በጎቼን መግብ፡ 1ኛ እና 2ኛ ጴጥሮስ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2017

ከግንቦት 5-11

ስምንተኛ ትምህርት

May 13 - 19


የሱስ በጴጥሮስ ጽሑፎች



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 1ጴጥ. 1:18- 19፣ ቆለ. 1:13-14፣ ኢሳ. 53:1–12፣ ዮሐ. 11:25፣ መዝ. 18:50፣ 2ጴጥ. 1:1


የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - “ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት መስቀል ላይ ተሸከመ፤ በእርሱ ቁስል እናንተ ተፈውሳችኋል” (1ጴጥ. 2:24)፡፡

በ አንደኛ ጴጥሮስ መልእክት ያደረግነው ጥናት እንደሚያሳየው ሐዋርያው የቱንም ያህል ልዩ ልዩ ሃሳቦችና ጉዳዮች ቢያነሳና ቢዳስስም ነገር ግን ትኩረቱ በየሱስ ላይ ነው፡፡ ደብዳቤው የሱስን እንደ ጥሩ ባለሙያ የእጅ ጥበብ በወርቃማ ድርና ማግ እየሸለመ በመልእክቱ አብልጦ እንዲንሰራፋ አድርጎታል፡፡

ጴጥሮስ ራሱን “ሐዋርያ” ብሎ ከጠራበት የመልክቱ ቀዳሚ መስመር አንስቶ “በክርስቶስ ላላችሁ ለሁላችሁ ሰላም ይሁን” (1ጴጥ. 5፡14) እስከሚለው መደምደሚያ--የሱስ የጽሑፉ ቁልፍ ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡ ሐዋርያው የሱስ ስለ እኛ መሥዋዕት ሆኖ ስለመሞቱ በዚህ ደብዳቤው ይናገራል፡፡ ጴጥሮስ የሱስ ስላለፈበት ታላቅ መከራ በመናገር--ስለ እኛ ያንን መከራ በመቀበል ምሳሌያችን መሆኑን ያሳየናል፡፡ ስለ የሱስ ትንሳኤና--ትንሳኤው ለእኛ ስላለው ትርጉም ይነግረናል፡፡ እንዲሁም ስለ ተቀባው ክርስቶስ መሲህነት ብቻ ሳይሆን ስለ መለኮታዊው የሱስ ጭምር ያወሳናል፡፡ በዚህም በአንደኛ ጴጥሮ መልእክት ስለ የሱስ መለኮታዊ ባህሪ ተጨማሪ መረጃዎችን እናገኛለን፡፡ የዘላለማዊ ህይወት ተስፋ ይኖረን ዘንድ ሰብዓዊውን ሥጋ ለብሶ የመጣው፣ በምድር የተመላለሰውና የሞተው እርሱ ራሱ እግዚአብሔር ነበር፡፡

ግንቦት 6
14-May

የሱስ--መሥዋዕታችን


እግዚአብሔር በኃጢአት የወደቀውን ሰብዓዊ ዘር ለማዳን የሠራው ሥራ የመጽሐፍ ቅዱስ ማእከላዊ ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡ በዘፍጥረት ከተዘገበው የአዳምና የሔዋን ውድቀት አንስቶ እስከ ራዕይ ዮሐንስ የባቢሎን ውድቀት እግዚአብሔር “የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን” (ሉቃ. 19:10) የሠራውን ሥራ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ይገልጽልናል፡፡ የዚህ መልእክት ጭብጥ በጴጥሮስ ደብዳቤ መንጸባረቁን ልብ ይሏል፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡- 1ጴጥ. 1:18-19፣ ቆለ. 1:13-14፡፡ የመዋጀት ትርጉም ምንድን ነው? ደም ከመዋጀት ጋር የሚያያይዘው ምንድን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

1ጴጥ. 1፡18-19 ለየሱስ ሞት የሚከተለውን አጽንኦት ይሰጣል፡ “የተዋጃችሁት በሚጠፋ ነገር፣ በብር ወይም በወርቅ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን የተዋጃችሁት ነውርና እንከን እንደ ሌለበት በግ ደም፣ በክርስቶስ ክቡር ደም ነው፡፡” በጥቅሱ ሁለት ቁልፍ ሃሳቦች የተንጸባረቁ ሲሆን እነርሱም መዋጀትና እንሳትን በመሥዋዕትነት ማቅረብ ናቸው፡፡

መዋጀት በመባል የሚታወቀው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ስፍራዎች ተጠቅሶአል፡፡ ለአብነት ያህል የአህያ በኩር (መሥዋዕት ሆኖ መቅረብ የማይችል) እና በኩር ወንድ ልጅ በበግ በጠቦት ይዋጅ ነበር (ዘሌዋ. 34፡ 19-20)፡፡ አንድ ሰው በድኽነት ምክንያት ርስቱን ቢሸጥና ውሎ አድሮ በለስ ቀንቶት ሐብት ቢያካብት ያን የሸጠውን መልሶ መግዛት (መዋጀት) ይችል ነበር (ዘሌዋ. 25፡25-26)፡፡ ባሪያ መዋጀት የሚችል መሆኑ ሌላው አበልጦ ትኩረት የተቸረው ጉዳይ ነበር (ዘሌዋ. 25፡47-49)፡፡ “ከቀድሞ አባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከንቱ ከሆነ ህይወት የተዋጃችሁት… ነውርና እንከን እንደሌለበት በግ ደም፣ በክርስቶስ በክቡር ደም ነው” (1ጴጥ. 1:18-19) በማለት ሐዋርያው ለአንባቢዎቹ መረጃ ይሰጣል፡፡ ከላይ የተጠቀሰው የበግ ጠቦት የእንስሳን የመሥዋዕት ሥርዓት በማመላከት ይታወቃል፡፡

ጴጥሮስ የክርስቶስን ሞት በዕብራውያኑ መጽሐፍ ከቀረበው የእንስሳ መሥዋዕት ጋር በማያያዝ ያቀርባል፡፡ ኃጢአተኛው እንከን የሌለበትን የበግ ጠቦት ይዞ ወደ ማደሪያው ድንኳን ከቀረበ በኋላ እጁን በእንስሳው ላይ ይጭናል (ዘሌዋ. 4፡32-33) ፡፡ ከዚያም ጠቦቱ ይታረድና ጥቂት ደም ተወስዶ መሠዊያው ይቀባል፡፡ የተቀረው ደም በሙሉ በመሠዊያው ግርጌ እንዲፈስ ይደረጋል (ዘሌዋ. 4፡34)፡፡ መሥዋዕት ሆኖ የሞተው እንስሳ መሥዋዕቱን ላመጣው ግለ ሰብ የኃጢአት “ሥርየት” ያስገኛል፡፡ የሱስ በእኛ ቦታ ሞቶ በእርሱ መሥዋዕትነት ባንዋጅ ኖሮ ለዘላለም ተኮንነን በቀረን ነበር--ሲል ጴጥሮስ ይነግረናል፡፡

የደኅንነታችን ህልውና የተመረተው በእኛ ምትክ ቅጣት በተቀበለው ጌታ ላይ መሆኑ--ብቸኛው መተማመኛችን እርሱ ስለ መሆኑ ምን ያስተምረናል?

ግንቦት 7
15-May

የክርስቶስ ጥልቅ ፍቅር የታየባቸው የመከራ ቀናት


ክርስቲያኖች አልፎ አልፎ የክርስቶስ ጥልቅ ፍቅር ስለ ታየባቸው ስለነዚያ የመከራ ቀናቶች ሲነጋገሩ ይደመጣሉ፡፡ በእንግሊዝኛው ጥቅም ላይ የዋለው ፓሽን የተሰኘው ቃል የተወሰደው ከግሪክኛው ሲሆን መከራ መቀበል የሚል ፍቺ አለው፡፡

ስለዚህ ፓሽን ኦቭ ክራይስት የተሰኘው ሃረግ የሱስ በድል አድራጊነት ወደ የሩሳሌም ከገባበት ጊዜ አንስቶ ያሉትን የመጨረሻዎቹን ቀናት ይመለከታል፡፡

የሚከተሉት ጥቅሶች የሱስ ስለ እኛ ስለ ደረሰበት መከራ ምን ይነግሩናል? 1ጴጥ. 2:21–25፣ ኢሳ. 53:1–12

የሱስ የደረሰበት መከራ ልዩ አንደምታ ተሰጥቶታል፡፡ “ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት (ከሐዋ. 5፡30 ጋር ያመሳክሩ) መስቀል ላይ ተሸከመ” (1ጴጥ. 2:24)፡፡ ኃጢአት ሞት ያስከትላል (ሮሜ 5፡12)፡፡ እኛ እንደ ኃጢአተኝነታችን ሞት የሚገባን ፍጡሮች ሆነን ሳለ፤ ነገር ግን በአፉ ተንኮል ያልተገኘበት ፍጹም የሆነው የሱስ በእኛ ቦታ ሞተ (1ጴጥ. 2፡22)፡፡ በውጤቱም የዘላለማዊው የደኅንነት ዕቅድ ባለቤት ሆንን፡፡

ጥቅሶቹን በድጋሚ ያንብቡ፡ ኢሳ. 53፡1-12፡፡ የሱስ የደኅንነትን ዕቅድ ገቢራዊ ሲያደርግ በእኛ ቦታ መከራ ስለመቀበሉ ጥቅሶቹ ምን ይነግሩናል? ስለ እግዚአብሔር ጸባይስ ምን ይሉናል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

“ሰይጣን በከባድ ፈተና የየሱስን ልብ አስጨነቀው፡፡ አዳኛችን ከመቃብሩ በር አሻግሮ ማየት ተሳነው፡፡ ከመቃብር በአሸናፊነት እንደሚነሳና የሚከፍለው መሥዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንደሚያገኝ ተስፋ ማድረግ ተሳነው፡፡ ኃጢአት እጅግ አስከፊ ከመሆኑ የተነሳ እርሱና አባቱ ለዘላለም ተለያይተው የሚቀሩ መሰለው፡፡ በዚህ ጊዜ የሱስ ይሰማው የነበረው ስቃይ ለኃጢአተኛው ሰብአዊ ዘር የሚደረገው የምሕረት ምልጃ ካበቃ በኋላ ኃጢአተኞች ከሚሰማቸው ስቃይ ጋር ይመሳሰላል፡፡ የእግዚአብሔርን ልጅ የጎዳውና የጠጣውንም ጽዋ እጅግ የመረረ ያደረገው በሰው ምትክ ሆኖ የእግዚአብሔርን ቁጣ እንዲቀበል ያደረገው የኃጢአት ምንነት ስለተሰማው ነው”--የዘመናት ምኞት ገጽ 798፡፡

ክርስቶስ ለእኛ ሲል ላለፈበት የመከራ ጎዳና ምላሻችን ምን ሊሆን ይገባል? በ1ጴጥ. 1፡21 የተጠቀሰውን የእርሱን ምሳሌ የምንከተለው እንዴት ነው?

ግንቦት 8
16-May

የየሱስ ትንሣኤ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡-- 1ጴጥ. 1:3-4፣ 21፣ 3:21፣ ዮሐ. 11:25፣ ፊልጵ. 3:10-11፣ ራእ. 20:6፡፡ ጥቅሶቹ የሚያመላክቱት ታላቅ ተስፋ ምን ይመስላል? ለእኛ ያለው ትርጉምስ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

አንደኛ ጴጥሮስ--በየሱስ ላይ ባላቸው እምነት ምክንያት መከራ እየደረሰባቸው ላሉ ወገኖች መጻፉን ቀደም ብለን ተመልክተናል፡፡ ከዚህ አኳያ ሐዋርያው በመልእክቱ መግቢያ የአንባቢዎቹን ትኩረት ወደ ሚጠብቃቸው ተስፋ መውሰዱ ተገቢ እንደሆነ እናያለን፡፡ የክርስቲያኖች ተስፋ በየሱስ ትንሳኤ ላይ በማረፉ ተስፋቸው ሕያው ነው--ሲል ጴጥሮስ ይነግረናል (1ጴጥ. 1፡3)፡፡ የሱስ ከሙታን በመነሳቱ ክርስቲያኖች የማይጠፋውን ወይም የማይበላሸውን ሰማያዊ ርስት ለመውረስ ተስፋ ማድረግ ይችላሉ (1ጴጥ. 1፡4)፡፡ በሌላ አነጋገር ነገሮች የቱንም ያህል አስከፊ ገጽታ ሊይዙ ቢችሉ፤ ለዘላለም ስለሚጠብቀን ነገር ዘወትር ያስቡ፡፡ የየሱስ ትንሳኤ እኛም ከሙታን መነሳት ለመቻላችን ዋስትና ነው (1ቆሮ. 15፡20-21)፡፡ ጳውሎስ ይህን ሃሳብ እንደሚከተለው ያቀርበዋል፡--“ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ እናንተም እስከ አሁን ድረስ ከነኃጢአታችሁ አላችሁ ማለት ነው” (1ቆሮ. 15:17)፡፡ ነገር ግን የሱስ ከሞት በመነሳት ራሱን ሞትን የማሸነፍ ኃይል እንዳለው አሳየ፡፡ ስለዚህ የክርስቲያኖች ተስፋ የተመሰረተው በታሪካዊው የየሱስ ትንሳኤ ክስተት ላይ ሆነ፡፡ ትንሳኤው የእስትንፋሳችን መጨረሻ ብቸኛ ተስፋ ነው፡፡

የጌታ ተስፋ ባይኖረን ምን ይውጠን ነበር? ክርስቶስ ለእኛ ያደረገው ማንኛውም ነገር መደምደሚያው የትንሣኤው ተስፋ ነው፡፡ የትንሣኤው ተስፋ ባይኖረን ከአንዳንድ የክርስትና እምነት አስተምህሮ በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው የሞቱ ጭልጥ ባለ እንቅልፍ ወድቀው በቀሩ አልነበር? “ሞት ለክርስቲያኖች በጸጥታና በጨለማ የተዋጠ እንቅልፍ ነው፡፡ ሕይወት ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ተሸሽጎ ይቆይና ‘ሕይወታችሁ የሆነው ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ እናንተም በዚያን ጊዜ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ’ (ዮሐ. 8:51-52፣ ቆለ. 3:4) በዚህ ክርስቶስ ዳግም በሚገለጥበት ትዕይንት በመቃብር ያንቀላፉ ወገኖች በሙሉ ድምፁን ይሰማሉ፤ በክብር የተሞላውን የማይሞት አካል ለብሰውም ይነሳሉ”— Ellen G. White, The Desire of Ages, p. 787፡፡

በግልጽ ስለሚታየው የሞት ድምዳሜ ያስቡ፡፡ ሞት መጥፎ፣ ይቅርታ የሌለውና በተጨባጭ የሚስተዋል እውነታ ነው፡፡ የትንሣኤው ተስፋ ለእምነታችንም ሆነ ተስፋ ለምናደርገው ማንኛውም ነገር በእጅጉ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ግንቦት 9
17-May

የሱስ እንደ መሲህ


ቀደም ብለን እንደ ተመለከትነው በየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ወሳኝ ከነበሩ ነጥቦች መሃል የሱስ ማን እንደሆነ አስመልክቶ ለቀረበው ጥያቄ ጴጥሮስ የሰጠው ምላሽ ነበር፡--“ ‘አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ’ ” (ማቴ. 16:16)፡፡ ክርስቶስ የተሰኘው ቃል ግሪክኛ ሲሆን “ቅቡ” (የተቀባው)፣ “መሲህ” የሚል ትርጉም አለው፡፡ ሆኖም በዕብራውያን ቋንቋ ይኸው ቃል mashiyach በሚል ይታወቃል፡፡ “መቀባት” የሚል ፍቺ ያለው ይህ ስርወ ቃል በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በተለያዩ ዐውዶች ቀርቦአል (እንደውም በአንድ ቦታ የአረማውያን ንጉሥ የሆነውን ጢሮስ ለማመላከት ጥቅም ላይ መዋሉን ልብ ይሏል [ኢሳ. 45:1]) ፡፡ ስለዚህ ጴጥሮስ የሱስን--ክርስቶስ ብሎ ሲጠራው በዕብራውያኑ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተጠቀሰውን ቃል ጥቅም ላይ ማዋሉን መመልከት ይቻላል፡፡

መሲህ ወይም የተቀባው የተሰኙትን ቃላት የያዙትን ከዚህ በታች የቀረቡትን የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች ያንብቡ፡፡ ዐውደ ሃሳቡ ስለ ቃላቱ ፍቺ ምን ያስተምረናል? ጴጥሮስ የሱስን መሲህ ብሎ ሲጠራው ምን ያህል የቃሉን ትርጓሜ አስተውሎ ነበር?

መዝ. 2:2 ______________________________________________________________________________

መዝ. 18:50____________________________________________________________________________

ዳን. 9:25______________________________________________________________________________

1ሳሙ. 24:6____________________________________________________________________________

ኢሳ. 45:1_______________________________________________________________________________

ምንም እንኳ ጴጥሮስ የሱስን መሲህ (ማቴ. 16:16-17) ብሎ ለመጥራት ከጌታ መነሳሳት ቢያገኝም ነገር ግን የቃሉን ፍቺ ሙሉ ለሙሉ አለማስተዋሉ ብዙም አያጠያይቅም፡፡ ሲጀመር--ስለ መሲህ ትክክለኛ ማንነትም ሆነ መሲህ ስለሚያከናውናቸው ተግባራት--እንደውም ወደ ምድር የመጣበትን ዓላማ እንዴት ወደ ፍጻሜ እንደሚያመጣ እንኳ በትክክል የሚያውቀው ነገር አልነበረም፡፡ እንደዚያ ዓይነቱ የማስተዋል ጉድለት የተከሰተው በጴጥሮስ ላይ ብቻ አልነበረም፡፡ እንደውም በድፍን እስራኤል ይስተዋል የነበረው የመሲህ አረዳድ በአያሌ የተራራቁ ጽንሰ ሃሳቦች የታጨቀ ነበር፡፡ ከላይ በቀረቡት ጥቅሶች የምናገኛቸው--መሲህ ወይም የተቀባው የተሰኙት ቃላት የጽንሰ ሃሳቡን ምሉዕ ሥዕል አይሰጡንም፡፡ ይልቁንም መሲህ በስተመጨረሻ በሚሆነውና በሚያደርገው ላይ በቅድሚያ ወደ ማስጠንቀቁ ያዘነብላሉ፡፡ ዮሐ. 7፡40--መሲህ ከዳዊት የትውልድ ሃረግ እንደሚመዘዝና በቤተልሔም እንደሚወለድ በመንገር ከመሲህ ስለሚጠበቁ አንዳንድ ነጥቦችን ይገልጻል (ኢሳ. 11፡1-16፣ ሚክ. 5፡2)፡፡ በእርግጥ እዚህን ሁለት ነጥቦች በትክክል ቢያገኙም ችግሩ ያለው ከዳዊት ትውልድ የሚመጣው መሲህ ዳዊት ያደረገውን በመድገም የአይሁድ ጠላቶችን ድል ያደርጋል የሚለው ላይ ነው፡፡ መሲህ በሮማውያን እጅ ወድቆ ይሰቀላል ብሎ የሚጠብቅ አንድም አይሁዳዊ አለመኖሩ እርግጥ ነው፡፡ ጴጥሮስ ኋላ ላይ መልእክቶቹን በጻፈበት ወቅት የየሱስን መሲህነት በጥልቅ መገንዘብ ችሎ ነበር፤ (ጴጥሮስ በሁለቱ ደብዳቤዎቹ ክርስቶስ ሲል 15 ጊዜ የሱስን መጥራቱን መመልከት ይቻላል) እርሱ ያንን ሁሉ ያከናወነው ስለ ሰብዓዊው ፍጡር መሆኑ ገብቶታል፡፡

ግንቦት 10
18-May

የሱስ--መለኮታዊ ባህሪ የተላበሰው መሲህ


ጴጥሮስ የየሱስን መሲህነት ብቻ ሳይሆን ጌትነቱንም ጠንቅቆ ይረዳ ነበር፡፡ ጴጥሮስ መልእክቶቹን በጻፈበት ወቅት መሲህ ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን አውቆአል፡፡ ምንም እንኳ “ጌታ” የተሰኘው ቃል ምድራዊ አንደምታ ቢኖረውም ግልጽ የመለኮት ማጣቀሻም መሆን ይችላል፡፡ ሐዋርያው በ1ጴጥ. 1:3 እና 2ጴጥ. 1:8፣ 14፣ 16-- የሱስን እንደ መሲህ፣ እንደ ክርስቶስ፣ እንደ ጌታና እንደ እግዚአብሔር ሲጠቅስ ይስተዋላል፡፡

ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደ ሌሎች የብሉይ ኪዳን ጸሐፊዎች ሁሉ በየሱስና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን ግንኙነት አብ እና ወልድ በሚል ሲገልጽ ይታያል፡፡ “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ” (1ጴጥ. 1:3፣ 2ጴጥ. 1:17)፡፡ የሱስ በተወዳጅ ልጅነት የተገለጠ ሲሆን (2ጴጥ. 1፡17) ሌሎቹም እንደ ጌትነቱና ሰማያዊ ሥልጣኑ ያሉት መገለጫዎች ከእግዚአብሔር አብ ጋር ያለውን የተለየ ትስስር መሰረት አድርገው የሚመጡ ናቸው፡፡

የሚከተሉት ጥቅሶች ስለ የሱስ መለኮትነት ለምን ይነግሩናል?--2ጴጥ. 1:1፣ ዮሐ. 1:1፣ ዮሐ. 20:28፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

በ2ጴጥ. 1፡1 “በአምላካችንና በአዳኛችን በየሱስ ክርስቶስ” የሚል ሃረግ እናገኛለን፡፡ አዲስ ኪዳን በተጻፈበት በግሪክኛው “አምላካችን” እና “አዳኛችን” የተሰኙት ቃላት የሱስን የሚገልጡ (ገላጭ ቃላት) ሆነው ቀርበዋል፡፡ በመሆኑም 2ጴጥ. 1፡1 የየሱስን ሙሉ መለኮትነት በግልጽ ከሚያስቀምጡ የአዲስ ኪዳን ጥቅሶች መሃል አንዱ ነው፡፡

የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የየሱስን ማንነት ለማስተዋል ብርቱ ጥረት ማድረጋቸውን ተከትሎ፤ ውሎ አድሮ እርስ በርስ የማይጣረስ ዐውድ የያዘውን አዲስ ኪዳን አበረከቱ፡፡ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እንደ ሌሎቹ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ በጴጥሮስም መልእክቶች ለየቅል ቀርበዋል (ለአብነት ያህል፡ አብ/ ወልድ፡ 1ጴጥ. 1:3፣ 2ጴጥ. 1:17፣ መንፈስ ቅዱስ: 1ጴጥ. 1:12፣ 2ጴጥ. 1:21)፡፡ ይህም ሆኖ የሱስ እንደ መንፈስ ቅዱስ ሙሉ የመለኮት ባህሪ ተላብሶ የቀረበበት ሁኔታ በመኖሩ--ከብዙ ጊዜና አያሌ ውይይቶች በኋላ ቤተ ክርስቲያን የመለኮትን ምስጢር ለመግለጽ የሥላሴን ኃይማኖታዊ አስተምህሮ አዳበረች፡፡ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች ይህን የሥላሴ ኃይማኖታዊ አስተምህሮ ከሃያ ስምንቱ መሰረታዊ አስተምህሮዎቻቸው እንደ አንዱ አድርገው አካተዋል፡፡ ጴጥሮስ የሱስን እንደ መሲህ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ራሱ መሆኑን በግልጽ ያሳየናል፡፡

ስለ የሱስ ህይወትና ሞት ሲያስቡና እርሱ እግዚአብሔር እንደ ነበር ሲገነዘቡ-- እያገለገልንና እያመለክን ያለው እግዚአብሔር ምን ዓይነት አምላክ ስለ መሆኑ ይህ ምን ይነግሮታል? ይህን አምላክ ልንወደውና ልንታመነው የሚገባው ለምንድን ነው? መልስዎን በሰንበት ትምህርት ጥናት ላይ ይዘው ለመቅረብ ይሞክሩ፡፡

