ወንጌል በገላትያ መጽሐፍ ውስጥ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2017

ከሰኔ 17-23

አንደኛ ትምህርት

June 24-30
 

ጳውሎስ፣ የአህዛብ ሐዋርያ

 

ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ የሐዋ. 6፡ 9-15፣ 9፡ 1-9፣ 1ኛ ሳሙ. 16፡ 7፣ ማቴ.7፡ 1፣ የሐዋ. 11፡ 19-21፣ 15፡ 1-5፡፡

 

የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - ‹‹ይህን በሰሙ ጊዜም ዝም አሉና፡-እንኪያስ እግዚአብሔር ለአህዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሐን ሰጣቸው እያሉ እግዚአብሔርን አከበሩ፡፡›› (የሐዋ. 11፡18)፡፡

 

የጠርሴሱን ሳውልን (ከተለወጠ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ የተባለውን) እና ያደረገውን ነገር ለምን እንዳደረገ መረዳት ይህን ያህል ከባድ አይደለም፡፡ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ የሕግን አስፈላጊነትና በቅርቡ ሊመጣ ስላለው የእሥራኤል ፖለቲካዊ መዋጀት ሲማር የቆየ ታማኝ አይሁድ እንደመሆኑ፣ ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው መሲህ አሳፋሪ በሆነ ሁኔታ እንደ ዋና ወንጀለኛ ሲገደል ማየት ሊታገሰው ከሚችለው በላይ ሆነበት፡፡

ስለዚህ የኢየሱስ ተከታዮች ለሕግ (Torah) ታማኝ ስለነበሩ እግዚአብሔር ለእሥራኤል ሕዝብ ያለው እቅድ ተፈጻሚ እንዳይሆን እንቅፋት እየሆኑ ነው ብሎ ማመኑም አያስደንቅም፡፡ የተሰቀለው ኢየሱስ መሲህ እንደሆነ መናገራቸውና ከሙታን ተነስቷል ማለታቸው ከፍተኛ ክህደት ነው ብሎ አመነ፡፡ እንደ እነዚህ ያሉትን የማይረቡ ሰዎች ወይም እነዚህን አመለካከቶች ለመተው ፈቃደኛ ያልሆነን ማንኛውንም ሰው ቢሆን መታገስ አያስፈልግም፡፡ ሳውል ከእሥራኤል መካከል እንደ እነዚህ ያሉ እምነቶችን ለማጥፋት የእግዚአብሔር ወኪል (መሳሪያ) ለመሆን ወስኖ ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ እርሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ላይ አስቀድሞ የታየው ኢየሱስ መሲህ መሆኑን የሚያምኑትን አይሁዶች እንደሚያሳድድ ጨካኝ አሳዳጅ ነው፡፡

ነገር ግን እግዚአብሔር ለሳውል የነበረው እቅድ እጅግ የተለየና እርሱ ለራሱ በፍጹም አስቦት የማያውቅ እቅድ ነበር፡፡ ያውም ይህ አይሁዳዊ፣ ኢየሱስ መሲህ ነው ብሎ ሊሰብክ ብቻ ሳይሆን መሲህነቱን ለአህዛብ ሊመሰክር ነበር! *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለሰኔ 24 ሰንበት ለመዘጋጀት አጥኑ፡፡
 

ሰኔ 18
Jun-25
 

የክርስቲያኖች አሳዳጅ

 

የጠርሴሱን ሳውል መጀመሪያ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ብቅ የሚለው በእስጢፋኖስ መወገር ላይ በመሳተፍና (የሐዋ. 7፡ 58) በኢየሩሳሌም ውስጥ ከተከሰተው ሰፊ ስደት ጋር በተገናኘ ሁኔታ ነበር (የሐዋ. 8፡ 1-5)፡፡ ጴጥሮስ፣ እስጢፋኖስና ፊልጶስ የክርስትና እምነት ከአይሁዱ ዓለም ባሻገር እንዲስፋፋ ባደረጉ ክስተቶች ላይ ስለተሳተፉ በሐዋርያት መጽሐፍ ውስጥ ጉልህ ሚና አላቸው፡፡ ስብከቱና ሰማዕትነቱ በጠርሴሱ ሳውል ላይ መሰረታዊ ተጽእኖ ከማሳደሩ የተነሳ እስጢፋኖስ የተለየ ቦታ አለው፡፡

እስጢፋኖስ ግሪክኛን ይናገር የነበረ እና ከመጀመሪያዎቹ ሰባት ዲያቆናት መካከል አንዱ ነበር (የሐዋ. 6፡ 3-6)፡፡ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ እንደተገለጸው በኢየሩሳሌም ለመኖር ከሌላ አገር የመጡ አይሁዶች እስጢፋኖስ ስለ ኢየሱስ ከሚያስተምረው ትምህርት የተነሳ ከእርሱ ጋር ተጋጩ፡፡ በዚህ ክርክር ውስጥ የጠርሴሱ ሳውልም ሳይሳተፍ አይቀርም፡፡

የሐዋ. 6፡ 9-15፡፡ በእስጢፋኖስ ላይ የቀረቡ ክሶች ምን ነበሩ? እነዚህ ክሶች ስለ ምን ያስታውሶታል? (ማቴ. 26፡ 59-61ን ይመልከቱ)፡፡




--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

 
John 6:1–21

በእስጢፋኖስ ስብከት ላይ የተፈጠረው ኃይለኛ ጥላቻ ከሁለት የተለያዩ ነገሮች የተነሳ ነበር፡፡ በመጀመሪያ የተቃዋሚዎቹን ቁጣ የቀሰቀሰው እስጢፋኖስ የአይሁዳዊነት የትኩረት ነጥብ ለሆኑትና ኃይማኖታዊና ብሔራዊ መለያ ምልክቶች ተደርገው ለተጠበቁት ለአይሁድ ሕግና ለቤተ መቅደሱ የመጀመሪያ ቦታ አለመስጠቱ ነበር፡፡ ነገር ግን እስጢፋኖስ እነዚህን እንደ ትልቅ ሀብት ተደርገው የሚቆጠሩትን ሁለት ምልክቶች ችላ ማለት ብቻ ሳይሆን ኢየሱስ፣ የተሰቀለውና የተነሳው መሲህ፣ የአይሁድ እምነት እውነተኛው ማዕከል መሆኑን በኃይል ሰበከ፡፡

ቀደምት ክርስቲያኖችን ለማጥፋት ቅናት የነበረው ሳውል ለውጥ ለማምጣት ግለት የነበረውና ጥብቅ ከሆኑትና የአርበኝነት ስሜት ከሚሰማቸው የፈሪሳውን ክንፍ አባል ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከዚህ የተነሳ የእስጢፋኖስ ስብከት ፈሪሳዊውን ሳውልን ማስቆጣቱ አያስደንቅም (ፊል. 3፡ 3-6)፡፡ ሳውል ታላላቆቹ የእግዚአብሔር መንግስት ትንቢታዊ ተስፋዎች እንዳልተፈጸሙ ተመለከተ (ዳን. 2፣ ዘካ. 8፡ 23፣ ኢሳ. 40-55)፤ ከዚህ የተነሳ ኢየሱስ መሲህ ነው የሚለውን ሀሳብ ጨምሮ እስራኤልን ከኃይማኖታዊ እርኩሰት በማንጻት ተፈጻሚ ሊሆን የሚችለውን ያን ቀን እንዲያመጣ እግዚአብሔርን ማገዝ የእርሱ ተግባር እንደሆነ ሳያምን አይቀርም፡፡

ራሱ ትክክል እንደሆነ በማመን፣ በስህተት ውስጥ እንዳሉ የሚያምናቸውን ሰዎች ለመግደል ሳውል ፈቃደኛ ነበር፡፡ ለምናምነው ነገር ቅናትና ግለት መኖር አስፈላጊ ሆኖ ሳለ አንዳንድ ጊዜ ልንሳሳት እንደምንችል በመገንዘብ ስሜታችንን መቆጣጠር እንዳለብን እንዴት መማር እንችላለን?

 
መጋቢት 18
Jun-26
 

የሳውል መለወጥ

 

‹‹ጌታ ሆይ፣ ማን ነህ? አለው፡፡ እርሱም፡- አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል አለው›› (የሐዋ. 9፡5)፡፡ ምንም እንኳን ጳውሎስ ቀደምት ቤተ ክርስቲያንን ማሳደዱ በግልጽ ሳይታይ ቢጀምርም (የእስጢፋኖስን ገዳዮች ልብስ ብቻ በመያዙ) በፍጥነት እየተፋፋመ ሄደ (የሐዋ. 8፡1-3፣ 9፡1፣ 13፣ 14፣ 21፤ 22፡3-5)፡፡ ሉቃስ ሳውልን ለመግለጽ ከተጠቀማቸው ቃላት መካከል በርካታዎቹ የሚስሉት ተቃዋሚዎቹን ለማጥፋት የወሰነን የጨካኝና ቁጡ አውሬ ወይም የዘራፊ ወታደር ስዕል ነው፡፡ ለምሳሌ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 8፡ 3 ላይ ‹‹ያፈርስ ነበር›› ተብሎ የተተረጎመው ቃል በብሉይ ኪዳን የግሪክ ትርጉም ላይ (መዝ. 80፡ 13) ጥቅም ላይ የዋለው ያልተገራ እና አጥፊ የሆነ የዱር ከርከሮን ባህርይ ለመግለጽ ነው፡፡ ሳውል በክርስቲያኖች ላይ ያደረገው ዘመቻ በግማሽ ልብ ያደረገው እንዳልነበረ ግልጽ ነው፤ የክርስትና እምነትን ለማጥፋት ሆን ብሎ የተደረገና ቀጣይነት የነበረው እቅድ ነበር፡፡ የሳውልን መለወጥ የሚገልጹ ሶስት መግለጫዎችን ይመልከቱ (የሐዋ. 9፡ 1-18፣ 22፡ 6-21፣ 26፡ 12- 19)፡፡ በዚህ ልምምድ ውስጥ የእግዚአብሔር ፀጋ ያለው ሚና ምንድን ነው? በሌላ አገላለጽ፣ እግዚአብሔር ለሳውል ያደረገለት በጎነት ምን ያህል የሚገባው ነበር?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

በሰብአዊ ዕይታ ሲታይ የሳውል መለወጥ የማይቻል ይመስል ነበር (ለዚህም ነበር ብዙዎች መጀመሪያ ስለ እርሱ በሰሙ ጊዜ የተጠራጠሩት)፡፡ ሳውል የሚገባው አንድ ነገር ቢኖር ቅጣት ብቻ ነበር፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ለዚህ የጋለ ስሜት ለነበረው አይሁዳዊ ፀጋን ሰጠው፡፡ ነገር ግን ልብ ማለት የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር የሳውል መለወጥ በባዶ ቦታ የተደረገ አልነበረም፣ በግድም የሆነ አልነበረም፡፡

ሳውል ከሃዲ አልነበረም፡፡ ምንም እንኳን ስለ እግዚአብሔር የነበረው መረዳት ከፍተኛ የሆነ ስህተት የነበረበት ቢሆንም ኃይማኖተኛ ሰው ነበር፡፡ለሳውል ‹‹የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል›› (የሐዋ. 26፡ 14) ብለው የተናገሩት የኢየሱስ ቃላት መንፈስ እየዘለፈው መሆኑን የሚገልጹ ናቸው፡፡

በጥንቱ ዓለም የመውጊያ ብረት የተባለው በሬዎች ማረስ እምቢ ሲሉ ለመውጋት የሚያገለግል ጫፉ የሾለ በትር ነው፡፡ ሳውል ለተወሰነ ጊዜ እግዚአብሔር ሲወጋው እምቢ ብሎ ነበር፣ ነገር ግን በመጨረሻ በደማስቆ መንገድ ላይ ከሙታን የተነሳውን ወንጌል በገላትያ መጽሐፍ ውስጥ ኢየሱስን ከተገናኘ በኋላ ዳግመኛ ከእርሱ ጋር ላለመዋጋት ወሰነ፡፡

የራስዎን የመለወጥ ልምምድ ወደ ኋላ ያስቡ፡፡ ምናልባት እንደ ጳውሎስ መለወጥ ትዕይንታዊ ላይሆን ይችላል (ብዙዎቹ ትዕይታዊ አይደሉም)፣ ነገር ግን እርስዎ የእግዚአብሔርን ፀጋ የተቀበሉበት በምን ተመሳሳይ ሁኔታ ነው፡፡ በክርስቶስ የተሰጠንን ነገር በፍጹም አለመርሳት አስፈላጊነቱ ለምንድን ነው?
 

መጋቢት 19
Jun-27
 

ሳውል በደማስቆ

 

ሳውል ከኢየሱስ ጋር በተገናኘ ጊዜ ታወረና ይሁዳ ወደሚባል ሰው ቤት እንዲሄድና ሌላ አናንያ የሚባል ሰውን እንዲጠብቅ መመሪያ ተሰጠው፡፡ የሳውል አካላዊ መታወር የኢየሱስን ተከታዮች እንዲያሳድድ የመራው ትልቁ የመንፈሳዊ እውርነት ኃይለኛ ማስታወሻ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡

ኢየሱስ በደማስቆ መንገድ ላይ ለእርሱ መገለጡ ሁሉንም ነገር ለወጠው፡፡ ሳውል ትክክል ነኝ ብሎ ባሰበበት ነገር እጅግ ተሳስቶ ነበር፡፡ ለእግዚአብሔር በመስራት ፈንታ እየተቃወመው ነበር፡፡ ሳውል ወደ ደማስቆ የገባው ኢየሩሳሌምን ለቆ በወጣበት ሰዓት ከነበረው ኩሩና ቀናተኛ ፈሪሳዊነት ወጥቶ የተለየ ሰው ሆኖ ነበር፡፡ በደማስቆ ያሳለፋቸውን የመጀመሪያዎቹን ሶስት ቀናት ያሳለፈው በመብላትና በመጠጣት ፈንታ የሆነውን ነገር ሁሉ እያሰላሰለ በፆምና በጸሎት ነበር፡፡ የሐዋ. 9፡ 10-14ን ያንብቡ፡፡ በሐናንያ አእምሮ ውስጥ ምን እየሆነ እንደነበረ ያስቡ፡ -አሳዳጅ የነበረው ሳውል፣ አሁን አማኝ የሆነ ብቻ ሳይሆን፣ ጳውሎስ ተብሎ የተሰየመና ወንጌልን ለአህዛቡ ዓለም ለመውሰድ በእግዚአብሔር የተመረጠ ሐዋርያም ነበር፡፡

ሐናንያ ትንሽ ግራ መጋባቱ አያስደንቅም፡፡ በኢየሩሳሌም የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ከተለወጠ ከሶስት አመት በኋላ ልትቀበለው ካመነታች (የሐዋ. 9፡26-30)፣ ክስተቱ ከተከሰተበት ቀናት በኋላ በደማስቆ የነበሩ አማኞችን ልብ የሞሉ ጥያቄዎችንና ጭንቀቶችን ማሰብ ይቻላል፡፡

ጌታ ስለ ጠርሴስ ሳውል ለሐናንያ አስደናቂና ያልተጠበቀ ዜና በራዕይ መንገሩንም ልብ ይበሉ፤ ስለ ሳውል የተነገረውን ነገር - የአይሁድ አማኞች ጠላት የነበረ ሰው አሁን ከእነርሱ አንዱ የመሆኑን እውነትነት ከራዕይ ያነሰ ነገር ሊያሳምነው አይችልም ነበር፡፡

ሳውል ከኢየሩሳሌም የወጣው የክርስትና እምነትን ከሥሩ ለመንቀል ከካህናት አለቆች ሥልጣንና ሀላፊነት ተሰጥቶት ነበር (የሐዋ. 26፡12)፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ለሳውል ከካህናት አለቆች ሥልጣን የሚበልጥ ሥልጣን ያለውና እጅግ ሰፊ የሆነ የተለየ ሥራ ነበረው፡፡ ሳውል ወንጌልን ለአህዛብ እንዲወስድ ተመርጧል፣ ይህ ደግሞ ለሐናንያና ለሌሎች አይሁድ አማኞች ከሳውል ከራሱ መለወጥ የበለጠ እጅግ አስደንጋጭ የሆነ ሀሳብ ሳይሆንባቸው አይቀርም፡፡ ሳውል የክርስትና እምነትን ስርጭት ለመግታት በፈለገበት፣ አሁን የአይሁድ አማኞች አስበው ከሚያውቁት ባሻገር ወደ ሩቅ ቦታ እንዲያሰራጭ እግዚአብሔር ይጠቀምበታል፡፡

1ኛ ሳሙ. 16፡7፣ ማቴ. 7፡1፣ 1ኛ ቆሮ. 4፡5ን ያንብቡ፡፡ ስለ ሌሎች ሰዎች መንፈሳዊ ልምምድ የሚኖረንን አመለካከት በተመለከተ ለምን መጠንቀቅ እንዳለብን እነዚህ ጥቅሶች የሚያስተላልፉት መልእክት ምንድን ነው? ስለ ሌሎች ባለዎት አስተያየቶች የፈጸሟቸው ስህተቶች ምንድን ናቸው? ከእነዚያ ስህተቶችስ ምን ትምህርት አገኙ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------


 

መጋቢት 20
Jun-28
 

ወንጌል ወደ አህዛብ ሄደ

 

የመጀመሪያዋ የአህዛብ ቤተ ክርስቲያን የተመሰረተችው የት ነበር? አማኞች ወደዚያ እንዲሄዱ ያደረጉት ክስተቶች ምን ነበሩ? (የሐዋ. 11፡ 19-21፣ 26)፡፡ ያ ከብሉይ ኪዳን ዘመን ምን አስታወሰዎት? (ዳን. 2ን ይመልከቱ)፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ከእስጢፋኖስ ሞት በኋላ በኢየሩሳሌም የተነሳው ስደት በርካታ አይሁዶች ወደ ሰሜን ሶስት መቶ ማይሎችን ርቆ ወደሚገኘው ወደ አንጾኪያ እንዲሸሹ አደረጋቸው፡፡ አንጾኪያ በሮም ግዛት ውስጥ ያለችው የሶሪያ ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማ እንደመሆኗ በጠቃሚነቷ ከሮምና ከአለክሳንደሪያ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ነበረች፡፡ ወደ አምስት መቶ ሺህ ገደማ የሚገመተው ሕዝቧ እጅግ ዓለም አቀፋዊ አመለካከት ስለነበረው የአህዛብ ቤተ ክርስቲያን የምትገኝበት ቦታ ብቻ ሳይሆን የቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፋዊ ተልዕኮዋን እንድትጀምርም ምቹ ቦታ ነበር፡፡

ባርናባስ አንጾኪያን እንዲጎበኝና ጳውሎስ አብሮት እንዲሰራ እንዲጋብዝ የሚያደርግ በከተማዋ የተደረገ ነገር ምን ነበር? በዚያ ስለነበረችው ቤተ ክርስቲያን የተሰጠው መልክ ምን ይመስል ነበር? (የሐዋ. 11፡ 20-26)፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የጳውሎስን ሕይወት ቅደም ተከተል ማስቀመጥ ከባድ ነው፣ ነገር ግን ከተለወጠ በኋላ ኢየሩሳሌምን በጎበኘበትና አብሮት እንዲሰራ ባርናባስ ወደ አንጾኪያ እንዲመጣ በጋበዘበት ጊዜ መካከል አምስት አመት ያለፈ ይመስላል (የሐዋ. 9፡ 2630)፡፡ እነዚህን አመታት በሙሉ ጳውሎስ ምን ያደርግ ነበር? ምን ያደርግ እንደነበረ በእርግጠኝነት ለመናገር ያዳግታል፡፡ ነገር ግን በገላትያ 1፡ 21 ላይ በሰጠው አስተያየት መሰረት በሶሪያና በሲሲሊያ አከባቢዎች ወንጌልን እየሰበከ ቆይቶ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዶች ሀሳብ እንደሰጡ ከሆነ ቤተሰቡ አንቀበልህም ብለው ስለካዱት በ2ኛ ቆሮ. 11፡23-28 ላይ የሚገልጻቸው መከራዎች የደረሱበት በዚህ ወቅት ሳይሆን አይቀርም (ፊል. 3፡8)፡፡ በመንፈስ ምሪት በአንጾኪያ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን አበበች፡፡ በሐዋርያት ሥራ 13፡1 ላይ ያለው መግለጫ እንደሚያመለክተው የከተማዋ ዓለም አቀፋዊ ባሕርይ ወዲያውኑ ቤተ ክርስቲያኗ በነበሯት የጎሳና የባህል ልዩነቶች ተንጸባርቆ ነበር፡፡ (ባርናባስ ከቆጵሮስ፣ ሉሲየስ ከሳይረን፣ ጳውሎስ ከሲሊሲያ፣ ስምዖን ምናልባት ከአፍሪካ ሲሆን ከአህዛብ የተለወጡትን ሁሉ ደግሞ ማሰብ ይቻላል)፡፡ አሁን መንፈስ ወንጌልን ከዚህ ለሚበልጡ አህዛቦች ለማድረስ አንጾኪያን እንደ መነሻ ቦታ በመጠቀም ከሶሪያና ከይሁዳ ባሻገር ስፋት ያላቸውን ሚስዮናዊ እንቅስቃሴዎች ለማድረግ ፈለገ፡፡

የሐዋ. 11፡ 19-26ን ያንብቡ፡፡ በባሕልና በጎሳ እጅግ በተለያየችው የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበረና ዛሬ ያሉ ቤተ ክርስቲያናት ምሳሌ አድረገው በመውሰድ እንዲሰሩ የሚረዳ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
 

መጋቢት 21
Jun-29
 

ግጭት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ

 

ሰብአዊ የሆነው ነገር ሁሉ ፍጹም ስላልሆነ በቀድሞዎቹ የአማኞች ማህበረሰብ ውስጥ ብዙም ሳይቆይ ችግር መከሰት ጀመረ፡፡ ጀማሪዎች እንደመሆናቸው በቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከአህዛብ የተመለሱ አማኞች በመቀላቀላቸው እያንዳንዱ ሰው ደስተኛ አልነበረም፡፡ አለመስማማት የነበረው ለአህዛብ በነበረው ተልእኮ ላይ ሳይሆን አህዛብ ወደ እምነቱ ሲመጡ በምን መሰረት አባል እንዲሆኑ በመፍቀድ ላይ ነበር፡፡ አንዳንዶች በኢየሱስ ማመን ብቻውን ክርስቲያንን ክርስቲያን እንደማያደርግ ተሰማቸው፤ እምነት በግዝረትና የሙሴን ሕግ በመታዘዝ መታገዝ አለበት ብለው ሞገቱ፡፡ እውነተኛ ክርስቲያን ለመሆን አህዛቦች መገረዝ ያስፈልጋቸዋል አሉ፡፡ (በሐዋርያት ሥራ 10፡ 1-11፣ 18 ላይ ጴጥሮስ ከቆርኔሊዎስ ጋር ከነበረው ልምምድ የተነሳ በአህዛብና በአይሁድ መካከል የነበረውን የክፍፍል መጠንና ተከትሎ የመጣውን ምላሽ ይመልከቱ)፡፡

ፊልጶስ በሳምራውያን መካከል የሚሰራውን ሥራ (የሐዋ. 8፡ 14) እና በአንጾኪያ ከአህዛብ ጋር የሚሰራውን ሥራ ለመቆጣጠር ከኢየሩሳሌም የተደረጉ ይፋዊ ጉብኝቶች (የሐዋ. 11፡ 22) አይሁድ ያልሆኑትን በአማኞች ማህበረሰብ ውስጥ ለማካተት የነበረውን ስጋት ሊጠቁም ይችላል፡፡ ሆኖም ጴጥሮስ ያልተገረዘውን ሮማዊ ወታደር የነበረ ቆርኔሊዎስን በማጥመቁ የነበረው ምላሽ በቀደምት አማኞች መካከል በአህዛብ ጥያቄ ላይ ስለነበረው አለመስማማት ግልጽ የሆነ ምሳሌ ነው፡፡ እንደ ቆርኔሊዎስ ያለ አልፎ አልፎ የሚመጣ አህዛብን ማካተት አንዳንዶች ምቾት እንዳይሰማቸው አድርጓቸዋል፣ ነገር ግን ጳውሎስ በኢየሱስ ላይ ባለው እምነት ብቻ በመመስረት የቤተ ክርስቲያንን በር ለአህዛቦች በሰፊው ክፍት ለማድረግ ሆን ብሎ ወንጌል በገላትያ መጽሐፍ ውስጥ ያደረገው ጥረት አንዳንዶች የጳውሎስን አገልግሎት ሆን ብለው እንዲሸረሽሩ አደረጋቸው፡፡

ጳውሎስ ከአህዛብ ክርስቲያኖች ጋር በአንጾኪያ የሚሰራውን ሥራ አንዳንድ ከይሁዳ የሆኑ አማኞች ለመቀልበስ የሞከሩት እንዴት ነበር? የሐዋ. 15፡ 1-5፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 15 ውስጥ የኢየሩሳሌም መማክርት በግዝረት ጉዳይ ላይ በመጨረሻ ከጳውሎስ ጋር ቢቆሙም በጳውሎስ አገልግሎት ላይ የነበረው ተቃውሞ ቀጠለ፡፡ ከሰባት አመት ገደማ በኋላ፣ ጳውሎስ ኢየሩሳሌምን ለመጨረሻ ጊዜ በጎበኘ ጊዜ፣ ብዙዎች አሁንም የጳውሎስን ወንጌል በጥርጣሬ ይመለከቱ ነበር፡፡ እንዲያውም ጳውሎስ ቤተ መቅደሱን በጎበኘ ጊዜ ከእስያ የሆኑ አይሁዶች ‹‹የእሥራኤል ሰዎች ሆይ፣ እርዱን፡- ሕዝብን ሕግንም ይህንም ስፍራ ሲቃወም ሰውን ሁሉ በየስፍራው የሚያስተምረው ሰው ይህ ነው›› ብለው በጮሁ ጊዜ ሕይወቱን ሊያጣ ትንሽ ቀርቶት ነበር (የሐዋ. 21፡ 28፤ 21፡ 20ና 21ንም ደግሞ ይመልከቱ)፡፡

የጳውሎስ ትምህርት ባሳሰባቸው በእነዚህ የአይሁድ አማኞች ቦታ ራስዎን ያስቀምጡ፡፡ የእነርሱ ጭንቀትና ተቃውሞ የሆነ ትርጉም የሚሰጠው ለምንድን ነው? የራሳችን አስቀድመው በአእምሮአችን ውስጥ የነበሩ ሀሳቦችና ባሕላዊ (እና ኃይማኖታዊ) አስተሳሰቦች ወደ ስህተት ሊመሩን እንደሚችሉ ከዚህ ምን መማር እንችላለን? የፈለገውን ያህል በደንብ ብናስብበትም፣ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ስህተቶችን ከመፈጸም ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
 

መጋቢት 22
Jun-30
 

ተጨማሪ ሃሳብ:

 

በግል መለወጥና በቤተ ክርስቲያን መካከል ስላለው ግንኙነት ለማወቅ የኤለን ጂ ኋይት ቴስቲሞኒስ ፎር ዘ ቸርች በሚለው ሶስተኛው መጽሐፍ ገጽ 430-434 ላይ ‹‹የግለሰብ ጥገኛ አለመሆን›› በሚለው ርዕስ ሥር ያለውን ሀሳብ ያንብቡ፡፡ አስቀድሞ ስለነበረው የጳውሎስ ሕይወትና ስለመለወጡ የተሰጡ ተጨማሪ ሀሳቦችን ለማግኘት የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ ኮመንቴሪን ስድስተኛውን መጽሐፍ ገጽ 226-234ን ይመልከቱ፡፡ ‹‹ጳውሎስ አስቀድሞ ይታወቅ የነበረው በአይሁድ ኃይማኖት አስከባሪነቱና የማይደክመው የኢየሱስ ተከታዮች አሳዳጅ በመሆኑ ነበር፡፡ ደፋር፣ ጥገኛ ያልሆነ፣ ያለማቋረጥ ጥረት የሚያደርግ ሰው ስለነበር መክሊቶቹና የተማረው ትምህርቱ በማንኛውም የስራ ቦታ እንዲያገለግል ያስችሉት ነበር፡፡ ሀሳብ ያቀርብ የነበረው ከተለመደው ውጭ በሆነ ግልጽነት ስለነበር በሚያጠወልግ አሽሙሩ ተቃዋሚዎቹን ማሳፈር ይችል ነበር፡፡ አሁን አይሁዶች ይህን ከተለመደው ወጣ ያለ ተስፋ የሚጣልበትን ወጣት ከዚህ በፊት ያሳድዳቸው ከነበራቸው ሰዎች ጋር አንድነት ፈጥሮ ያለ አንዳች ፍርሃት በኢየሱስ ስም ሲሰብክ ተመለከቱት፡፡

‹‹በጦር ሜዳ የሚሞት ጄኔራል ለሰራዊቱ ኪሳራ ነው፣ ነገር ግን የእርሱ ሞት ለጠላት ተጨማሪ ብርታት አይሰጥም፡፡ ነገር ግን እውቅና ያለው ሰው ተቃዋሚ ኃይልን ሲቀላቀል፣ እርሱ የሚሰጠው አገልግሎት የሚቀር ብቻ ሳይሆን እርሱ የሚቀላቀላቸው ከፍተኛ ጥቅም ያገኛሉ፡፡ የጠርሴሱ ሳውል በደማስቆ መንገድ ላይ እያለ እግዚአብሔር ሊገድለው ይችል ነበር፤ ያንን ቢያደርግ ኖሮ አሳዳጅ የነበረው ኃይል ብዙ ብርታት ያጣ ነበር፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በአርቆ አስተዋይነቱ የተጋዳዩን ሕይወት ያዳነ ብቻ ሳይሆን እርሱን በመለወጥ ከጠላት ወገን ወደ ክርስቶስ ወገን አሸጋግሮታል፡፡ አንደበተ-ርቱእና ኃይለኛ የመተቸት አቅም ስለነበረው፣ ጳውሎስ፣ በዓላማ ጽናቱና ፍንክች በማይል ድፍረቱ የቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋት ብቃት ነበረው፡፡›› —Ellen G. White, The Acts of the Apostles, p. 124.

 

የመወያያ ጥያቄዎች:

 

ጳውሎስን አምርረው ይቃወሙ የነበሩት እንደ እርሱ በኢየሱስ ያምኑ የነበሩ አይሁዶች ከመሆናቸው እውነታ ምን ትምህርት መማር እንችላለን?

እግዚአብሔርን ሳይዋጉ ለኃይማኖታዊ መርሆ መቆምዎን እርግጠኛ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?

ማጠቃለያ፡- ጳውሎስ በደማስቆ መንገድ ከኢየሱስ ጋር የተገናኘበት ጊዜ በሕይወቱና በቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ቅጽበት ነበር፡፡ እግዚአብሔር በአንድ ወቅት የቤተ ክርስቲያን አሳዳጅ የነበረውን ለወጠውና ወንጌልን ለአሕዛቡ ዓለም የሚያደርስ የተመረጠ ሐዋርያ አደረገው፡፡ ነገር ግን ጳውሎስ አህዛብን በእምነት ብቻ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማካተቱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለነበሩት ለአንዳንዶች አስቸጋሪ ጽንሰ ሀሳብ ሆነባቸው፡፡ ይህ ደግሞ አስቀድሞ የተያዘ ሀሳብና አግባብ የሌለው ጥላቻ ተልእኮአችንን እንዴት እንደሚያደናቅፈው ኃይለኛ የሆነ ምሳሌ ነው፡፡