የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የዮሐንስ ወንጌል ዋና ዋና ሐሳቦች



4ኛ ሩብ ዓመት 2024



ጥቅምት፣ ህዳር፣ ታህሣሥ 2017 ዓ.ም.

መደበኛ እትም

Sep 28 - Dec 27




አዘጋጅ : ኤድዋርድ ዚንኬና ቶማስ ሼፐርድ

ትርጉም : ኤፍሬም ዳዊት



ይህ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ የሚዘጋጀው በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ዋና መሥሪያ ቤት በሆነው በጀነራል ኮንፍረንስ ውስጥ ሆኖ፣ የጎልማሶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያን በሚያዘጋጀው ቢሮ ነው። መምሪያዎቹ የሚዘጋጁት የጀነራል ኮንፈረንስ አስተዳደር ኮሚቴ ንዑስ ኮሚቴ በሆነውና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያዎችን በሚያሳትመው የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድ ነው። የታተመው መምሪያ በውስጡ ዓለም አቀፋዊ የሆነ የምዘና ኮሚቴ ሀሳቦችንና የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድን ማረጋገጫ ስለሚያንጸባርቅ የአዘጋጁን (የአዘጋጆቹን) ሀሳብ ብቻ የሚወክል አይደለም። በተለየ ሁኔታ ካልተጠቀሰ በቀር በዚህ ሰንበት ትምህርት ውስጥ የሚገኙት የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የተወሰዱት በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በ1954 ዓ.ም ከታተመው ዕትም ነው። (The Bible in Amharic © United Bible Societies 1962. ISBN: 978-9966-27-561-5 R042PL)
4ኛ ሩብ ዓመት
ከመስከረም 18 እስከ ታህሣሥ 19 / 2017 ዓ.ም.


በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ማተሚያ ቤት ታተመ የዮሐንስ ወንጌል ዋና ዋና ሐሳቦች

በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን በሚገኝ አንድ ሱቅ ውስጥ የፋርስ ምንጣፍ ይታያል።

በዚህ ምንጣፍ ላይ ጥንታዊ ደን ተስሏል። ምንጣፉ በስዊዘርላንድ ውስጥ የሚገኝን አንድ ትዕይንት በሚያምር ሁኔታ የሚያስቃኝ ነው። ተራሮች፣ ፏፏቴ፣ አረንጓዴና ሰማያዊ ቀለም የሚንጸባረቅበት ሐይቅ፣ በደን የተሸፈኑ ኮረብታዎች፣ እና የደመና ነጠብጣብ የሚታይበት ሰፊው ሰማያዊው ሰማይ ተዘርግቷል።

በዚያ ሱቅ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ሰው በምንጣፉ ላይ የሚታዩትን ዝርዝር ነገሮች ማለትም፣ በእያንዳንዱ ካሬ ላይ የሚገኙ የክር ቋጠሮዎች ብዛት፣ የምንጣፉን የጨርቅ ዓይነት፣ ጥቅም ላይ የዋሉ ቀለሞችንና ምንጣፉ ላይ ያሉ ሌሎች ደቃቅ ነገሮችን ሁሉ በመመልከት ጊዜውን ማሳለፍ ይችላል። ወይም ሌላው አማራጭ፣ ለምንጣፉ ለየት ያለ ውበት በሰጡት የአሠራር ዘዴዎች እና ጭብጦች፣ ማለትም በሐይቁ ላይ በተንፀባረቀው ሰማይ፣ ተራሮችን በሸፈነው በረዶና የድንጋይ ሽበት በብዛት በሚታይበት አረንጓዴው ደን ላይ አንድ ሰው ትኩረቱን ሊያደርግ ይችላል። የምንጣፉ ዋና ዋና ገጽታዎች እርስ በርሳቸው ውበትን በቅንጅት በሚገለፅ መልኩ፣ በአልፕስ ተራሮች ላይ የሚገኘውን የዚያን ጸጥ ያለ ቦታ ግርማ ያሳያሉ።

