ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 1ጴጥ. 5:1–10፣ ሐዋ. 6:1–6፣ ኤር. 10:21፣ ማቴ. 20:24–28፣ ምሳሌ 3:34፣ ራእዕ 12:7–9፡፡
የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - “የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” (1ጴጥ. 5:7)፡፡
አ መርቂ ዕድገት ያስመዘገቡ ቤተ ክርስቲያኖችን ምስጢር የመፈተሸ ጥናቶች
በየጊዜው የተካሄዱ ሲሆን፤ ከሞላ ጎደል ሁሉም ጥናቶች--ውጤታማ
የሥራ አመራር ክህሎት አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ የዚህ ሥራ
አመራር ጥበብ ራእይ የተወሰደው ከግዚአብሔርና ከቃሉ ሲሆን ይኸውም
እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን አባል እንደ ተሰጠው መንፈሳዊ ስጦታ አገልግሎት
የሚሰጥበትን ዕድል በማመቻቸት የወንጌልን ተልዕኮ ወደፊት ማራመድ በመቻሉ
ነው፡፡
በእርግጥ የቤተ ክርስቲያን ሥራ አመራር በብርቱ ተግዳሮቶች የተሞላ ነው፡፡ በጎ
ፈቃደኞች ያሏቸውን የተጣበቡ ጊዜያት መሥዋዕት አድርገው አብላጫውን የቤተ
ክርስቲያን አገልግሎት መውሰዳቸው የታወቀ ነው፡፡ አባላት አገልግሎት መስጠት
የማይችሉባቸው ሁናቴዎች ከገጠሟቸው ሌሎች ኃላፊነቱን ወስደው እንዲመረጡ
ለማድረግ የተቻላቸውን ጥረት ያደርጋሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሥራ
አመራሮች ህይወት ከክርስቶስ ጋር በጥልቅ የተቆራኘ ሊሆን ይገባል፡፡ ደግሞም
ጴጥሮስ ስደት ለገጠማቸው አብያተ ክርስቲያናት የጻፈውን መልእክት መዘንጋት
የለብንም፡፡ ታዲያ በእንዲህ ያለ ፈታኝ ወቅት የቤተ ክርስቲያን መሪ ደካማ ከሆነ
ኃላፊነቱን ወስዶ ሥራውን ወደፊት የሚያራምድ ማን ሊሆን ነው?
ሐዋርያው በ1ጴጥ. 5፡1-10 መልእክቱ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ደረጃ መሰጠት
ስለሚኖርበት አመራር ይናገራል፡፡ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ-
ምዕመናኑም እውነተኛ አማኝ ሊኖረው የሚገባ ጸባይ ባለቤት ሊሆኑ እንደሚገባ
ይናገራል፡፡ የጴጥሮስ መልእክት ለእርሱ ዘመን ቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ እንደነበር
እነሆ ለእኛም ገጣሚነት አለው፡፡
ጥቅሶቹን ይመልከቱ፡ የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ስለ ገጠሟት ተግዳሮቶችና
ስለ መሪዎቿ ሚና በሚከተሉት ጥቅሶች የምናገኘው ዕውቀት ምን ይመስላል?--
ሐዋ. 6:1–6፣ 14:23፣ 15:6፣ 1ጢሞቴ. 5:17፣ 1ጴጥ. 5:2
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
እጅግ ብዙ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሱስን አዳኝነት ተቀብሎ ቤተ ክርስቲያንን
መቀላቀሉ ከእግዚአብሔር የተላከ ታላቅ በረከት ቢሆንም--ፈጣን ዕድገት የራሱን
ችግሮች ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ከቀደመችው ቤተ ክርስቲያን ተሞክሮ መመልከት
እንችላለን፡፡ ለምሳሌ በሐዋ. 1-5 ባሉት ምዕራፎች ስለ መንፈስ ቅዱስ ምሪትና ስለ
ብዙዎች ወደ ክርስትና እምነት መለወጥ እናነባለን፡፡ ውጤቱ በሐዋ. 6፡1-6
የተመለከተ ሲሆን--በዚህም የሕዝቡ ብዛት በአመራር ላይ የነበረው አካል
ሊያስተባብር ከሚችለው በላይ በመግዘፉ የየዕለቱ የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ
የሚመራበት መዋቅር ማዘጋጀት አስላጊ ሆኖ ተገኘ፡፡
በአማኞች መካከል ልዩነት ተደርጓል በሚል የቀረበ አቤቱታ፤ በድርጅታዊው
አወቃቀር እስከ ላይ ባለው የኃላፊነት እርከን ጉድለት እንዲገኝ መንስኤ ሆኖ ነበር፡፡
የግሪክ ቋንቋ ተናጋሪ አይሁዶች በዕለታዊው ምግብ የማደል አሠራር ላይ ከእነርሱ
ወገን የሆኑት መበለቶች ችላ ተብለዋል በሚል በይሁዳ በሚኖሩ አይሁዶች ላይ
አቤቱታ አቀረቡ፡፡ በምላሹ የቤተ ክርስቲያኗን ሃብት ለማስተዳደር አስራ ሁለቱን
ደቀ መዛሙርት የሚረዱ ልዩ የዲያቆናትና የአማኞች ስብስብ በማዋቀር እገዛ
እንዲያደርጉ ተመደቡ፡፡
የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በልዩ የመንፈስ ቅዱስ ምሪት መባረኳ እውነት ነው፡፡
እዚህ ላይ በዚያን ጊዜም ቢሆን የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ማደራጀት አስፈላጊ እንደ
ነበር ልብ ይሏል፡፡ ገና በጠኋቱ በእጅጉ ካስፈለጉ ቁልፍ የቤተ ክርስቲያን አመራሮች
መሃል በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኖች እንዲቋቋም የተደረገው የሽማግሌዎች
መንፈሳዊ አገልግሎት ዘርፍ በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ጳውሎስና
በርናባስ ገና ስለ የሱስ ወዳልሰሙ ሰዎች ያደርጉ በነረበው ጉዞ እግረመንገዳቸውን
አዲሱን የክርስትና ዘርፍ የሚመሩ ሽማግሌዎች እየሾሙ የማቋቋም ሥራ ይሠሩ
ነበር (ሐዋ. 14፡23)፡፡
የክርስትና እምነት በተቀቋቋመበት በዚያ ዘመን ብዛት ያላቸው ልዩ ልዩ ኃላፊነቶች
ለሽማግሌዎች ተሰጥተው ነበር፡፡ ሽማግሌዎች የየአጥቢያውን ማኅበረሰብ
የመምራት አገልግሎት እየሰጡ አዳዲስ ነፍሳትን የማስተማር ሥራ ይሠሩ ነበር፡፡
ከስብከት አገልግሎት በተጨማሪ ለማህበረሰቡ ደህንነት አስፈላጊ የሆኑትን
ተግባራት በሙሉ ያደርጉ ነበር (ሐዋ. 15:6፣ 1ጢሞቴ. 5:17፣ 1ጴጥ. 5:2)፡፡
ሁሌም ወደ አንድ ተመሳሳይ ሃሳብ መምጣት አዳጋች ሊሆን ቢችልም--ከአጥቢያ
ቤተ ክርስቲያንዎ ሽማግሌዎች ጋር በተሻለ ሊሠሩ የሚችሉባቸው ምን ዓይነት
አቅጣጫዎች መመልከት ይችላሉ?
ጥቅሱን ያንብቡ፡ 1ጴጥ. 5፡1-4፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ቤተ ክርስቲያንን
በመምራት ሚናቸው ምን ዓይነት ጠባይና አኳኋን ሊታይባቸው ይገባል?
