በጎቼን መግብ፡ 1ኛ እና 2ኛ ጴጥሮስ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2017

ከሰኔ 10-16

13ኛ ትምህርት

June 17 - 23


የአንደኛና ሁለተኛ ጴጥሮስ አበይት ርዕሰ ጉዳዮች



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኢሳ. 53:5- 6፣ 9፣ ዘሌዋ. 16:16–19፣ 11:44፣ ሮሜ 13:1–7፣ 1ቆሮ. 14:40፣ 2ጢሞቴ. 3:16፡፡


የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - “ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት መስቀል ላይ ተሸከመ፤ በእርሱ ቁስል እናንተ ተፈውሳችኋል” (1ጴጥ. 2:24)፡፡

ሁ ለቱ የጴጥሮስ መጽሐፎች በክርስቲያኖች ላይ በተጨባጭ የደረሱ ችግሮችን ያማከሉ ጽሑፎች ይዘዋል፡፡ ሐዋርያው በአንደኛ መልእክቱ ያነሳው ግዙፍ ጉዳይ በክርስቲያኖች ላይ እያደረሰ የነበረውን ስደት የዳሰሰ ነበር፡፡ የሁለተኛው መጽሐፍ መልእክቱ ዐቢይ ርዕሰ ጉዳይ ደግሞ የሐሰት መምህራን ሁኔታ ነበር፡፡ በክርስቲያኖች ፊት ፈታኝ ተግዳሮቶች መደቀናቸውን ተከትሎ አንባቢዎቹን የማበረታታት እንዲሁም የማስጠንቀቅ ብርቱ ምኞት የነበረው ጴጥሮስ መልእክቱን በኃይልና በሥልጣን አስፍሮአል፡፡

ጴጥሮስ ነገረ መለኮትን ተጠቅሞ ለሁለቱም ጉዳዮች ምላሽ መስጠቱ ጽሑፉን የከበረ ያደርገዋል፡፡ ስደት በክርስቲያኖች ላይ ያደረሰው መከራ--የሱስ እኛን ለማዳን የተቀበለውን ሥጋይና ሞት ጴጥሮስ በጥልቅ እንዲያሰላስል አስችሎት ነበር፡፡ የሱስ ዳግም ከተገለጠ በኋላ የሐሰት መምህራን በተጨባጭ በአምላካዊው ፍርድ ፊት መቆማቸው--ጴጥሮስ በሁለቱ መልእክቶቹ የዳሰሳቸው አንኳር ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው፡፡

የዚህ ሩብ ዓመት የመጨረሻ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ጴጥሮስ ባሰፈራቸው በሚከተሉት አምስት ጭብጦች ዙሪያ ዝርዝር ትኩረት ያደርጋል፡፡ (1) የመዳናችን መንስኤ የሆነው የየሱስ መከራ፣ (2) እምነታችንን በተግባር ከመግለጻችን አኳያ በእግዚአብሔር ፍርድ ፊት የምንሰጠው ተጨባጭ ምላሽ (3) በቅርብ ገቢራዊ በሚሆነው የየሱስ ዳግም ምጽአት ላይ ያለን ተስፋ፣ (4) የማኅበረሰባዊውንና የቤተ ክርስቲያንን ሕግና ደንብ ማስጠበቅ (5) መጽሐፍ ቅዱስ ለህይወታችን ምሪት በመስጠት ያለው ሚና፡፡

ሰኔ 11
18-Jun

መከራ፣ የሱስና ደኅንነት


ከዚህ በታች የቀረቡትን ጥቅሶች በማንበብ ስለ ደኅንነት የሚገልጸውን እያንዳንዱን ነጥብ ለማስተዋል ይሞክሩ፤

1ጴጥ. 1:2 __________________________________________________________________________________

1ጴጥ. 1:8-9 ________________________________________________________________________________

1ጴጥ. 1:18-19 ______________________________________________________________________________

1ጴጥ. 2:22–25 ______________________________________________________________________________

1ጴጥ. 3:18 _________________________________________________________________________________