ግንቦት 11
19-May

ተጨማሪ ሃሳብ፡


“ቤተ ክርስቲያን " ‘የተቀባው’ ለሚለው ቃል ተመጣጣኝ ከሆነው ‘ክርስቶስ’ ከተሰኘው ስያሜ መጠሪያ ያገኘች እንደ መሆኗ፤ ‘መሲህ’ ከተሰኘው ቃል መጀመር ከነገረ አስተሳሰብ ወይም ከአስተሳሰብ ሕግ አኳያ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ የዕብራውያኑ ቃል የእግዚአብሔር ወኪል በመሆን ለእግዚአብሔር ሕዝቦች የአዲስ ዘመን ጅማሮ ከሚያበስረው አይሁዳውያን ሲጠባበቁት ከኖሩት አዳኝ ከተሰኘው ሥዕላዊ መግለጫ ጋር ዝምድና አለው፡፡ የዕብራውያኑም ሆነ የግሪኩ ቃል መጠሪያ ምንጭ ‘መቀባት’ የሚለው ሥርወ ቃል ነው፡፡ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የሱስን ‘ክርስቶስ’ ብለው በመጥራት የተለየ ዓላማና ተግባር እንዳለው ሲመለከቱት ይስተዋላል፡፡ “ክርስቶስ የተሰኘው መጠሪያ ቃል በአዲስ ኪዳን ከአምስት መቶ ጊዜ በላይ ተጠቅሶአል፡፡ ምንም እንኳ የሱስ በኖረበት ዘመን መሲህነት ከአንድ በላይ ጽንሰ ሃሳብ ቢይዝም፤ በአንደኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ አይሁዶች መሲህን ከእግዚአብሔር ጋር የተለየ ግንኙነት እንዳለው ሰው አድርገው ይመለከቱ ነበር፡፡ መሲህ የእግዚአብሔር መንግሥት በሚቋቋምበት በዘመኑ መጨረሻ ከተፍ ማለት ነበረበት፡፡ እርሱ እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመዋጀት ጣልቃ ገብቶ አዲስ ታሪክ የሚጽፍበት ነው፡፡ ምንም እንኳ የሱስ ‘መሲህ’ የተሰኘውን ቃል ቢቀበለውም መጠሪያው አድርገው እንዲጠቀሙበት ግን አላበረታታም፡፡ ለዚህ መንስኤው ስያሜው ዘርፈ ብዙ ችግር ፈጣሪ ፖለቲካዊ አንደምታዎች በመያዙ ነው፡፡ ምንም እንኳ የሱስ መሲህነቱን ባደባባይ ለማወጅ ፈቃደኛ ባይሆንም ጴጥሮስም ሆነ (ማቴ. 16፡16-17) ሳምራዊቷ ሴት (ዮሐ. 4፡25- 26) ይህን መጠሪያ በመጠቀማቸው ሲገስጻቸው አይስተዋልም፡፡ የሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ለአንዱ አንድ ኩባያ ውሃ መስጠት ዋጋ እንዳለው በተናገረበት በሉቃስ ዘገባ (ማር. 9፡41) መሲህ መሆኑን ጠንቅቆ ያውቅ እንደ ነበር መገንዘብ ይቻላል”— The SDA Bible Commentary, vol. 10 12, p. 165


የመወያያ ጥያቄዎች:



በኢሳ. 53፡1-12 በቀረበው መሰረት የሱስ ለእኛ ያደረገው ነገር ምንድን ነው? እርሱ ስለ እኛ ያደረገውን በዝርዝር ለመጻፍ ይሞክሩ፡፡ የሱስ በእኛ ምትክ የተቀበለውን መከራ በጥቅሶቹ በግልጽ መመልከት የምንችለው እንዴት ነው? እርሱ የእኛን ቦታ እንዲወስድ የፈለግነው ለምንድን ነው?

አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የዘላለማዊ ህይወት ተስፋ ሌሎችን መጨቆኛ መሣሪያ ሲያደርጉት በታሪክ ታይቶአል፡፡ ምድራዊው ህይወት በብዙ አስቸጋሪ ውጣ ውረድ የተሞላ ቢሆንም፤ እግዚአብሔር--የሱስ ዳግም ሲገለጥ ለእኛ ያዘጋጀውን መመልከት ተገቢ ነው፡፡ አንዳንዶች ሌሎችን ለመጨቆን እንደ ማታለያ ዘዴ በመጠቀማቸውና ይህ በእግዚአብሔር ቃል የቀረበ አስተምህሮ ጉዳት የሚያደርስ ፍቺ በማግኘቱ--ብዙዎች ስለ ሰማያዊ ርስት ባለቤትነት የቀረበውን የክርስትናን ዘላለማዊ ህይወት አስተምህሮ እንዲቃወሙ መንስኤ ሆኗል፡፡የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?

 በሐሙስ ጥናት ስለ ክርስቶስ መለኮትነትና መለኮትነቱ ስለ እግዚአብሔር ጸባይ ስለሚነግረን ነገር የሰጡትን መልስ ይመልከቱ፡፡ ክርስቶስ መለኮታዊ ባህሪ እንዲኖረው ለምን አስፈለገ? እንዲህ ያለው መልካም የምስራች ስለ እግዚአብሔር የሚገልጽልን ነገር ምንድን ነው?