በየትኛውም ዓይነት የአገልግሎት ዘርፍ ብንሰማራ በእነዚህ መርኅዎች ስር
መተዳደር የምንችለው እንዴት ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ራሱን ከሽማግሌዎች እንደ አንዱ የቆጠረው ጴጥሮስ ለሽማግሌዎች መመሪያ
መስጠት ሲጀምር ይስተዋላል፡፡ ጴጥሮስ ስለ ራሱ ሁለት ነገሮችን ማለትም--
ክርስቶስ ለተቀበለው መከራ ምስክር መሆኑንና ወደፊት የሚገለጠው ክብር
ተካፋይነቱን ተገንዝቧል፡፡ ሐዋሪያው ይህን የሚናገረው በሽማግሌ ውስጥ
በቀዳሚነት መታየት ስለሚኖርበት ጻባይ አጽንኦት እየሰጠ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን
ሽማግሌ ክርስቶስ ስለ እኛ የደረሰበትን ሥቃይና ስለ ሰጠን ታላቅ ተስፋ ጥልቅ
ማስተዋል ሊኖረው ይገባል፡፡
ጴጥሮስ የሽማግሌን ሚና የእግዚአብሔርን መንጋ ከመንከባከብ ጋር ያያይዘዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያንን ከበግ ጋር በማነጻጸር የሚያቀርብበት ምክንያት አባላት አንዳንዴ
እንደ በግ በራሳቸው ከመንጋው ተነጥለው ሊጠፉ ስለሚችሉ ነው፡፡ ይህ ሲሆን
መልሶ ወደ መንጋው የሚመራቸውና ከመንጋው ጋር ተዋህደው መሥራት
እንዲችሉ የሚረዳቸው እረኛ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ
በተጨማሪ በአንድ ክርስቲያን ሊታይ የሚገባውን ምግባር የሚያሟላ ምሳሌ ሆኖ
መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል፡፡
የእረኝነት አገልግሎት ለሚሰጡ በሚከተሉት ጥቅሶች ምን ዓይነት ማስጠንቀቂያ
እናገኛለን--ኤር. 10:21፣ ሕዝ. 34:8–10፣ ዘካ. 11:17?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
እረኞች ከገዛ የበግ መንጋዎቻቸው ጋር የሚያከናውኗቸው ተግባራት እንዳሏቸው
ሁሉ ከቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በትዕግሥት መሥራት
በእጅጉ አስፈላጊ የክርስቲያን መሪ ሚና ነው፡፡ ሽማግሌዎች የሱስንና በየሱስ
የሚገኘውን ደኅንነት ለማወቅ የሚፈልጉ ወገኖችን ለአምልኮ ብሎም የጌታን
መልእክት ለማካፈል በእርጋታ ሊያመጧቸው የግድ ነው፡፡ ሽማግሌዎች በግዳጅና
በጫና ሳይሆን በማስተዋልና በፈቃደኝነት አገልግሎት ሊሰጡ እንደሚገባ ጴጥሮስ
ግንዛቤው ነበረው፡፡ በብዙ ተግዳሮቶች የተሞላውን የመሪነት አገልግሎት
በፈቃደኝነት የሚወስዱ ሰዎችን ማግኘት ሁል ጊዜም ቀላል አይደለም፡፡ ይህ
በተለይ አገልጋዮችን በዕጩነት በሚያቀርበው ኮሚቴ እንቅስቃሴ ወቅት በጉልህ
ይታያል፡፡ አንድ ቤተ ክርስቲያን የሚጠበቅባትን አገልግሎት ለመስጠት ዘርፈ ብዙ
ጎዶሎዎች መሙላት ግድ ይላታል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አባላት የሚቀርብላቸውን
የመሪነት ሚና ለመቀበል እንዲያመነቱ የሚያደርጓቸው አያሌ ምክንያቶች አሉ፡፡
አንዳንድ አገልግሎቶች በቂ ጊዜ መሥዋዕት ማድረግ ይጠይቃሉ፡፡ ለአንዳንድ
ዘርፎች ገጣሚ ተደርገው የታሰቡ ሰዎች ደግሞ አስቀድሞውኑ በብዙ መርኀግብሮች
የተጣበቡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሌላው--ኃላፊነቱን ለመውሰድ በቂ ዝግጅት
እንደሌላቸው አድርገው ማሰባቸው ነው፡፡ ነገር ግን የመሪነት አገልግሎት
እንድንሰጥ እስከ ተጠየቅን ድረስ በተቻለን አገልግሎቱን ለመውሰድ ፈቃደኞች
ልንሆን እንደሚገባ ጴጥሮስ ይመክራል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡-- 1ጴጥ. 5:3፣ ማቴ. 20:24–28፡፡ በጥቅሶቹ የምናገኛቸው
አንገብጋቢ የክርስትና መሪነት መርኅዎች ምንድን ናቸው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
በ1ጴጥ. 5፡3 በግሪክኛው katakurieuontes የሚል የቀረበ ቁልፍ ቃል እናገኛለን፡፡
ይህን ቃል በተመሳሳይ በማቴ. 20፡25 የምናገኝ ሲሆን--በሌሎች ላይ ማለትም
“በላያቸው በመሠልጠን” ወይም “ጌቶች” በመሆን በሚል ቀርቦአል፡፡ ከዚህ አኳያ
ሐዋርያው በ1ጴጥ. 5.3 ለሽማግሌዎች የሰጠው መምሪያ “ኃላፊነታችሁን በአማኞች
ላይ እየሠለጠናችሁ ጌቶቻቸው ለመሆን አትጠቀሙበት” የሚል አንደምታ አለው፡፡
በተጨማሪ ሃሳቡ የሱስ በማቴ. 20፡25 የተናገረውን ያንጸባርቃል፡፡
በማቴ. 20፡20-23 የምናነበው መልእክት የሱስ በማቴ. 20፡24-28 የተናገረውን
ዐውደ ሃሳብ ይሰጠናል፡፡ የያዕቆብና የዮሐንስ እናት ወደ የሱስ ቀርባ በመንግሥቱ
ሲገለጥ አንደኛው ልጇ በቀኙ ሌላው ደግሞ በግራው እንዲቀመጡ ይፈቅድ ዘንድ
ጠይቃው ነበር፡፡
“የሱስም ከወንድሞቻቸው የተለየ አስተያየት እንዲያደርግላቸው ባሳዩት የራስ
ወዳድነት አስተሳሰባቸው ከመገሰጽ ተቆጥቦ በርኅራኄ አነጋገራቸው፡፡ በልባቸው
ውስጥ የነበረውን ስሜት ስለሚያነብ ስለ እርሱ የነበራቸውን የፍቅር ጥልቀት
ያውቃል፡፡ ምንም እንኳ ሰብዓዊ ፍጡራን በመሆናቸው ምክንያት ፍቅራቸው
በዓለማዊነት ቢጎድፍም ለእርሱ የነበራቸው ፍቅር ከራሱ ከየሱስ ከአዳኝ ፍቅር
የፈለቀ እንጂ ተራ ሰብዓዊ ፍቅር አልነበረም፡፡ ስለዚህ የሱስ እንዲህ ያለውን ፍቅር
ጥልቀት ያለውና የጠራ እንዲሆን ያደርጋል እንጂ በመገሰጽ አያቀዘቅዘውም”--
የዘመናት ምኞት ገጽ 563-564፡፡
የሱስ ሰማያዊው ክብር በእርሱ ሳይሆን በአብ እንደሚሰጥ ሲያብራራ ይታያል፡፡
በእርሱ መንግሥትና በአሕዛብ መንግሥታት መካከል ያለውን ቁልፍ ልዩነት
ማብራራቱን የቀጠለው የሱስ፤ በንጉሥነቱ የሚተዳደረው የመንግሥቱ ባለሟል
መሆን የሚሹ ሁሉ እርሱ አገልጋይ እንደሆነ እነርሱም የእርሱን ፈለግ መከተል
ይጠበቅባቸዋል “ ‘የሰው ልጅ እንዲያገለግሉት ሳይሆን፣ ለማገልገልና ነፍሱንም
ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት መጥቶአልና’ ” (ማቴ. 20:28)፡፡ የቤተ ክርስቲያን
መሪዎች የሥጋን ፈቃድ ክደው ራሳቸውን ለእርሱ አሳልፈው እንዲሰጡና በየሱስ
የታየው ማንነት በተመሳሳይ በእነርሱም እንዲገለጥ ጴጥሮስ ጥሪውን የቀርባል፡፡
ጳውሎስ በፊልጵ. 2፡4-8 የጻፈው--ከጴጥሮስ መልእክት ጋር ስምሙ የሆነው
እንዴት ነው? በጥቅሶቹ--እንድናደርግ የተጠራንባቸውን ነገሮች ማድረግ
የምንችለው እንዴት ነው?
ጴጥሮስ የኖረበት የጥንቱ ዓለም ማኅበረሰብ አብልጦ በመደብ የተከፋፈለ ነበር፡፡
ሥልጣኑን በመዳፋቸው ካረጉት የሥርዓቱ ቁንጮዎች በታች ገባሪው የኅብረተሰብ
ክፍል የሚገኝ ሲሆን--ከዚያ ወርዶ በመጨረሻው ወለል ባሪያ በመባል ይታወቅ
የነበረው እጅግ ዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል ይገኝ ነበር፡፡ እጅግ ዝቅ ያለው
ማኅበረሰብ ከፍ ብሎ ለሚገኘው መደብ ያሳይ የነበረው ፍጹም መሽቆጥቆጥ
የደረጃው መገለጫ ነበር፡፡ አዲስ ኪዳን የተጻፈበት የግሪክ ቋንቋ ይህንን ትህትና--
ራስን ዝቅ ማድረግ፣ እኔነትን እንደ ምናምንቴ መቁጠር፣ የገዛ ማንነትን እንደ ደካማ
ማየት የሚሉ ፍቺዎችን ይዞአል፡፡ ሰዎችን በማኅበረሰቡ ውስጥ ካላቸው ሥልጣንና
ማዕረግ በተለየ ይገልጻቸዋል፡፡ ከክርስትናና ከአይሁድ እምነት ውጪ ለሚገኘው
ዓለም--ትሑት የተሰኘው ቃል ዝምድናው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው
የኅብረተሰብ ክፍል ጋር በመሆኑ የገዢውን መደብ ወይም የነፃውን ሕዝብ ባህሪ
አይወክልም፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡-- 1ጴጥ. 5፡5-7፡፡ ጴጥሮስ መልእክቱን በቀጥታ የላከለትን
ማኅበረሰብና የዚያን ዘመኑን ተደራሲ ከግምት ውስጥ ስናስገባ ምን ዓይነት
አስገራሚ ሃሳብ ተንጸባርቋል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጴጥሮስ ከኖረበት ዘመንና ባህል አኳያ ሲታይ--ትህትና ቀደም ባለው የመጽሐፍ
ቅዱስ መልእክት ለየት ባለ ብርሃን መቅረቡን መመልከት ይቻላል፡፡ ጴጥሮስ በያዕ.
4፡6 የተጠቀሰውንና በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ምሳ. 3፡34 የሚገኘውን ይጠቅሳል፡፡
የትዕቢተኞችን እብሪት መሻርና እነርሱን ማዋረድ ከእግዚአብሔር ተግባራት አንዱ
እንደ ነበር በብሉይ ኪዳን እናያለን (ኢሳ. 13:11፣ 23:9፣ ኢዮብ 40:11)፡፡
አንድ ሰው በእግዚአብሔር ፊት በትህትና ሊቀርብ የተገባ ነው፡፡ “ስለዚህ እርሱ
በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን
ዝቅ አድርጉ” (1ጴጥ. 5:6)፡፡ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት ብቻ
ሳንወሰን እርስ በርሳችንም በአንተ ትብስ--አንቺ ትብሽ መንፈስ ራሳችንን ዝቅ
አድርገን በትህትና እንድንመላለስ ተጠርተናል (1ጴጥ. 5፡5)፡፡ ክርስቲያኖችም ሆንን
የክርስትና እምነት መሪዎች ኃጢአተኞች መሆናችንንና በእግዚአብሔር ጸጋ
መዳናችንን ጠንቅቀን እንረዳለን፡፡ ይህ ደግሞ ሁላችንም እኩል መሆናችንንና
ራሳችንን በመስቀሉ ፊት ዝቅ ማድረግ እንደሚኖርብን ግንዛቤ ይሰጠናል፡፡ ይህ
ትህትና በተለይ አገልግሎታችንን የሚጠባበቁ ወገኖችን አማክሎ፤ ከወንድም
እህቶች ጋር ባለን ግንኙነት ጎልቶ መታየቱ የግድ ይሆናል፡፡ ሰዎች ሰማይንና
ምድርን በፈጠረው አምላክ ፊት ራሳቸውን ትሁት አድርገው ለማቅረብ
መሞከራቸው እሙን እንደመሆኑ--በሥልጣንም ሆነ በደረጃ ከእኛ “ከፍ” ያሉትን
ተሸቆጥቁጠን ለመቅረብ እምብዛም አንቸገርም፡፡ ሆኖም እውነተኛው ፈተና ያለው
ከእኛ “ዝቅ” ላሉ ወገኖች ተገቢውን ትህትና ማሳየቱ ላይ ነው፡፡ ጴጥሮስ እየተናገረ
ያለው ስለዚህኛው የትህትና ዓይነት ነው፡፡
ሁሌም በትህትና እንድንመላለስ የሚረዳን በመስቀሉ የተገለጠው ምስጢር ምንድን
ነው?
ጴጥሮስ በስደት ታሪካዊ ዳራ ዙሪያ የጻፈውን መልእክት ቀደም ብለን ለመመልከት
ሞክረናል፡፡ ሰብዓዊው ፍጡር ከፍጹም ሰላማዊ ስፍራ በተቃራኒ ከሚገኘው ታላቅ
ተቃርኖ ውስጥ በመመላለሱ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ የጻፈው ይህ መልእክት ተጨባጭ
እንጂ ሃሳባዊ አለመሆኑን ለአንባቢዎቹ አሳይቶአል፡፡ ዛሬ በእኛ ዘመን ለመድረስ
ጊዜው ባይመስልም--በጥንት አማኞች የደረሰውን ስደት ግን ገልጦልናል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡-- 1ጴጥ. 5:8–10፣ ራእ. 12:7–9፡፡ ጥቅሶቹ ስለ ክፉው
መጸነስና ሰይጣን በዓለማችን እየሠራ ስላለው ሥራ ምን ያስተምሩናል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ በመልካምና በክፉ ኃይላት መካከል እየተካሄደ ባለው
ውጊያ ክርስቲያኖች ያላቸውን ሚና ይገልጣል፡፡ የመልካም ኃይላት የእግዚአብሔር
