በጎቼን መግብ፡ 1ኛ እና 2ኛ ጴጥሮስ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2017

ከሚያዝያ 7-13

አራተኛ ትምህርት

April 15 - 21


ማኅበራዊ ግንኙነቶች



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 1ጴጥ. 2:13–23፣ 1ጴጥ. 3:1–7፣ 1ቆሮ. 7:12–16፣ ገላ. 3:27-28፣ ሐዋ. 5:27–32፣ ዘሌዋ. 19:18፡፡


የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - “ፍቅር ብዙ ኃጢአትን ይሸፍናልና ከሁሉ በላይ እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ” (1ጴጥ. 4:8)፡፡

የ ጴጥሮስ መልእክት በዘመኑ የነበሩ አንዳንድ አስቸጋሪ ማኅበራዊ ጥያቄዎችንም በማንሳት ክርስቲያኖች በጨቋኝና ለዜጎች ታማኝነት በማይኖረው መንግሥታዊ አስተዳደር ስር እንዴት መኖር እንዳለባቸው ምላሽ ይሰጣል፡፡ ለምሳሌ በአብዛኞቹ የዚያን ዘመን ክርስቲያኖች ላይ ሥቃይ ያደረሰው--የአረማዊው ሮም አስተዳደር? ጴጥሮስ ለአንባቢዎቹ እያለ የነበረው ምን ነበር? እነዚያ ቃላት ዛሬ ለእኛ ያላቸው ትርጉም ምን ይመስላል? በዘመኑ በባርነት ቀንበር ሥር ወድቀው የነበሩ ክርስቲያን አገልጋዮች አሳዳሪዎቻቸው ለሚያደርሱባቸው በደልና ኢፍትሐዊ እንግልት ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት ነበረባቸው? ምንም እንኳ የዘመናችን የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ሕጎች ከአንደኛው ምዕተ ዓመት የባሪያና የአሳዳሪ ግንኙነት ጋር ሲተያዩ የሰማይና የምድር ያህል የተራራቁ ቢሆንም--የጴጥሮስ መልእክት ለዚያን ዘመን ኢፍትሐዊ የባሪያ አሳዳሪ ጌቶች በትክክል አስተጋብቶአል ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ክርስቲያኖች ሊደርስባቸው ለሚችል ማንኛውም ዓይነት መከራ ሊከተሉ እንደሚገባ እርሱን በምሳሌ መጥቀሱ ልብ የሚነካ አቀራረብ ነው (1ጴጥ. 2፡21-24)፡፡

የክርስቶስን ፈለግ ባልና ሚስት በተለይ እንደ ኃይማኖት ባለ መሰረታዊ ነገር በመሃላቸው ልዩነት ሲኖር የትስስራቸው ገጽታ ምን ሊመስል ይገባል?

በመጨረሻ--ማኅበራዊው/ፖለቲካዊው ሥርዓት ዜጎችን በእኩል ማየት ሲሳነው፣ የሚጠበቅበትን ታማኝነት የሚያጎድልና የክርስትና እምነት ተቃዋሚ ሲሆን ክርስቲያኖች ከእንዲህ ያለው ሥርዓት ጋር ምን ዓይነት ተዛምዶ ሊኖራቸው ይገባል?

ሚያዝያ 8
16-Apr

ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት


ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በእነዚያ ጥንታዊ ዘመናት ቢሆንም፤ ለምሳሌ ለዘመናችን ገጣሚነት ካላቸው መካከል አንዱ የሆነውን--በክርስቲያኖችና በመንግሥት መካከል ሊኖር ስለሚገባ ግንኙነት ያነሳል፡፡

ይህ ጉዳይ ቁልጭ ብሎ የተቀመጠባቸው ሁናቴዎች አሉ፡፡ የፖለቲካ ኃይላትን መታዘዝ እግዚአብሔርን አለመታዘዝ የሚሆንበት ጊዜ እንደሚመጣ ራእ. 13 ይናገራል፡፡ እንዲህ ያለ ሁናቴ ሲከሰት ምርጫች ምን ሊሆን እንደሚገባ በግልጽ ተቀምጦአል (የሐሙስን ትምህርት ይመልከቱ)፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡-- 1ጴጥ. 2፡13-17፡፡ ከመንግሥት ጋር ሊኖረን ስለሚገባ ግንኙነት አስመልክቶ በጥቅሶቹ የቀረበው ጠቅለል ያለ ሃሳብ ምን ይመስላል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የሮም መንግሥት ክፉ ድርጊቶች በግዛቱ ሕዝቦች በሚገባ ይታወቁ ነበር፡፡ ጨካኝና አረመኔ የጦር ሠራዊት የነበረው የሮም ንጉሣዊ አስተዳደር በስሜት የሚገፋፉ ችኩል ውሳኔዎችን ይወስን ነበር፡፡ ማንኛውንም ተቃውሞ በኃይል ከመጨፍለቅ ውጪ ለሰላማዊ የመፍትሔ ሃሳቦች ዕድል አይሰጥም ነበር፡፡ አሰቃቂ የማሰቃያ ዘዴዎች እና በመስቀል ላይ ቸንክሮ መግደል--ሰዎች የማይፈልጉትን እንዲቀበሉ የሚያስገድዱባቸው ሁለት የቅጣት ስልቶቻቸው ነበሩ፡፡ የሮም መንግሥት በችሎታ ሳይሆን በአምቻ ጋብቻ--በንጽህና ሳይሆን በንቅዘትና ሙስና የተንሰራፋ ሥርዓት ነበር፡፡ የሥርዓቱ ቁንጮዎች ዕብሪተኞና ፍጹም ጨካኞች ነበሩ፡፡ በዚህ ሁሉ ግፍና በደል መሃል ጴጥሮስ አንባቢዎቹን--ከንጉሡ እስከ በታች ባለሟሎቹ ማንኛውም የግዛቱ መዋቅር አካል ለሆነ “የበላይ ባለ ሥልጣን ሁሉ ተገዙ” ሲል ተማጽኖ ያቀርባል (1ጴጥ. 2፡13)፡፡

ነገሥታትና ገዢዎች ክፉ አድራጊዎችን እንደሚቀጡ--ትክክል የሚያደርጉትን ደግሞ እንደሚያመሰግኑ በመናገር ጴጥሮስ ለሃሳቡ ድጋፍ የሚሆነውን ነጥብ በማንሳት ይሞግታል (1ጴጥ. 2፡14)፡፡ ይህን በማድረጋቸው ማኅበረሰቡን በትክክለኛው መንገድ በማነጹ ረገድ እጅግ አስፈላጊ ሚና ይጫወታሉ፡፡

በእርግጥ የሮም ንጉሣዊ ሥርዓት ያን ሁሉ አሰቃቂ ድርጊት ቢፈጽምም በግዛቱ ነዋሪዎች መሃል ሰላምና መረጋጋት ማስፈኑ ግን አንድና ሁለት የለውም፡፡ ጦርነትን እንደ ብቸኛ መፍትሔ በመጠቀም ነጻነት እንዲሰፍን አድርጎአል፡፡ ሥርዓቱ ለዜጎች ይሰጥ የነበረው ፍርድ ጥብቅና ኃይለኛ ቢሆንም ነገር ግን በዘመኑ ይሠራበት የነበረውን የፍትሐ ብሔርም ሆነ የወንጀል ሕግ መሰረት ያደረገ ፍትሕ ገቢራዊ ይሆን ነበር፡፡ የሮም ንጉሣዊ ሥርዓት ለወታደራዊ ሠፈሮች አስፈላጊውን ስንቅም ሆነ ቁሳቁስ ለማጓጓዝ እንዲረዳ መንገዶችንና የገንዘብ ማስተላለፊያ ተቋሞችን ገንብቶ ነበር፡፡ ሮም ይህን በዘመኑ ወደፊት የተራመደ የመሰረተ ልማት እንቅስቃሴ መፍጠር መቻሏ የሕዝብ ቁጥር እንዲያድግና ብልጽግና እንዲመጣ አስችሎ ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ ስለዚያ መንግሥት ይህን በጎ በጎውን የተመለከተው የጴጥሮስ አዎንታዊ አስተያየት ትርጉም ያለው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በተለይ ጴጥሮስ--ያቺ መልእክት የጻፈላት ቤተ ክርስቲያን ትተዳደርበት የነበረውን ሥርዓት ጨምሮ በዚህ ምድር ፍጹም የሆነ አንድም ምድራዊ መንግሥት የለም፡፡ ምድራዊ ገዢዎቻቸው ፍጹም ባይሆኑም እንኳ--ክርስቲያኖች መልካም ዜጎችና በተቻላቸው የምድራቸውን ሕጎች የሚታዘዙ ሊሆኑ እንዲሚገባ ከጴጥሮስ መልእክት ትምህርት ማግኘት እንችላለን፡፡

ምድራዊው ፖለቲካ ምቹም ባይሆን ክርስቲያኖች በተቻላቸው መልካም ዜጎች መሆናቸው አስፈላጊነቱ ምኑ ላይ ነው? የተሻለ ማኅበረሰብ በመፍጠሩ ረገድ በመጠኑም ቢሆን ምን ማድረግ ይችላሉ?

ሚያዝያ 9
17-Apr

ጌቶችና አገልጋዮች


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡-- 1ጴጥ. 2፡18-23፡፡ የእነዚህን ጥቅሶች አስቸጋሪ ይዘት ዛሬ በዚህ ዘመን የምናስተውለው እንዴት ነው? ምን ዓይነት መርኅ ከውስጣቸው ወስደን ጥቅም ላይ ማዋል እንችላለን?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

በ 1ጴጥ. 2፡18-23 የቀረበውን መልእክት በጥንቃቄ ከተመለከትን ጥቅሶቹ ለባሪያ አሳዳሪ ሥርዓት ድጋፍ እንድንሰጥ አያደርጉንም፡፡ ይልቁንም በወቅቱ ሊለወጥ ይችል ስላልነበረው አስቸጋሪ ሁኔታ እንዴት ማሰብ እንዳለብን መንፈሳዊ የምክር አገልግሎት ይሰጡናል፡፡

በ 1ጴጥ. 2፡18 “አገልጋይ” ወይም “ባሪያ” በሚል የተጠቀሰው ቃል oiketes ከሚል የግሪክ ቃል የተተረጎመ ሲሆን፤ ቃሉ በተለይ የሌላ አገር መጤን ሳይሆን ነገር ግን የዛው አገር ዜጎች የሆኑ ባሪያዎችን ለመጥቀስ ጥቅም ላይ እንደዋለ ይታወቃል፡፡

በከፍተኛ ሁኔታ በእርከን ተከፋፍሎ በነበረው በሮም ግዛት፤ ባሪያዎች በጌቶቻቸው አምባገነን ቁጥጥር ስር የነበሩ--በመልካም ወይም በክፉ እንደ ፈለጉ የሚያደርጓቸው ሕጋዊ ሐብቶቻቸው ነበሩ፡፡ ዜጎች በባርነት ቀንበር ሊወድቁ ይችሉባቸው ከነበሩ መንስኤዎች አንዳዶቹ፡--በጦርነት ድል መሆን፣ ከባሪያዎች መወለድ ወይም ዕዳን ባለ ክፈል “መሸጥ” ናቸው፡፡ ለአንዳንድ ባሪያዎች ከፍተኛ ኃላፊነት ይሰጥ ነበር፡፡ ጥቂቶች የጌቶቻቸውን ሰፊ ርስት አስተዳድረዋል፡፡ ሌሎችም የአሳዳሪዎቻቸውን ንብረት መጠበቅ፣ የንግድ እንቅስቃሴዎቻቸውን መምራትና ልጆቻቸውን የማስተማር ኃላፊነት ወስደዋል፡፡

አንድ ባሪያ በገንዘብ ክፍያ ነጻነቱን ሊቀዳጅ የሚችልበት አሠራር ተዘርግቶ የነበረ ሲሆን ይኸውም “ቤዛነት” በመባል ይታወቃል፡፡ ጳውሎስ የሱስ ለእኛ ያደረገውን ለመግለጽ ይህን ቃል ይጠቀማል (ኤፌ. 1:7፣ ሮሜ. 3:24፣ ቆለ. 1:14፣ 1ጴጥ. 1:18- 19)፡፡

ከመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች መሃል አብዛኞቹ በባርነት ቀንበር ስር የወደቁ እንደ ነበሩ ማስታወሱ ተገቢ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ እነዚህ ወገኖች ራሳቸውን ፈጽሞ ሊለውጡት በማይችሉት ሁናቴ ውስጥ አግኝተውት ነበር፡፡ ጨካኝና መሰሪ ጌታ የገጠሟቸው አንዳንዶች በከባድ ሁናቴ ውስጥ ማለፋቸው የግድ ቢሆንም--የተሻለ የሚባል ዓይነት ጌታ የነበሯቸውም ቢሆኑ በፈታኝ ድባብ ውስጥ መውደቃቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ጴጥሮስ በባርነት ቀንበር ስር ወድቀው ለነበሩ ለሁሉም ክርስቲያኖች ያስተላለፋቸው መመሪያዎች ከሌሎች የአዲስ ኪዳን መልእክቶች ጋር ጎን ለጎን የሚሄዱ ናቸው፡፡ ክርስቶስ መከራን ለመቀበል ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠ ሁሉ፤ በተመሳሳይ እነርሱም ራሳቸውን ማስገዛትና በጽናት ማለፍ ነበረባቸው (1ጴጥ. 2፡18-21)፡፡ እዚህ ላይ ከእውነተኛው የክርስቶስ መንፈስ ጋር ለማመሳሰል የተሞከረው--ጥፋት ሠርተው ብርቱ ቅጣት የተቀበሉትን ሳይሆን ያለ ወንጀላቸው ግፍ የደረሰባቸውን ነው፡፡ በዚያን ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች እንደ ክርስቶስ ሁሉ ይደርስባቸው ለነበረ ክፉ ድርጊት ወይም አስጊ ሁናቴ ራሳቸውን ለቅን ፈራጃቸው እግዚአብሔር ከማስገዛት ውጪ አጸፋዊ ምላሽ አይሰጡም ነበር (1ጴጥ. 2፡23)፡፡

ከላይ ከቀረበው የጴጥሮስ መልእክት ምን ዓይነት ተጨባጭ ሃሳቦችን ማዋቀር እንችላለን? አባባሉ ለመብታችን መቆም የለብንም የሚል አንደምታ አለው? መልስዎን በሰንበት ትምህርት ጥናት ይዘው ለመቅረብ ይሞክሩ፡፡

ሚያዝያ 10
18-Apr

ሚስቶችና ባሎች


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡-- 1ጴጥ. 3፡1-7፡፡ ጴጥሮስ በተለይ እያነሳ ያለው ተጨባጭ ጉዳይ ምንድን ነው? ስለ ጋብቻ እያነሳ ያለው ነጥብ ለዘመናችን የትዳር ሕይወት ምን ያህል ገጣሚ ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጴጥሮስ ከቁ. 1-7 እያለ ያለውን ነገር አንባቢው በጥንቃቄ እንዲያስተውል ሊረዳው የሚችል አንድ አጽንኦት ሊሰጠው የሚገባ ፍንጭ አለ፡፡ ጴጥሮስ በቁ. 1 መልእክቱ “ያለ ቃል” ስለሚመላለሱ ወይም እግዚአብሔርን ስለማይታዘዙ ባሎች ይናገራል፡፡ በሌላ አነጋገር ክርስቲያን የሆነች ሚስት አማኝ ያልሆነውን ሰው ስታገባ (አማኝ ያልሆኑት ቁጥር አነስተኛም ቢሆን) ሊከሰት ስለሚችለው ነገር ጴጥሮስ ይናገራል፡፡

ክርስቲያን ሴት ከእምቷ ውጪ ከሆነ ሰው ጋር ስትጋባ አያሌ አስቸጋሪ ሁናቴዎች ሊገጥሟት ይችላሉ፡፡ ታዲያ ለዚህ ችግሯ መፍትሔ የምታበጀው እንዴት ነው? ባሏን ትፍታው? እንደ ጳውሎስ ሁሉ ጴጥሮስም ክርስቲያን ሚስቶች አማኝ ያልሆኑ ባሎቻቸውን ትተዋቸው ይሂዱ ሲል አይመክርም (1ቆሮ. 7፡12-16)፡፡ በዚህ ፋንታ ሚስቶች አማኝ ባልሆነው ባል ፊት አርአያነት ያለው ሕይወት ይኑሩ በማለት ይናገራል፡፡

ሮም ዓለምን ይገዛ በነበረበት በአንደኛው ክፍለ ዘመን የሴቶች ሚና እንደ ማኅበረሰቡ ሁናቴ የተወሰነ ነበር፡፡ ለምሳሌ ከንብረትና ሕጋዊ መብቶች አኳያ-- ጴጥሮስ መልእክቱን ከጻፈላቸው ከአብዛኞቹ ሴቶች ይልቅ ሮማውያን ሚስቶች ከፍ ያለ ባለ መብት ነበሩ፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ማኅበረሰቦች ዘንድ ሴቶች ከፖለቲካ፣ ከመንግሥታዊ አስተዳደርና መሪነት የተገለሉ ነበሩ፡፡ ክርስቲያን ሴቶች በዚያው በሚኖሩበት ሁናቴ ተደናቂነት ሊያተርፍላቸው በሚችል ንጹህና ፍጹም አክብሮት በተሞላው አካሄድ እንዲመላለሱ ጴጥሮስ አጥብቆ ያስገነዝባል (1ጴጥ. 3፡2)፡፡ ክርስቲያን ሴት አብልጦ ሊገዳት የሚገባው ውጫዊው ሹሩባ፣ በወርቅ ማጌጥና በውድ ልብሶች መሽሞንሞን ሳይሆን ውስጣዊ ቁንጅናዋ ሊሆን እንደሚገባ ምክሩን ይለግሳል (1ጴጥ. 3፡3-5)፡፡ ክርስቲያን ሴት የክርስትና እምነት የሚጠይቀውን ጣዕምና ጠረን ባህሪዋ አድርጋ ከሕይወት አጋር-- ባሏ ጋር በጥምረት ትኖራለች፡፡

የጴጥሮስ መልእክት ባሎች በሚስቶቻቸው ላይ አጓጉል ድርጊቶች እንዲፈጽሙ መብት እንደሚሰጥ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ ይልቁንም ባሎች ለሚስቶቻቸው ያላቸውን አሳቢነት ገልጠው ማሳየት ይጠበቅባቸዋል (1ጴጥ. 3፡7)፡፡

ጴጥሮስ አማኝ ያልሆኑ ባሎችን ያገቡ ክርስቲያን ሚስቶችን ጉዳይ መግለጡ-- በክርስትና እምነት ጥላ ስር በጋብቻ ተሳስረው ስለሚኖሩ ተጓዳኞች ትክክለኛ ውሳኔ በመጠኑም ቢሆን ሃሳብ ይሰጠናል፡፡ ክርስቲያን ባለ ትዳሮች በየዕለቱ እግዚአብሔርን እያመለኩ በጋራ ሊረዳዱና ሕይወታቸው ግለጽነት በሰፈነበት ጥምረት ሊመራ ይገባል፡፡

ሚያዝያ 11
19-Apr

ማኅበራዊ ግንኙነቶች


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡-- ሮሜ 13:1–7፣ ኤፌ. 5:22-33;፣ 1ቆሮ. 7:12–16፣ ገላ. 3:27- 28፡፡ ጳውሎስ የሚናገረው ጴጥሮስ በ1ጴጥ. 2፡11-3፡7 ከተናገረው ጋር መስተያየት የሚችለው እንዴት ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጳውሎስ በ1ጴጥ. 2፡11—3፡7 የቀረቡትን አንዳንድ ነጥቦች በብዙ ቦታዎች ጠቅሷል፡፡ ጳውሎስ የሰጣቸው ሀሳቦች በአንደኛ ጴጥሮስ ከምናገኛቸው መልእክቶች ጋር አስደናቂ ተደጋጋፊነት አላቸው፡፡ ለምሳሌ እንደ ጴጥሮስ ሁሉ ጳውሎስም ማንኛውም ሰው “በሥልጣን ላሉት ሹማምንት” መገዛት እንደሚገባው ይናገራል (ሮሜ 13፡1)፡፡ ገዢዎች በእግዚአብሔር ስለሚሾሙ ክፉ ለሚያደርጉ እንጂ መልካም ለሚሠሩ አስፈሪ አለመሆናቸውን ጳውሎስ ይናገራል (ሮሜ 13፡3)፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኖች “ለእያንዳንዱ የሚገባውን ስጡ፤ ግብር ከሆነ ግብርን፣ ቀረጥ ከሆነም ቀረጥን፣ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፣ ክብር ለሚገባውም ክብርን ስጡት (ሮሜ 13፡7)፡፡

አማኝ ያልሆኑ ወንዶችን ያገቡ ሴቶች አርአያነት ያለው ሕይወት ሲኖሩ--በውጤቱ ባሎቻቸው ቤተ ክርስቲያንን ሊቀላቀሉ እንደሚችሉ ጳውሎስ ያስገነዝባል (1ቆሮ. 7፡12-16)፡፡ ጳውሎስ በአርአያነት የጠቀሰው የክርስትና ትዳር ባልና ሚስት-- ሁለቱም አማኝ የሆኑበትን ጥምረት ነው፡፡ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ባሎችም ሚስቶቻቸውን ሊወዱ የተገባ ነው (ኤፌ. 5፡25)፡፡ በተጨማሪ ባሪያዎች ክርስቶስን እንደሚታዘዙ፤ ምድራዊ ጌቶቻቸውንም በቅንነት መታዘዝ እንደሚጠበቅባቸው ምክሩን ይሰጣል (ኤፌ. 6፡5)፡፡

ጳውሎስ አገልግሎት ይሰጥባቸው የነበሩ ግዛቶችን ሕግና ባህል አክብሮ ለመሥራት ፈቃደኛ ነበር፡፡ ከእርሱ ባህላዊ እሴቶች መሃል መለወጥ የሚችሉትንና የማይችሉትን ጠንቅቆ ያውቅ የነበረው ጳውሎስ--ማኅበረሰቡ ስለ ሰዎች የሚያስበውን የኋላ ኋላ ሊለወጥ የሚችል ነገር በክርስትና እምነት ውስጥ መመልከት ችሎ ነበር፡፡ የሱስ ሕብረተሰቡ ተቀብሎ ይተዳደርበት የነበረውን እሳቤ አብዮት አካሂዶ እንዳልገረሰሰው ሁሉ ጴጥሮስና ጳውሎስም ከዚህ የተለየ አላደረጉም፡፡ በሕብረተሰቡ የአኗኗር ዘይቤ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት የሚቻለው አብዮት በማካሄድ ሳይሆን የእግዚአብሔር ሕዝቦች በህብረተሰቡ ላይ በሚያሳድሩት ተጽእኖ ነው፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡-- ገላ. 3፡27-29፡፡ ምንም እንኳ የሀሳቡ ሥነ መለኮታዊነት ግለጽ ቢሆንም--የሱስ ካደረገላቸው ነገር አኳያ በክርስቲያኖች መሀል ሊኖር ስለሚገባ የእርስ በርስ ግንኙነት በጥቅሶቹ የቀረበው አንደምታ ምን ይመስላል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------



ሚያዝያ 12
20-Apr

ክርስትናና የኅረተሰብ አኗኗር ዘይቤ


ሰብዓዊም ሆነ መንግሥታዊ ተቋማት በእንከን የተሞሉና አልፎ አልፎም ኃጢአተኛ ይዘት ያላቸውን አሠራሮች እንደሚተገብሩ ብናውቅም--ይኸው መጥፎ ተሞክሮ ከመንግሥት ኃላፊዎችና የኃይማኖት መሪዎች ጋር የተነካካ መሆኑን ብናስተውልም ነገር ግን ጳውሎስም ሆነ ጴጥሮስ ቀደምት ክርስቲያኖች ለባለሥልጣናት እንዲገዙ አበክረው ያስገነዝባሉ (1ጴጥ. 2፡13-17፣ ሮሜ 13፡1-10)፡፡ ክርስቲያኖች ግብር እንዲከፍሉና ከመንግሥት የሚፈለግባቸውን ተግባር እንዲያከናውኑ ይጠይቃሉ፡፡ ክርስቲያኖች በተቻለ ለሌሎች ምሳሌ ዜጎች መሆን ይጠበቅባቸው ነበር፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡--ሐዋ. 5፡27-32፡፡ ጴጥሮስ ባለሥልጣናትን መታዘዝ እንደሚገባ (1ጴጥ. 2፡13-17) የተናገረው ነገር በአንድ አጋጣሚ እርሱና ሌሎች ሐዋርያት በዚህ ዙሪያ አድርገውት ከነበረው ነገር ጋር ያለው ዝምድና ምን ይመስላል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ስኬት ለዮሐንስና ለጴጥሮስ መታሰር መንስኤ ሆኖ ነበር (ሐዋ. 4፡1-4)፡፡ ሐዋርያት--በአለቆች፣ በሽማግሌዎችና በጸሐፍት ጥያቄ ከቀረበላቸው በኋላ ከእንግዲህ እንዳይሰብኩ በሚያዝ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ተለቀው ነበር (ሐዋ. 4፡5-23)፡፡ ነገር ግን ሐዋርያቱ ብዙም ሳይቆዩ እንደገና ታስረው ባለ ሥልጣናት ፊት ቀረቡ፡፡ አታድርጉ ያሏቸውን ነገር ለምን ደግመው እንዳደረጉ ሲጠየቁ (ሐዋ. 5፡28) “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” (1ጴጥ. 5፡29) በማለት ጴጥሮስ መለሰላቸው፡፡

ከእነዚህ ቃላት ልንወስድ የሚገባ እውነት ምንድን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጴጥሮስ አንድ ነገር ተናግሮ ሌላ ነገር እያደረገ የነበረ ግብዝ አልነበረም፡፡ ነገሩ ከእግዚአብሔርና ከሰው ማንን መከተል እንደሚኖርባቸው የሚጠይቅ ብርቱ ጉዳይ ሲሆን ምርጫው ግልጽ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ክርስቲያኖች የሕብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ ለመለወጥ ከሚያደርጉት ሙከራ ባይገቱም፤ እንዲህ ያለው ያፈጠጠ ውሳኔ የሚጠይቅ ነገር ካልተከሰተ በቀር ለመንግሥት ድጋፍ የሚያደርጉና ታዛዥ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ሥነ ምግባር ነክ የሆኑ ጉዳዮች ሚዛናቸውን ሲስቱና አደጋ ላይ ሲወድቁ ክርስቲያኖች ሕብረተሰባዊ ለውጥ ማምጣት የሚችሉትን የክርስቶስ እሴቶችና አስተምህሮዎች እያንጸባረቁና በሕጋዊ መንገድ እያስተጋቡ እንደኖሩ ሁሉ አሁንም ይህን ማድረጋቸውን መቀጠል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ገቢራዊ የሚሆንባቸው አካሄዶች በብዙ ነገሮች ላይ የተመሰረቱ ቢሆኑም ነገር ግን ታማኝና ትክክለኛ ዜጋ መሆን--ክርስቲያን ለማኅበረሰቡ እሳቤ መሻሻል ድጋፍ ማድረግ አይችልም ወይም ፍላጎት የለውም የሚል አንደምታ የለውም፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡-- ዘሌዋ. 19፡18፣ ማቴ. 22፡39፡፡ የባልንጀራዎን ህይወት በእርግጠኝነት ማቅለል የሚችለው--ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን እንድንወድ የተሰጠን ትእዛዝ ለለውጥ የመሥራታችንን አስፈላጊነት ያካተተው እንዴት ነው?

ሚያዝያ 13
21-Apr

ተጨማሪ ሃሳብ:-


Read Ellen G. White, “The Impending Con- flict,” pp. 582–592; “The Scriptures a Safeguard,” pp. 593–602; and “The Time of Trouble,” pp. 613–634 in The Great Controversy.

ኤለን ጂ. ኋይት--ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች የሚኖሩበትን ምድር ሕጎች የሚታዘዙ መልካም ዜጎች ሊሆኑ እንደሚገባ በመናገር ለዚህ ሃሳብ ያላትን ድጋፍ ትሰጣለች፡፡ እንደውም ሰዎች ገና የአስገዳጅነት ደረጃ ያልደረሰውን የእሁድን ሕግ በግልጽ ወይም በጉልህ መቃወም እንደሌለባቸው ተናግራለች፡፡ ይህ ማለት--ምንም እንኳ እግዚአብሔር ባዘዘው መሰረት ሰባተኛውን ቀን ሰንበት ቅዱስ አድርገው መጠበቅ ቢኖርባቸውም ነገር ግን በእሁድ ቀን መሠራት የለበትም የሚለውን ሕግ ሆነ ብለው መቃወም የለባቸውም፡፡ በእርግጥ በአንድ በኩል አድቬንቲስቶች ይህን ሕግ መታዘዝ እንደሌለባቸው በግልጽ የምትናገርባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ አንድ ባሪያ ከጌታው አምልጦ ቢሄድ ሕጉ ተመልሶ ወደዚያው አሳዳሪው እንዲመጣ ይጠይቀዋል፡፡ ሕጉን አለመታዘዝ የሚያመጣው መዘዝ ሊኖር ብችልም እርሷ ግን ይህን ሕግ በመቃወም አድቬንቲስቶች እንዳይከተሉት አምርራ ተናግራለች፡ “ሰብዓዊው ሕግ ከአምላካዊው ቃልና ሕግ ጋር ተቃርኖ ውስጥ ሲገባ መዘዙ ምንም ሊሆን ቢችል መከተል የሚኖርብን የእግዚአብሔርን ቃል ነው፡፡ የምድራችን ሕግ የጠፋውን ባሪያ መልሰን ለጌታው እንድንሰጥ ቢያዘንም ይህን ሕግ አንታዘዝም፡፡ ስለዚህ ሕጉን መጣሳችን ሊያስከትልብን የሚችለውን ማንኛውንም ነገር ለመቀበል ከወዲሁ ዝግጁዎች እንሁን፡፡ ባሪያ የማንም ሰው አንጡራ ሀብት አይደለም፡፡ ትክክለኛ ጌታው እግዚአብሔር ነው፡፡ ሰው የእግዚአብሔርን እጆች ሥራ የመውሰድም ሆነ የእኔ የማለት መብት የለውም፡፡”—Testimonies for the Church, vol. 1, pp. 201, 202.


የመወያያ ጥያቄዎች:



በሰኞ ትምህር መጨረሻ ላይ ክርስቲያኖች ለመብታቸው መቆም የለባቸውም ወይ? በሚል በቀረበው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፡፡ ለመሆኑ መብቶቻችን ምንድን ናቸው?

ማኅበረሰቡን በበጎ ለመለወጥ የሚያስችሉ--ክርስቲያኖች በማኅበረሰቡ ላይ የሚያሳድሩት አርአያነት የትኞቹ ናቸው? ከእነዚህ ነጥቦች ምን መማር እንችላለን?  ክርስቲያኖች ለማኅበረሰቡ ነቀርሳ የሆኑ ነገሮችን ለመለወጥ እገዛ በማድረግ ፋንታ ጭራሹኑ ከእነዚህ ክፉ ደዌዎች ጋር ተስማምተው እየኖሩ ትክክለኝነታቸውን ለማሳየት ከሚሞክሯቸው መሃል ለአብነት አንዳንዶቹን ጥቀሱ? ከእነዚህ ታሪኮች ምን እንማራለን?

 በ 1ጴጥ. 2፡17 “ንጉሥን አክብሩ” የሚል ጥቅስ እናገኛለን፡፡ የወቅቱ የሮም ንጉሥ ኔሮ እንደ ነበር የሚገመት ሲሆን፤ ከኔሮ የከፋ ክፉና ምግባረ ብልሹ ሰብዓዊ ፍጡር የለም ይባላል፡፡ ይህ ዛሬ ለእኛ ያለው መልእክት ምን ይመስላል? ጴጥሮስ በጥቅሱ መጀመሪያ “ለሰው ሁሉ ተገቢውን አክብሮት ስጡ” በማለት የጻፈው መልእክት ለማለት የፈለገውን በተሻለ እንድናስተውል የሚረዳን እንዴት ነው?

 ጥቅሶቹን በክፍል ውስጥ ያንብቡ፡--1ጴጥ. 2፡21-25፡፡ የወንጌል መልእክት በእነዚህ ጥቅሶች ተጠቃሎ የቀረበው እንዴት ነው? ምን ዓይነት ተስፋ ይሰጡናል? ምን እንድናደርግ ጥሪ ያቀርቡልናል? እንድናደርግ የተነገርንን ምን ያህል በቁርጠኝነት እየተገበርን እንገኛለን?