ጴጥሮስ ስለ መዳን ሲናገር መልእክቱን የሚያስተላልፈው የሱስ ለኃጢአተኞች ሲል ከተቀበለው መከራ ዐውድ ተነስቶ ነው፡፡ ለምሳሌ ሐዋርያው በ1ጴጥ. 2:22–24 ስለ የሱስ መከራ ሲጽፍ የተጠቀመው ቋንቋ በኢሳ. 53፡5-6፣9 የምናገኛቸውን ጥቅሶች ያንጸባርቃል--“ኃጢአታችንን በእንጨት መስቀል ላይ ሸከመ፤ በእርሱ ቁስል እናንተ ተፈውሳችኋል” (1ጴጥ. 2፡22-24)፡፡

በብሉይ ኪዳን የኃጢአት መሥዋዕት ሥርዓት--ኃጢአተኛው ለበደሉ ማስተሰርያ የሚሆነውን እንስሳ ይዞ ወደ ቤተ መቅደሱ በመቅረብ እጁን እንዲጭንበት ይደረግ ነበር፡፡ የበደለኛው ኃጢአት ወደ እንስሳው በሚተላለፍበት በዚህ ምሳሌያዊ ሥርዓት እንስሳው ስለ በደለኛው መተላለፍ የኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ ይታረድ ነበር (ዘሌዋ. 4:29-30፣ 33-34፣ 14:10–13)፡፡ በስርየት ቀን በመሠዊያው ላይ የተከማቸው ኃጢአት እንዲነጻና እንዲወገድ ይደረጋል (ዘሌዋ. 16፡16-19)፡፡ በመሥዋዕትነት የቀረበው የእንስሳ ደም፤ ኃጢአትን በማንጻቱ ረገድ እጅግ ቁልፍ ሚና ነበረው፡፡ ክርስቲያኖች እንከን በሌለበት በከበረው የየሱስ ደም ተዋጅተዋል (1ጴጥ. 1፡18-19)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም ከዚህ ተመሳሳይ ጽንሰ ሃሳብ በመጋራት-- ኃጢአት የማያውቀው የሱስ ስለ እኛ ኃጢአት ሆነ ሲል ይነግረናል (2ቆሮ. 5፡21)፡፡ ሐዋርያው በ1ጴጥ. 3፡18 እንደጠቀሰው--ጻድቁ ጻድቅ ላልሆንነው ስለ እኛ ኃጢአት መከራ ተቀበለ፡፡

እንደ ጳውሎስ ሁሉ (ሮሜ 3፡21-22) ጴጥሮስም ስለ እምነት አስፈላጊነት አጽንኦት ይሰጣል፡ “እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤… የእምነታችሁን ፍጻሜ እርሱም የነፍሳችሁን ድነት እየተቀበላችሁ ነውና” (1ጴጥ. 1:8, 9)፡፡ ደኅንነት የመልካም ምግባር ባለቤት በመሆን አይገኝም፡፡ ይልቁንም የሱስ ለእኛ ያደረገውን ስናምንና እርሱን እንደ ግል አዳኛችን ስንቀበል የደኅንነት ባለቤት እንሆናለን፡፡ የመዳናችን መሰረት እርሱ እንጂ ራሳችን አይደለንም፡፡ ሆኖም የዳንነው በራሳችን ቢሆን ኖሮ እንዴት ነው የተረጋገጠ ተስፋ ሊኖረን ይችል የነበረው?

በእኛ ምትክ መከራ የተቀበለው የሱስ የመዳናችን ታላቅ ተስፋ የሆነው እንዴት ነው? ከዚህ አስደናቂ እውነት ምን ዓይነት መጽናኛ ማውጣት ይችላሉ?

ሰኔ 12
19-Jun

እንዴት ዓይነት ሰዎች ልንሆን ይገባል?


ጴጥሮስ ከመልእክቶቹ መካከል በተደጋጋሚ መለስ ቀለስ የሚልበትን ርዕሰ ጉዳይ በ2ጴጥ. 3፡11 በጥያቄ መልክ አቅርቦታል፡ “እንግዲህ ሁሉም ነገር በዚህ ሁኔታ የሚጠፋ ከሆነ፣ እናንተ እንዴት ዐይነት ሰዎች ልትሆኑ ይገባችኋል?”

ጴጥሮስ ስለ ክርስቲያናዊ ባህሪ ምን ይለናል? ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ጴጥ. 1:15–17፣ 22፣ 1ጴጥ. 2:1፣ 1ጴጥ. 3:8-9፣ 1ጴጥ. 4:7–11፣ 2ጴጥ. 3:11፡፡



--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጴጥሮስ በሁለቱም መልእክቶቹ በክርስቲያናዊ ባህሪ ዙሪያ አጽንኦት ይሰጣል፡፡ በሐዋርያው ጽሑፎች ብዛት ያላቸው ርዕሰ ጉዳዮች በተደጋጋሚ ሲከሰቱ መመልከታችን የተለመደ ነው፡፡ በቅድሚያ ጴጥሮስ በእግዚአብሔር ፍርድና በክርስትና ባህሪ መካከል ስላለው የግንኙነት መስመር ሁለት ጊዜ አጽንኦት ይሰጣል (1ጴጥ. 1:17፣ 2ጴጥ. 3:11)፡፡ እያንዳንዱ ሰው እምነቱን በተግባር መግለጡ ተገቢ ከመሆኑ አንጻር በእግዚአብሔር ፊት ይዳኛል፡፡ ስለዚህ ክርስቲያን የቅድስና ህይወት እንዲመራ ይጠበቅበታል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ፡--ጴጥሮስ ደጋግሞ የሚጠቅሰው ክርስቲያኖች የተቀደሰ ህይወት ሊመሩ ይገባል የሚለውን ነጥብ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት--ቅዱስ የተባሉ ነገሮች ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት (ዘፀ. 26:34፣ 28:36፣ 29:6፣ 37) ወይም ለእግዚአብሔር ዓላማ (ለምሳሌ ሰንበት ዘፍ. 2፡3) ይለዩ ነበር፡፡ በእርግጥ የእግዚአብሔር ዓላማ ሕዝቡ እንደ እርሱ ቅዱስ እንዲሆን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ጴጥሮስ በመልእክቱ የዳሰሰው ጉዳይ እንደሆነ እንመለከታለን (ዘሌዋ. 11:44፣ 19:2፣ 1ጴጥ. 1:15-16)፡፡ አንድን ነገር ለተቀደሰ መንፈሳዊ ተግባር ለይቶ ማዋል “መቀደስ” በሚል ስያሜ ይታወቃል፡፡ በተመሳሳይ ጴጥሮስ አንባቢዎቹ በመንፈስና የሱስን በመታዘዝ ይቀደሱ ዘንድ ምኞቱ ነበር (1ጴጥ. 1፡2)፡፡

በሦስተኛ ደረጃ፡--በክርስቶስ የተቀደሱ ወገኖች ለእነርሱ ገጣሚ ካልሆኑ ባህሪያት ራሳቸውን እንዲያርቁ ጴጥሮስ በተለይ ያስቀመጣቸው ጥቂት መዘርዝሮች አሉ፡-- ክፋት፣ ማታለል፣ ግብዝነት፣ ቅናት፣ ሐሜት (1ጴጥ. 2፡1)፡፡ ለጌታ የተለዩ አማኞች በአንድ ሐሳብ የሚስማሙ፣ እርስ በርሳቸው የሚተሳሰቡ፣ ርኅሩኆችና ትሑታን ሊሆኑ ይገባል (1ጴጥ. 3፡8-9)፡፡ በእውነተኛ መንፈሳዊነት ላይ ወንድማዊ መተሳሰብን፣ በወንድማዊ መተሳሰብ ላይ ፍቅርን መጨመር ከተቀደሱ ክርስቲያኖች ይጠበቃል (2ጴጥ. 1፡5-7)፡፡ በእርግጥ እያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው ያለማቋረጥ ፍቅርን ሊገልጽ የተገባ ነው (1ጴጥ. 4፡7-11)፡፡ በመጨረሻ--አድማጮቹ የሚያስጨንቃቸውን ሁሉ በየሱስ ላይ እንዲጥሉ ሐዋርያው ያደፋፍራል (1ጴጥ. 5፡7)፡፡

ክርስቲያኖች በማያስፈርድባቸው አምላካዊ ፈቃድ መሰረት ሊመላለሱ ይገባል ሲል ጴጥሮስ በሁለቱ መጽሐፎቹ በሚያቀርበው ጥሪ መሰረት ወገኖች ይመላለሱ ዘንድ አንዳችን ሌላውን ማበረታታት መማር የምንችለው እንዴት ነው?

ሰኔ 13
20-Jun

በዳግም ምጽአቱ ላይ ተስፋ ማድረግ


የሚከተሉትን ጥቅሶች ካነበቡ በኋላ በመጨረሻ ስለሚሆነው ነገር የተነገረውን በጥልቅ ለማስተዋል ይሞክሩ፡

1ጴጥ. 1:4 __________________________________________________________________________________

1ጴጥ. 1:17 _________________________________________________________________________________

1ጴጥ. 4:5-6 ________________________________________________________________________________

1ጴጥ. 4:17 _________________________________________________________________________________

2ጴጥ. 3:1–10 _______________________________________________________________________________

የጴጥሮስን የመጀመሪያ መልእክት የሚያነቡ ወገኖች በቅድሚያ ከሚያገኟቸው አንግብጋቢ ጉዳዮቹ አንዱ ስደት ነው፡፡ ምንም እንኳ ምድራዊ ህይወታቸው በስደት ቢሰናከልም ነገር ግን ማንም ሊነጥቃቸው የማይችል ሽልማት በሰማይ እንደሚጠብቃቸው በመንገር ጴጥሮስ አንባቢዎቹን ያጽናናል፡፡ ክርስቲያኖች በሰማይ የማይጠፋና የማይበላሽ ርስት እንደተዘጋጀላቸው ሐዋርያው ቀደም ባለው የመጀመሪያው መጽሐፉ ይጠቅሳል (1ጴጥ. 1፡4)፡፡

ጴጥሮስ በመጨረሻ ገቢራዊ የሚሆኑትን ሁለት ነገሮች በደማቁ የሚያሳየን ሲሆን አነርሱም--የመጨረሻው ፍርድ እና የክፉው በእሳት መውደም ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር ምንም እንኳ ስደት ዛሬም ቢኖርም--ፍትሕና ፍርድ ግን ይሰጣል፡፡ አማኞችም ዘላለማዊ ሽልማታቸውን ይቀበላሉ፡፡

ጴጥሮስ በሦስት የተለያዩ ምክንያቶች ስለ ፍርድ ይጠቅሳል (1ጴጥ. 1:17፣ 4:5-6፣ 17)፡፡ እግዚአብሔር አብ መላውን ሰብዓዊ ፍጡር እንደ ሥራው ያለ አድሎ እንደሚዳኝ (1ጴጥ. 1፡17) የሚናገረው ጴጥሮስ የሱስ ራሱ በሕያዋንንና በሙታን ላይ ሊፈርድ መዘጋጀቱን ይጠቁመናል (1ጴጥ. 4፡5)፡፡ እንዲሁም ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት እንደሚጀምር የሚያወሳውን ማራኪ ምልከታ ያካፍለናል (1ጴጥ. 4፡17)፡፡

በተጨማሪ ጴጥሮስ “ክፉ ምኞት የሚከተሉ” ሰማያትንና ምድርን በሚበላው እሳት ይጠፋሉ በማለት ይናገራል (2ጴጥ. 3፡7)፡፡

በየሱስ ዳግም መገለጥ እርግጠኝነት ዙሪያ የተነሱ አንዳንድ ችግሮችን ለመፍታት በቂ ጊዜ (2ጴጥ. 3፡1-10) ሲወስድ የሚተዋለው ጴጥሮስ--ጌታ “የዘገየ” ቢመስልም ነገር ግን ይህ የሆነው ማንም እንዳይጠፋና ሁሉም በንስሐ በፊቱ እንዲቀርብ በመታገስ መሆኑን ይገልጻል፡፡ እንዲሁም የዛሬው የእያንዳንዱ ሰው የተቀደሰና እንከን የለሽ ህይወት--የወደፊቱን በብሩህ በተስፋ የተሞላና የተረጋገጠ አድርጎ ለመገመት እንደሚያስችል ይናገራል፡፡

ሐዋርያው የቱንም ያህል በምድራዊው የተቀደሰ ህይወትና በተጨባጩ የክርስትና አኗኗር ዙሪያ ትኩረት ቢያደርግ፤ አንባቢዎቹ የሚጠብቃቸውን የወደፊት ተስፋ ከማመላከት ወደ ኋላ ያለበት ጊዜ የለም፡፡ በአጭሩ--ይብዛም ይነስ የዛሬው የዕለት ከዕለት ህይወታችን በእምነትና በመታዘዝ ወደፊት እንድናመራ ኃይል ሊሆነን ይገባል፡፡

እርስዎ በየትኛውም ሁናቴ ላይ ቢገኙ--በእምነትና በመታዘዝ ወደፊት መጓዝዎን መቀጠል የሚኖርብዎት ለምንድን ነው? ከዚህ ውጪ የተቀመጠ ምን ዓይነት አማራጭ አለ?

ሰኔ 14
21-Jun

የማኅበረሰባዊውንና የቤተ ክርስቲያንን ሕግና ደንብ ማስጠበቅ


ከዚህ በታች የቀረቡትን ጥቅሶች ያንብቡ፡፡ ጴጥሮስ በመንግሥታዊውና ቤተ ክርስቲያናዊው አመራር አስፈላጊነት እንዲሁም ክርስቲያኖች ለሁለቱም አካላት ሊሰጡ ስለሚገባው ምላሽ ምን ይላል? በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ብንኖር-- የሐዋርያውን ጽሑፍ ከዛሬው ሁኔታችን አኳያ ጥቅም ላይ ማዋል የምንችለው እንዴት ነው?

1ጴጥ. 2:11–21 __________________________________________________________________________________

1ጴጥ. 5:1–5 ____________________________________________________________________________________

ጴጥሮስ በመንግሥት ኃይሎችና በኃይማኖት መሪዎች አማካይነት በክርስቲያኖች ላይ አልፎ አልፎ ስደት ይደርስ በነበረበት ዘመን የኖረ ሐዋርያ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ እማኝነቱ መንግሥት ሕዝብን በመምራትና በማስተዳደር በሚኖረው አግባብ ያለው ሚና ዙሪያ እርሱና ጳውሎስ ትርጉም ያለው መልእክት እንዲጽፉ መንስኤ እንደሆናቸው ይታመናል (1ጴጥ. 2:13–17፣ ሮሜ 13:1–7)፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ክፉ አድራጊዎችን ለመግታት በራሱ በእግዚአብሔር ኃላፊነት ላይ እንደተቀመጡ ጴጥሮስም ሆነ ጳውሎስ ያስቡ ነበር፡፡ በእርግጥ በሥልጣን ላይ ያለው ኃይል ችግር የሚሆንበትም ጊዜ አለ፡፡ በጴጥሮስ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች የዚህ ችግር ሰለባ የነበሩ ሲሆን ሁናቴው ከመሻሻል ይልቅ ለተጨማሪ አያሌ ዓመታት እየተባባሰ ቀጥሎ ነበር፡፡

ነገር ግን ጉዳዩ በጥቅሉ ሲታይ--ሕግና ደንብ ማስከበር እንዲሁም የማኅበረሰቡን ደኅንነት ማስጠበቅ ከመልካም አስተዳደር ይጠበቃል፡፡ ዛሬም በዚህ ዘመን ሕግና ደንብ የሚጥሱ ኢፍትሐዊ አሠራሮችን ስንመለከት ዜጎችን በቅንነት የሚያስተዳድር የሥርዓት እጦት መኖሩን መረዳት እንችላለን፡፡ መልካም አስተዳደር እግዚአብሔር ለሰብዓዊው ፍጡር ከሰጣቸው በረከቶች አንዱ መሆኑ እሙን ነው፡፡

ጴጥሮስ በመልካም የቤተ ክርስቲያን አመራር አስፈላጊነት ዙሪያ የጳውሎስን ሃሳብ ያለ አንዳች ማንገራገር ይጋራል፡፡ የቤተ ክርስቲያን የአምልኮ መርኅ ግብር “በአግባብና በሥርዓት ይሁን” (1ቆሮ. 14:40) ሲል ሐዋርያው ጳውሎስ ይሞግታል፡፡ በተመሳሳይ ጴጥሮስ “በእናንተ ኀላፊነት ሥር ያለውን የእግዚአብሔር መንጋ ጠብቁ” (1ጴጥ. 5:2) በማለት ለቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ይነግራል፡፡ መሪዎች በትህትናና በእንክብካቤ ይህን እንዲያደርጉም ይጠይቃል፡፡ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኖች መልካም አመራር ሊኖራቸው ይገባል፡፡ መልካም መሪዎች ራእይና አመክንዮአቸውን በሥራ ላይ እያዋሉ አባላት ለእግዚአብሔር ክብር የሚውለውን መንፈሳዊ ስጦታዎቻቸውን እንዲለማመዱ ያደፋፍራሉ፡፡

ጴጥሮስ--ሁላችሁም እርስ በርስ በመከባበር ትህትናን ልበሱ በማለት በ1ጴጥ. 5፡5 ይናገራል፡፡ ይህን ማድረግ መማር የምንችለው እንዴት ነው? እርስዎ ከወንድም እህቶች ጋር ባሎት ግንኙነት ይህን ጥቅም ላይ ለማዋል ምን ማድረግ ይችላሉ?

ሰኔ 15
22-Jun

የአምላካዊ ቃል ሥልጣን


ከዚህ በታች የቀረቡትን ጥቅሶች ያንብቡ፡፡ ዛሬን ማስተዋል ስለሚያስችለን መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላሉ? አምላካዊው ቃል በህይወታችንና በእምነታችን ላይ ምን ዓይነት ሚና ሊኖረው ይገባል?

1ጴጥ. 1:10–12 __________________________________________________________________________________

2ጴጥ. 1:16–20 __________________________________________________________________________________

2 ጴጥ. 3:2 _____________________________________________________________________________________

2 ጴጥ. 3:16 ____________________________________________________________________________________

ጴጥሮስ በሁለተኛው መልእክቱ የሐሰት መምህራንን ፊት ለፊት ይጋፈጣል፡፡ ሐዋርያው “ደግሞም ቀድሞ በቅዱሳን ነቢያት የተነገረውን ቃል እንዲሁም በሐዋርያት አማካይነት በጌታችንንና በአዳናችን የተሰጠውን ትእዛዝ እንድታሰቡ ነው” (2ጴጥ. 3:2) ሲል አንባቢዎቹን ወደ ሁለት የሥልጣን ምንጮች ያመላክታል፡፡

ዛሬ እኛም ተመሳሳይ ርዳታና ምክር ልናገኝ የምንችልባቸው የብሉይ ኪዳን “ቅዱሳን ነቢያት” አሉን፡፡ ምንም እንኳ ህያዋን የዓይን ምስክሮቹ ሐዋርያት በአካል አብረውን ባይሆኑም ከዚያ የተሻለው ግን በእጃችን አለ--በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የጻፏቸው የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት! ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ--የየሱስን ህይወት፣ ሞትና ትንሣኤ የሚገልጠውን ታሪክ ትተውልናል፡፡ የሐዋርያቱ ዝርዝር እንቅስቃሴ መግለጫ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ቀርቦልናል፡፡ ደግሞም ሐዋርያቱ ራሳቸው በመንፈስ ቅዱስ ተነክተው ያሰፈሯቸውን ሃሳቦች ማግኘታችን እሙን ነው፡፡ ጳውሎስ የእግዚአብሔር ቃል ስላለው ሥልጣን አበክሮ ይናገራል (2ጢሞቴ. 3፡16) ፡፡ ጴጥሮስም እንዲሁ መጽሐፍ ቅዱስ በኃይማኖታዊ አስተምህሮና በሥነ ምግባር ላይ ሥልጣን አለው ሲል ወደዚሁ አምላካዊ ቃል ይመላክታል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ የእውነት ምንጭ ቢሆንም ነገር ግን መልእክቱን መንፈስ ቅዱስ እንዲገልጥልን በመፍቀድ በጥንቃቄ ለማጥናት ካልሞከርን ይኸው የእውነት ምንጭ ራሱ በስህተት ሊስተዋልና ወደ ከፋ ስህተት ሊመራን ይችላል ሲል ሐዋርያው በ1ጴጥ. 3፡1 አንባቢዎቹንና አድማጮቹን ያስጠነቅቃል፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስን መሰረታዊ መርኅዎች ለማጥናት የእግዚአብሔር ቃል ራሱ ጥሩ መርጃ መሣሪያ ሊሆነን ይገባል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅስ በጸሎት መንፈስ ሆነን ማንበብ ይኖርብናል፡፡ አንድን መልእክት የምናነበው ከምዕራፉ፣ ከመጽሐፉና ከራሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ዐውደ ሃሳብ አከኳያ ሊሆን ይገባል፡፡ ጸሐፊው መልእክቱን ሲያሰፍር በተለይ እየተናገረ የነበረው ስለምንድን ነው? መልእክቱ የተጻፈባቸውን ታሪካዊ ሁነቶች በብርሃንነት ተጠቅመን ማንበብ ተገቢነት ይኖረዋል፡ (ለምሳሌ ሁለቱ የጴጥሮስ መልእክቶች የተጻፉት በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት የሮም መንግሥት አገዛዝ ዘመን ነበር)፡፡ መዳንን ያስገኘው የክርስቶስ መሥዋዕትነት ሞት የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ማዕከላዊ ክፍል መሆኑን በመንዘብና መንፈሳዊውን ብርሃን ለማግኘት በመሻት መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ይኖርብናል (1ጴጥ. 1:10–12) ፡፡ በመጨረሻ--መጽሐፍ ቅዱስን የገዛ ህይወታችን ከሚገኝበት ዐውድ አኳያ ማንበባችን ተገቢ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ--የትኛውን እውነት እንድንቀበል ነው? አምላካዊው ቃል የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የሚያስችል አዎንታዊ አስተዋእጾ በህይወታችን በሚያመጣ መልኩ ጥቅም ላይ የምናውለው እንዴት ነው?

ሰኔ 16
23-Jun

ተጨማሪ ሃሳብ፡-



ለክርስትና ህይወትና ለእርስ በርስ ግንኙነት ብርቱ አጽንኦት የሚሰጡት ሁለቱ የጴጥሮስ መልእክቶች ጠጠር ካሉት የነገረ መለኮት አስተምህሮዎች ተርታ መመደብ የሚችሉ ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር የሱስ እንዳለው እውነትን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ሆኖም ከዚያ በላቀ--በእውነት ልንኖርና ልንመላለስም ይገባል፡፡ ቀደም ባለው ጥናታችን ይህን ከፍ ያለ ሃሳብ ተመልክተናል “እንግዲህ ለእውነት በመታዘዝ ነፍሳችሁን ስላነጻችሁ፣ ለወንድሞቻሁ ቅን ፍቅር ይኑራችሁ፤ እርስ በርሳችሁም አጥብቃችሁ ተዋደዱ” (1ጴጥ. 1:22)፡፡ እዚህ ላይ ጴጥሮስ የነፍሳችንን መንጻት ከመታዘዝና ከእውነት ጋር እንዴት እንደሚያያይዘው ልብ ማለቱ ተገቢ ነው፡፡ እውነት ይለውጠናል፣ “በንጹህ ልብ” እርስ በርሳቸው አጥብቀው የሚወቀደዱ ሰዎችም ያደርገናል፡፡ መታዘዝ፣ የልብ ንጽህናና ፍቅር-- እነዚህ ሦስቱ እርስ በርስ የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ይህ የራሳችን ለማድረግ አጥብቀን ልንጥር የሚገባ ምርጥ ነገር ነው፡፡ ይህን ትእዛዝ ተከትለን ቢሆን ህይወታችንና ቤተ ክርስቲያናችን አሁን ከያዘው ገጽታ ምን ያህል የተለየ ይሆን እንደ ነበር መገመት ይችላሉ? ሌላው ቢቀር ለቤተ ክርስቲያን ኅበረት ስለሚኖረው ፋይዳ ያስቡ፡፡

“ወንድሞች፤ ከቤተ ክርስቲያን ወደ ቤትም ሆነ ከቤት ወደ ቤተክርስቲያን ስትመላለሱ የክርስቶስ መንፈስ አብሯችሁ ነቀፋን ታስወግዳላችሁ? ከመቼውም ይልቅ ሳንነጣጠል በአንድነት የምንሠራበት ጊዜ ላይ እየተቃረብን እንገኛለን፡፡ በኅብረት ውስጥ ጥንካሬ አለ፡፡ ካለመስማማትና ከመለያየት ሊገኝ የሚችለው ደካማነት ብቻ ነው”—Ellen G. White, Selected Messages, book 2, pp. 373, 374.


የመወያያ ጥያቄዎች:



ሐዋርያው በ2ጴጥ. 3፡12 መልእክቱ “ደግሞም የእግዚአብሔርን ቀን እየተጠባበቃችሁ መምጫውን ልታፋጥኑ ይገባል፡፡ በዚያን ቀን ሰማያት በእሳት ተቃጥለው ይጠፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በታላቅ ትኩሳት ይቀልጣል” በማለት ጽፎአል፡፡ የእግዚአብሔርን መምጫ “ልታፋጥኑ” ይገባል ሲል ምን ማለቱ ነው? የክርስቶስ ዳግም ምጽአት የሆነውን የእግዚአብሔር ቀን ማፋጠን የምንችለው እንዴት ነው?

ተፈጥሮ የእግዚአብሔር “ሁለተኛው” መጽሐፍ እንደሆነ እንናገራለን፡፡ የሚያሳዝነው ይህ ሁለተኛ መጽሐፍ እንደ መጀመሪያው (መጽሐፍ ቅዱስ) ሁሉ የተሳሳተ ፍቺ ሲሰጠው ይታያል፡፡ ለምሳሌ የምድር አፈጣጠር ንድፍና ዓላማ ከብዙዎች አእምሮ ተደምስሶ በዳርዊን የዘፈቀደ ዝግመተ ለውጥ አመለካከት አራማጆች ተተክቶአል፡፡ ይህች ዛሬ የምንመለከታት ዓለም የአምላካዊው ንድፍ ውጤት ሳትሆን ምድር በራሷ ያገኘችው ገጽታ እንደሆነ እየነገሩን--ሁለተኛውን መጽሐፍ በትክክለኛ መንገድ መተርጎም የምንችለው እንዴት ነው? ሁለተኛው መጽሐፍ ስለ እግዚአብሔር ሊያስተምረን የሚችለው እስከ የት ድረስ ነው? ሁለተኛውን መጽሐፍ በትክክል ለማስተዋል ከመጀመሪያው መጽሐፍ ልናገኝ የምንችለው እርዳታ ምንድን ነው? ስለ ተፈጥሮ ማለትም ስለ ሁለተኛው መጽሐፍ የምንሰጠው አተረጓጎም ከመጀመሪያው መጽሐፍ ማለትም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሲቃረን ምን ሊከሰት ይችላል? ችግሩ ያለው የት ላይ ነው?