ቃል በሆነው የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ የሱስ ይመራሉ (ራእ. 19፡13፣16)፡፡
የክፉ ኃይላት ደግሞ ሰይጣን ተብሎ በሚጠራውና በዘንዶ በተመሰለው ዲያብሎስ
ይመራሉ (ራእ. 12፡7-9፣ 20፡7-8)፡፡ ምንም እንኳ አንዳንድ ክርስቲያኖችን ጨምሮ
ታዋቂ የመገናኛ ብዙሃን የሰይጣንን ህልውና ባይቀበሉም--ሰይጣን ሁሌም በክፉ
ውጥኖች ብቻ የተሞላ ብርቱ ባላንጣችን መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ሆኖም
መልካም የምስራች እንዳለን አምላካዊው ቃል ይነግረናል--በስተመጨረሻ ሰይጣን
ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይጠፋል! (ራእ. 20፡9-10)፡፡
ዲያብሎስ የሚወክለው ክፉ
የሚያስከትለውን አደጋ ጴጥሮስ አሳንሶ
አይመለከተውም፡፡ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ ወዲህ
ወዲያ መዟዟሩን ለአፍታም መንዘንጋት የለብንም (1ጴጥ. 5፡10)፡፡ ዲያብሎስ ምን
ያህል ኃይል እንዳለው አንባቢዎቹ እየደረሰባቸው ካለው ፈተና አኳያ መመልከት
እንደሚችሉ ጴጥሮስ አጽንኦት ይሰጣል፡፡ ሆኖም ይህ ሁሉ መከራ ክርስቶስ
በዘላለማዊው ክብር ሲገለጥ ያከትማል (1ጴጥ. 5፡10)፡፡
ሐዋርያው በ1ጴጥ. 5፡10 ምን እያለን ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ምንም እንኳ በእነዚያ ክርስቲያን ወገኖች ላይ የደረሰውን መከራ ዓይነትና ተፈጥሮ
በትክክል ለይተን ማወቅ ባንችልም ጴጥሮስ የሰጠውን ተስፋ ግን መመልከት
እንችላለን፡፡ ራሱን ዲያብሎስ ጨምሮ ከእርሱ እየሰነዘረ ያለው እልህ አስጨራሽ
ውጊያም ሆነ መከራ በተጨባጭ ያለና የሚስተዋል ነው፡፡ በጸጋ የተሞላው አምላክ
ዲያብሎስን አሸንፎአል፡፡ ስለዚህ የቱንም ዓይነት መከራ ብንቀበል--እስከ ሞት
በታማኝነታችን ጸንተን እስከ ቆምን ድረስ፤ ምስጋና ለየሱስ ይሁንና አሸናፊነታችን
የተረጋገጠ ነው (ዕብ. 11፡13-16)፡፡
በመንገዳችን ምንም ቢገጥመን--እስከ መጨረሻው እምነታችንን በጽናት አጥብቀን
መያዝ የምንማረው እንዴት ነው?
የየሱስን አገልጋይነት ከመሪነት ጋር በአንድ
አጣምሮ የያዘውን ታላቅ ምሳሌ በመጨረሻው የጌታ ራት ሥነ ሥርዓት ላይ
መመልከት ይቻላል፡፡ በዚያን ጊዜ ማን እንደ ነበር (የእግዚአብሔር ልጅነቱን)
ጠንቅቆ ያውቅ የነበረው የሱስ ወደ አብ የመመለሻው ጊዜ ተቃርቦ ነበር (ዮሐ. 13፡1)
፡፡ ከጌታ ራት በኋላ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ እንዲህ አላቸው፡ “እንግዲህ
እኔ ጌታችሁና መምህራችሁ ሁኜ ሳለሁ እግራችሁን አጠብሁ፣ እናንተም እንደዚሁ
እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባችኋል፡፡ እኔ እንዳደረግሁላችሁ
