ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብቡ፡- ገላ. 4፡21-23፤ ዘፍ. 1፡ 28፤ 2፡2፣ 3፤ 3፡15፤ 15፡1-6፤ ዘጸ. 6፡2-8፤ 19፡3-6፡፡
የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - ‹‹ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር ናት እርስዋም እናታችን ናት›› (ገላ. 4፡ 26)፡፡
የብሉይ ኪዳንን ሥልጣን የማይቀበሉ ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ በሲና የተሰጠውን ሕግ ከወንጌል ጋር እንደማይጣጣም አድርገው ይመለከታሉ፡፡ በሲና የተሰጠው ቃል ኪዳን በሰብአዊ ታሪክ ውስጥ ድነት ሕግን በመታዘዝ የሚገኝ መሆኑን የሚያመለክት ዘመንን፣ ኃይማኖታዊ ስርዓትን ይወክላል ብለው ይደመድማሉ፡፡ ነገር ግን ሰዎች ሕግ እንደሚፈልግባቸው መኖር ስላልቻሉ እግዚአብሔር አዲስ ኪዳንን፣ በክርስቶስ መልካም ሥራ የጸጋ ኪዳንን ጀመረ ይላሉ፡፡ ከዚህ የተነሳ ሁለቱን ቃል ኪዳኖች የሚረዱት እንደሚከተለው ነው፡አሮጌው ኪዳን በሕግ የተመሰረተ ሲሆን አዲሱ ኪዳን ደግሞ በጸጋ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
ይህ አመለካከት ምንም ያህል የተለመደ ቢሆንም ስህተት ነው፡፡ ድነት ሕግን በመታዘዝ ተግባራዊ ሆኖ አያውቅም፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊው አይሁድነት ከጅምሩ ጀምሮ ሁል ጊዜም የጸጋ ኃይማኖት ነበር፡፡ ጳውሎስ በገላትያ እየተጋፈጠ የነበረው ሕጋዊነት የተዛባ ክርስትናን ብቻ ሳይሆን የተዛባ የብሉይ ኪዳን ትምህርትንም ነበር፡፡ ሁለቱ ኪዳኖች የጊዜ ጉዳዮች አይደሉም፤ ነገር ግን ሰብአዊ አመለካከቶችን የሚያንጸባርቁ ናቸው፡፡ ከቃየልና ከአቤል ጊዜ ጀምሮ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት የሚሞክሩባቸውን ሁለት የተለያዩ መንገዶች ይወክላሉ፡፡ አሮጌው ኪዳን እንደ ቃየል በስህተት እግዚአብሔርን ለማስደሰት በራሳቸው መታዘዝ የሚደገፉ ሰዎችን ይወክላል፤ በተቃራኒው አዲሱ ኪዳን እንደ አቤል እግዚአብሔር ቃል የገባላቸውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ጸጋ የሚደገፉ ሰዎችን ልምምድ ይወክላል፡፡
ብዙ ሰዎች ጳውሎስ በገላትያ 4፡ 21-31 ላለው የእስራኤል ታሪክ የሰጠውን ትርጉም በደብዳቤው ውስጥ ካሉ ንባቦች ሁሉ እጅግ በጣም ከባድ ንባብ እንደሆነ አድርገው ይመለከታሉ፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት በብሉይ ኪዳን ውስጥ ያሉ ግለሰቦችንና ክስተቶችን ሰፊ እውቀት የሚሻ እጅግ ውስብስብ ክርክር ስለሆነ ነው፡፡ ይህን ንባብ ለማስተዋል የመጀመሪያው እርምጃ የጳውሎስ ክርክር ማዕከል ለሆነው የቃል ኪዳን ሀሳብ፣ ለብሉይ ኪዳን መሰረታዊ መረዳት መኖር ነው፡፡
‹‹ኪዳን›› ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ ቃል ቤሪት ነው፡፡ ይህ ቃል በብሉይ ኪዳን ውስጥ ወደ ሶስት መቶ ጊዜ ያህል የተጻፈ ሲሆን የሚያመለክተው አስገዳጅ የሆነ ኮንትራትን፣ ስምምነትን ወይም ውልን ነው፡፡ ቃል ኪዳኖች ለብዙ ሺህ አመታት በጥንቱ የቅርብ ምስራቅ አገሮች በህዝቦችና በአገሮች መካከል የነበሩትን ግንኙነቶች ለመግለጽ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል፡፡ እንስሳትን ማረድ (ቃል በቃል ሲተረጎም ‹‹መቁረጥ››) ቃል ኪዳኖቹን የመፈጸም ሂደት አካል ነበር፡፡ እንስሳቱን መግደል የሚያመለክተው ቃል ኪዳኑንና ግዴታዎቹን መጠበቅ ያቃተው አካል ምን እንደሚሆንበት ነበር፡፡
ከአዳም እስከ ኢየሱስ ድረስ እግዚአብሔር ከሰብአዊ ዘር ጋር ግንኙነት የፈጠረው የአዳኙን መምጣት ማዕከል ባደረጉ እና በዳዊታዊው ቃል ኪዳን ፍጻሜ ባገኙ ተከታታይ በሆኑ የቃል ኪዳን ተስፋዎች ነበር (ዘፍ. 12፡ 2፣ 3፤ 2 ሳሙ. 7፡ 12-17፤ ኢሳ. 11)፡፡ በባቢሎን ምርኮ ለነበሩ እስራኤላውያን ከሚመጣው ዳዊታዊው መሲህ ጋር በተገናኘ ሁኔታ (ሕዝ. 36፡ 26-28፤ 37፡ 22-28) እግዚአብሔር እጅግ ውጤታማ የሆነ ‹‹አዲስ ኪዳን›› ቃል ገባላቸው (ኤር. 31፡ 31-34)፡፡›› —Hans K.LaRondelle, Our Creator Redeemer (Berrien Springs, Mich.:Andrews University Press, 2005), p. 4.
ኃጢአት ከመግባቱ በፊት በኤደን ገነት እግዚአብሔር ከአዳም ጋር የገባው የመጀመሪያው ቃል ኪዳን መሰረቱ ምን ነበር? ዘፍ. 1፡ 28፤ 2፡ 2፣ 3፣ 15-17፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጋብቻ፣ ሥራ እና ሰንበት የፍጥረት ቃል ኪዳን አጠቃላይ መሰናዶዎች አካል ሆነው ሳሉ የእነዚህ ሁሉ የትኩረት ነጥብ የተከለከለውን ፍሬ እንዳይበሉ የተሰጠው የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ነው፡፡ የቃል ኪዳኑ መሰረታዊ ባሕርይ ‹‹ታዘዝና ኑር!›› የሚል ነበር፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር በተጣጣመ ሁኔታ ከተፈጠረ ተፈጥሮ ጌታ የማይቻል ነገርን አይጠይቅም፡፡ መታዘዝ የሰብአዊነት የተፈጥሮ ዝንባሌ ነበር፤ ሆኖም አዳምና ሔዋን ተፈጥሮአዊ ያልነበረውን ለማድረግ መረጡ፤ በዚህ ድርጊታቸው የፍጥረትን ኪዳን የጣሱ ብቻ ሳይሆን አሁን በኃጢአት ለተበላሹ ሰብአዊ ፍጡራን ስምምነቶቹን መጠበቅ የማይቻል እንዲሆን አደረጉ፡፡ አዳምና ሔዋን ያጡትን ግንኙነት መመለስ የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነበር፡፡ ይህን ያደረገው በአዳኙ ዘላለማዊ ተስፋ ላይ የተመሰረተ የጸጋ ቃል ኪዳን ሕግ በማውጣት ነበር (ዘፍ. 3፡ 15)፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን የመጀመሪያውን የወንጌል ተስፋ በዘፍጥረት 3፡ 15 ላይ ያንብቡ፡፡ በዚያ ጥቅስ ውስጥ በክርስቶስ ስላለን ተስፋ ፍንጭ የሚያገኙት የት ነው?
እግዚአብሔር በዘፍጥረት 12፡1-5 ላይ ከአብርሃም ጋር የፈጸማቸው የቃል ኪዳን ተስፋዎች ምንድር ናቸው? የአብርሃም ምላሽ ምን ነበር? እግዚአብሔር በመጀመሪያ ከአብርሃም ጋር የፈጸማቸው የተስፋ ቃሎች በብሉይ ኪዳን ውስጥ ካሉ በጣም ኃይለኛ ንባቦች አንዱ ነው፡፡ እነዚህ ጥቅሶች በሙሉ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ የሚገልጹ ናቸው፡፡ ተስፋዎቹን የሚፈጽመው አብርሃም ሳይሆን እግዚአብሔር ነው፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ወይም የእርሱ መልካምነት ይገበኛል ለማለት አብርሃም ያደረገው ምንም ነገር አልነበረም፤ እግዚአብሔርና አብርሃም ከዚህ ስምምነት ላይ ለመድረስ አብረው የሰሩት ነገር መኖሩን የሚያመለክት ነገርም የለም፡፡ ሁሉንም ቃል የሚገባው እግዚአብሔር ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ አብርሃም በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል እርግጠኛነት እንዲኖረው ተጠርቷል፤ ‹‹እምነት›› የሚል ስም የተሰጠው የማይመስል እምነት ሳይሆን በሰባ አምስት ዓመት ዕድሜው የአባቱን ቤትና ዘመዶቹን በመተውና እግዚአብሔር የተስፋ ቃል ወደገባው ምድር በመሄድ የተገለጠ ዓይነት እምነት ነው፡፡
‹‹በአብርሃም ላይ እና በእርሱ አማካይነት በሰብአዊ ፍጡራን ሁሉ ላይ ከተሰጠው ‹በረከት› ጋር ፈጣሪ የማዳን ዓላማውን ጀመረ፡፡ አዳምንና ሔዋንን በገነት ውስጥ ‹ባርኮአቸው› (ዘፍ. 1፡ 28፣ 5፡ 2) ‹ኖህንና ልጆቹን› ከውኃ ጥፋት በኋላ ባረካቸው (9፡ 1)፡፡ በዚህ መንገድ እግዚአብሔር ሰብአዊ ዘርን ለማዳን፣ ክፉን ለማጥፋትና ገነትን ለመመለስ (ዘፍ. 3፡ 15) አስቀድሞ የገባውን የተስፋ ቃል ግልጽ አደረገ፡፡ እግዚአብሔር በዓለም አቀፋዊው ሰዎችን የመድረስ ዕቅዱ ‹ሕዝቦችን ሁሉ› የመባረክ ተስፋውን አረጋገጠ፡፡›› —Hans K.LaRondelle, Our Creator Redeemer, pp. 22, 23.
ተስፋ የተሰጠው ልጅ እንዲወለድ አስር አመት ከጠበቀ በኋላ አብርሃም ስለ እግዚአብሔር ተስፋ ምን ጥያቄዎች ነበሩት? ዘፍ. 15፤ 1-6፡፡ አብርሃም ጥያቄዎችን ወይም ጥርጣሬን ያላስተናገደ ሰው ስለነበር ብዙ ጊዜ በቀላሉ እንደ እምነት አባት ከፍ ከፍ እናደርገዋለን፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ የሚስለው ስዕል የተለየ ነው፡፡ አብርሃም አመነ፣ ነገር ግን በመንገድ ላይ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩት፡፡ እምነቱ የሚያድግ እምነት ነበር፡፡ በማርቆስ 9፡ 24 ላይ እንደተገለጸው አባት አብርሃም በዘፍጥረት 15፡ 8 ላይ በመሰረታዊነት ‹‹አምናለሁ፣ አለማመኔን እርዳው›› አለ፡፡ ለዚህ መልስ እንዲሆን እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን በመግባት ተስፋው እርግጠኛ ስለመሆኑ በቸርነቱ ማረጋገጫ ሰጠው (ዘፍ. 15፡ 718)፡፡ ይህን ንባብ አስደናቂ የሚያደርገው እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን መፈጸሙ ሳይሆን እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን ለመፈጸም ራሱን ዝቅ ያደረገበት መጠን ነው፡፡ ከአገልጋዮቻቸው ጋር አስገዳጅ የሆኑ ቃል ኪዳኖችን በመፈጸም ሀሳብ ላይ የተሰናከሉ በቀድሞው የቅርብ ምስራቅ አገሮች የነበሩ ገዦች ከሚያደርጉት በተለየ ሁኔታ እግዚአብሔር ቃሉን ብቻ የሰጠ ሳይሆን ምሳሌያዊ በሆነ ሁኔታ በታረዱ እንስሳት ቁርጥራጮች መካከል በማለፍ የራሱን ሕይወት ለአደጋ አጋለጠ፡፡ በርግጥ ኢየሱስ የተስፋውን ቃል እውነት ለማድረግ በመጨረሻ ሕይወቱን በቀራንዮ ሰጠ፡፡
አሁን በእምነት መድረስ ያለብዎና ሊሆን የማይችል በሚሰል ነገር ማመን ያለብዎ አንዳንድ አከባቢዎች ምንድር ናቸው? ምንም ቢሆን በእምነት ጸንተው መቆምን መማር የሚችሉት እንዴት ነው?
አብርሃም ከአጋር ጋር ስለነበረው ገጠመኝ ጳውሎስ እንዲህ ያለ የማንኳሰስ አመለካከት ያለው ለምንድር ነው? ገላ. 4፡ 21-23፣ ዘፍ. 16፡፡ ይህን የብሉይ ኪዳን ታሪክ በመጠቀም ስለ ድነት ምን ወሳኝ የሆነ ነጥብ እየገለጸ ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
አጋር በዘፍጥረት ታሪክ ውስጥ ያላት ቦታ አብራም የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ካለማመኑ ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነው፡፡ አጋር በአብራም ቤተሰብ ውስጥ ያለች ግብጻዊት ባሪያ መሆኗ አብራም በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል አለማመኑን ካሳየበት ከመጀመሪያ ተግባሩ ጋር በተገናኘ ሁኔታ ፋርኦን ሳራን ለመውሰድ በልዋጭ ከሰጣቸው ብዙ ስጦታዎች መካከል አንዷ ሳትሆን አትቀርም (ዘፍ. 12፡ 11-16)፡፡ የተስፋ ቃል የተሰጠው ልጅ እንዲወለድ አስር አመት ከጠበቁ በኋላ አብራምና ሳራ ልጅ መውለድ አልቻሉም፡፡ እግዚአብሔር የእነርሱ እርዳታ እንደሚያስፈልገው በማሰብ ሳራ ጣውንቷ እንድትሆን አጋርን ለአብራም ሰጠች፡፡ ዛሬ ለእኛ እንግዳ ነገር ቢሆንም የሳራ እቅድ ብልህነት ያለበት ነው፡፡ እንደ ጥንቱ ባህል ሴት ባሪያ መካን ለሆነች እመቤት እንደ ምትክ (ልጅ ተሸካሚ) እናት ሆና ታገለግል ነበር፡፡ ስለዚህ ሳራ ከባሏና ከአጋር የሚወለደውን ማንኛውንም ልጅ እንደ ራሷ ልጅ አድርጋ መቁጠር ትችል ነበር፡፡ እቅዱ ልጅ ቢያስገኝም ልጁ ግን እግዚአብሔር ቃል የገባው ልጅ አይደለም፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው እንኳን ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ሲገጥሙት የእምነት መዛባት ደርሶበታል፡፡ በዘፍጥረት 17፡ 18፣ 19 ላይ እግዚአብሔር እስማኤልን እንደ ወራሽ አድርጎ እንዲቀበልለት አብርሃም ተማጸነ፤ በእርግጥ ይህን ጥያቄ ጌታ አልተቀበለውም፡፡ በእስማኤል ልደት ውስጥ የተፈጸመው ብቸኛው ‹‹ተአምር›› ሳራ ባሏን ከሌላ ሰው ጋር ለመጋራት ፈቃደኛ መሆኗ ነው! ከዚህች ሴት ስለተወለደው ልጅ፣ ‹‹እንደ ሥጋ ፈቃድ የተወለደ›› ልጅ እንደመሆኑ ምንም ተራ ከሆነ ውጭ የነበረ ነገር አልነበረም፡፡ አብርሃም ሁኔታዎች እንዲያሸንፉት ከመፍቀድ ይልቅ እግዚአብሔር ቃል በገባለት ነገር እምነት ኖሮት ቢሆን ኖሮ ከሆኑ ነገሮች አንዱም አይፈጸምም ነበር፣ የደረሰበት ብዙ ሀዘንም አይደርስበትም ነበር፡፡
ከእስማኤል ልደት በተቃራኒ በእስማኤል ልደት ዙሪያ የነበሩ ሁኔታዎችን ይመልከቱ፡፡ ዘፍ. 17፡ 15-19፤ 18፡ 10-13፤ ዕብ. 11፡ 11፣ 12፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች የአብርሃምንና የሳራን እምነት የፈለጉበት ምክንያት ምንድር ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
እግዚአብሔር ቃል በገባልዎ ተስፋዎች እምነት ማጣትዎ ስቃይ ያመጣብዎ በምን መንገዶች ነው? የሚገጥምዎ ነገር ምንም ቢሆን ከእነዚህ ስህተቶች እግዚአብሔርን በቃሉ ለመያዝ እንዴት መማር ይችላሉ? በእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች የመታመን ችሎታዎን ሊያጠነክሩልዎ የሚችሉ ምን ምርጫዎችን ማድረግ ይችላሉ?
እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር በሲና ተራራ ላይ ምን ዓይነት የቃል ኪዳን ግንኙነት ለመመስረት ፈለገ? ይህ እግዚአብሔር ለአብርሃም ከገባለት የተስፋ ቃል ጋር ምን ተመሳሳይነት አለው? ዘጸ. 6፡ 2-8፣ 19፡ 3-6፣ ዘዳ. 32፡ 10-12፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
እግዚአብሔር በሲና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ለመጋራት የፈለገው ቃል ኪዳን ያው ከአብርሃም ጋር የተጋራው ቃል ኪዳን ነበር፡፡ እንዲያውም እግዚአብሔር በዘፍጥረት 12፡ 1-3 ለአብርሃም በተናገራቸው ቃላትና በዘጸአት 19 ላይ ለሙሴ በተናገራቸው ቃላት መካከል ተመሳሳይነት አለ፡፡ በሁለቱም አጋጣሚዎች እግዚአብሔር አጽንዖት የሰጠው ለሕዝቡ በሚያደርገው ነገር ላይ ነው፡፡ እስራኤላውያን የእርሱን በረከቶች ለማግኘት አንድን ነገር ለማድረግ ቃል እንዲገቡ አይጠይቃቸውም፤ በዚያ ፈንታ ለእነዚያ በረከቶች ምላሽ እንዲሆን መታዘዝ አለባቸው፡፡ በዘጸአት 19፡ 5 ላይ ‹‹መታዘዝ›› ተብሎ የተተረጎመው ቃል ቀጥተኛው ትርጉም ‹‹መስማት›› የሚል ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃሎች ጽድቅ በሥራን አያመለክቱም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ እስራኤላውያን አብርሃም ለእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች ምላሽ የሰጠበትን ሁኔታ የሚገልጽ ዓይነት እምነት እንዲኖራቸው ፈለገ (ቢያንስ አብዛኛውን ጊዜ!)፡፡
እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን በሲና የሰጠው የቃል ኪዳን ግንኙነት ለአብርሃም ከተሰጠው ጋር ተመሳሳይ ቢሆን ኖሮ ጳውሎስ የሲና ተራራን አሉታዊ ከሆነው የአጋር ልምምድ ጋር ለምን ያመሳስለዋል? ዘጸ. 19፡ 7-25፤ ዕብ. 8፡ 6፣ 7፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
በሲና የተፈጸመው ቃል ኪዳን በቤተ መቅደስ አገልግሎቶች ምሳሌ የተገለጸውን የሰብአዊ ዘርን ኃጢአተኛነት እና የእግዚአብሔርን የተትረፈረፈ ፈውስ ለማመልከት የታቀደ ነበር፡፡ በሲና በተፈጸመው ቃል ኪዳን ላይ ችግሩ በእግዚአብሔር በኩል ሳይሆን ሕዝቡ በገባው የስህተት ቃል ኪዳን ነበር (ዕብ. 8፡ 6)፡፡ ለእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች በትህትና እና በእምነት ምላሽ በመስጠት ፈንታ እስራኤላውያን በራሳቸው በመታመን እንዲህ በማለት መልስ ሰጡ፡- ‹‹እግዚአብሔር ያለንን ሁሉ እናደርጋለን› ›› (ዘጸ. 19፡ 8)፡፡
በግብጽ አገር ከአራት መቶ አመታት በላይ በባርነት ስለኖሩ ስለ እግዚአብሔር ታላቅነትም ሆነ ስለ ራሳቸው የኃጢአተኛነት ደረጃ ትክክለኛ የሆነ ግንዛቤ አልነበራቸውም፡፡ አብርሃምና ሳራ እግዚአብሔር ተስፋውን እንዲፈጽም ለመርዳት እንደሞከሩት ሁሉ እስራኤላውያንም የእግዚአብሔርን የጸጋ ቃል ኪዳን ወደ ሥራ ቃል ኪዳን ለመለወጥ ሞከሩ፡፡ አጋር ሲናን የምትወክልበት ምክንያት ሁለቱም ድነት በሥራ ለማግኘት የሚደረገውን ሰብአዊ ጥረትን ስለሚያሳዩ ነው፡፡ ጳውሎስ በሲና የተሰጠው ሕግ ክፉ ነው ወይም ተሽሮአል አይልም፡፡ እርሱን ያሳሰበው የገላትያ ሰዎች ሕግን በተመለከተ የነበራቸው ትክክለኛ መረዳት የሌለው ሕጋዊነት ነበር፡፡ ‹‹ሕግን በመጠበቅ እግዚአብሔርን በፍጹም ማስደሰት እንደማይቻል ከማሳመን ይልቅ ሕግ እግዚአብሔርን ለማስደሰት በግል ግብዓቶች ላይ እንዲደገፉ በውስጣቸው እጅግ ሥር የሰደደ ውሳኔን ፈጠረባቸው፡፡ ስለዚህ ሕግ የአይሁዳዊነት አቀንቃኞችን ወደ ክርስቶስ በመምራት የጸጋን ዓላማዎች አልፈጸመም፡፡ ከዚህ ይልቅ ከክርስቶስ ለያቸው፡፡›› PalmerRobertson, The Christ of the Covenants (Phillipsburg, N.J.:Presbyterian and Reformed Publishing Co., 1980), p. 181.
ጳውሎስ ስለ እስራኤል ታሪክ የጻፈው አጭር ንድፍ ታቅዶ የነበረው የአብርሃም ዝርያዎች ነን የሚሉና የአይሁድ ክርስትናና ሕግ ማዕከል የሆነችው ኢየሩሳሌም ደግሞ እናታቸው እንደሆነች የሚናገሩ ተቃዋሚዎቹ የሚያቀርቡአቸውን መከራከሪያዎች ለመመከት ነበር፡፡ አህዛብን ከሕግ ውጭ ናቸው በማለት ከሰዋቸዋል፤ የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች መሆን ከፈለጉ ለግዝረት ሕግ ራሳቸውን በማስገዛት በመጀመሪያ የአብርሃም ልጅ መሆን አለባቸው፡፡ ጳውሎስ እውነታው ከዚህ ተቃራኒ ነው ይላል፡፡ እነዚህ ሕጋውያን የአብርሃም ልጆች ሳይሆኑ እንደ እስማኤል ከሕግ ውጭ የሆኑ ልጆች ናቸው፡፡ በግዝረት በመታመናቸው ሳራ ከአጋር ጋር እንዳደረገችውና እስራኤላውያን በሲና ከእግዚአብሔር ሕግ ጋር እንዳደረጉት ‹‹በሥጋ›› እየተደገፉ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከአህዛብ የተመለሱት አማኞች በተፈጥሮአዊ የዘር ግንድ ሳይሆን እንደ ይስሐቅ በመለኮታዊ አሰራር የአብርሃም ልጆች ናቸው፡፡ ‹‹እንደ ይስሐቅ ከአብርሃም ጋር የተደረገው የተስፋው ቃል ኪዳን ፍጻሜ ናቸው…፤ እንደ ይስሐቅ ወደ ነጻነት መወለዳቸው የመለኮታዊ ጸጋ ውጤት ነው፤ እንደ ይስሐቅ በተስፋው ቃል ኪዳን ረድፍ ውስጥ ይገኛሉ፡፡›› —James D. G. Dunn, The Epistle to theGalatians (London: Hendrickson Publishers, 1993), p. 256.
የአብርሃም እውነተኛ ዝርያዎች በዚህ ዓለም ውስጥ ምን ይገጥማቸዋል? ገላ. 4፡ 28 -31፣ ዘፍ. 21፡ 8-12፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
የተስፋው ልጅ መሆን ለይስሐቅ በረከቶችን ብቻ ሳይሆን ተቃውሞንና ስደትንም አምጥቶበታል፡፡ ስደትን በተመለከተ ጳውሎስ በአእምሮው ውስጥ ያለው በዘፍጥረት 21፡8-10 ላይ ይስሐቅ ክብር ሲሰጠው እስማኤል ደግሞ ሲያሾፍበት የሚታየው ሁኔታ ነው፡፡ በዘፍጥረት 21፡9 ላይ ያለው የዕብራውያን ቃል ትርጉም ‹‹መሳቅ›› የሚል ሲሆን ግን ሳራ የሰጠችው ምላሽ የሚያመለክተው እስማኤል በይስሐቅ ላይ እያሾፈ ወይም እየቀለደ መሆኑን ነው፡፡ የእስማኤል ባሕርይ ዛሬ ላለን ለእኛ ወሳኝነት ያለው መስሎ ባይታየንም የቤተሰቡ ብኩርና አደጋ ውስጥ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ያለውን ጥልቅ ጠላትነት አሳይቷል፡፡ በጥንት ዘመን የነበሩ ገዥዎች ወንድሞችንም ጨምሮ ማንኛውንም ተቀናቃኝ በማስወገድ ሥልጣናቸውን ለማቆየት ይሞክሩ ነበር (መሳ. 9፡1-6)፡፡ ምንም እንኳን ይስሐቅ ተቃውሞ ቢገጥመውም የአባቱ ወራሽ መሆን የሚያስገኛቸውን ፍቅርን፣ ጥበቃን፣ እና ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡
የይስሐቅ መንፈሳዊ ዝሪያዎች እንደመሆናችን በውስጥ ካሉት የቤተ ክርስቲያን አባላት ሳይቀር ችግርና ተቃውሞ ሲደርስብን መደነቅ የለብንም፡፡ ከእምነትዎ የተነሳ በተለየ ሁኔታ እጅግ ከሚቀርቡዎት ሰዎች ስደት የደረሰብዎ በምን መንገዶች ነው? ወይም ይህን ከባድ ጥያቄ ራስዎን ይጠይቁ፡- እርስዎ ሌሎችን ከእምነታቸው የተነሳ በማሳደድ በደለኛ ይሆኑ ይሆን? ስለዚህ ነገር ያስቡ፡፡
ኤለን ጂ ኋይት በጻፈችው አበውና ነቢያት በሚለው መጽሐፍ ውስጥ ከገጽ 363-373 ላይ ‹‹ሕግና ቃል ኪዳን›› የሚለውን ክፍል ያንብቡ፡፡
‹‹የአብርሃም ቃል ኪዳን የድነት ተስፋን ከያዘ በሲና ሌላ ቃል ኪዳን የተፈጸመው ለምንድር ነው? ሕዝቡ በባርነት በነበሩበት ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ ስለ እግዚአብሔርና ስለ አብርሃማዊው ቃል ኪዳን መርሆዎች እውቀት አጥተው ነበር . . . ፡፡
‹‹እግዚአብሔር ወደ ሲና አመጣቸው፤ ክብሩን ገለጠላቸው፤ ከታዘዙ ብዙ በረከቶችን እንደሚያገኙ ቃል በመግባት ሕጉን ሰጣቸው፡- ‹አሁንም በእውነት ቃሌን ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ . . . የካህናት መንግስት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ› (ዘጸ. 19፡5፣ 6)፡፡ ሕዝቡ የራሳቸውን ልብ ኃጢአተኛነት አልተገነዘቡም ነበር፣ ለእነርሱ ያለ ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ሕግ መታዘዝ የማይቻል ነገር ሆኖ ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን አደረጉ….ሆኖም ቃል ኪዳኑን ከፈጸሙ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ከእግዚአብሔር ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን በመጣስ ለተቀረጸ ምስል ወድቀው ሰገዱ፡፡ ራሳቸው በጣሱት ቃል ኪዳን አማካይነት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ተስፋ ማድረግ አልቻሉም፤ ከዚህ የተነሳ ኃጢአተኛነታቸውንና ይቅርታ እንደሚያስፈልጋቸው በማየታቸው በአብርሃማዊው ቃል ኪዳንና በመስዋዕት ስጦታዎች አማካይነት የተገለጠው አዳኝ እንደሚያስፈልጋቸው እንዲሰማቸው ተደረጉ፡፡ አሁን ከእግዚአብሔር ጋር እንደ ነጻ አውጭያቸው በእምነትና በፍቅር ተሳስረው ነበር፡፡ አሁን የአዲስ ኪዳንን በረከቶች ለማድነቅ ተዘጋጅተው ነበር፡፡›› —Ellen G. White, Patriarchs and Prophets, pp. 371, 372.
ከእግዚአብሔር ጋር ያለዎት ጉዞ በአብዛኛው ‹‹የብሉይ ኪዳን›› ዓይነት ነው ወይስ ‹‹የአዲስ ኪዳን›› ዓይነት? ልዩነቱን እንዴት መንገር ይችላሉ?
በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናችሁ በውስጣችሁ ውጥረት እየፈጠሩ ያሉ አንዳንድ ጉዳዮች ምንድር ናቸው? እንዴት መፍትሄ እየተሰጣቸው ነው? ራስዎን ‹‹የስደት›› ተጋላጭ ሆነው ቢያገኙም እንኳን እያሳደዱ ያሉት እርስዎ አለመሆንዎን እንዴት እርግጠኛ መሆን ይችላሉ? በዚህ ቦታ ላይ መለያ መስመሩ እምኑ ላይ ነው? (ማቴ. 1፡ 15-17ን ደግሞ ይመልከቱ)፡፡
ይህን ወይም ያን አላደርግም እያሉ ለእግዚአብሔር ቃል የገቡትና አለደርግም ያሉትን ሲያደርጉ ራስዎን ያገኙት ስንት ጊዜ ነው? ይህ አሳዛኝ እውነታ የጸጋን ምንነት እንዲያስተውሉ የረዳዎት እንዴት ነው? ማጠቃለያ፡- የአጋር፣ የእስማኤልና በሲና የተፈጸሙ የእስራኤል ልጆች ታሪኮች እግዚአብሔር ለእኛ ሊያደርግልን ቃል የገባውን ነገር ለመፈጸም በራሳችን ጥረት ላይ የመደገፍን ሞኝነት ያሳያሉ፡፡ ይህ በራስ ጽድቅ የመደገፍ ዘዴ አሮጌው ኪዳን ተብሎ ተጠቅሷል፡፡ አዲሱ ኪዳን በመጀመሪያ ኃጢአት ከገባ በኋላ ከአዳምና ከሔዋን ጋር ተፈጽሞ፣ ከአብርሃም ጋር የታደሰውና በመጨረሻም በክርስቶስ የተፈጸመው ዘላለማዊው የጸጋ ኪዳን ነው፡፡