የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
3ኛ ሩብ ዓመት 2025
ሰኔ፣ ሐምሌ፣ ነሐሴ፣ ጳጉሜ፣ መስከረም 2017/18 ዓ.ም.
መደበኛ እትም
Jun 28 - Sep 26
አዘጋጅ : ጂሪ ሞስካላ
ትርጉም : ታምሬ ሻዕማሎ
ይህ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ የሚዘጋጀው
የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ-ክርስቲያን ዋና መሥሪያ ቤት በሆነው በጀነራል
ኮንፈረንስ ሥር መምሪያውን በሚያዘጋጀው ቢሮ ነው። መምሪያው የሚዘጋጀው
በሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድ ሲሆን፣ ቦርዱ የጀነራል ኮንፈረንስ አስተዳደር
ኮሚቴ ንዑስ ኮሚቴና የመምሪያው አሳታሚ ነው። መምሪያው ዓለም አቀፋዊ
የሆነ የምዘና ኮሚቴ ሐሳቦችንና የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድን ማረጋገጫ
ስለሚያንጸባርቅ፣ የአዘጋጁን ሐሳብ ብቻ የሚወክል አይደለም።
3ኛ ሩብ ዓመት
ከሰኔ 21/2017 እስከ መስከረም 16 2018
በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ማተሚያ ቤት ታተመ
ዘጸአት:- ወደ ተስፋው ምድር
የተደረገ ጉዞ
በዘጸአት መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸው እግዚአብሔር፣ በራሱ ጊዜ ብርቱ
በሆኑ እርምጃዎቹ ለሕዝቡ ነጻ መውጣትንና ድነትን ያመጣ አፍቃሪ አምላክ
ነው (ዘፍ. 15:12–16)። ከግብጽ መውጣትና ቀይ ባህርን መሻገር ወሳኝና የተለዩ
ክስተቶች ሲሆኑ አስገራሚና ድንቅ የእግዚአብሔር ሥራዎች ነበሩ። ከመስቀሉ
በፊት በነበረችው በጥንቷ የእሥራኤል ታሪክ ከዚህ የሚበልጥ ታላቅና በግርማ
የተሞላ ክስተት ሆኖ አያውቅም። ይህ ሙሴ የጻፈው ወንጌል ነው።
ምንም እንኳን ዕብራውያን ሁልጊዜ ወደ ኋላ ቢያፈገፍጉም፣ እግዚአብሔር
ለእነርሱ ያለውን ጥንቃቄና ጥበቃ ለማሳየት ተአምራዊ በሆነ ሁኔታና በተደጋጋሚ
ተነስቷል። ጌታ በተዘረጋ ክንዱ ሕዝቡን ወደ ነጻነት መራ። ይህ ከዚህ በፊት ታይቶና
ተደርጎ የማያውቅ ተግባር ነበር። ይህ በቀጣይነት የተፈጸመው የእግዚአብሔር
ጣልቃ መግባት እነርሱ ከግብጽ ወደ ከነዓን ለመጓዝ ከእግዚአብሔር ጋር የፈጸሙት
የጉዞ እድሳት ጅምር ነበር።
በመውጣቱ ሂደት ሙሴ ወሳኝ ሚና ቢጫወትም፣ ይህ መጽሐፍ ስለ
ሙሴ ሳይሆን የፍቅር፣ የእውነት፣ የፍትህ፣ የነጻነትና የይቅርታ አምላክ ስለሆነው እና
በመጨረሻም ስለ እኛ ወደ መስቀል ስለሄደው ስለ እግዚአብሔር ነው። የዘጸአትን
መጽሐፍ ስናጠና አምላካችን በእርግጠኝነት ምን እንደሚመስል ልዩ የሆነ እይታ እናገኛለን።
እርሱ በርግጥ ምን ይመስላል? ሕዝቡ ታማኝ ባይሆኑም ለእነርሱ ታማኝ
የሆነ አምላክ ነበር። እነርሱ ቢቃወሙትም ሁልጊዜ የሚቆምላቸው አምላክ ነበር።
በተደጋጋሚ ማደፋፈሪያን፣ እርምትንና መለኮታዊ ምሪትን በማምጣት ምህረቱን
አሳያቸው። በተቻለ መጠን በመልካም መንገድ በመምራት፣ በራሳቸው ፍላጎት፣
ለእርሱና ለባህሪዩ ካላቸው ፍቅር በመነሳት. ለራሳቸው ጥቅም እንዲያመልኩትና
እንዲታዘዙት ፈለገ።
የሙሴ አምላክ የግንኙነት አምላክ ነው። እጅግ ወሳኝ የነበረው
የእግዚአብሔር ዓላማ የሆነ ነገርን ማከናወን ወይም የሆነ ዕቅድን መፈጸም
ሳይሆን ከተመረጠው ሕዝቡ፣ ከእሥራኤል፣ ጋር ትርጉም ያለው ግንኙነት መፍጠር
ነበር። ጥልቅ የሆነ ግንኙነት ለመመስረት ወደ ሲና መራቸው።
ባለፈው ጊዜ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ የደረሰው ነገር ከእነርሱ
ስህተቶች መማር እንድንችልና ዛሬ ጌታን በታማኝነት እንድንከተል ለትምህርታችን
እንደተቀመጠ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ያስተምራል፡- “ይህም ሁሉ
እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፥ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ”
(1ኛ ቆሮ. 10:11)። እነዚህ ተፈጽመው ያለፉ ክስተቶች አሁን ለእኛ ማስጠንቀቂያና
የማይረሳ ትምህርት መሆን አለባቸው። ሁኔታዎቹ ምንም ያህል የተለያዩ
ቢሆኑም፣ ከኋላቸው ያሉ መንፈሳዊ መርሆዎች ተመሳሳይ ስለሆኑ እነርሱን
ማንበብ፣ ማጥናትና ከእነርሱ መማር አለብን።
በእነዚህ አስራ ሶስት ሳምንታት የዘጸአትን መጽሐፍ ለማጥናት ያለን ዕቅድ
ግልጽ ነው። መጽሐፉ በየሳምንቱ በምንማራቸው የተለያየ ርዝመት ባላቸው
ምዕራፎች ተከፍሏል (ለጥናት እንዲመች በአርእስት ተከፍሏል)፡- (1) በግብጽ
ባርነት፣ የሙሴ መወለድ፣ እና የመጀመሪያዎቹ አርባ ዓመታት (ዘጸ. 1–2)። (2)
የሙሴ ተልዕኮ ተሰጥቶት መላክ (ዘጸ. 3–4)። (3) የሁኔታዎች መወሳሰብ፡-
ሕይወት አስከፊ ሲሆን (ዘጸ. 5–6)። (4) የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ መቅሰፍቶች
(ዘጸ. 7–10)። (5) አሥረኛው መቅሰፍትና ፋሲካን ማክበር (ዘጸ. 11–12)። (6)
ከግብጽ ነጻ መውጣት እና የቀይ ባህሩ ልምምድ (ዘጸ. 13–15)። (7) ጉዞ ወደ
ሲና ተራራ (ዘጸ. 16–18)።: (8) የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን እና የአስርቱ ትዕዛዛት ስጦታ (ዘጸ. 19–20)። (9) የእግዚአብሔር ሕግ በሥራ ላይ ሲውል (ዘጸ. 21–23)።
(10) የቃል ኪዳኑ መጽናትና የቤተ መቅደሱ ንድፍ (ዘጸ. 24–31). (11) የወርቅ ጥጃ
በማምለክ የተፈጸመ ክህደትና የሙሴ ምልጃ (ዘጸ. 32)። (12) የእግዚአብሔር ራሱን መግለጥና ያንጸባረቀው የሙሴ ፊት (ዘጸ. 33–34)። (13) የቤተ መቅደሱ
መገንባትና መመረቅ (ዘጸ. 35–40)። በየሳምንቱ እዚህ ላይ በተመለከቱ
ምዕራፎች ውስጥ ባሉ ቁልፍ ንባቦችና ክስተቶች ላይ እናተኩራለን።
እግዚአብሔር ሕዝቡን ከባርነት ወደ ነጻነት፣ ከሞት ወደ ሕይወት እና
ከምድረ በዳ ወደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለመምራት እንደሚፈልግ የሚያስታውሰንን
ይህን ወሳኝ መጽሐፍ ስናጠና በጸጋ የተሞላው አምላካችን ይባርከን (ዕብ. 12:22)።
ጂሪ ሞስካላ የብሉይ ኪዳን ትርጉምና ሥነ-መለኮት ትምህርት ፕሮፌሰርና በአንድሪውስ
ዩኒቨርሲቲ ባለው የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ሥነ-መለኮት ማሰልጠኛ ተቋም ዲን ናቸው።
Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL