ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ያንብቡ፡ 1ጴጥ. 1:6፣ 3:13–22፣ 2ጢሞቴ. 3:12፣ 1ጴጥ. 4:12–14፣ ራእ. 12:17፣ 1ጴጥ. 4:17–19፡፡
የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - “የተጠራችሁትም ለዚሁ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌ ሊተውላችሁ ነው” (1ጴጥ. 2:21)፡፡
በ መጀመሪያዎቹ ምዕተ ዓመታት በክርስትና እምነት ላይ የደረሰው ስደት
የዓለም ታሪክ አካል ሆኖ በታሪክ ድርሳናት ሰፍሯል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም
ቢሆን--በተለይ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ቤተ ክርስቲያንን እየጠበቃት
ስለ ነበረው ነገር በውልብታም ቢሆን የሚሰጠው ፍንጭ አለ፡፡ ስደት ሥቃይ
ማስከተሉ እሙን ነው፡፡ በመሆኑም ይህ እውነታ ጴጥሮስ መልእክቱን ለጻፈላቸው
ክርስቲያኖች ሁሉ በተጨባጭ የሚስተዋል የህይወታቸው አካል ነው፡፡ ጴጥሮስ
በመጀመሪያው ምዕራፍ መልእክቱ የሚከተለውን አስፍሯል “አሁን በብዙ ዓይነት
ፈተና ወስጥ ሆናችሁ ለጥቂት ጊዜ መከራን ብትቀበሉም እንኳ በዚህ እጅግ ደስ
ይላችኋል፡፡ እነዚህ ነገሮች በእናንተ ላይ የደረሱት፣ በእሳት ተፈትኖ ቢጠራም፣ ጠፊ
ከሆነው ወርቅ ይልቅ እጅግ የከበረው እምነታችሁ እውነተኛ መሆኑ እንዲረጋገጥና
ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን ክብርንና፣ ውዳሴን እንዲያስገኝላቸሁ
ነው” (1ጴጥ. 1:6-7)፡፡ በተጨማሪ ጴጥሮስ በመጀመሪያው መልእክቱ መደምደሚያ
አካባቢ ተመሳሳይ ሃሳብ ያነሳል “በክርስቶስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ
ሁሉ አምላክ፣ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እርሱ ራሱ መልሶ
ያበረታታችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል” (1ጴጥ. 5:10)፡፡
ጥቂት ምዕራፎች ባሉት የጴጥሮስ የመጀመሪያ መልእክት፤ አማኞች የክርስቶስ
በመሆናቸው ሊደስባቸው ስለሚችል ሥቃይ የሚያወሱ ከሦስት ያላነሱ ዘርዘር ያሉ
ጽንሰ ሃሳቦች ቀርበዋል (1ጴጥ. 2:18–25፣ 3:13–21፣ 4:12–19)፡፡ በአማኞች ላይ
ሥቃይ ከሚያስከትሉ ምክንያቶች በዋናነት የሚጠቀሰው--የአንደኛ ጴጥሮስ
መልእክት ጭብጥ የሆነው ስደት ነው፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡-- 1ጴጥ. 1፡6፣ 5፡10፡፡ ጴጥሮስ ስለ ምን እየተናገረ ነው?