እናንተም እንዲሁ እንድታደርጉ ትቼላችኋለሁ” (ዮሐ. 13:14-15)፡፡ በየጊዜው አንዱ
የሌላውን እግር የሚያጥብበት ይህ ምሳሌ የተተወበት ምክንያት በየሱስ መንግሥት
መሪ ለመሆን የሚሻ ራሱን ዝቅ አድርጎ የአገልጋይነትን ስፍራ ሊወስድ የተገባ
መሆኑን የየሱስ ተከታዮች እንዲያስታውሱ ለማድረግ ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ
በተለይ የሱስ ማን እንደ ነበር በተሻለ ማስተዋል ካገኙ በኋላ ይህን ራስን ዝቅ
የማድረግ ሥርዓት በጌታቸው ቦታ ሆነው ቀሪ ህይወታቸውን ሲተገብሩ መኖራቸው
አያጠራጥርም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች በሌሎች ላይ በመሠልጠን ፋንታ
ትህትና እንዲላበሱ ጥሪ ባደረገው በጴጥሮስ አእምሮ ውስጥ ይህ እንደ ነበር መካድ
አይቻልም፡፡
“ክርስቶስቶስ ሰማያዊ አካላትን ባስደነቀ ትህትና ሰብዓዊውን ተፈጥሮ ለመውሰድ
ፈቃደኛ ሆነ፡፡ እርሱ ሰብዓዊውን ተፈጥሮ ለመውሰድ ያሳየው ቁርጠኝነት በከበረ
ዘላለማዊ ማንነቱ ላይ የሚያመጣው ውርደት አልነበረም፡፡ ሰብዓዊው ቤተሰብ
የእግዚአብሔር ወንዶችና ሴቶች ልጆች ተብሎ እንዲጠራ የሚያስችለው የግብረገብ
ልዕልና ባለቤት ይሆን ዘንድ--ክርስቶስ ሰብዓዊውን ፍጡር ባለበት ሁናቴ
ለመገናኘት ሲል ንጉሣዊ መጎናጸፊያውን፣ አክሊሉንና አዛኝነቱን ወደጎን ብሎ
መለኮትን ከሰብዓዊነት ጋር ለብሶ ወደዚህ ምድር የመምጣቱን ሁኔታ ዐይኖቻችንን
ከፍተን ማስተዋል ይኖርብናል፡፡
“እርሱ እንደ ተመላለሰ ሊመላለስ’ የሚገባው አማኝ--የክርስቶስ ህይወት መለያ
የነበረው የዋህነትና ትህትና መገለጫው ይሆናል”— Ellen G. White, Sons and
Daughters of God, p. 81
የሱስ ሰይጣንን ፊት ለፊት በመቃወም አገልግሎቱን ጀመረ፡፡ ለአርባ ቀናት
ምግብ ሳይቀምስ በጾም ጸሎት ብቻ የከረመው የሱስ አምላካዊውን ቃል
እየጠቀሰ የዲያብሎስን ፈተና መቋቋም ቻለ (ማቴ. 4:1–11፣ ማር. 1:12-13፣
ሉቃስ 4:1–13)፡፡ እኛም በህይወታችን ዲያብሎስን መቋቋም እንደምንችል
አስመልክቶ መልእክቱ ምን ይነግረናል?
ለሌሎች እውነተኛ ትህትና ስለ ማሳየት የተመለከቷቸው ምሳሌዎች ምን
ይመስላሉ? ከምሳሌዎቹ ምን ይማራሉ?
በዚህ ሳምንት ከጴጥሮስ መልእክት ካገኘናቸው ትምህርቶች መሃል
ከመልካም ክርስቲያን የሚጠበቁ የመሪነት ክህሎቶች የትኞቹ ናቸው?
እነዚህ ክህሎቶች በዓለማዊ የሥራ መሪዎች መሃል እንደ መልካም ጎን
የሚቆጠሩት እንዴት ነው? ከዓለማዊ የመሪነት ዘይቤ የሚለዩትስ በምን
መልኩ ነው?
ሰይጣን የተሰኘው መጠሪያ በሰብዓዊው ተፈጥሮ ውስጥ ለሚገኘውን ክፉ
ሃሳብ ተሰጠ ስያሜ እንጂ እንዲህ የሚባል ፍጡር የለም--ለሚለው
አመለካከት የሚሰጡት ምላሽ ምንድን ነው?