በጎቼን መግብ፡ 1ኛ እና 2ኛ ጴጥሮስ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2017

ከግንቦት 26-ሰኔ 2

11ኛ ትምህርት

June 3 - 9


የሐሰት መምህራን



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 2ጴጥ. 2:1- 22፣ ዮሐ. 8:34-36፣ ማቴ. 12:43-45፣ ይሁዳ 4-19፣ ዘፍ. 18:16-33፡፡


የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - “እነርሱ ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው ሳሉ፣ ሌሎችን ነጻ ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጧቸዋል፤ ሰው ለተገዛለት ለዚያ ነገር ባሪያ ነውና” (2ጴጥ. 2:19)፡፡

ጴ ጥሮስ እንደ መጋቢነት ከነበረው መቆርቆር በመጀመሪያው ደብዳቤው አንባቢዎቹ ከተጋረጠባቸው የስደት መከራ ሊያበረታታቸው ፈልጎ ነበር፡፡ ምንም እንኳ እርሱ በተለይ የጠቀሰው ስደት ምን ዓይነት ቅርጽ እንደነበረው በትክክል ባናውቅም ነገር ግን አረማዊው የሮም አስተዳደር ዝናው እየናኘ የመጣውን የክርስትና እንቅስቃሴ ለማጥፋት ከነበረው ምኞት አኳያ ቤተ ክርስቲያን ለአስከፊ መከራ ልትዳረግ እንደምትችል እናውቃለን፡፡

ነገር ግን ሰይጣን በሁለት አቅጣጫ ውጊያ ከፈተ፡፡ አንደኛው በግልጽ የሚታወቀው ከውጪ የሚሰነዘረው በጭካኔ የተሞላ ነውጠኛ ጥቃት ሲሆን ሌላው ግን ምናልባትም ከዚህ እጅግ አደገኛው--ከውስጥ የተሰነዘረ ጥቃት ነበር፡፡ ቀደም ያሉት የአይሁድ ሕዝቦች ከሐሰተኛ ነቢያት ጋር መጋፈጥ እንደ ነበረባቸው ሁሉ በጴጥሮስ ዘመን የነበሩትም የየሱስ ተከታዮች “ጥፋት የሚያስከትል የስህተት ትምህርት በስውር” (2ጴጥ. 2:1) ወደ ቤተ ክርስቲያን ከሚያስገቡ ሐሰተኛ መምህራን ጋር መጋፈጥ ነበረባቸው፡፡ ከዚህ የከፋው ደግሞ--ብዙዎች ይህን “አስነዋሪ ድርጊቶቻቸውን ይከተላሉ” ሲል ጴጥሮስ ማስጠንቀቁ ነው፡፡ ጴጥሮስ ማስጠንቀቂያ ከሰጠባቸው ከእነዚህ ትምህርቶች መካከል አንዳንዶቹ ምን ነበሩ? የጴጥሮስ ምላሽ ምን ነበር? እኛም ከውስጥ የሚነሱ አደገኛ ሁናቴዎችን እየተጋፈጥን ከመሆናችን አኳያ ከእርሱ ማስጠንቀቂያ ምን መቅሰም እንችላለን?

ግንቦት 27
4-Jun

ሐሰተኞች ነቢያትና መምህራን


ስለ ቀደሙት የየሱስ አማኞች ስናስብ በመሃላቸው እጅግ ሰላማዊ ኅብርና መተሳሰብ እንደ ነበር በመገመት ያቺን ቤተ ክርስቲያን ፍጹም አድርገን ለመሳል በጣም ይቀለናል፡፡ ሆኖም እንዲህ ያለው ግምት የተሳሳተ ነው፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ገና ከየሱስ ጊዜ አንስቶ ከውስጥ የሚነሱ ፍትጊያዎችን አስተናግዳለች (ስለ ይሁዳ ያስቡ)፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ከደረሱባት አያሌ ችግሮች መካከል የአብዛኞቹ መንስኤ ከውስጥ የተነሱ ሐሰተኛ መምህራን መሆናቸውን የአዲስ ኪዳን መልእክቶች ያሳዩናል፡፡ ቀደምቷ ቤተ ክርስቲያን የተፋለመችው ከውጨኛው የስደት መከራ ጋር ብቻ ሳይሆን ከውስጥ ከተነሱ ችግሮችም ጋር ነበር፡፡ ጴጥሮስ በዚህ መልእክቱ ቤተ ክርስቲያን የገጠሟት አንዳንድ የውስጥ ተግዳሮቶች ምን እንደነበሩ እንደሚከተለው ያነሳል፡፡ “ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት በሕዝቡ መካከል እንደ ነበሩ እንዲሁም በእናንተ መካከል ሐሰተኞች መምህራን ይነሣሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው ጥፋት የሚያስከትል የስሕተት ትምህርት በስውር ያስገባሉ፤ በዚህም በራሳቸው ላይ ድንገተኛ ጥፋት ያመጣሉ፡፡ ብዙዎች አስነዋሪ ድርጊቶቻቸውን ይከተላሉ፤ በእነርሱም ምክንያት የእውነት መንገድ ይሰደባል፡፡ እነዚህ ሐሰተኛ መምህራን እየተስገበገቡ በፈጠራ ታሪካቸው ይበዘብዙዋችኋል፡፡ ፍርዳቸው ከጥንት ጀምሮ ዝግጁ ነው፤ መጥፈያቸውም አያንቀላፋም” (2ጴጥ. 2:1-3)፡፡ መልእክቱ ታላቅ ሰላም ይሰፍናል--በወንድምና እህቶች መካከል አስደናቂ ኅብርና መተሳሰብ ይሰርጻል የሚል አንደምታ ይኖረው ይሆን?

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡-- 2ጴጥ. 2፡1-3፣ 10-22፡፡ ጴጥሮስ ስለ ምን እያስጠነቀቀ ነው? በአብያተ ክርስቲያናቱ ተደማጭነት አግኝተው የነበሩ አንዳንድ የሐሰት አስተምህሮዎች ምን ነበሩ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጴጥሮስ ደብዳቤውን እንዲጽፍ ከጌታ መነሳሳት ያገኘበትን ምክንያት 2ጴጥ. 2፡1 ይገልጽልናል፡፡ ጥንት በአይሁዳውያን ዘመን የሐሰት ነቢያት ተነስተው እንደ ነበር በተመሳሳይ ወደፊት ሐሰተኛ መምህራን ይኖራሉ ሲል ሐዋርያው እያስጠነቀቃቸው ነበር፡፡ ጴጥሮስ እነዚህ መምህራን “ጥፋት የሚያስከትል የስህተት ትምህርት” (2ጴጥ. 2፡1) ከማሰራጨት--ሌሎችን የጥፋት ባሪያ (2ጴጥ. 2፡19) አድርጎ እስከ መምራት ይደርሳሉ ሲል ይከሳቸዋል፡፡ እነዚህ በእርግጥ አደገኛ ትምህርቶች መሆናቸውን ብርቱ አጸፋዊ ምላሽ ከሰጠው የጴጥሮስ መልእክት መመልከት እንችላለን፡፡

ጴጥሮስ በሐሰተኛ መምህራን ላይ የነበረው ተቃውሞ ምን ያህል ጥብቅ እንደ ነበር ይመልከቱ፡፡ እውነት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይህ ምን ይነግረናል? የሐሰት አስተምህሮን ወደ ቤተ ክርስቲያን ለማምጣት ከሚደረገው ማንኛውም ዓይነት ሙከራ ራሳችንን መከላከል የምንችለው እንዴት ነው?

ግንቦት 28
5-Jun

በክርስቶስ ነጻ መውጣት?


“ከንቱ ቃል እየደረደሩ በስሕተት ከሚኖሩት መካከል አምልጠው የመጡትን ሰዎች ከሴሰኛ ሥጋዊ ምኞት በማባበል ያታልላሉና” (2ጴጥ. 2:18)፡፡ ጴጥሮስ ስለ ምን እያስጠነቀቀ ነው? ሐዋርያው ሥጋቱን የገለጸበት 2ጴጥ. 2፡19 ምን ይላል? ነጻ መውጣት የሚለው ሃረግ አስፈላጊነት ምንድን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጴጥሮስ አንባቢዎቹ ሐሰተኞች መምህራን ሊያደርሱ ከሚችሉት አደጋ እንዲጠበቁ እያስጠነቀቀ ነበር፡፡ ሐዋርያው በ2ጴጥ. 2፡18-21 መልእክቱ--ሐሰተኞች መምህራን በክርስቶስ አርነት የመውጣትን የተስፋ ቃል እየሰበኩ በተቃራኒው ሰዎችን ወደ ተጨባጭ ባርነትና ግዞት ይመራሉ ሲል ያስጠነቅቃል፡፡

እዚህ ላይ የወንጌልን መልእክት ሙሉ ለሙሉ ለመጠምዘዝ የሚሞክረውን የሐሰተኞች አስተምህሮ ልብ ይሏል፡፡ በክርስቶስ ነጻ መውጣት ከኃጢአት ባርነት ነጻ መውጣት የሚል ትርጉም ሊኖረው ይገባል (ሮሜ 6፡4-6)፡፡ አንድን ሰው ወደ ኃጢአት ባርነት የሚጥል ማንኛውም ዓይነት በክርስቶስ ነጻ የመሆን ጽንሰ ሃሳብ-- ጴጥሮስ እያስጠነቀቀ ያለው ስህተት አካል ነው፡፡ ምንም እንኳ ጴጥሮስ እየተናገረ የነበረው ስህተት የነገረ መለኮት ምሑራንን ቢያከራክርም፤ ነገር ግን ጉዳዩ ከአጠቃላዩ የኃጢአት ጥያቄና ለኃጢአት ባሪያ ከመሆን ጋር የተሳሰረ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

ክርስቶስ በዮሐ. 8፡34-36 የሰጠው መልእክት ጴጥሮስ እየተናገረ ያለውን ሃሳብ ማስተዋል እንድንችል እንዴት ይረዳናል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

እነዚህ ሐሰተኞች መምህራን በሚያቀርቡት ከትክክለኛው ምንጭ ያፈነገጠ የትኛውም ዓይነት ትምህርት--በቅርቡ የሱስን የተቀበሉትን አዳዲሶቹን አማኞች ወደ ቀድሞው ኃጢአተኛ ሕይወት በመመለስ ተከታዮች ማፍራት ችለው ነበር፡፡ አንድ ክርስቲያን በንጽህናና በቅድስና የመመላለስን አስፈላጊነት ዝቅ አድርጎ እንዲመለከት መንስኤ ከሆኑት አስተምህሮዎች አንዱ የሆነው የርካሽ ጸጋ ወንጌል አስተምህሮ-- ሰዎች አምልጠውት ወደ ነበረው ዓለማዊ ህይወት ዳግም እንዲነከሩና በቀላሉ “የጥፋት ባርያዎች” (2ጴጥ. 2:19) ሆነው እንዲወድቁ በማድረግ በምክንያትነት መጠቀስ ይችላል፡፡ ከዚህ አኳያ ጴጥሮስ እነዚህን አስተምህሮዎች በግልጽና በጽኑ መቃወሙም ሆነ ትምህርቶቹን ተከትሎ የሚመጡትን ውጤቶች ማስቀመጡ እምብዛም ላያስገርም ይችላል፡፡

በክርስቶስ ነጻ መውጣት የተሰኘውን አባባል እንዴት ያስተውሉታል? ክርስቶስ ነጻ ያወጣዎት ከምንድን ነው?

ግንቦት 29
6-Jun

ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡- 2ጴጥ. 2:17-22፣ ማቴ. 12:43-45፡፡ ክርስቶስን እንደ አዳኙ ተቀብሎ ክርስትናን የተቀላቀለ አማኝ ወደ ቀድሞው ህይወት ቢመለስ አደጋው ምንድን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

በሐሰተኞች መምህራን አማካይነት ወደ ቀድሞው ኃጢአት እንዲማልሉ የተደረጉ አማኞች ሁኔታ በተለይ ጴጥሮስን አሳስቦት ነበር (2ጴጥ. 2፡18)፡፡ ምንም እንኳ ሐሰተኞቹ መምህራን ነጻ ወጥታችኋል ሲሉ ቢሰብኩላቸውም ነገር ግን ጴጥሮስ እንዳመለከተው፤ እነርሱ የሰጧቸው የነጻነት ተስፋ የሱስ ለተከተሉት ወገኖች ከሰጠው ተስፋ ጋር ሲነጻጸር መሰረታዊ ልዩነት አለው፡፡

ጴጥሮስ የሰጠውን ጥብቅ ማስጠንቀቂያ እንመልከት፡ “የጽድቅን መንገድ ካወቁ በኋላ ከተሰጣቸው ቅዱስ ትእዛዝ ወደ ኋላ ከሚመለሱ፣ ቀድሞውኑ የጽድቅን መንገድ ባላወቁት ይሻላቸው ነበር” (2ጴጥ. 2:21)፡፡

በእርግጥ መልእክቱ የእነርሱ ጉዳይ ተስፋ የለውም የሚል ፍቺ የለውም፡፡ ከጌታ ከራቁ በኋላ ዳግመኛ ወደ እቅፉ የተመለሱ አያሌ ሰዎችን ታሪክ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ከአዳኛቸው ርቀው የነበሩ ወገኖች እንዲህ ያለው ግሩም ውሳኔ ላይ ደርሰው ዳግም ወደ ጌታ ሲመጡ የሱስ እነርሱን ለመቀበል ምን ያህል ደስተኛ እንደሆነ ይገባናል (ሉቃ. 15፡11-32)፡፡ ወደ ቀድሞው ዓለማዊ ህይወት መመለስ አደገኛ አካሄድ ከመሆኑ በተጨማሪ አስደሳች አይደለም ከማለት በዘለለ ምንም ማለት አይቻልም፡፡ ውሻ ወደ ትፋቱ የመመለሱ ምሳሌ ጥብቅና መራር ቢሆንም ነገር ግን ጴጥሮስ ይህን ሥዕላዊ ማሳያ ተጠቅሞ ሲሞግት ይስተዋላል፡፡

ሐዋርያው የሱስ የተናገራቸውን ቃላት በ2ጴጥ. 2፡20 ያስተጋባው ያለ ምክንያት እንዳልሆነ ይታመናል (ማቴ. 12:45፣ ሉቃ. 11:26)፡፡ የሱስ ርኩስ መንፈስ ወጥቶለት ስለነበር አንድ ሰው በምሳሌ ሲናገር፤ መጥፎው መንፈስ ከግለሰቡ ከወጣ በኋላ ማረፊያ ፍለጋ ይንከራተታል፡፡ ሆኖም የሚሻውን ዕረፍት ስለማያገኝ “ ‘ወደ ነበርሁበት ቤት ተመልሼ ልሂድ’ ይላል” (ማቴ. 12:44)፡፡ ታዲያ ተመልሶ ሲመጣ ውስጡ ባዶ ሆኖ፣ ጸድቶና ተዘጋጅቶ ያገኘዋል፡፡ አሁን ርኩስ መንፈሱ ተመልሶ ወደ ግለሰቡ ሲገባ ከእርሱ የባሱ ሌሎች ክፉ መናፍስቶችን ጨምሮ ይዞ ይመጣል፡፡ የሱስ እንደ ተናገረው “ ‘የዚያም ሰው የኋለኛው ሁኔታ ከፊተኛው የከፋ ይሆናል’ ” (ማቴ. 12:45)፡፡ በየሱስ ምሳሌ የቀረበውም ሆነ በጴጥሮስ የተገለጠው አደጋ መታበል የማይችል ተጨባጭ ሐቅ ነው፡፡ የቀድሞውን አሮጌ ህይወት በበላይ ይቆጣጠሩ የነበሩ ሁሉ የመንፈስ በሆኑ ነገሮች እንደሚተኩ አዲሱ አማኝ እርግጠኛ ሊሆን ይገባል፡፡ የአንድ ሰው የቀድሞ ዓለማዊ ህይወት በቤተ ክርስቲያን ተሳትፎና በአዲሱ እምነት ጥናትና ኅብረት ካልተሳሰረ፤ ወደ ቀድሞው ልማድ መመለስ ዳገት አይሆንም፡፡

እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያን ቤተሰብ አባሎቻችንን--በተለይም አዳዲሶችን በተሻለ ለመመገብና ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ልንጠቀማቸው የሚገቡ መንገዶች ምንድን ናቸው?

ግንቦት 30
7-Jun

ጴጥሮስና ይሁዳ


በይሁዳ መጽሐፍ ከቁ. 4-19 የቀረበው መልእክት በ2ጴጥ. 2፡1-37 የምናገኘውን ሃሳብ ይደግማል የሚለውን አስተያየት ብዙዎች ይጋራሉ፡፡ በአምላካዊው ቃል የቀረቡ መልእክቶች የቱንም ያህል ተደጋጋሚነት ሊኖራቸው ቢችል እግዚአብሔር ሊያስተላልፍ የፈለገው ብርቱ መልእክት መኖሩን አንባቢው ሊያስተውል የተገባ ነው፡፡ ጴጥሮስና ይሁዳ ብዙ ርቀት ተጉዘው በእነዚህ ተመሳሳይነት ባላቸው መልእክቶቻቸው--የአመጸኞች መጨረሻ በእግዚአብሔር አምላክ ቁጥጥር ስር የመሆኑን አስፈላጊ እውነታ ያሳውቁናል፡፡ እግዚአብሔር አመጸኞችን በቅርብ እየተቆጣጠረ መሆኑን አስመልክቶ ሁለቱም ሐዋርያት የሚተዉት የጥርጣሬ ቀዳዳ የለም፡፡ አምላካዊውን ጽድቅ ለተቃወሙ ሰብዓዊ ፍጡራንም ሆነ ለወደቁት መላእክት ርክስና እግዚአብሔር ፍትሐዊ ቅጣት በፍርድ ቀን አዘጋጅቷል (2ጴጥ. 2:9፣ 17፣ ይሁዳ 6)፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡- 2ጴጥ. 2:1-3፣7፣ ይሁዳ 4-19፡፡ ጴጥሮስና ይሁዳ እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ ለጣላቸው የቀደሙ ፍትሐዊ ቅጣቶች አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ ከእነዚህ መሃል እንደ አብነት የሚጠቀሱት የትኞቹ ናቸው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

እግዚአብሔር ቀደም ሲል በአመጸኞች ላይ የጣላቸውን ሦስት ፍትሐዊ ቅጣቶች ጴጥሮስና ይሁዳ በጽሑፎቻቸው ያስነብቡናል፡፡ በቀድሞው ዓለም የደረሰው የጥፋት ውሃ ውድመት፣ የሰዶምና የገሞራ ከተሞች ዐመድ መሆንና የአመጸኛ መላእክት መጣል (2ጴጥ. 2:4-6፣ 3:7፣ Jude 6-7) የመልእክቶቻቸው አካል ናቸው፡፡ ትዕይንቶቹ በሙሉ የመጨረሻ ፍጻሜያቸውን የያዘ በሚመስል ድባብ በዚያው እንደ ጸኑ ይቆያሉ፡፡ ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ከፍ ባለ ድምፀት ስለ አምላካዊው ምህረትና ጸጋ ቢናገርም፤ ኃጢአትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከሥሩ በመገርሰሱ ረገድ የእግዚአብሔር ፍትሕ ብርቱ ሚና ይኖረዋል፡፡

ለመሆኑ ለእንደዚያ ዓይነቱ ጽኑ ቅጣት መንስኤ የሆኑ ኃጢአቶች ምን ነበሩ? ጥፋት የሚያስከትሉ የስህተት ትምህርቶችን ማስረጽ፣ ሥልጣንን መናቅ፣ ለዓለማዊው ነገር ባሪያ መሆን፣ አምላካዊውን ጸጋ የርኩሰት ሥራ አባሪ ማድረግ፣ የሱስ ክርስቶስ ብቸኛው ልዑል ገዢና ጌታ መሆኑን መካድ፣ የገዛ አካልን ማርከስ፣ ባዶና የታበዩ የስድብ ቃላት መሰንዘር ናቸው (2ጴጥ. 2:1፣ 10፣ 19፣ ይሁዳ. 4፣ 8፣ 2ጴጥ. 2:18፣ ይሁዳ 10)፡፡

መግለጫዎቹ አጥብቀው ስሜታችንን የሚጎዱትን ሁከትና ብጥብጦች ወደ ጎን ብለው በብዙዎች የሚስተዋለውን ረቂቅ ኃጢአት መግለጻቸው አስገራሚ ነው፡፡ ኃጢአቶቹ አልፎ አልፎ በቤተ ክርስቲያን ኅብረት ሳይቀር ልዩ ልዩ መሸፋፈኛና ሰበብ ሲቀርብባቸው ይስተዋላል፡፡ እውነታው ካሸለብንበት ነቅተን በቤተ ክርስቲያን ልባዊ ንስሐና ተሐድሶ ማድረግ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያሳያል፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡- 1ጴጥ. 2፡12፣ ይሁዳ 10፡፡ ጴጥሮስ “በስሜታቸው ብቻ የሚመሩ ልቦናም እንደሌላቸው አራዊት ናቸው” ብሎ አመጸኞችን ሲገልጽ ይሁዳ ደግሞ “አእምሮ እንደሌላቸው እንስሳት በደመነፍስ” የሚመሩ መሆናቸውን ጽፏል፡፡ እንዲህ ያለው አገላለጽ እግዚአብሔር መጀመሪያ ሰውን ሲፈጥር ከነበረው ሁኔታ ጋር እንዴት ይነጻጸራል? በእርስዎ እንዳይደርስ እንዴት መከላከል ይችላሉ?

ሰኔ 1
8-Jun

ተጨማሪ የብሉይ ኪዳን ትምህርቶች


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡-- 2ጴጥ. 2:6-16፡፡ ርክስና ሰብዓዊውን ፍጡር ወዴት እንደሚመራው አስመልክቶ ጴጥሮስ የሚያቀርባቸውን ሌሎች ምሳሌዎች ይጥቀሱ፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ስለ ሰዶም ውድመት መጽሐፍ ቅዱስ የዘገበው የመጀመሪያው ተጨባጭ መረጃ በዘፍ. 13፡12-13 ቀርቦአል፡፡ አብርሃምና ሎጥ የየራሳቸውን ሐብትና ንብረት ከማፍራት ጋር ተያይዞ ለመለያየት ወሰኑ፡፡ በዚህም ሎጥ በረባዳው የዮርዳኖስ ሸለቆ “በሰዶም አቅራቢያ ድንኳኑን ተከለ” (ዘፍ. 13፡12)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አገሬው ሕዝብ አስተያየት ሲሰጥ “የሰዶም ሰዎች ግን ክፉዎችና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኃጥአን ነበሩ” ይላል (ዘፍ. 13:13)፡፡ ቆየት ብሎ እግዚአብሔር ሰዶምን ለማጥፋት መወሰኑን ለአብርሃም አሳወቀው፡፡ አብርሃም ከጌታ ጋር ያደረገውን ድርድር ተከትሎ በከተማይቱ አሥር ጻድቃን ከተገኙ እግዚአብሔር ከተማዋን እንደማያጠፋ ቃል ገባለት (ዘፍ. 18፡16-33)፡፡

የተጠቀሱትን አሥር ጻድቃን እንኳ ማግኘት አለመቻሉ--ሎጥን ለመጎብኘት በሄዱት መልእክተኞች የሆነውን ነገር በበቂ ሁኔታ የሚሳይ ሆነ፡፡ ሎጥና ሁለት ሴት ልጆቹ ብቻ ሲተርፉ፤ ነዋሪቿን ጨምሮ ከተማዋ ሙሉ ለሙሉ ወደመች (ዘፍ. 19:12-25)፡፡

ጴጥሮስ ከዚህ ታሪክ ሁለት ትምህርቶች ነቅሶ ያወጣል፡፡ በርኩሳን ሕዝቦች ላይ የመጣው ቅጣት በሁለቱ ከተሞች ላይ ውድመት ማድረሱ የመጀመሪያው ምሳሌ ሲሆን (2ጴጥ. 2፡6) ሁለተኛው ደግሞ ጌታ ጻድቆችን እንዴት ከመከራ መታደግ እንደሚያውቅበት ያሳየናል (2ጴጥ. 2:7-8 9)፡፡ ጴጥሮስ በሰዶምና ገሞራ የአምላካዊው ቁጣ ሰለባ የሆኑ ሕዝቦችን አንዳንድ ጸባዮች እንደሚከተለው ያስቀምጣል፡--በርኩስ ምኞት የሥጋ ፍላጎታቸውን የሚከተሉ፣ ሥልጣንን የሚንቁ፣ ደፋሮችና እብሪተኞች (2ጴጥ. 2:10-11)፡፡ እነዚህ ጸባዮች ጴጥሮስ ሐሰተኛ መምህራኖችንና ተከታዮቻቸውን ከሚገልጽበት መንገድ ጋር ተመሳሳይነት አላቸው፡፡

እስራኤላውንን እንዲረግም በሞአብ ንጉሥ ባላቅ የተላከበትን የበለዓም ታሪክ በዘኁ. 22፡1-24፣ 25 እናገኛለን፡፡ በለዓም መጀመሪያ እስራኤላውያንን ለመርገም አመንትቶ የነበረ ቢሆንም፤ ቃል የተገባለት ከፍ ያለ ወሮታ ልቡን አነሁልሎት ነበር (ዘኁ. 22፡7-21)፡፡ እስራኤላውያንን ለመርገም ባደረገው ጉዞ በመንገዱ “የእግዚአብሔርን መልአክ” (ዘኁ. 22፡22-35) የተጋፈጠው በለዓም--አህያው ከመልአኩ ፊት ዞር ባትል ሊሞት ይችል ነበር፡፡ ሆኖም የበለዓም ጉዞ መጨረሻው እስራኤላውያንን በመባረክ ተጠናቀቀ (ዘኁ. 23፡24-25)፡፡ በሴሰኝነትና በዝሙት ለሚማልሉና ለሚሳቡ ሰዎች ጴጥሮስ በለዓምን በምሳሌነት ሲያስቀምጥ ይታያል (2ጴጥ. 2፡14-15)፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች ከበለዓም ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ሊከተሉ የሚገባውን መንገድ ትተዋል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ መልእክትም ሆነ በኤለን ጂ. ኋይት ጽሑፎች ስለተሰጡን ነገሮች አሰብ ያድርጉ፡፡ እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስትነታችን ማስተጠንቀቂያ አልተሰጠንም ማለት የማንችለው እንዴት ነው?

ሰኔ 2
9-Jun

ተጨማሪ ሃሳብ:-


አያሌ ክርስቲያኖች “በክርስቶስ ነጻ መውጣት” ስለተሰኘው ጽንሰ ሃሳብ በተደጋጋሚ ሲናገሩ እንሰማለን፡፡ በእርግጥ ጽንሰ ሃሳቡ ህጋዊና ተገቢነት ያለው ነው፡፡ በእኛ በጎ ሥራ ሳይሆን ነገር ግን ክርስቶስ ለእኛ ያደረገውን ተከትሎ ከሕጉ ኩነኔ ነጻ መውጣታችንና የመዳናችንን ማረጋገጫ ማግኘታችን በእግጥ ነጻነት መቀዳጀት ነው፡፡ ማርቲን ሉተር አምላካዊውን ጸጋ ከማስተዋሉ አስቀድሞ ይገኝበት የነበረው የግዞት ህይወት የዚህን ነጻነት ትርጉም ለመረዳት የሚያስችል ታላቅ ምሳሌ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ በጴጥሮስ መልእክት እንደ ተመለከትነው ግሩምና አስደናቂ የተባለው እውነት የመጠምዘዝ አደጋ ሊገጥመው ይችላል፡፡ “መዳናችንን ሙሉ ለሙሉ በክርስቶስ ላይ አድርገን የመመካታችን ታላቅ እውነታ--እውነት ነው ተብሎ ለተገመተ ስህተት ቅርበት አለው፡፡ በክርስቶስ የሚገኘው ነጻነት--አምላካዊውን ሕግ መጠበቅ አያስፈልግም በሚል አንድ ሺ የተሳሳተ አስተሳሰብ ተጽእኖ ስር ወድቆአል፡፡ ክርስቶስ ከሕጉ ኩነኔ ነጻ ሊያወጣን በመምጣቱ ሕጉ ራሱ ተወግዶአል--እንደውም ሕጉን የሚጠብቁ ከጸጋው ውጪ ናቸው ብለው የሚያምኑ ብዙዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም የእውነትና ሐሰት ወደ መመሳሰል መቃረብ--በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ስር ያልሆኑ አእምሮዎች ሐሰቱን ለመቀበል በሚከተሉት አካሄድ ራሳቸውን በሰይጣን የማታለያ ኃይል ስር ያኖራሉ፡፡ ሰዎች በእውነት ፋንታ ሐሰትን እንዲቀበሉ በሚመሩ፣ በእንደነዚህ ዓይነቶቹ የሚጠቀመው ሰይጣን--በፕሮቴስታንቱ ዓለም አክብሮትና ተቀባይነት ለማግኘት እየሠራ ይገኛል”—Ellen G. White, Christ Triumphant, p. 324.


የመወያያ ጥያቄዎች:



በ2ጴጥ. 2፡19 የቀረበውን ሃሳብ ጨምሮ፤ ጴጥሮስ የሐሰት አስተምህሮ ኃይማኖታዊ በየግላችን፣ አስተምህሮዎችን ውጤት የሚላቸውን ሌሎች መልእክቶች በጥልቅ ለመመልከት ይሞክሩ፡፡ መሰረታዊ በጥልቅ ለማስተዋላችን እርግጠኞች መሆን ያለብን ለምንድን ነው? ሁላችንም በምናምነው ላይ በትክክል መስማማታችን ምን ያህል አስፈላጊ ነው? ኃይማኖታችንን የሚጋሩ ወገኖች ከሚከተሏቸው ጽንሰ ሃሳቦች ውጪ የሆኑትን ማሰብ “አደገኛ” የሚሆነው መቼ ነው?

ጴጥሮስ ከአጠቃላዩ ቅጣትና ፍርድ አኳያ ከሚሰነዝራቸው አንዳንድ ጠንካራ አነጋገሮች መሃል ጥቂቶቹን ይመልከቱ፡ “በራሳቸው ላይ ድንገተኛ ጥፋት ያመጣሉ” (2ጴጥ. 2:1)፣ “የሚጠፉትም እንደ እንስሳ ነው” (2ጴጥ. 2:12)፣ “ለፍርድ ቀን እንዴት ጠብቆ እንደሚያቆያቸው ያውቃል” (2ጴጥ. 2:9)፣ “መጥፊያቸውም አያንቀላፋም” (2ጴጥ. 2:3, 21)፡፡ ጥቅሶቹ ስለ ፍርድ ተጨባጭ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን፤ ሕዝቦቹን ወደ ስህተት የሚመሩትን እግዚአብሔር እንዴት በጽኑ እንደሚኮንን ምን ይነግሩናል?

 አራተኛውን የሰንበት ትእዛዝ ተቀብለው ነገር ግን በክርስቶስ (ሕጉን ከመጠበቅ) ነጻ ነን ብለው ስለሚያስተምሩ ሰዎች ምን ይላሉ? እንዲህ ያለው አመለካከት በክርስቶስ ነጻ የመሆን ጽንሰ ሃሳብ በቀላሉ መጠምዘዝ እንደሚችል ለመመልከት የሚረዳን እንዴት ነው?