በጎቼን መግብ፡ 1ኛ እና 2ኛ ጴጥሮስ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2017

ከመጋቢት 30-ሚያዝያ 6

ሶስተኛ ትምህርት

April 8 - 14


የንጉሥ ካኅናት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 1ጴጥ. 2:1–3፣ ዕብ. 4:12፣ 1ጴጥ. 2:4–8፣ ኢሳ. 28:16፣ ዘፀ. 19:3–6፣ 1ጴጥ. 2:5፣ 9- 10፡፡


የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - “እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ፣ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካኅናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ለራሱ የለያችሁ ሕዝብ ናችሁ” (1ጴጥ. 2:9)፡፡



ው ልደቱም ሆነ ዕድገቱ በአይሁድ ባህል፣ ኃይማኖትና ታሪክ ተጽእኖ ስር የነበረው ጴጥሮስ ክርስቲያኖችን “ቅዱስ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ለራሱ የለያችሁ” በማለት ሲጠራ ይታያል፡፡ በዚህም ጴጥሮስ-- የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ የጥንቶቹን እስራኤላውያን ለመጥቀስ ተጠቅሞ የነበረውን ይህን ኪዳናዊ ቋንቋ ወስዶ ለአዲስ ኪዳኗ ቤተ ክርስቲያን አውሎአል፡፡

አሕዛብ የነበሩ የሱስን ማመናቸውን ተከትሎ በግንዱ ላይ በመጣበቃቸው የኪዳኑ ሕዝቦች ተብለው መጠራታቸው ብዙም አስገራሚ አይሆንም፡፡ አሁን ግን እነዚህ ሕዝቦች የኪዳኑ ተስፋዎች ወራሾች ናቸው “ከቅርንጫፎቹ አንዳንዶቹ ሲሰበሩ፣ አንተም የበረሓ ወይራ ሆነህ ሳለ በሌሎቹ መካከል ገብተህ ከተጣበቅህና ከወይራው ዘይት ሥር የሚገኘው በረከት ተካፋይ ከሆንህ፣ በእነዚያ ቅርንጫፎች ላይ አትኩራራ፡፡ ብትኩራራ ግን ይህን አስተውል፤ አንተ ሥሩን አትሸከምም፤ ሥሩ ግን አንተን ይሸከምሃል እንጂ” (ሮሜ 11:17-18)፡፡

በዚህ ሣምንት ምልከታ በምናደርግባቸው ጥቅሶች--ጴጥሮስ በወይራው ዘይት ላይ የተጣበቁ አንባቢዎቹን (የጳውሎስን አገላለጽ በመጠቀም) እንደ እግዚአብሔር ሕዝብነታቸው ወደ ተቀደሰው ኃላፊነትና ከፍ ወዳለው ጥሪ ያመላክታል፡፡ ይህ ጥሪና ኃላፊነት ከጥንቶቹ እስራኤላውያን ኃላፊነቶች አንዱ የሆነውን--በጌታ የተሰጠውን ታላቁን የደኅንነት እውነት ማወጅ ነው፡፡

ሚያዝያ 1
9-Apr

እንደ ክርስቲያን መኖር


1ጴጥ. 2፡1 የሚጀምረው “እንግዲህ” በሚል ቃል ነው፡፡ ቃሉ--በቀጣይነት የሚመጣው የቀድሞውን ውጤት መሰረት ያደረገ መሆኑን ያሳያል፡፡ በአንደኛ ጴጥሮስ ምዕ. 1 ክርስቶስ ለእኛ ያደረገልንን ነገርና የእኛ ምላሽ ምን ሊሆን እንደሚገባ የሚያሳየውን ድንቅ ሥራ ቀደም ብለን ተመልክተናል፡፡ በቀጣዩ ምዕራፍ ጴጥሮስ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ምልክታ ያደርጋል፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡-- 1ጴጥ. 2፡1-3፡፡ ጴጥሮስ እንዴት መኖር እንዳለብን አስመልክቶ ምን እያለን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጴጥሮስ የክርስቲያኖች ኃላፊነት እጥፍ መሆኑን ለማሳየት ሁለት የተለያዩ ገጽታዎችን ይጠቀማል፡፡ አንደኛው አሉታዊና ሊወገድ የሚገባው--ሌላኛው አዎንታዊና አንዳች በጎ ለማድረግ ልንመኘው የሚገባ፡፡ ጴጥሮስ ባቀረበው የመጀመሪያው ገጽታ ክርስቲያኖች ክፋትን፣ ማታለልን፣ ግብዝነትን፣ ቅናትንና ሐሜትን እንዲያስወግዱ (1ጴጥ. 2፡1) አጥብቆ ያስገነዝባል፡፡ ይህን በማድረጋቸው ክርስቲያኖች በዙሪያቸው ካሉ ከብዙዎች በተለየ ምግባር ራሳቸውን ይመራሉ፡፡ ክፋትን በማስወገዳቸው ሌሎችን የመጉዳት ምኞት አያድርባቸውም--ይልቁንም መልካማቸውን ሁሉ አጥብቀው ይሻሉ፡፡ ክርስቲያኖች አለመታመንን ስለሚጸየፉ ሌሎችን የማታለል ሥራ አይሠሩም--እነርሱ ግልጽ፣ ቀጥተኛና ታማኝ ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች ከአቅማቸው በላይ ሐብት ባካበቱ ሰዎች አይቀኑም፡፡ እነርሱ በሕይወታቸው ደስተኞች፣ መለኮት ጣልቃ እየገባ የሚያሳድጋቸውና የሚያበለጽጋቸው ናቸው፡፡ ሆነ ተብሎ የሌላውን ክብርና ዝና የሚያጎድፍ ቃል ከአንደበታቸው አይወጣም፡፡

ጴጥሮስ በሁለተኛ ደረጃ ጥቅም ላይ ያዋለው አዎንታዊ ገጽታ የተላበሰው አስተምህሮ--ወተት በተራበ ጨቅላ ህፃን ተመስሎ ቀርቦአል (1ጴጥ. 2፡2)፡፡ የክርስትና ሕይወት መጥፎ ነገሮችን በመተው ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ እንደውም እንዲህ ያለው ሕይወት ባዶ ነው፡፡ ጉዳዩ ያለው--የተራበው ጨቅላ ሕፃን ወተት ሽቶ የማያባራ እሪታ ከሚያሰማበት ሁናቴ በተመሳሳይ ክብደት መንፈሳዊ ምግብን አጥብቆ በመፈለጉ ላይ ነው፡፡ ጴጥሮስ አንባቢዎቹን የመንፈሳዊ ምግብ ምንጭ ወደ ሆነው ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ያመላክታል (በተጨማሪ እነዚህን ይመልክቱ፡ ዕብ. 4:12፣ ማቴ. 22:29፣ 2ጢሞቴ. 3:15–17)፡፡ በመንፈስና በሥነ ምግባር ማደግ የምንችለው የእግዚአብሔርን ቃል መመገብ ስንችል ነው፡፡ ምክንያቱም--ቢያንስ እኛ በየሱስ ክርስቶስ የተሰጠን የቃሉ ሙሉ መገለጥ አለን፡፡ ቅዱስ የሆነውን የእግዚአብሔር ጸባይና ተፈጥሮ እንድንወደውና እንድናገለግለው የተሰጠን የየሱስ ምሳሌ አለን፡፡

እነዚህ ሁለት ጽንሰ ሃሳቦች የሚዛመዱት እንዴት ነው? በጴጥሮስ ጽሑፍ መሰረት መንፈሳዊ ምግብን ከእግዚአብሔር ቃል መፈለጋችን መጥፎዎቹን ድርጊቶችና አመለካከቶች እንድንተው የሚረዳን እንዴት ነው?

