የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የእግዚአብሔር ፍቅር እና ፍትሕ



1ኛ ሩብ ዓመት 2025



ጥር፣ የካቲት፣ መጋቢት 2017 ዓ.ም.

መደበኛ እትም

Dec 28 - Mar 28




አዘጋጅ : ጆን ሲ. ፔካም

ትርጉም : ጋሻው አሻግሬ

አርትኦት : መላሽ አለማየሁ
ተመስገን ቡልቲ (ፓ/ር)
ማንደፍሮ አለማየሁ (ፓ/ር)
ውብሸት ላቀው (ዶ/ር)



ይህ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ የሚዘጋጀው የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ-ክርስቲያን ዋና መሥሪያ ቤት በሆነው በጀነራል ኮንፈረንስ ሥር መምሪያውን በሚያዘጋጀው ቢሮ ነው። መምሪያው የሚዘጋጀው በሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድ ሲሆን፣ ቦርዱ የጀነራል ኮንፈረንስ አስተዳደር ኮሚቴ ንዑስ ኮሚቴና የመምሪያው አሳታሚ ነው። መምሪያው ዓለም አቀፋዊ የሆነ የምዘና ኮሚቴ ሐሳቦችንና የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድን ማረጋገጫ ስለሚያንጸባርቅ፣ የአዘጋጁን ሐሳብ ብቻ የሚወክል አይደለም።

በዚህ ሰንበት ትምህርት መምሪያ ውስጥ የሚገኙት ጥቅሶች የተወሰዱት በ1954 ዓ.ም በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ከታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። The Bible in Amharic © United Bible Societies 1962. ISBN: 9966 843 63 9. ማሳሰቢያ፡- ሁሉም የትንቢት መንፈስ ጽሑፎች ከእንግሊዝኛው ቀጥታ የተተረጎሙ ስለሆነ፣ ገጻቸው ከአማርኛው ጋር አይገጥምም።


1ኛ ሩብ ዓመት
ከታህሳስ 19 - መጋቢት 19/2017 ዓ.ም


በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ማተሚያ ቤት ታተመ የፍቅር እና የፍትሕ አምላክ

1 ዮሐ. 4:8 እና 16 እግዚአብሔር ፍቅር ነው ይላል። መላው መጽሐፍ ቅዱስ ይህን እውነታ ይመሰክራል። የክርስትና እምነት ማዕከሉ የእግዚአብሔር ፍቅር ነው። ፍቅር የእግዚአብሔር ማንነት እምብርት ነው፤ እኛም የምናምነውና የምንሰራው ነገር ሁሉ ማዕከል ፍቅር መሆን አለበት። በዚህ መሠረት ፍቅርን የምንረዳበት መንገድ በእምነታችን እና በድርጊታችን ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል።

ለምሳሌ አንድ ሰው የእግዚአብሔር ፍቅር በሥራ ይገኛል ብሎ ካመነ፣ ኃጢአተኛና ያልበቃ ስለሆነ እግዚአብሔር እንደማይወደው ሊያስብ ይችላል። ከሌሎችም ጋር ባለው ግንኙነት፣ ሰዎችን ይወዳቸው ዘንድ፣ እነርሱ አስቀድመው መልካም ነገር ማድረግ ይኖረባቸዋል ብሎ ያስባል፡- ይህም ለውድቀት መንስኤ ይሆናል።

ስለዚህ የእግዚአብሔርን ፍቅር የምንረዳበት መንገድ በእምነታችን እና በልምምዳችን ላይ ትልቅ አንድምታ አለው። ለመሆኑ ፍቅር ምንድን ነው? ፍቅርን እንዲገልጹ አሥር ሰዎችን ቢጠይቋቸው፣ አሥር የተለያዩ ምላሾችን ሊያገኙ ይችላሉ። በክርስቲያኖች መካከል እንኳን፣ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብዙ አፈ-ታሪኮች እና የተሳሳቱ መረዳቶች አሉ።

ለምሳሌ ክርስቲያኖች ለሚቀጥሉት ጥያቄዎች የተለያዩ ምላሾችን ይሰጣሉ፡ - የእግዚአብሔር ፍቅር መስጠት ብቻ እንጂ ምላሽ አይጠብቅምን? መለኮታዊው ፍቅር ራሱን መስዋዕት የሚያደርግ ብቻ ነው ወይስ እግዚአብሔር በሰዎች ሐሴት ሊያደርግ ይችላል? የእግዚአብሔር ፍቅር ስሜታዊ ነው? በእርግጥ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ይጠነቀቃል? የእግዚአብሔር ፍቅር ቸል ሊባል ወይም ሊገፋ ይችላል? እግዚአብሔር ከፍጡራን ጋር የሰጥቶ መቀበል የፍቅር ግንኙነት ውስጥ ይገባል? ቁጣ ከፍቅር ጋር አይጣጣምም? ፍቅር እና ፍትሕ እንዴት አብረው ይኖራሉ? እግዚአብሔር ፍቅር ከሆነ፣ ክፋት በዚህ ዓለም ላይ ለምን እጅግ በዛ? ሰዎች እንደ እግዚአብሔር ሊወዱ ይችላሉ? ከሆነ ያ ምን ሊመስል ይችላል?

ከላይ ለተጠቀሱት ለአንዳንዶቹ ጥያቄዎች የሚሰጡት መልሶች ግልጽ ሊመስሉ ይችላሉ፤ ነገር ግን ክርስቲያኖች ለመለኮታዊው ፍቅር ያላቸውን አመለካከት አስመልክቶ ብዙ ጊዜ ክርክሮች ይነሳሉ። ግልጽ የሚመስሉ ብዙ ምላሾች በጥልቀት ስንመረምራቸው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ከሚያስተምረው ጋር የማይጣጣሙ ሆነው ይገኛሉ።

እነዚህን ጥያቄዎች ሁሉ በአንድ ጊዜ አንፈታቸውም፤ ነገር ግን እነዚህን እና ሌሎች ጥያቄዎችን በዚህ ሩብ አመት እንዳስሳለን። በዚህም የእግዚአብሔር ፍቅር ከምናስበው በላይ እጅግ ከፍ ያለ መሆኑን እናያለን። በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የተገለጸው የእግዚአብሔር ፍቅር፣ በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን "ስለ ፍቅር" ከሚነገሩ ሃሳቦች እጅግ የላቀ ነው። በሚቀጥሉት ሳምንታት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር የተገለጹትን አንኳር እና ውብ ገጽታዎች በጥልቀት እንመለከታለን።

ጥናታችንን ስንቀጥልም መለኮታዊው ፍቅር እና ፍትሕ እንዳይነጣጠሉ ሆነው የተጋመዱ መሆናቸውን እናያለን። በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጸው እግዚአብሔር ፍትሕን ይወዳል (ለምሳሌ፡- ኢሳ. 61፡8ን ይመልከቱ)። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጠው፣ መለኮታዊው ፍቅር እና ፍትሕ ስለማይነጣጠሉ፣ አንዱ ከሌላው ውጭ ሊኖር አይችልም። እግዚአብሔር ፍቅር ስለሆነ፣ በዚህ ዓለም ያለው ኢ-ፍትሃዊነትና ስቃይ እጅግ ያሳስበዋል፤ ራሱንም ከተጨቆኑና ከተሰቃዩት ጋር አንድ አድርጎ በመቁጠር፣ ክፋት በፍጥረት ላይ ባመጣው ስቃይና ሀዘን ውስጥ በፈቃዱ ራሱን ሰጠ—ራሱ ከሁሉም በላይ ተሰቃየ። ስለዚህም እግዚአብሔር ራሱ ከሁሉ ይልቅ የክፋት ተጠቂ ሆነ።

እግዚአብሔር እያንዳንዱን ሰው ከምንገምተው በላይ ስለሚወድ፣ በክፋት እና በስቃይ በተደጋጋሚ ማዘኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን።

የእግዚአብሔርን ጥልቅ ፍቅር፣ ክርስቶስ በሕዝቡ ላይ፡- “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፣ ዶሮ ጫጩቶቿን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም” እያለ በተናገረው እንጉርጉሮ ውስጥ ማየት ይቻላል (ማቴ. 23፡37)።

ፍቅር የሆነው የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ፣ ያ ፍቅር ችላ ስለተባለና ስለተገፋ ልቡ እንደተሰበረና እንዳዘነ በቃሉ ውስጥ ተገልጧል። ቃሉ እግዚአብሔር ፍቅሩን በዓለማት ሁሉ ለማስፈን ስላደረገውና እያደረገ ስላለው ነገር ይተርካል። ይህ የዚህ ሩብ ዓመት ትምህርት ርዕስ ነው።

ጆን ሲ. ፔካም የአድቬንቲስት ሪቪው ተባባሪ አርታኢ ናቸው። ይህ የጥናት መመሪያ በተጻፈበት ጊዜ፣ እሳቸው በአንድርውዝ ዩኒቨርሲቲ በሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት ስነመለኮት ሴሚነሪ የነገረ መለኮት እና የክርስቲያን ፍልስፍና ፕሮፌሰር ነበሩ።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL