ወንጌል በገላትያ መጽሐፍ ውስጥ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2017

ከነሐሴ 27-ጳጉሜ 3

አስራ አንደኛ ትምህርት

Sept2-8
 

በክርስቶስ ነጻነት

 

ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡-ገላ. 5፡ 1-15፤ 1 ቆሮ.6፡ 20፤ ሮሜ 8፡ 1፤ ዕብ. 2፡ 14፣ 15፤ ሮሜ 8፡ 4፤ 13፡ 8፡፡

 

የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - “ወንድሞች ሆይ፣ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያት አይስጥ፣ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ›› (ገላ. 5፡ 13)፡፡

በገላትያ 2፡14 ውስጥ ጳውሎስ በክርስቶስ ኢየሱስ ያገኘነውን ‹‹ነጻነት›› የመጠበቅን አስፈላጊነት በአጭሩ አስቀምጦአል፡፡ ነገር ግን ጳውሎስ ሌላ ጊዜም በብዛት እንደሚያደርገው ስለ ‹‹ነጻነት›› ሲናገር ምን ማለቱ ነው? ይህ ነጻነት ምንን ያካትታል? ይህ ነጻነት እስከ ምን ድረስ ነው የሚሄደው? ገደቦች አሉት ወይ? በክርስቶስ የተገኘው ነጻነት ከሕግ ጋር ምን ግንኙነት አለው? ጳውሎስ እነዚህን ጥያቄዎች የሚመልሰው የገላትያን ሰዎች ስለ ሁለት አደጋዎች በማስጠንቀቅ ነው፡፡ የመጀመሪያው ሕጋዊነት ነው፡፡ በገላትያ ያሉ የጳውሎስ ተቃዋሚዎች በራሳቸው ባሕርይ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን በማግኘት ሀሳብ ላይ ስለተጠመዱ ነጻ የማውጣት ባሕርይ ያለውን የክርስቶስን ሥራ፣ በክርስቶስ አማካይነት በእምነት ያገኙትን ድነት ማየት አቅቶአቸዋል፡፡ ሁለተኛው ስጋት ክርስቶስ ለእኛ የገዛልንን ነጻነት በመተው ወደ ፍትወት በመንሸራተት ያለ አግባብ የመጠቀም ዝንባሌ ነው፡፡ ይህ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ነጻነት ከሕግ ጋር ፍጹም ተቃራኒ እንደሆነ አድርገው በስህተት ይገምታሉ፡፡

ሕጋዊነትና ፍትወት በእኩል ደረጃ ተገዥዎቻቸውን በባርነት ውስጥ ስለሚያደርጉአቸው የነጻነት ተቃራኒዎች ነው፡፡ ነገር ግን ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች ያለው ተማዕጽኖ በክርስቶስ መብት ያለው ባለቤት በሆኑበት እውነተኛው ነጻነት ጸንተው እንዲቆሙ ነው፡፡
 

ነሐሴ 28
Sept-3
 

ክርስቶስ ነጻ አውጥቶናል

 

“በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ›› (ገላ. 5፡ 1)፡፡

አንድ ወታደራዊ አዛዥ እያመነቱ ላሉ ሰራዊቶቹ ወደ ፊት እንዲቀጥሉ ትዕዛዝ እንደሚሰጥ ሁሉ የገላትያ ሰዎች በክርስቶስ ያገኙትን ነጻነት አሳልፈው እንዳይሰጡ ያበረታታቸዋል፡፡ የጳውሎስ ንግግር ኃይለኛነትና ጥልቀት ቃሎቹ ከወረቀት ወደ ተግባር እንዲዘሉ ያደርጋል፡፡ በርግጥ የጳውሎስ ሀሳብ በትክክል ይህን ይመስላል፡፡ ምንም እንኳን የዚህ ጥቅስ ዋና ሀሳብ አስቀድሞ ከነበረውና ቀጥሎ ከመጣው ጋር የተገናኘ ቢሆንም ድንገተኛነቱና ከግሪክ ጋር የቃል አገባብ ግንኙነት አለመኖሩ ጳውሎስ ይህ ጥቅስ እንደ ትልቅ የማስታወቂያ ሰሌዳ እንዲቆም መፈለጉን ያሳያል፡፡ በክርስቶስ ነጻነት የሚለው ሀሳብ መላውን የጳውሎስ መከራከሪያ ስለሚያጠቃልል የገላትያ ሰዎች ነጻነታቸውን አሳልፈው በመስጠት አደጋ ውስጥ ነበሩ፡፡ ገላትያ 1፡3፣ 4፤ 2፡ 16፤ እና 3፡ 13ን ያንብቡ፡፡ በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉ አንዳንድ ዘይቤአዊ አነጋገሮች ምንድር ናቸው? ክርስቶስ ለእኛ ያደረገልንን ነገርስ እንድናስተውል እንዴት ይረዱናል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

‹‹ለነጻነት ክርስቶስ ነጻ አውጥቶናል›› (ገላ. 5፡1) የሚሉት የጳውሎስ ቃላት በአእምሮው ሌላ ተለዋጭ ሀሳብ እንዳለ ያሳያል፡፡ በዚህ ሀረግ ውስጥ ያለው የቃሎቹ አቀማመጥ ባሪያዎች ነጻ ከሚወጡበት የተቀደሰ ነጻ መውጣት መሰረታዊ ደንብ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ባሪያዎች ሕጋዊ መብቶች ስለሌሉአቸው አማልክት የእነርሱን የነጻነት ዋጋ ከፍለው ነጻ ሊያወጡአቸው ይችላሉ ተብሎ ስለሚታመን ባሪያው ነጻ እንኳን ቢሆን የአምላኩ ንብረት ነው፡፡ በርግጥ ልምምዱ ተግባር ላይ የሚውልበት ሂደት ልበ ወለድ ነው፤ ነጻ የመውጣት ዋጋ የሆነውን ገንዘብ ወደ ቤተ መቅደስ ግምጃ ቤት ወስዶ የከፈለው ባሪያው ነበር፡፡ ለምሳሌ ከ201 ዓ.ዓ. እስከ 100 ዓ.ም በነበረው ጊዜ በዴልፊ ለፓይቲያን አፖሎ በተሰራው ቤተ መቅደስ ውስጥ በተገኙ ወደ አንድ ሺህ በሚጠጉ የተቀረጹ ጽሁፎች ላይ ያለውን መሰረታዊ ደንብ ልብ ይበሉ፡- ‹‹ነጻነት ለመስጠት የፓይቲያን አፖሎ ከአምፊሳ ሶሲባስ ስሟ ኒካይያ የተባለች ባሪያ ገዝቷል…፡፡ ነገር ግን ለነጻነት የሚከፈለውን የግዥ ዋጋ ለአፖሎ የሰጠችው ኒካይያ ነበረች፡፡› ›› —Ben Witherington III, Grace in Galatia (Grand Rapids, Mich.: William B. Eerdmans Publishing Company, 1998), p. 340. ይህ መሰረታዊ ደንብ ጳውሎስ ከተጠቀመው ቃል ጋር መሰረታዊ የሆነ ተመሳሳይነትን ይጋራል፣ ነገር ግን መሰረታዊ የሆነ ልዩነትም አለ፡፡ ጳውሎስ በተጠቀመው ዘይቤአዊ አነጋገር ውስጥ ልበ ወለድ ነገር የለም፡፡ የግዥውን ዋጋ እኛ አልሰጠንም (1 ቆሮ. 6፡ 20፣ 7፡ 23)፡፡ ዋጋው ከእኛ አቅም በላይ ነው፡፡ እኛ ራሳችንን የምናድንበት አቅም የለንም፣ ነገር ግን እኛ ለራሳችን ማድረግ ያልቻልነውን ነገር ኢየሱስ ጣልቃ በመግባት አደረገልን፡፡ የኃጢአታችንን ቅጣት በመክፈል ከኩነኔ ነጻ አወጣን፡፡

የራስዎን ሕይወት ይመልከቱ፡፡ ራስዎን ማዳን እንደሚችሉ አስበው ያውቃሉ? መልስዎ በኢየሱስ ስለተሰጠን ነገር ምን ያህል አመስጋኞች መሆን እንዳለብን ምን ሊነግርዎት ይገባል?
 

ነሐሴ 29
Sept-4
 

የክርስቲያን ነጻነት ባህርይ

 

በነጻነት ጸንቶ ስለመቆም ጳውሎስ የሰጠው ትዕዛዝ በተናጥል የተደረገ አይደለም፡፡ ይህን የሚቀድም አስፈላጊ የሆነ አረፍተ ነገር አለ፡- ‹‹ክርስቶስ ነጻ አውጥቶናል፡፡›› ክርስቲያኖች በነጻነታቸው ጸንተው መቆም ያለባቸው ለምንድር ነው? ክርስቶስ ነጻ ስላወጣቸው ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ የእኛ ነጻነት ክርስቶስ አስቀድሞ ለእኛ ያደረገልን ነገር ውጤት ነው፡፡

የዚህ ዓይነት እውነትን የሚገልጽ አረፍተ ነገርን ተከትሎ ግፊት የማድረግ አቀራረብ በጳውሎስ ደብዳቤዎች ውስጥ የተለመደ ነው ( 1 ቆሮ. 6፡ 20፤ 10፡ 13፣ 14፤ ቆላ. 2፡ 6)፡፡ ለምሳሌ፣ ጳውሎስ በሮሜ ምዕራፍ 6 ውስጥ በክርስቶስ ስንሆን ስለሚኖረን ሁኔታ የሚገልጹ እንደ ‹‹አሮጌው ሰውነታችን ከእርሱ ጋር ተሰቅሎአል›› (ሮሜ 6፡ 6) ያሉ በርካታ አመልካች አረፍተ ነገሮችን አስቀምጦአል፡፡ በዚህ እውነት መሰረት ጳውሎስ አስገዳጅ የሆነ ማደፋፈሪያ ይሰጣል፣ ‹‹ስለዚህ በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት እንዲሰለጥን አትፍቀዱ›› (ሮሜ 6፡ 12)፡፡ ይህ ጳውሎስ በተለየ ሁኔታ ‹‹በክርስቶስ የሆናችሁትን ሁኑ›› የሚልበት መንገድ ነው፡፡ በወንጌል ያለው የስነ-ምግባር ሕይወት የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ለማረጋገጥ ነገሮችን ለማድረግ የመጣርን ሸክም አያቀርብም፡፡ ክርስቶስ ነጻ ያወጣን ከምንድር ነው? ሮሜ 6፡ 14፣ 18፤ 8፡ 1፤ ገላ. 4፡ 3፣ 8፤ 5፡ 1፤ ዕብ. 2፡ 14፣ 15፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የክርስትና ሕይወትን ለመግለጽ ነጻነት የሚለውን ቃል መጠቀም በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከማንኛውም ቦታ ይልቅ በጳውሎስ ደብዳቤዎች ውስጥ የበለጠ ጎልቶ ይታያል፡፡ ነጻነት የሚለው ቃልና ተዛማጅ ቃላት በጳውሎስ ደብዳቤዎች ውስጥ 28 ጊዜ የተጠቀሱ ሲሆን በሌላ ቦታ ግን 13 ጊዜ ብቻ ተጠቅሰዋል፡፡

ጳውሎስ ነጻነት ሲል ምን ማለቱ ነው? ፖለቲካዊ ነጻነትን፣ ኢኮኖሚያዊ ነጻነትን ወይም ደስ እንዳሰኘን የመኖር ነጻነትን አያመለክትም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ባለን ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ነጻነት ነው፡፡ አገባቡ እንደሚነግረን ጳውሎስ እያመለከተ ያለው በሕግ ከሚመራ ክርስትና የተነሳ ከሚመጣው ባርነትና ኩነኔ ነጻ ስለመውጣት ነው፣ ነገር ግን ነጻነታችን ከዚህ የበለጠ ብዙ ነገር ያካትታል፡፡ ከኃጢአት፣ ከዘላለማዊ ሞት እና ከሰይጣን ነጻ መውጣትን ያካትታል፡፡ “ከኢየሱስ ክርስቶስ ውጭ የሰው ኑሮ የሚገለጸው በባርነት ነው፡- የሕግ ባርነት፣ ዓለምን ለሚቆጣጠሩ ክፉ ኃይሎች ባርነት፣ የኃጢአት ባርነት፣ የሥጋ ባርነት፣ እና የሰይጣን ባርነት፡፡ እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው የእነዚህን ባሪያ አሳዳሪዎች ግዛት ለማፍረስ ነው፡፡›› —TimothyGeorge, Galatians, p. 354.

በሕይወትዎ ባሪያ የሆኑላቸው ነገሮች ምንድር ናቸው? ገላትያ 5፡ 1ን በአእምሮዎ ያጥኑና በክርስቶስ ያለዎትን ነጻነት በሕይወትዎ እውነት እንዲያደርግልዎት እግዚአብሔርን ይጠይቁ፡፡
 

ነሐሴ 30
Sept-5
 

የሕጋዊነት አደገኛ ውጤቶች (መዘዞች)፡ (ገላ. 5፡ 2-12)

 

ጳውሎስ ገላትያ 5፡2-12ን የሚያስተዋውቅበት መንገድ እርሱ ለመናገር የፈለገውን ነገር አስፈላጊነት ያመለክታል፡፡ ለማስተዋወቅ የተጠቀመባቸው ቃላት በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ‹‹ተመልከቱ (ESV)፣ ‹‹አድምጡ!›› (NRSV)፣ ‹‹ቃሎቼን ልብ በሉ!›› (NIV)፣ ‹‹እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ›› (ESV) የሚሉ ናቸው፡፡ ጳውሎስ የማሞኘት ጨዋታን እየተጫወተ አይደለም፡፡ ተመልከቱ የሚለውን ኃይለኛ ቃል በመጠቀም አንባቢዎቹ ሙሉ ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ እያቀረበ ብቻ ሳይሆን የሐዋርያነት ስልጣኑንም እየገለጠ ነው፡፡ አህዛቦች መዳንን ለማግኘት ለግዝረት ሕግ መገዛት ካለባቸው የገላትያ ሰዎች ደግሞ በውሳኔያቸው ውስጥ ያሉ አደገኛ ውጤቶችን መገንዘብ እንዳለባቸው እንዲያስተውሉ ይፈልጋል፡፡

ገላትያ 5፡2-12ን ያንብቡ፡፡ መላውን የግዝረት ጥያቄ በተመለከተ ጳውሎስ ምንድር ነው የሚያስጠነቅቀው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ለግዝረት ራስን በማስገዛት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት የመሞከር የመጀመሪያዎቹ ውጤቶች ግለሰቡ መላውን ሕግ እንዲታዘዝ ማድረጉ ነው፡፡ ጳውሎስ በቁጥር 2 እና 3 ላይ የተጠቀመው ቋንቋ ደስ የሚል የቃላት ጨዋታን ያካትታል፡፡ እርሱ ክርስቶስ አይጠቅማቸውም ይላል (ophelesei)፤ ይልቁን ለሕግ ለመታዘዝ ይገደዳሉ (opheiletes)፡፡ ሰው ሕግ እንደሚፈልገው መኖር ከፈለገ መከተል የሚፈልጋቸውን ትዕዛዛት መምረጥ አይችልም፡፡ ያለው ምርጫ ሁሉንም መታዘዝ ወይም አንዱንም አለመታዘዝ ነው፡፡ ሁለተኛ፣ ከክርስቶስ ‹‹ይቆረጣሉ›› ወይም ይለያሉ፡፡ በስራ ለመጽደቅ መወሰን በክርስቶስ የመጽደቅን የእግዚአብሔርን መንገድ አለመቀበል ነው፡፡ ‹‹ሁለቱንም መንገዶች መያዝ አይቻልም፡፡ ራሳችሁን ማዳን እንደማትችሉ አምናችሁ በመቀበል ክርስቶስን መቀበል ትችላላችሁ፣ ግዝረትን ስትቀበሉ ግን ራሳችሁን ማዳን እንደምትችሉ እየገለጻችሁ ናችሁ፡፡›› — John R. W. Stott, The Message of Galatians (Leicester, England: InterVarsity Press, 1968), p. 133.

ጳውሎስ ለግዝረት ያቀረበው ሶስተኛው ተቃውሞ መንፈሳዊ እድገትን ስለመገደቡ ነው፡፡ ለንጽጽር የተጠቀመው ሩጫውን ለመጨረስ እየገሰገሰ ያለን ሯጭ ሩጫውን እንዳይጨርስ ሆን ብሎ ማደናቀፍን ነው፡፡ እንዲያውም ‹‹አደናቀፈ›› ተብሎ የተተረጎመው ቃል (ቁ. 7) ጥቅም ላይ የዋለው በወታደራዊ ክበቦች ውስጥ ‹‹መንገድን ማበላሸት ወይም ድልድይን ማፍረስ ወይም ጠላት በነጻነት እንቅስቃሴ እንዳያደርግ በመንገድ ላይ እንቅፋቶችን ማስቀመጥ›› የሚለውን ሀሳብ ለመግለጽ ነው ፡፡›› —The SDA BibleCommentary, vol. 6, p. 978. በመጨረሻ፣ ግዝረት የመስቀልን ስድብ ወይም አሳፋሪነት ያስወግዳል፡፡ እንዴት? የግዝረት መልእክት ራሰህን ማዳን እንደምትችል ያመለክታል፤ እንደዚህ ከመሆኑ የተነሳ ለሰብአዊ ኩራት መደለያ ነው፡፡ ነገር ግን የመስቀል መልእክት ሙሉ በሙሉ በክርስቶስ መደገፋችንን ስለምንቀበል ለሰብአዊ ኩራት አስጸያፊ ነው፡፡ ጳውሎስ በግዝረት ላይ ሙጭጭ በሚሉ ሰዎች ላይ እጅግ ከመናደዱ የተነሳ ቢለዋው ቦታውን ስቶ ስልብ ባደረጋቸው ብሎ ይመኛል! ቃላቱ ጠንካራ ቢሆኑም የጳውሎስ አነጋገር ይህን ጉዳይ ምን ያህል የምር አድርጎ እንደሚመለከት ያሳያል፡፡
 

ጳጉሜ 1
Sept-6
 

ፍትወት ሳይሆን ነጻነት (ገላ. 5፡ 13)

 

ገላትያ 5፡13 በገላትያ መጽሐፍ ውስጥ ነገሮች አዲስ መልክ የሚይዙበትን ነጥብ ያመለክታል፡፡ እስከዚህ ነጥብ ድረስ ጳውሎስ ሙሉ በሙሉ ትኩረት ያደረገው በመልእክቱ ስነ-መለኮታዊ ይዘት ላይ ሲሆን አሁን ጉዳዩን ወደ ክርስቲያን ባሕርይ ይመልሳል፡፡ በሕግ ስራ ያልዳነ ሰው እንዴት መኖር አለበት? ጳውሎስ የገላትያ ሰዎች እንዳይፈጽሙ ለመከልከል የፈለገው የነጻነት አጠቃቀም የቱ ነው? ገላ. 5፡ 13፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጳውሎስ በጸጋና አማኞች በክርስቶስ ባገኙት ነጻነት ላይ አጽንዖት መስጠቱ ሊያስከትል ያለውን የተሳሳተ መረዳት በደንብ አውቆ ነበር (ሮሜ 3፡ 8፤ 6፡ 1፣ 2) ፡፡ ነገር ግን ችግሩ የጳውሎስ ወንጌል ሳይሆን የሰብአዊ ዘር የፈለገውን ነገር የማድረግ ዝንባሌ ነበር፡፡ የታሪክ ገጾች የሰብአዊ ዘር ብልሽትና ወደ ሞራል ውዝግብ መውረድ ራሳቸውን ለመግዛት ካለመቻላቸው ጋር በቀጥታ የተገናኘ መሆኑን በሚያሳዩ የሰዎች፣ የከተሞችና ሕዝቦች ታሪኮች ቆሽሸዋል፡፡ ይህ ዝንባሌ በራሱ/በራሷ ሕይወት ውስጥ ያልተሰማው/ያልተሰማት ማን ነው/ናት? ለዚህ ነው ጳውሎስ የኢየሱስ ተከታዮች የስጋን ፈቃድ እንዳይፈጽሙ ግልጽ የሆነ ጥሪ የሚያቀርብላቸው፡፡ እንዲያውም የዚህ ተቃራኒ የሆነውን እንዲያደርጉ ይፈልጋል፣ ‹‹በፍቅር አንዱ ሌላውን ያገልግል፡፡›› ሌሎችን በፍቅር የሚያገለግል ሰው ይህ ለራስና ለሥጋ በመሞት ብቻ ሊፈጸም የሚችል ነገር መሆኑን ያውቃል፡፡ የሥጋቸውን ፈቃድ የሚያደርጉ ሰዎች ሌሎችን ወደ ማገልገል የሚያዘነብሉ አይደሉም፡፡ ነገር ግን የዚህን ተቃራኒ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

ስለዚህ በክርስቶስ ያገኘነው ነጻነት ከዓለም ባርነት ነጻ መውጣት ብቻ ሳይሆን ወደ አዲስ ዓይነት አገልግሎት፣ ሌሎችን ከፍቅር የተነሳ ወደ ማገልገል ኃላፊነት ጥሪ ነው፡፡ ‹‹ጎረቤትን ያለ አንዳች እንቅፋት ለመውደድ መልካም ዕድል፣ ለሥልጣንና

ለማዕረግ ጥያቄ ከማቅረብ ይልቅ የጋራ በሆነ ራስን መስጠት ላይ የተመሰረተ ሰብዓዊ ማህበረሰብን ለመፍጠር አጋጣሚ ነው፡፡›› — Sam K. Williams, Galatians (Nashville, 1997), p. 145. Tenn.: Abingdon Press, ከክርስትና ጋር ከመተዋወቃችን የተነሳ እና አዳዲሶቹ ትርጉሞች ገላትያ 5፡ 13ን ካስቀመጡበት የቃላት አቀማመጥ የተነሳ እነዚህ ቃላት ለገላትያ ሰዎች ያስተላለፉትን አስደናቂ ኃይል ችላ ልንል እንችላለን፡፡ በመጀመሪያ፣ የዚህን ዓይነት አገልግሎት የሚቀሰቅስ ፍቅር ሊሆን የማይችል ተራ የሆነ ሰብአዊ ፍቅር አለመሆኑን የግሪክ ቋንቋ ያመለክታል፤ ሰብአዊ ፍቅር በሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ጳውሎስ በግሪክ ቋንቋ ፍቅር ከሚለው ቃል በፊት ‹‹ዘ›› የሚል አርቲክል መጠቀሙ በመንፈስ አማካይነት ብቻ ልንቀበለው የምንችለውን መለኮታዊ ፍቅር እያመለከተ መሆኑን ያሳያል (ሮሜ 5፡ 5)፡፡ በትክክል የሚያስደንቀው ነገር ቢኖር ‹‹ማገልገል›› ተብሎ የተተረጎመው ቃል በግሪክ ቋንቋ ‹‹ባሪያ መሆን›› የሚል ነው፡፡ ነጻነታችን ማንም አይድረስብን ብለን ለራሳችን ብቻ እንድንኖር ሳይሆን በእግዚአብሔር ፍቅር ላይ ተመስርተን አንዳችን ለሌላችን ባሪያ እንድንሆን ነው፡፡

ታማኝ ይሁኑ፡- በክርስቶስ ያገኙትን ነጻነት እዚያም እዚህም ትንሽ ኃጢአት ለመፈጸም መጠቀም እንደሚችሉ አስበው ያውቃሉ? የዚህ ዓይነት አመለካከት መጥፎነቱ ምንድር ነው?
 

ጳጉሜ 2
Sept-7
 

ሕግን ሁሉ መፈጸም (ገላ. 5:13–15)

 

ጳውሎስ ‹‹ሕግን ሁሉ ስለመፈጸም›› (ገላ. 5፡3) የሰጣቸውን አሉታዊ አስተያየቶች ‹‹ሕግን ሁሉ ስለመፈጸም›› (ገላ. 5፡14) ከሰጠው አዎንታዊ አረፍተ ነገር ጋር እንዴት ማስታረቅ ይችላሉ? ሮሜ 10፡ 5፤ ገላ. 3፡ 10፣ 12፤ 5፡ 3ን ከሮሜ 8፡4፤ 13፡ 8፤ ገላ. 5፡ 14 ጋር አነጻጽሩ፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ብዙ ሰዎች ጳውሎስ ‹‹ሕግን ሁሉ ስለመፈጸም›› በሰጣቸው አሉታዊ አስተያየቶችና ‹‹ሕግን ሁሉ ስለመፈጸም›› ባቀረባቸው አዎንታዊ ንግግሮች መካከል ያለውን ንጽጽር እርስ በርሱ እንደሚጋጭ አባበል አድርገው አይተውታል፡፡ ነገር ግን እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ሀሳቦች አይደሉም፡፡ የዚህ መፍትሄ ያለው ጳውሎስ ከሕግ ጋር በተገናኘ ሁኔታ የክርስቲያን ባሕርይን ለመተርጎም የሚጠቀምባቸው ሁለት የተለያዩ ዘዴዎች በመሆኑ ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ጳውሎስ አዎንታዊ በሆነ መልኩ ሕግን ስለመጠበቅ ሲናገር በፍጹም ‹‹ሕግን ማድረግ›› በማለት አይገልጽም፡፡ ይህን ሀረግ የሚያቆየው ከሕግ በታች እየኖሩ ሕግ የሚያዘውን ነገር ‹‹በማድረግ›› የእግዚአብሔርን ማረጋገጫ ለማግኘት የሚሞክሩ ሰዎችን የተሳሳተ ባሕርይ ለማመልከት ነው፡፡

ይህ ድነትን በክርስቶስ ያገኙ ሰዎች አይታዘዙም ማለት አይደለም፡፡ ምንም ነገር ከእውነት መራቅ አይችልም፡፡ ጳውሎስ ሕግን ‹‹ይፈጽማሉ›› ይላል፡፡ እንዲህ ማለቱ እውነተኛ የክርስቲያን ባሕርይ ዝም ብሎ ሕግን ‹‹ከማድረግ›› ውጫዊ መታዘዝ እጅግ የሚበልጥ ነው ማለቱ ነው፤ ሕግን ‹‹ይፈጽማል፡፡›› ጳውሎስ መፈጸም የሚለውን ቃል የሚጠቀመው ‹‹ከማድረግ›› ባሻገር ስለሚሄድ ነው፡፡ የመታዘዝ ዓይነቱ ስር የሰደደው በኢየሱስ ነው (ማቴ. 5፡ 17ን ይመልከቱ)፡፡ ሕግን መተው ወይም ወደ ፍቅር ብቻ መቀነስ ሳይሆን አማኙ የመላውን ሕግ እውነተኛ ሀሳብና ትርጉም የሚለማመድበት መንገድ ነው!

እንደ ጳውሎስ ከሆነ የህግ ሙሉ ትርጉም የሚገኘው የት ነው ? ዘሌ. 19፡ 18፤ ማር. 12፡ 31፣ 33፤ ማቴ. 19፡ 19፤ ሮሜ 13፡ 9፤ ያዕ. 2፡ 8፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ምንም እንኳን ከዘሌዋውያን መጽሐፍ የተጠቀሰ ቢሆንም ጳውሎስ በገላትያ መጽሐፍ ውስጥ የተናገረው አረፍተ ነገር ኢየሱስ ዘሌዋውያን 19፡ 18ን በተጠቀመበት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ነገር ግን ዘሌዋውያን 19፡ 18ን እንደ መላው የህግ ማጠቃለያ አድርጎ የጠቀሰው አይሁዳዊ መምህር ኢየሱስ ብቻ አልነበረም፡፡ ከኢየሱስ በፊት አንድ ትውልድ ቀደም ብሎ የኖረ ረቢ ሂሌል እንዲህ ብሎ ነበር፣ ‹‹ለራስህ የምትጠላውን ነገር ለባልንጀራህ አታድርግ፤ ይህ የህግ ሁሉ ማጠቃለያ ነው፡፡›› ነገር ግን ኢየሱስ ሕግን ያየበት ሁኔታ በመሰረታዊነት የተለየ ነው (ማቴ. 7፡12)፡፡ የበለጠውን አዎንታዊ ብቻ ሳይሆን ሕግና ፍቅር የማይጣጣሙ ነገሮች አለመሆናቸውንም ያሳየ ነበር፡፡ ያለ ፍቅር ሕግ ባዶና ቀዝቃዛ ነው፤ ያለ ሕግ ፍቅር አቅጣጫ የለውም፡፡

ቀላሉ ነገር ምንድር ነው? ለምን? መልስዎን ወደ ክፍል ያምጡ፡፡
 

ጳጉሜ 3
Sept-8
 

ተጨማሪ ሀሳብ፡-

 

“ትክክለኛ እምነት ሁል ጊዜ በፍቅር ይሰራል፡፡ ወደ ቀራንዮ ስትመለከቱ ዓላማው ተግባራችሁን እንዳትፈጽሙ ነፍሳችሁን ጸጥ ለማድረግ አይደለም፣ ራሳችሁን ለእንቅልፍ እንድታዘጋጁ ለማድረግ አይደለም፣ ነገር ግን በኢየሱስ እምነትን ለመፍጠር፣ ነፍስን ከራስ ወዳድነት ቆሻሻ በማንጻት የሚሰራ እምነትን ለመፍጠር ነው፡፡ በእምነት ክርስቶስን ስንይዝ ስራችን ተጀመረ ማለት ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ብርቱ በሆነ ጦርነት መሸነፍ ያለባቸው የተበላሹ እና ኃጢአተኛ የሆኑ ባሕርያት አሉት፡፡ እያንዳንዱ ነፍስ የእምነትን ገድል እንዲጋደል ይጠበቅበታል፡፡ አንድ ግለሰብ የክርስቶስ ተከታይ ከሆነ ለግል ጥቅሙ ንቁ መሆን አይችልም፣ ልበ ደንዳና መሆን አይችልም፣ ርኅራኄ የሌለው አይሆንም፡፡ በንግግር ሸካራ አይሆንም፡፡ ጉረኛና ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ አይሆንም፡፡ የሰውን ሀሳብ በማጣጣል ራሱን ከፍ የሚያደርግ አይሆንም፣ ሌሎችን የሚጎዱ ቃላትን በመጠቀምና በመገሰጽ አይኮንንም፡፡

“የፍቅር ሥራ የሚመነጨው ከእምነት ሥራ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ኃይማኖት ማለት የማያቋርጥ ሥራ ማለት ነው፡፡ ‹መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያከብሩ ዘንድ ብርሃናችሁ በሰዎች ፊት ይብራ፡፡› ‹የራሳችሁን መዳን በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ ሥሩ›፣ የእርሱን መልካም ፈቃድ እንድትፈጽሙ በውስጣችሁ መፈለግንም ማድረግንም የሚሰራ እግዚአብሔር ነው፡፡ ለመልካም ሥራ የምንቀና ሰዎች መሆን አለብን፤ የጀመራችሁትን መልካም ስራ ለማስቀጠል ተጠንቀቁ፡፡ እውነተኛው ምስክር እንዲህ ይላል፣ ‹ሥራህን አውቃለሁ፡፡›› “የራሳችን የትጋት ተግባራት በራሳቸው ድነትን እንደማያረጋግጡልን እውነት ቢሆንም ከክርስቶስ ጋር የሚያገናኘን እምነት ደግሞ ነፍስን ለተግባር ያነሳሳል፡፡ (MS 16, 1890).” —Ellen G. White Comments, The SDA Bible Commentary, vol. 6, p. 1111

 

የውይይት ጥያቄዎች፡

 

- እንደ ሰንበት ትምህርት ክፍል በሐሙስ ጥናታችሁ ለቀረበው የመጨረሻው ጥያቄ የሰጣችኋቸውን መልሶች እንደገና ተመልከቷቸው፡፡ አብዛኞቹ ሰዎች ቀሎአቸው የሚያገኙት የትኛውን አማራጭ ነው? ለምን? ሕግን መፈጸም ማለት ምን ማለት እንደሆነ መልስዎ ምን አስፈላጊ የሆኑ እውነቶችን ጠቆመልዎ?

ጳውሎስ እምነት በፍቅር ‹‹ይሰራል›› ይላል፡፡ ምን ማለቱ ነው?

በክርስቶስ ያገኙትን ነጻነት ኃጢአትን ለመስራት ለመጠቀም የመፈለግን ሀሳብ ይመርምሩ፡፡ ይህን ማድረግ በጣም የሚቀለው ለምንድር ነው? ሰዎች እንደዚህ ሲያስቡ ምን ዓይነት ወጥመድ ውስጥ እየወደቁ ናቸው? (1 ዮሐ. 3፡ 8ን ይመልከቱ፡፡)

ማጠቃለያ፡- ጳውሎስ ወንጌል ምን እንደሆነ ለመግለጽ ከሚጠቀማቸው ተወዳጅ ቃላት መካከል አንዱ ነጻነት ነው፡፡ ክርስቶስ ከዓለም ባርነት ነጻ ሊያወጣን ያደረገልንን እና እንዴት ክርስቲያናዊ ሕይወትን እንድንኖር እንደተጠራን ያካትታል፡፡ ነገር ግን ነጻነታችን የሕጋዊነት ወይም የፍትወት ግዳይ ሆኖ እንዳይወድቅ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ክርስቶስ ነጻ ያወጣን ራሳችንን እንድናገለግል ሳይሆን በአገልግሎት ሕይወታችንን ለባልንጀሮቻችን እንድንሰጥ ነው፡፡