ሚያዝያ 2
10-Apr

ሕያው ድንጋይ


ጥቅሱን ያንብቡ፡-- 1ጴጥ. 2፡4-8 (በተጨማሪ፡--ኢሳ. 28:16፣ መዝ. 118:22፣ ኢሳ. 8:14-15)፡፡ ጴጥሮስ እየጠቀሰ ያለው መሰረታዊ እውነት ምንድን ነው? ለየሱስ የምንሰጠው አጸፋዊ ምላሽ ምን መምሰል ይኖርበታል እያለን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጴጥሮስ አንባቢዎቹ መንፈሳዊውን ምግብ አጥብቀው እንዲፈልጉ ከነገራቸው በኋላ- በፍጥነት ትኩረታቸውን ከኢየሩሳሌሙ ቤተ መቅደስ ጋር አጣቅሶ ከሚያቀርበው ሕያው ድንጋይ ወደ ሆነው ወደ የሱስ ክርስቶስ ይወስዳል፡፡ የሱስ በቤተ ክርስቲያኑ ስላለው ሚና የሚያወሳው ጴጥሮስ--ስለ ማእዘን ድንጋይ አጽንኦት የሚሰጡ ሦስት የብሉይ ኪዳን ጥቅሶችን በ 1ጴጥ. 2፡4-8 ይጠቅሳል፡፡ ጥቅሶቹን ከየሱስ ጋር በአንድ አስተሳስሮ በማቅረቡ ረገድ ጴጥሮስ ብቸኛው ሰው አልነበረም፡፡ የሱስ ራሱ ከተናገራቸው ምሳሌያዊ ታሪኮች በአንዱ (ማቴ. 21፡42) መደምደሚያ ላይ መዝ. ተመሳሳይ አቀራረብ ተጋርቶአል (በሐዋ. 4፡11)፡፡

ጴጥሮስ የሚያነሳው ነጥብ--ምንም እንኳ የሱስ ነቀፋ ቢደርስበትና በመስቀል ላይ ቢሰቀልም፤ የእግዚአብሔር መንፈሳዊ ቤት የማእዘን ድንጋይ እንዲሆን በእግዚአብሔር ተመርጦአል--የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ቤት ሆነው የተገነቡ ሕያዋን ድንጋዮች ናቸው፡፡ ጴጥሮስ የማእዘን ድንጋይ፣ የተመረጠ ድንጋይ በማለት ሙያዊ የግንባታ ቃላትን እየተጠቀመ የቤተ ክርስቲያንን ገጽታ ከፊታችን ያስቀምጣል፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሰረት የተጣለው በየሱስ ላይ ሲሆን-- የተሞላችው ግን በእርሱ ተከታዮች ነው፡፡

ክርስቲያን መሆን የክርስትና ማኅበረሰብ ወይም የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አካል መሆን ነው፡፡ አንድ ጡብ የግዙፉ ግንባታ አካል ሆኖ እንደሚገነባ ሁሉ ክርስቲያኖችም ከእምነት አጋሮቻቸው ተነጥለው የሱስን እንዲከተሉ አልተጠሩም፡፡ የእግዚአብሔርን መንግሥት በማፋጠኑ ረገድ ከክርስቲያኖች ጋር ሕብረት ፈጥሮ አምልኮ የማያደርግና የማያገለግል አማኝ በተቃርኖ እንደሚኖር መናገር ይቻላል፡፡ ክርስቲያኖች በጥምቀት የክርስቶስ አካል ሆነዋል፡፡ በጥምቀት የክርስቶስ አካል መሆናቸው ደግሞ የቤተ ክርስቲያኑ አካል አድርጓቸዋል፡፡

እንዲሁም ጴጥሮስ ስለ ቤተ ክርስቲያን አሠራር ይናገራል፡፡ ቤተ ክርስቲያን “መንፈሳዊ መሥዋዕት” የሚያቀርቡ “ቅዱሳን ካህናት”ን (1ጴጥ. 2፡5) መቅረጽ ይጠበቅባታል፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን ካህናት በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መሃል ሆነው አገልግሎት ይሰጡ ነበር፡፡ ቤተ መቅደስ እና ካህናት በሚል በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በጴጥሮስና በሌሎች ጸሐፊዎች በብዙ ቦታዎች የተጠቀሱት እነዚህ ቃላት ቤተ ክርስቲያንን እንደ እግዚአብሔር ሕያው መቅደስ--ሕዝቡን ደግሞ በካህናት መስለው ያቀርባሉ፡፡ ዛሬ ክርስቲያኖች እንዴት መኖርና አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው አስመልክቶ አንዳንድ እውነታዎችን ለመግለጽ የፈለገው ጴጥሮስ አማኞችን ወደ ብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዓት ሲያመላክት ይስተዋላል፡፡

ይህን ጥቅስ በድጋሚ ያንብቡ፡-- 1ጴጥ. 2፡5፡፡ “መንፈሳዊ መሥዋዕት ታቀርቡ ዘንድ” ሲል ምን ማለቱ ነው? ክርስቲያኖች እንደ ማኅበረሰቡ የአምልኮ አካልነታቸው ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነው?

ሚያዝያ 3
11-Apr

የእግዚአብሔር የኪዳኑ ሕዝቦች


በጴጥሮስ መልእክቶች ላይ ብሉይ ኪዳናዊው አመለካከት አጥብቆ ይስተዋላል፡፡ የአይሁድና የክርስትና ኃይማኖታዊ አስተምህሮ አማካይ ርዕሰ ጉዳይ የሆነው የኪዳኑ ጽንሰ ሃሳብ የዚሁ አመለካከት እምብርት ነው፡፡

ለመሆኑ ኪዳን ስንል ምን ማለታችን ነው?

በዕብራውያን ቤሪት በመባል የሚታወቀው “ኪዳን” የተሰኘው ቃል በሁለት ወገኖች መካከል የሚደረግን ሕጋዊ ውል ወይም ስምምነት ይገልጻል፡፡ ስምምነቱ በሁለት ግለሰቦች መካከል ሊፈጸም ይችላል (ለምሳሌ በላባና በያዕቆብ ዘፍ. 31፡44) ወይም በሁለት ንጉሦች መሃልም እንዲሁ (ለምሳሌ በሰሎሞን እና በኪራም)፡፡ ኪዳን-- በዳዊትና በእስራኤል ሽማግሌዎች መሃል እንደ ተደረገው ዓይነት በአንድ አገር ንጉሥና በሕዝቦቹ መካከልም ሊደረግ ይችላል (2ሳሙ. 5፡3)፡፡

በእግዚአብሔርና የአብርሃም ዝርያዎች በሆኑት ሕዝቦቹ መካከል የተደረገው በዓይነቱ ልዩ የሆነው የኪዳን ትስስር በገናናነቱ ይታወቃል፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡-- ዘፍ. 17:1–4፣ ዘፀ. 2:24፣ 24:3–8፡፡ እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር ስለገባው ኪዳን ምን ይነግሩናል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው መጽሐፍ የሆነው ኦሪት ዘፍጥረት እግዚአብሔር እንዴት ከአብሔርሃም ጋር ኪዳን እንደገባ ይነግረናል (ዘፍ. 15፡9-21፣ 17፡1-26)፡፡ እግዚአብሔር ይህን የገባውን ኪዳን በማሰብ ሕዝቡን ከግብፅ ባርነት ታደገ (ዘፀ. 2፡24)፡፡ እግዚአብሔር አስሩን ትእዛዛትና ሌሎች ሕጎችን ለእስራኤል ልጆች ሲሰጥ፤ ማለትም በሙሴ ጊዜ ይህን ኪዳን አድሶ ነበር (ዘፀ. 19:1–24:8፣ ዘፀ. 24:3–8)፡፡

ነገር ግን የኪዳኑ ተስፋዎች በሁኔታዎች ያልተገደቡ አልነበሩም፡፡ “እነዚህ ሕዝቦች የጌታን ፈቃድ ለመፈጸም ታማኝ እስከሆኑ ድረስ ሊያበዛቸውና የእጆቻቸውን ሥራ ሊባርክ ከእነርሱ ጋር ኪዳን ገባ፡፡”—Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 2, p. 574.

በእርግጥ ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ሕግ አለመታዘዙ ሊያመጣበት የሚችለውን አደጋ ነቢያት ኪዳኑን በማስታወስ እስራኤላውያንን በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል፡፡ ከተለመደው ወጣ ያሉትን ትንቢተ ዳንኤልንና ራእይ ዮሐንስን ትተን አብዛኞቹ በመጽሐፍ ቅዱስ የምናገኛቸው ትንቢቶች በሁናቴዎች የተወሰኑ ናቸው የሚል ሙግት አለ፡፡ ይህ ደግሞ የመታዘዝ ጸንሰ ሃሳብ ምን ያህል የኪዳኑ ተስፋዎች ማዕከል እንደሆነ ያሳያል፡፡ ኪዳናዊዎቹ የበረከት ተስፋዎች ለእግዚአብሔር ሕግ በመታዘዝ የተገደቡ--የጥፋትና ኩነኔ ትንቢት ግን የማይታዘዙትን ብቻ የሚጎበኝ ነበር፡፡

ከእግዚአብሔር ጋር በኪዳን መጣመር ለእርስዎ ምን ዓይነት ትርጉም አለው? ይህ ኪዳናዊ ግንኙነት በእርስዎ ላይ የሚያስቀምጠው ግዴታዎችስ ምንድን ናቸው?

ሚያዝያ 4
12-Apr

የንጉሥ ካህናት


ጌታ በኦሪት ዘፀአት መጽሐፍ ሙሴን እንዲህ ይለዋል “ከዚያም ሙሴ ወደ እግዚአብሔር መጣ፤ እግዚአብሔርም ከተራራው ጠራውና እንዲህ አለው ‘ለያዕቆብ ቤት የምትለው ለእስራኤልም ሕዝብ የምትናገረው ይህ ነው በግብፅ ላይ ያደረግሁትን፣ በንስርም ክንፍ ተሸክሜ ወደ ራሴ እንዴት እንዳመጣኋችሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል፡፡ አሁንም በፍጹም ብትታዘዙኝና ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ እነሆ ከአሕዛብ ሁሉ እናንተ የወተደደ ርስቴ ትሆናላችሁ፤ ምንም እንኳ ምድር ሁሉ የእኔ ብትሆንም፣ እናንተ ለእኔ የመንግሥት ካህናት የተቀደሰ ሕዝብ ትሆናላችሁ ለእስራኤላውያን የምትነግራቸው ቃሎች እነዚህ ናቸው ’ ” (ዘፀ. 19:3–6)፡፡

በእነዚህ ከመስቀሉ አንድ ሺ ዓመታት ቀደም ብለው በተነገሩ ቃላት የወንጌልን መልእክት እናገኛለን፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን ይቤዣል፣ ከኃጢአትና ከኃጢአት ግዞትም ይታደጋል--ከዚያም እንደ ተለዩ የኪዳኑ ሕዝቦች በእርሱና በዓለም ፊት በፍቅር እንዲታዘዙት ይጠይቃቸዋል፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡-- 1ጴጥ. 2:5፣ 9-10፣ ዘፀ. 19:6፡፡ ጴጥሮስ ክርስቲያኖችን “የንጉሥ ካህናት” እና “ቅዱስ ሕዝብ” (1ጴጥ. 2፡9) ብሎ የመጥራቱ ፍቺ ምንድን ነው? እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ክርስቲያንነታችን ግዴታዎቻችንን አስመልክቶ ሃሳቡ የተገለጸበት ቋንቋ ለእኛ ያለው መልእክት ምን ይመስላል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

“መንፈሳዊ ቤት”፣ “የተመረጠ ትውልድ”፣ “የንጉሥ ካህናት”፣ “ቅዱስ ሕዝብ” እና “እግዚአብሔር ለራሱ የለያችሁ ሕዝብ” በሚል በመጽሐፍ ቅዱስ የምናገኛቸው እነዚህ የክብር መጠሪያዎች እግዚአብሔር የአብርሃም ዘር ከሆኑ ሕዝቦቹ ጋር የነበረውን በዓይነቱ ልዩ የሆነ ግንኙነት ይገልጻሉ፡፡ አሁን ደግሞ ጴጥሮስ ያንኑ ቋንቋ ከአዲስ ኪዳን፣ ከየሱስና ከመስቀሉ ዐውድ ለቤተ ክርስቲያን አባላት ጥቅም ላይ ሲያውል እንመለከታለን፡፡ እነዚያ ለእስራኤላውያን ብቻ ተገብተው የነበሩ ኪዳናዊ ተስፋዎች አሁን አይሁዶችን ብቻ ሳይሆን ነገር ግን በየሱስ የሚያምኑትን አሕዛብ አማኞች በሙሉ እንዲያካትቱ ሆነው ተስፋፉ፡፡ አዎ--በየሱስ አማካይነት አሕዛብም የአብርሃም ልጆች ነን ለማለት ባለ መብት ሆኑ! “የክርስቶስ ከሆናችሁ፣ እናንተ የአብርሃም ዘር ናችሁ፤ እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ” (ገላ. 3:29)፡፡ ማንም ሰው ከየትኛውም ትውልድ ወይም ብሔር ቢሆን በክርስቶስ የዚህ “የንጉሥ ካህናት” አካል መሆን ይችላል፡፡

የተመረጠ ትውልድ እና የንጉሥ ካህናት የተሰኙትን ክብር ያላቸው መጠሪያዎች እንደ ማኅበረሰብም ሆነ እንደ ግለሰብ ለራሳችን ብናውላቸው ከዛሬው የክርስትና ሕይወታችን አኳያ ምን ዓይነት ትርጉም ሊኖራቸው ይችላል? ይህን ከፍ ያለ ጥሪ ሊያሳካ በሚችል በተሻለ መመላለስ የምንችለው እንዴት ነው?

ሚያዝያ 5
13-Apr

በክብር የተሞላውን ደኅንነት ለሌሎች ማጋራት Proclaiming the Praises


የአዲስ ኪዳኗን ቤተ ክርስቲያን ከብሉይ ኪዳን መልእክት ጋር ጎን ለጎን የማስኬዱ ነገር በደኅንነታችን፣ በመጠራታችንና በእግዚአብሔር በመመረጣችን ብቻ አያበቃም፡፡ ጥያቄው፡ የተጠራነውና የተመረጥነው ለምንድን ነው? የሚል ሲሆን ጴጥሮስ ለዚህ ፈጣን ምላሽ አለው፡፡ ይህ የተለየ ግንኙነት ዓላማ እንዳለው የሚጠቅሰው ጴጥሮስ--ክርቲያኖች ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሐን የተጠሩት የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንዲያውጁ (1ጴጥ. 2:9) መሆኑን ይነግረናል፡፡ ይህ-- የጥንት እስራኤላውያን እንዲያደርጉ የተሰጣቸው ሲሆን--እነዚህ ሕዝቦች ለዓለም ምስክር እንዲሆኑ በእግዚአብሔር ተጠርተው ነበር፡፡ መላውን ዓለም በእነዚህ ጥንታዊ የኪዳን ሕዝቦቹ አማካይነት መባረክ የእግዚአብሔር ዓላማ ነበር፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡-- ዘዳ. 4:6፣ 26:18-19፣ ኢሳ. 60:1–3፣ ዘካ. 8:23፡፡ ክርስቲያኖችና የጥንት እስራኤላውያን በአንድ የሚጋሩት ነጥብ ምንድን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የጥንት እስራኤላውያን እንደ ኪዳን ሕዝብነታቸው በጌታ የተሰጠውን ደኅንነት ለዓለም የማድረስ ተልዕኮ ነበራቸው፡፡ ተመሳሳይ መለኮታዊ ተልዕኮ ያላቸው ክርስቲያኖችም እንዲሁ የክርስትና ተሞክሮአቸውንና በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን ዕውቀት ለሌሎች እንዲያጋሩና እርሱ በክርስቶስ በኩል ለዓለም ያደረገውን እንዲያካፍሉ ተጠርተዋል፡፡ ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡-- 1ጴጥ. 2፡10 ጥቅሱ በአጠቃላይ የክርስቲያን ተልዕኮና ዓላማ ማእከል የሆነው ለምንድን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ይህ በኃጢአት የተነከረና በሞት ጥላ ስር የወደቀ ዓለም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚጠፋበት ቀን ተቃርቦአል፡፡ ሆኖም የሱስ ማንኛውንም ሰብዓዊ ፍጡር ከዚህ ጥፋት ለመታደግ ሲል ሕይወቱን ሰጥቶአል፡፡ እስራኤላውያን እንደ እግዚአብሔር ሕዝብነታቸው ከሌሎች ሕዝቦች ልቀው መገኘታቸው--የላቀ ኃላፊነት እንደነበረባቸው የሚያሳይ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ክርስቲያኖችም እንደ እግዚአብሔር ሕዝብነታቸው ከሌሎች ከፍ ባለ ማዕረግ መመላለሳቸው እሙን ነው፡፡ ይህ በከፍታ መመላለስ ሌሎችም የከፍታው ሕይወት ተጋሪ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን ግብዣ የማቅረብ ኃላፊነትን አካቶአል፡፡ ክርስቲያኖች አሁን የእርሱ ወገን ሕዝቦች መሆናቸው በ1ጴጥ. 2፡10 ተጠቅሶአል፡፡ በአንድ ወቅት ሕዝቡ ያልነበሩት እነዚህ ወገኖች አሁን ግን ምህረት ተቀብለው ቅዱስ ሕዝቦች ሆነዋል (ሆሴ. 1 እና 2)፡፡ “ቅዱስ” የተሰኘው ቃል ለአምልኮ የተለየ የሚል መጽሐፍ ቅዱሳዊ አንደምታ አለው፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኖች እንደ “ቅዱስ” ሕዝብ--ከዓለም የተለዩ መሆናቸው በሕይወታው ሊታይ ይገባል፡፡ እንዲሁም ሁሉም ለመሞቅ እንደሚከቡት በቀዝቃዛ ሌሊት እንደሚነድ እሳት መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ክርስቲያኖች ተካፋይ የሆኑትን ይህን በክብር የተሞላ ደኅንነት ለሌሎች የማጋራት ብርቱ ኃላፊነት ተቀብለዋል፡፡

ሚያዝያ 6
14-Apr

ተጨማሪ ሃሳብ፡-


“ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ዐይን እጅግ የከበረች ናት፡፡ እርሱ ዋጋ የሚሰጠው ለውጪያዊው ታይታ ሳይሆን ነገር ግን ከዓለም ለምትለይበት ውስጣዊ ታማኝ ቅድስናዋ ነው፡፡ አባላት በክርስቶስ ዕውቀት ማደጋቸውና መንፈሳዊ ተሞክሮን ያማከለ መሻሻል ማሳየታቸው እርሱ ቤተ ክርስቲያንን የሚለካበት መንገድ ነው፡፡

“ክርስቶስ የቅድስናንና ከራስ ወዳድነት የራቀን ፍሬ ከወይን ተክሉ ለማግኘት አጥብቆ ይሻል፡፡ የፍቅርንና የመልካምነትን መርኅዎች በህዝቡ ውስጥ ለመመልከት ይጠባበቃል፡፡ እጅግ ውብ የሚባሉ ማናቸውም የልዩ ተሰጥኦ የሥዕል ሥራ ውጤቶች በክርስቶስ ተወካዮች የሚገለጠውን የባህሪና የጸባይ ቁንጅና አጣምረው መያዝ አይችሉም፡፡ አምላካዊው ጸጋ የአማኙን ነፍስ እንደ ከባቢ አየር ዙሪያውን ሲሞላ--መንፈስ ቅዱስ በአእምሮውና በልቡ እየሠራ በሕይወት ላይ ሕይወት እንዲያድን መንስኤ ይሆነዋል፡፡ በዚህም እግዚአብሔር አገልግሎቱን ሊባርክ የሚችልበትን ቀዳዳ ያገኛል፡፡”—Ellen, G. White, Christ’s Object Lessons, p.


የመወያያ ጥያቄዎች:



ከጨለማ ወደ “አስደናቂ ብርሃኑ” መጠራት ማለት ምን ማለት ነው? ይህን ጽንሰ ሃሳብ በየሱስ ለማያምን ሰው መግለጽ ቢኖርቦት እንዴት ያስረዱታል? ጨለማ ምንድን ነው? ብርሃንስ? ከጴጥሮስ መልእክት አኳያ በእነዚህ በሁለቱ መካከል ያሉት ልዩነቶች ምንድን ናቸው? “ ‘ገብታችሁ በምትወርሷት ምድር እንድትፈጽሟቸው እግዚአብሔር አምላኬ ባዘዘኝ መሰረት ሥርዐትንና ሕግን አስተምሬአችኋለሁ፡፡ በጥንቃቄ ጠብቋቸው፤ ስለ እነዚህ ሥርዓቶች ሁሉ ለሚሰሙና “በእውነቱ ይህ ታላቅ ሕዝብ የቱን ያህል ጥበበኛና አስተዋይ ነው፡፡” ለሚሉ ሕዝቦች ይህ ጥበባችሁንና ማስተዋላችሁን ይገልጣልና፡፡ በምንጠራው ጊዜ ሁሉ አምላካችን እግዚአብሔር ለእኛ ቅርብ እንደ ሆነ አማልክቱ የሚቀርቡት ሌላ ታላቅ ሕዝብ ማነው? ዛሬ እኔ በፊታችሁ እንዳስቀመጥሁት ሕግ ያለ ጽድቅ የሆነ ሥርዓትና ሕግ ያሉት ሌላ ታላቅ ሕዝብስ ማነው?’ ” (ዘዳ. 4:5–8)፡፡ እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስትነታችን በእግዚአብሔር ከተሰጠንና እንድንሠራ ከተጠራንበት አኳያ እነዚህ ቃላት በምን መልኩ ለእኛ ገጣሚ ይሆናሉ?

 ጴጥሮስ “ጌታ መልካም መሆኑን ቀምሳችኋልና” (1ጴጥ. 2፡3) ሲል ምን ማለቱ ነው? የጌታን ጸጋ ቀምሰዋል?

 በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንዎ ዙሪያ እየሆነ ያለውን ነገር በጥንቃቄ ይመልከቱ፡፡ ቤተ ክርስቲያንዎም ሆነች አባል የሆኑት እርስዎ--ስለ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ወይም ስለ እምነታችን አንዳችም እውቀት ለሌላቸው ወገኖች ይህን እውነት ይፋ በማድረጉ ረገድ ምን እየሠሩ ነው?