥ ፍቅርን የመጀመሪያው አድርጎ ማስቀመጡ በድንገት የሆነ ነገር አይደለም፡፡ ፍቅር በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ስላለው ማዕከላዊ ሚና በገላትያ 5፡6ና 13 ላይ አስቀድሞ አስምሮበታል፣ በመልካም ባሕርያት ዝርዝር ውስጥ በሌላ ቦታም አካቷል (2 ቆሮ. 6፡6፣ 1 ጢሞ. 4፡12፣ 6፡ 11፣ እና 2 ጢሞ. 2፡22))፡፡ ሌሎች መልካም ባሕርያት በሌሎች ክርስቲያናዊ ባልሆኑ ምንጮች ውስጥም የሚገኙ ቢሆኑም ፍቅር ግን በተለየ ሁኔታ ክርስቲያናዊ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚያመለክተው ፍቅር ከብዙ መካከል አንዱ መልካም ባሕርይ ሆኖ ሳይሆን ለሌሎች መልካም ባሕርያት ሁሉ ቁልፍ የሆነ ዋና የክርስቲያን ባሕርይ ሆኖ መታየት እንዳለበት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜም ፍቅርን ማሳየት ከባድ ቢሆንም፣ ፍቅር ከሁሉ የላቀ የመንፈስ ፍሬ ስለሆነ (1 ቆሮ. 13፡ 13፣ ሮሜ 5፡ 5) የእያንዳንዱን ክርስቲያን ሕይወትና አመለካከቶች መደንገግ አለበት (ዮሐ. 13፡34፣ 35)፡፡ በፍቅር ውስጥ ምን ያህል ራስን መካድ ተካቶአል? ራስዎን ሳይክዱ መውደድ ይችላሉን? ኢየሱስ ስለ ፍቅርና ራስን ስለ መካድ ምን ያስተምረናል?
ምንም እንኳን በሥጋና በመንፈስ መካከል ያለው ውስጣዊ ጦርነት በእያንዳንዱ አማኝ ልብ ውስጥ ሁል ጊዜ እየጦፈ የሚቀጥል ቢሆንም የክርስቲያን ሕይወት በሽንፈት፣ በውድቀትና በኃጢአት ቁጥጥር ስር መሆን የለበትም፡፡ እንደ ገላትያ 5፡ 16-26፣ መንፈስ በሥጋ ላይ የሚገዛበትን ሕይወት የመኖር ቁልፉ ምንድር ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ገላትያ 5፡ 16-26 መንፈስ የሚገዛበትን ዓይነት ሕይወት ለመግለጽ አምስት ቁልፍ ግሶችን ይዟል፡፡ መጀመሪያ፣ አማኙ በመንፈስ ‹‹መራመድ›› ያስፈልገዋል (ቁ. 16)፡፡ ፔሪፓቶ (peripateo) የሚለው ቃል በቀጥታ ሲተረጎም ‹‹መመላለስ ወይም መከተል›› የሚል ትርጉም አለው፡፡ ታዋቂ የግሪክ ፈላስፋ የነበረው የአሪስቶትል ተከታዮች እርሱ ወደ ሄዳበት ሁሉ ስለተከተሉት ዟሪዎች ተብለው ይታወቁ ነበር፡፡ ቃሉ በአሁኑ ጊዜ መሆኑ የሚያመለክተው ጳውሎስ አልፎ አልፎ ስለሚደረግ መራመድ ሳይሆን ቀጣይነት ስላለው ዕለታዊ ልምምድ እየተናገረ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቃሉ በመንፈስ ‹‹እንድንራመድ›› የተሰጠ ትዕዛዝ እስከሆነ ድረስ በመንፈስ መራመድ በየዕለቱ ማድረግ ያለብን ምርጫ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ሁለተኛው ግስ ‹‹መመራት›› የሚል ነው (ቁ. 18)፡፡ ይህም ደግሞ የሚያመለክተው መሄድ ወዳለብን ቦታ መንፈስ እንዲመራን መፍቀድ እንዳለብን ነው (ሮሜ 8፡ 14፣ 1ቆሮ. 12፡ 2ን አነጻጽሩ)፡፡ የእኛ ሥራ መምራት ሳይሆን መከተል ነው፡፡
ቀጥለው ያሉት ሁለት ግሶች በገላትያ 5፡ 25 ላይ ይገኛሉ፡፡ የመጀመሪያው ‹‹መኖር›› (በግሪክ ዛኦ) የሚል ነው፡፡ ‹‹ኑሩ›› ሲል ጳውሎስ እያመለከተ ያለው የእያንዳንዱን አማኝ ሕይወት መለየት ስላለበት የአዲስ ልደት ልምምድ ነው፡፡ ጳውሎስ የአሁኑን ጊዜ መጠቀሙ የሚያመለክተው በየቀኑ መታደስ ያለበትን የአዲስ ልደት ልምምድ ነው፡፡ በመንፈስ ስለምንኖር በመንፈስ ደግሞ ‹‹መራመድ›› አለብን በማለት ይጽፋል፡፡ ‹‹መራመድ›› ተብሎ የተተረጎመው ቃል በቁጥር 16 ላይ ካለው ይለያል፡፡ በዚህ ቦታ ያለው ቃል እስቶቺኦ የሚል ነው፡፡ ይህ ቃል ወታደራዊ ቃል ሲሆን ቃል በቃል ሲተረጎም ‹‹በመስመር መሰለፍ፣›› ‹‹እርምጃን መጠበቅ፣›› ወይም ‹‹መከተል›› የሚል ትርጉም አለው፡፡ በዚህ ቦታ ያለው ሀሳብ መንፈስ ሕይወትን መስጠት ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ ሕይወታችንን መምራት አለበት የሚል ነው፡፡ ጳውሎስ በቁጥር 24 ላይ የሚጠቀመው ግስ ‹‹መስቀል›› የሚል ነው፡፡ ይህ ትንሽ አስደንጋጭ ነው፡፡ መንፈስን መከተል ካለብን የሥጋን ሥራዎች ለመግደል ጽኑ ውሳኔ ማድረግ አለብን፡፡ በርግጥ ጳውሎስ እየተናገረ ያለው በምሳሌያዊ አነጋገር ነው፡፡ ሥጋን የምንሰቅለው መንፈሳዊ ሕይወታችንን በመመገብና የሥጋ ፍላጎቶችን በማስራብ ነው፡፡
በክርስቶስ ቃል የተገቡላችሁን ድሎች ለማግኘት አሁን በቀጣይነት እያመለጡአችሁ ያሉትን ምን ለውጦችና ምርጫዎች ማድረግ አለባችሁ?
“የክርስቲያን ሕይወት ሙሉ በሙሉ የተስተካከለ አይደለም፡፡ መጋፈጥ ያለበት ኮስተር ያሉ ጦርነቶች አሉ፡፡ ከባድ ፈተናዎች ይገጥሙታል፡፡ ‹‹ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመቀኛል፡፡›› ወደዚች ምድር ታሪክ መዝጊያ ስንቃረብ የጠላት ጥቃቶች የበለጠውን አሳሳችና ወጥመድ የበዘባቸው እየሆኑ ይሄዳሉ፡፡ ጥቃቶቹ ኃይለኞችና በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ ይሆናሉ፡፡ ብርሃንን እና እውነትን የሚቃወሙ ሰዎች ደንዳኖችና እውነትን የማይቀበሉ፣ እግዚአብሔርን የሚወዱትንና ትዕዛዛቱን የሚጠብቁትን አምርረው የሚጠሉ ይሆናሉ፡፡ (MS 33, 1911).”—Ellen G. White Comments, The SDA Bible Commentary, vol. 6, p. 1111.
“የመንፈስ ቅዱስ ተጽእኖ በነፍስ ውስጥ የክርስቶስ ሕይወት ነው፡፡ ክርስቶስን ማየትና ማናገር አንችልም፣ ነገር ግን የእርሱ ቅዱስ መንፈስ በአንድ ቦታ እንደሆነ ሁሉ በሌላ ቦታም ቅርባችን ነው፡፡ ክርስቶስን በሚቀበል በእያንዳንዱ ግለሰብ ውስጥና አማካይነት ይሰራል፡፡ የመንፈስን በውስጥ መኖር የሚያውቁ ሰዎች የመንፈስ ፍሬዎች የሆኑትን ፍቅርን፣ ደስታን፣ ትዕግስትን፣ የዋህነትን፣ ቸርነትን፣ እና እምነትን ያሳያሉ፡፡ (MS41, 1897).”—Ellen G. White Comments, The SDA Bible Commentary, vol. 6, p. 1112.
የሥጋ ፍላጎቶችን በመስቀል ሀሳብ ላይ ጊዜ ውሰዱ፡፡ ያ ማለት ምን ማለት ነው? እንዴት ነው የምናደርገው? በምን ያህል ፍጥነት ነው ማድረግ ያለብን? ጳውሎስ እንደዚህ ያለ ጠንካራ ግስ የተጠቀመው ለምንድር ነው? መስቀል የሚለውን ቃል መጠቀሙ ከራስ ጋር የሚደረግ ጦርነት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ምን ይነግረናል?
የመንፈስ ፍሬን በማፍራት ሂደት ሰብአዊ ጥረት ምን ሚና ይጫወታል? ስለዚህ ሚና የራሰዎ ልምምድ ምን ይነግሮታል?
የሥጋን ሥራዎች የሚለማመዱ ሰዎች ይህን አባባል ጳውሎስ የዳንነው በሥራ ሳይሆን በእምነት ነው ከሚለው ጋር ማስታረቅ አይችሉም፡፡
ከጌታ ጋር በሚያደርጉት ጉዞ የሚጋፈጡት ትልቁ ትግል ምንድር ነው? ኃጢአትንና ኃጢአት ከእግዚአብሔር ጋር ባለዎት ግንኙነት ላይ የሚፈጽመውን ነገር አይደለምን? ኃጢአት በሕይወቱ ካስከተለው ነገር የተነሳ፣ በተለይም በዚያ ኃጢአት ላይ ድልን እንድንቀዳጅ ከተሰጠን የተስፋ ቃል አንጻር ብቸኝነት፣ ጥርጣሬ፣ እና ተስፋ መቁረጥ ያልተሰማው ክርስቲያን ማን ነው? በኃጢአት ላይ ከሚገኘው ድል አንጻር ይህ እውነታ ተሰጥቶ ሳለ ድነታችን ሙሉ በሙሉ የሚያርፈው ኢየሱስ ለእኛ ባደረገልን ነገር ላይ መሆኑን ሁል ጊዜ ማስታወስ ያለብን ለምንድር ነው?
ማጠቃለያ፡- ምንም እንኳን በሁሉም አማኞች ሕይወት በሥጋ ፍላጎቶችና በመንፈስ ፍላጎቶች መካከል ግጭት ቢኖርም የክርስቲያን ሕይወት ለውድቀት የተፈረደበት መሆን የለበትም፡፡ ክርስቶስ የኃጢአትንና የሞትን ኃይል ስላሸነፈ የክርስቲያን ሕይወት መንፈስ የሥጋ ፍላጎቶችን በርቀት ለማቆየት የሚያስችለውን የእግዚአብሔርን ጸጋ በየቀኑ በማምጣት የሚነግስበት ሕይወት መሆን ይችላል፡፡