አንባቢዎቹ እየደሰባቸው ለነበረው ችግር እንዴት ምላሽ መስጠት
እንደሚኖርባቸው የነገረበት መንገድ ምን ይመስላል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ክፍለ ዘመኖች ክርስቲያን መሆን ለአስከፊ ሞት ይዳርግ
ነበር፡፡ ለዚያን ዘመኑ የሮም ንጉሥ ትራጃን የተጻፈ ደብዳቤ የመጀመሪያዎቹ
ክርስቲያኖች ደኅንነት ምን ያህል የማያስተማምን እንደ ነበር ያሳያል፡፡ ደብዳቤውን
የጻፈው ፕሊኒ (111 – 113 ዓ.ም.) ሲሆን በወቅቱ ይህ ሰው በ1ጴጥ. 1፡1 የተጠቀሱት
ሁለቱ ክፍለ አገሮች--የጳንጦስ እና የቢታንያ ገዢ ነበር፡፡
ክርስቲያን በመሆናቸው ክስ የተመሰረተባቸው ሰዎች ጉዳይ ሊያገኝ ስለሚገባው
ውሳኔ ምክር ለመጠየቅ ፕሊኒ ወደ ትራጃን ደብዳቤ ጽፎ ነበር፡፡ የክርስትናን
እምነት አጥብቀው በመያዝ የጸኑትን በሞት እንደ ቀጣ ፕሊኒ በመልእክቱ
አብራርቷል፡፡ ቀደም ሲል የክርስትና እምነት ተከታዮች የነበሩ አሁን ግን እምነቱን
የተዉ መኖራቸውንም ገልጾአል፡፡ እነዚህ ሰዎች ትራጃን በመባል ይታወቅ ለነበረው
ጣዖትና ለሌሎች አማልክት የዕጣን መስዋዕት አቅርበው የሱስን በመራገም
ታማኝነታቸውን እንዲያሳዩ ፕሊኒ ፈቅዶላቸው ነበር፡፡
በህይወት ያለውን ንጉሥ እንደ አማልክት ማምለክ በሮም ግዛት እምብዛም
የተለመደ ባይሆንም--የጴጥሮስ የጀመሪያው መልእክት የተላከበት የምስራቃዊው
የሮም ግዛት ነገሥታት ግን ይህን ይፈቅዱ ነበር፡፡ አልፎ አልፎ በራሳቸው የተሰየሙ
ቤተ አምልኮዎች እንዲቋቋሙም ያበረታቱ ነበር፡፡ ከእዚህ ቤተ አምልኮዎች
አንዳንዶቹ የራሳቸው ካህናትና መሠዊያዎች ነበሯቸው፡፡ ፕሊኒ የቆየውን የኤሽያ
ማይኖር ልምድ በመከተል ክርስቲያኖች ለንጉሠ ነገሥቱ በቆመው ሃውልት ፊት
የዕጣን መሥዋዕትና አምልኮ በማቅረብ ታማኝነታቸውን እንዲያሳዩ ያደርግ ነበር፡፡
በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች የክርስትና እምነት ተከታይ
በመሆናቸው ብቻ አስጊ ሁናቴ ላይ ወድቀው ነበር፡፡ ይህ አደጋ በተጨባጭ የታየው
በተለይ ሮማን ይገዛ በነበረው ኔሮ (54 – 68 ዓ.ም) እና ዶሚቲያን (81 – 96
ዓ.ም.) ዘመን ነበር፡፡
በ1ጴጥ. የተመለከተው ስደት አብልጦ የሚያሳየው የአንድን አካባቢ ሁኔታ ነው፡፡
ጴጥሮስ ስደትን አስመልክቶ በመልእክቱ የሚጠቅሳቸው ተለይተው የተቀመጡ
ምሳሌዎች ጥቂት ቢሆኑም ምናልባት የሐሰት ውንጀላዎችን (1ጴጥ. 2፡12)
ነቀፌታንና ስድብን (1ጴጥ. 3፡9፣ 4፡14) በተጨማሪ ሊያካትቱ ይችላሉ፡፡ ፈተናዎቹ
ጥብቅና ኃይለኛ ቢሆኑም እስራትና ሞት--ቢያንስ በዚያ ዘመን አገር አቀፍ ገጽታ
አልያዘም ነበር፡፡ በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት እንደ ክርስቲያን መኖር በአማኞች
ላይ ሊያመጣ ይችል የነበረው መዘዝ ሰፊና በእምነታቸው የተነሳ ብዙ ሥቃይ
የተቀበሉበት ነው፡፡ ጴጥሮስ በዚህ ዙሪያ የነበረውን ብርቱ ስጋት በመልእክቱ
አስፍሯል፡፡
በ1ጴጥ. 3፡13-22 መሰረት ክርስቲያኖች በእምነታቸው ምክንያት መከራ
ለሚያደርሱባቸው ሊሰጡ የሚገባው ምላሽ ምን ሊሆን ገባል? በየሱስና አማኞች
በእምነታቸው የተነሳ በደረሰባቸው መከራ መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጴጥሮስ “ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራ ቢደርስባችሁ ብፁዓን ናችሁ” (1ጴጥ.
3:14) በሚል የጻፈው “ ‘ስለ ጽድቅ ብለው የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው’ ” (ማቴ.
5:10) የሚሉትን የየሱስ ቃላት ያስተጋባሉ፡፡ በመቀጠል ክርስቲያኖች ጥቃት
የሚሰነዝሩባቸውን ሊፈሩ እንደማይገባ ይልቁንም ክርስቶስን ጌታ አድርገው
በልባቸው እንዲቀድሱ ይናገራል (1ጴጥ. 3፡15)፡፡ የሱስን በዚህ መልኩ በልባቸው
ሲያጸኑ--የሚቃወሟቸው የሚሰነዝሩባቸውን ጥቃት እንዳይፈሩና መቋቋም
እንዲችሉ ይረዳቸዋል፡፡
በመቀጠል ክርስቲያኖች በልባቸው ውስጥ ያለውን ተስፋ ለሌሎች መግለጽ መቻል
እንደሚኖርባቸውና ይህንንም በትህትናና በአክብሮት ሊያደርጉ እንደሚገባ ይናገራል
(1ጴጥ. 3፡15-16)፡፡
ክርስቲያኖች ሌሎች እነርሱን ሊከሱ የሚችሉባቸው ምንም ቀዳዳ ሊተዉ
እንደማይገባ ጴጥሮስ አበክሮ ይመክራል፡፡ ሁሌም ህሊናቸውን በንጽህና ሊጠብቁ
የተገባ ነው (1ጴጥ. 3፡16)፡፡ እንከን የለሹ የክርስቲያኖች ህይወት መልሶ ከሳሾችን
ውርደት ላይ ስለሚጥላቸው ይህ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ክፉ መሥራት ከመከራ
ውጪ የሚያስገኘው ሽልማት አለመኖሩ ዕሙን ነው (1ጴጥ. 3፡17)፡፡ ነገር ግን
መልካም እያደረጉ ለትክክለኛው ነገር መከራ መቀበል ፋይዳው የጎላ ለውጥ
ማምጣት ይችላል (1ጴጥ. 3፡17)፡፡
ጴጥሮስ በመቀጠል የየሱስን ምሳሌ ጥቅም ላይ ሲያውል ይታያል፡፡ ክርስቶስ ስለ
ጽድቅ መከራ ተቀበለ፡፡ የገዛ ህይወቱ ቅድስናና ንጽህና እርሱን ይጠሉ ለነበሩ
የዘወትር ግሳጼ ነበር፡፡ በጎውንና ትክክለኛውን ነገር በማድረጉ መከራ የተቀበለ ሰው
ቢኖር--የሱስ ነበር፡፡
ሆኖም ይህ በእርሱ ላይ የደረሰ መከራ ብቸኛውን መዳኛ ይዞ ከተፍ አለ፡፡ በእርሱ
የሚያምኑ ሁሉ የዘላለም ህይወት ተስፋ ይኖራቸው ዘንድ እነሆ በኃጢአተኞች
ምትክ እርሱ ሞተ (“ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ” (1ጴጥ. 3:18)፡፡
ስህተት በመሥራትዎ ሳይሆን ትክክለኛውን ነገር በማድረጎ መከራ ደርሶቦት
ያውቃል? ክርስቲያን ስለ መሆንና የክርስቶስን ጸባይ ስለ ማንጸባረቅ ከዚህ
ተሞክሮው ምን ተማሩ?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ጴጥ. 4:12–14፡፡ ጴጥሮስ ክርስቲያኖች በሚደርስባቸው
መከራ ሊደነቁ እንደማይገባ አስመልክቶ ምን ይላል? 2ጢሞቴ. 3፡12፣ ዮሐ.
15፡18፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
በክርስትና እምነት ምክንያት ስደት መቀበል የክርስቶስ መከራ አካል መሆን ነው--
ሲል ጴጥሮስ በግልጽ ይናገራል፡፡ ይህ ጉዳይ እንደ እንግዳ ነገር ወይም ዱብዕዳ
መቆጠር የለበትም፡፡ “በእርግጥም በክርስቶስ ኢየሱስ በእውነተኛ መንፈሳዊ
ሕይወት መኖር የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ” (2ጢሞቴ. 3:12)፡፡ የሱስም ቢሆን
ተከታዮቹ ሊደርስባቸው ስለሚችሉ ነገሮች አስጠንቅቋቸዋል፡ “ ‘በዚያን ጊዜ
ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፣ ይገድሏችኋል፣ በስሜ ምክንያት በሕዝብ ሁሉ
ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፡፡ በዚያን ጊዜ ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ እርስ በርስ
አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ ይጠላላሉም’ ” (ማቴ. 24:9-10)፡፡
“በክርስቶስ ኢየሱስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሚመላለሱ ሁሉ ላይ ይህ
ይደርሳል፡፡ በክርስቶስ መንፈስ የተሞሉትን ስደትና ነቀፋ ይጠብቃቸዋል፡፡ ምንም
እንኳ የስደቱ ዓይነትና ባህሪ እንደ ጊዜው ሁናቴ ተለዋዋጭ ሊሆን ቢችልም--
ከአቤል አንስቶ በጌታ የተመረጡትን የሰየፈው መንፈስ የሚከተለው መርኅ ያው
አንድ ዓይነት ነው”—The Acts of the Apostles, p. 576.
በራእ. 12፡17 የቀረበው መልእክት በመጨረሻው ዘመን ክርስቲያኖች ላይ
ስለሚደርሰው ስደት ምን ይላል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጴጥሮስ ክርስቲያኖች የሚጋፈጡትንና “በእሳት መፈተን” ሲል አንባቢዎቹን
የሚያስጠነቅቀው ስደት፤ ሁሌም ከታማኝ ክርስቲያኖችን የማይለይ ተጨባጭ
እውነታ መሆኑ ብዙም አጠያያቂ አይደለም፡፡ እሳት--መልካም ዘይቤአዊ አነጋገር
ነው፡፡ እሳት አውዳሚም ቢሆን ኃጢአትን የማንጻት ባህሪ አለው፡፡ ሸማ በየፈርጁ
ይለበሳል እንዲሉ እሳትም ቤት ሊያቃጥል ወይም ብርና ወርቅ ሊያነጥር ይችላል፡፡
አንድ ሰው ሆነ ብሎ ስደት ማምጣት ባይኖርበትም እግዚአብሔር ግን ከዚያ ውስጥ
በጎውን ማምጣት ይችላል፡፡ ጴጥሮስ በዚህ ዙሪያ የሚከተለውን ምክር ይለግሳል፡
ስደት መጥፎ ቢሆንም የክርስትና እምነትን ተከትሎ ሊመጣ እንደማይችል እንግዳ
ክስተት አትቁጠሩት፡፡ በእምነት ገስግሱ፡፡
ስለ እምነታቸው መከራ እየተቀበሉ ያሉ ወገኖችን ሊያነቃቃና ሊያበታ የሚችል ምን
ዓይነት ነገር ማድረግ እንችላለን?
ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ 1ጴጥ. 4:17–19 ኢሳ. 10:11-12፣ ሚልክ. 3:1–6፡፡ በጋራ
የያዟቸው መልእክቶች ምን ምንድን ናቸው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
የፍርድ ሂደት በእግዚአብሔር ሕዝቦች እንደሚጀምር ሆኖ በጥቅሶቹ ቀርቦአል፡፡
እንደውም ጴጥሮስ በአንባቢዎቹ ላይ የሚደርሰውን መከራ ከእግዚአብሔር ፍርድ
ጋር አያይዞ ሲያቀርብ ይስተዋላል፡፡ ለእርሱ--መልእክቱን የጻፈላቸው ክርስቲያን
አንባቢዎቹ ላይ የሚደርሰውና በእግዚአብሔር ቤት የሚጀምረው መከራ
ከእግዚአብሔር ፍርድ ያነሰ አይደለም “ስለዚህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራ
የሚቀበሉ ሁሉ ነፍሳቸውን ለታመነው ፈጣሪ ዐደራ ሰጥተው መልካም
ማድረጋቸውን ይቀጥሉ” (1ጴጥ. 4:19)፡፡
ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡ ሉቃ.18፡1-8፡፡ መልእክቱ አምላካዊውን ፍርድ
እንድናስተውል የሚረዳን እንዴት ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን ፍርድ ሰዎች አጥብቀው ይሹት የነበረ ጉዳይ
ነው፡፡ በሉቃ. 18፡1-15 ፍርድ ለማግኘት ያለመታከት ልመናዋን ያቀረበችው ምስኪን
መበለት ታሪክ ለዚህ ግዙፍ ማሳያ መሆን ይችላል፡፡ መበለቲቱ ጉዳይዋን
የሚያይላት ዳኛ ማግኘት ከቻለች እንደምትረታና እንደሚፈረድላት እርግጠኛ
ነበረች፡፡ ምንም እንኳ ጉዳይዋ ተሰሚነት እንዲያገኝ የሚያስችል የገንዘብ አቅምም
ሆነ ሥልጣን ባይኖራትም በመጨረሻ ዳኛው እንዲሰማትና በደሏን አይቶ አጥብቃ
የሻተችውን ፍትሕ እንዲሰጣት ታደርጋለች፡፡ የሱስ እንዲህ ይላል፡ “እግዚአብሔር
ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን?” (Luke 18:7)፡፡
ኃጢአት ክፉ የሆነውን ሃሳብ ወደዚህ ምድር አመጣ፡፡ እግዚአብሔር
የተጣመመውን ዳግም ያቃና ዘንድ በዘመናት በዚህ ምድር የተመላለሱ
የእግዚአብሔር ሕዝቦች ሲጠባበቁ ኖረዋል፡፡
“ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተን የማይፈራ፣ ስምህን የማያከብርስ ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ
ነህና፡፡ የጽድቅ ሥራህ ስለ ተገለጠ፣ ሕዝቦች ሁሉ ይመጣሉ፤ በፊትህም ይሰግዳሉ’
” (ራእ. 15:4)፡፡
በምድር ላይ ተገቢውን ቅጣት ሳይቀበል ዛሬ ድረስ ተንሰራፍቶ ስለሚገኘው ክፋት
አሰብ ያድርጉ፡፡ የፍትሕና የአምላካዊው ጻድቅ ፍርድ ጽንሰ ሃሳብ እንደ ክርስቲያን
ለእኛ አንገብጋቢ የሆነው ለምንድን ነው? ፍትሕ እንደሚሰፍን ከተሰጠው አምላካዊ
ቃል የሚያገኙት ተስፋ ምን ይመስላል?
ጴጥሮስ ስለ እምነታቸው መከራ ለደረሰባቸው ወገኖች የጻፈውን መልእክት
ተመልክተናል፡፡ ከክርስትና እምነት ታሪክ መቃኘት እንደምንችለው በወቅቱ ነገሮች
እየከፉ ከመሄድ ውጪ የመሻሻል ባህሪ አይታይባቸውም ነበር፡፡ በእነዚያ ተከታታይ
ዓመታት አያሌ ክርስቲያኖች በጴጥሮስ መልእክት መጽናናትና መበረታታት
ማግኘታቸው እንደ ተጠበቀ ሆኖ--መልእክቱ የዚህንም ዘመን አማኞች
እንደሚያጽናና በእርግኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ለመሆኑ በምድር መከራ ለምን
ተፈቀደ? በእርግጥ ጥያቄው ለዘመናት በሰው ልጆች አእምሮ ሲመላለስ የኖረ--
ዕድሜ ጠገብ የሚሉት ዓይነት ነው፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀደምት መጽሐፎች
መካከል በግንባር ቀደም የሚጠቀሰው የመጽሐፈ ኢዮብ መልእት--ቁልፍ የመከራ
ጭብጦችን ይዞአል፡፡ እንደ የሱስ ሁሉ “ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ወንጀለኛ
ወይም በሰው ነገር ጣልቃ ገቢ” ሳይሆን (1ጴጥ. 4:15) መከራን የተቀበለ ሰው ቢኖር
ኢዮብ ነው፡፡ “ ‘አገልጋዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ
ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን፣ እግዚአብሔርን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ሰው የለም’ ” (ኢዮ.
1:8) ብሎ እግዚአብሔር ስለ ኢዮብ መመስከሩን ልብ ይሏል፡፡ ይህም ሆኖ ኢዮብ
ክፉ በመሆኑ ሳይሆን መልካም ሰው በመሆኑ ብቻ ያለፈባቸውን አስቸጋሪ ጎዳናዎች
መመልከት ተገቢ ነው፡፡
በመቀጠል የቀረቡት ጥቅሶች ስለ መከራ መጠንሰስ መልስ መሆን የሚችሉት
እንዴት ነው? 1ጴጥ. 5:8፣ ራእ. 12:9፣ ራእ2:10፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
መከራ የሚደርስብን በክርስቶስና በሰይጣን መካከል ገቢራዊ እየሆነ ባለው ታላቁ
ፍልሚያ መሃል መገኘታችን ነው፡፡ ይህ ለጥያቄው አጭር መልስ መሆን ይችላል፡፡
ከዚህ ውጪ የተፈጥሮአችን አካል ለሆነው መልካምና ክፉ በተለምዶ የሚሰነዘር
ዘይቤአዊ አነጋገር አይደለም፡፡ ስለ ሰብዓዊው ፍጡር በጎና ውድመት እየተፋለሙ
ያሉ የሱስና ሰይጣን በተጨባጭ አሉ፡፡
ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡ 1ጴጥ. 4፡19፡፡ እየገጠመን ያለው ፈተና የቱንም ያህል ከባድና
አስቸጋሪ ቢሆን፤ የጴጥሮስ መልእክት እንዴት ሊረዳን ይችላል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
መከራ ሲደርስብንና በተለይ ደግሞ መከራው የመጣው ያለ ጥፋታች ሲሆን እንደ
ኢዮብ ለምን? ብለን በተደጋጋሚ መጠየቃችን ተፈጥሮአዊ ቢሆንም፤ ምላሽ ሳናገኝ
ልንቀር እንችላለን፡፡ ነገር ግን በመከራ ውስጥ ሆነንም እንኳ--ጴጥሮስ እንዳለው
ነፍሳችንን “ለታመነ ፈጣሪ” በዐደራ ሰጥተን “መልካም ማድረጋችንን” ” (1ጴጥ.
4:19) መቀጠል ይጠበቅብናል፡፡
የእግዚአብሔርን ጸባይ በግል ለይቶ ማወቅና ለእርስዎ ያለውን መልካምነትና ፍቅር
መገንዘብ አንድ ክርስቲያን--በተለይ በከራ ውስጥ ያለ ሊያስተውለው የሚገባ ወሳኝ
የእምነቱ ግብአት አይደለምን? ሰለ እግዚአብሔርን በተሻለ መማርና ፍቅሩን
በተጨባጭ ማስተዋል የምንችለው እንዴት ነው?
ተጨማሪ ሐሳብ፡ በእሁድ ጥናታችን በክርስቲያኖች ላይ ስለ ደረሰው
ስደት ተነጋግረናል፡፡ በእነዚያ ዘመኖች በመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ላይ
የደረሰውን መከራ የሚያሳየው ለንጉሡ የተጻፈ ሙሉ ምንባብ እንደሚከተለው
ቀርቦአል “... ክርስቲያኖች ናቸው ተብለው ውግዘት የደረሰባቸውን ለመመርመር
የተጠቀምኩት ዘዴ ይህን ይመስላል፡ በመጀመሪያ ክርስቲያን መሆን
አለመሆናቸውን እጠይቃቸዋለሁ፡፡ ክርስቲያን መሆናቸውን አምነው የሚቀበሉ
ከሆነ ሊደርስባቸው የሚችለውን የሞት ቅጣት በመጠቆም ጥያቄዬን በድጋሚ
ለሁለተኛ ጊዜ አቀርብላቸዋለሁ፡፡ አሁንም በዓላማቸው የሚጸኑ ከሆነ በሞት
እንዲቀጡ ትእዛዝ አስተላልፋለሁ፡፡ የእምነታቸው ተፈጥሮ ምንም ይሁን ምን
የምለውን ለመቀበል የሚቃወሙና ለመስማማት የማይሸነፉ ከሆነ ያለ ጥርጥር
የቁጣ በትር ሊያርፍባቸው እንደሚገባ ይሰማኛል፡፡
“ክርስቲያን መሆናቸውን የሚክዱትን ወይም ፈጽሞ የእምነቱ ተከታይ እንዳልነበሩ
የሚናገሩትን--እኔ ለአማልክት የማቀርበውን የልመና ቃል ደግመው እንዲሉ፣
የወይን ጠጅና የዕጣን መሥዋዕት በማቅረብ ለዚሁ ዓላማ ብዬ ላስመጣሁት
ለግርማዊነትዎ እንዲሁም ለሌሎች ጣኦታት ምስሎች አክብሮታቸውን እንዲያሳዩና
ክርስቶስን እንዲራገሙ አድርጌያለሁ፡፡ መጀመሪያ ላይ የክርስትናን ስም ይዘው
የነበሩ አንዳንዶች እምነቱን ክደዋል፡፡ ከመካከላቸው በእምነቱ ውስጥ ለሦስት
ዓመታት የቆዩና ከዚያም በላይ እስከ ሃያ አምስት ዓመታት ያስቆጠሩ ጥቂቶች
ነበሩ፡፡ ሁሉም ለግርማዊነትዎ ምስልና ለአማልክቱ በመስገድ ክርስቶስን
ረግመዋል፡፡”—Pliny Letters (London: William Heinemann, 1915), book
10:96 (vol. 2, pp. 401–403).
ጴጥሮስ በጻፈው መሳጭ መልእክት ጎልቶ መታየት የቻለው--ክርስቲያኖች
የተጋፈጡት ጉዳይ ምን ነበር? መልእክቱ በራእ. 14፡9-12 የምድር ታሪክ
መደምደሚያን አስመልክቶ ሦስተኛው መልአክ ገቢራዊ ይሆናል ከሚለው ጋር
ምን ዓይነት መመሳሰል አለው? ጉዳዩ የታላቁ ውዝግብ አካል ስለሆኑ አንዳንድ
ዐበይት ጉዳዮች ምን ይነግረናል?
“ለእግዚአብሔር ሕግ ከበሬታ የሰጡ ወገኖች በምድር ላይ ፍርድ እንደሚያመጡ
ተደርገው ተከሰሱ፡፡ ተፈጥሮን ላናወጠው፣ ምድርን በዋይታ ለሞላው መቅሰፍትና
በሰዎች መሃል ለተከሰተው ደም መፋሰስ የእግዚአብሔር ሕዝቦች እንደ መንስዔ
ታዩ፡፡ የመጨረሻውን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ የተገለጠው ኃይል ኃጥአንን ክፉኛ
በማስቆጣቱ ቁጣቸው መልእክቱን በተቀበሉ ላይ ገነፈለ፡፡ ሰይጣን ከፍተኛ
መጠላትና ስደት እንዲያደርሱባቸው አድርጎ ኃጥአንን አነሳሳ”—Ellen G. White,
The Great Controversy, pp. 614, 615. ምንም እንኳ ይህ ሁሉ ገቢራዊ
የሚሆንበትን ጊዜ ባናውቅም ነገር ግን ሁሌም እምነታችንን ተከትሎ ሊመጣ
ለሚችል ማንኛውም ተቃውሞ ዝግጁ ሆነን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
የመዘጋጃው ቁልፉ ምንድን ነው?