ቃላቶች በአውዳቸው ውስጥ ሆነው ሲነበቡ ትርጉም አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ሊናገር ያሰበውን ሰው መረዳት ይችል ዘንድ በዐውድ ውስጥ ሆኖ ማለትም ዓረፍተ ነገሮች፣ ምዕራፎች እና ክፍሎች እንዲሁም አጠቃላይ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት መጠናት አለበት።

በአጠቃላይ መላው መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ምሪት የተጻፈ ስለሆነ እያንዳንዱ ክፍል ሙሉ ከሆነው ሐሳብ አንፃር በዐውድ መጠናት አለበት ማለት ነው።

የዚህ ሩብ ዓመት ትምህርት ዓላማ የዮሐንስ ወንጌል መልእክትን መረዳት ይሆናል።

የዮሐንስ ወንጌል ከአራቱ ወንጌላት የተለየ ነው፤ ብዙውን ጊዜ በየሱስና በአንድ ወይም ሁለት ሰዎች መካከል በተደረጉ የግል ቃለ ምልልሶች ላይ ትኩረቱን ያደርጋል። ለምሳሌ ከናትናኤል፣ ከኒቆዲሞስ፥ በጕድጓዱ አጠገብ ከነበረችው ሴት፥ በቤተ ሳይዳ በውሃው ገንዳ ከነበረው ሽባ፣ ዕውር ሆኖ ከተወለደው፣ ከአልዓዛርና እኅቶቹ፣ ከጲላጦስ፣ ከጴጥሮስ ወይም ከቶማስ ጋር የተደረጉ ቃለ ምልልሶች ይገኛሉ። ብዙዎቹ እነዚህ ታሪኮች የሚገኙት በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ብቻ ነው።

የዮሐንስ ወንጌል በሐዋርያው አማካኝነት ለእኛ የተላለፈ የእግዚአብሔር ቃል ነው። እንደ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ፣ ወንጌል የመጣው በሰብዓዊ ፍጡር ፈቃድ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። ዮሐንስ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ወሳኝ ጭብጦችን ለማስተላለፍ የተጠቀመበት ፈቃደኛ የሆነ መሣሪያ ብቻ ነበር። ከእነዚህም ጭብጦች መካከል፣ ቃሉ (ሎጎስ)፣ ብርሃን፣ እንጀራ፣ ውሃ፣ መንፈስ ቅዱስ፣ አንድነት፣ ምልክቶች፣ ምስክርነት እና ትንቢት ይገኙበታል። እነዚህ ዋና ዋና ሐሳቦች በወንጌል አንዳቸው ሌላውን የሚያጎሉ እና የሚያበሩ ናቸው።

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ብዙውን ጊዜ የሚያተኩረው በአንድ ቃል ወይም በትንሽ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍል ላይ ነው። እኛም የቃሉን ትርጉም በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ ያለውን በመመልከት እናረጋግጣለን። ሰዋሰውን፣ የቅርብ አውዱንና ታሪካዊውን አውድ እንመረምራለን። የምንጣፉን ምሳሌ ብንጠቀም፣ በየካሬው ያሉትን ትንንሽ ቋጠሮዎችን፣ የጨርቁን (የስጋጃውን) ዓይነት፣ ማቅለሚያዎቹንና ሌሎች ጥቃቅን ዝርዝሮቹን እንደማለት ነው። ይህ ሁሉ ዝርዝር አስፈላጊ ነው። ነገር ግን ዝርዝሮችን እየመረመር ትልቁን ምስል መሳት የለብንም። በእርግጥ ልክ የፋርሱ ምንጣፍ አንድን ሰው ወደዚያ ውብ የአልፕስ ተራራዎች ትእይንት እንሚያጓጉዝ፣ እንዲሁ የዮሐንስ ወንጌል፣ እርሱን ማወቅ የዘላለም ሕይወት ወደ ሆነው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወትና አገልግሎት ይመልሰናል። ዝርዝሮቹ አንድ ሚና አላቸው፣ እርሱም እኛን ወደ ትልቁ ሥዕል ማመላከት ነው። በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ያለው ትልቁ ምስል በመለኮታዊው መንፈስ መሪነት የተገለጠው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ነው።

ኢ ኤድዋርድ ዚንኬ፣ በሰባተኛው ቀን አድቬንቲስቶች የጀነራል ኮንፈረንስ የቀድሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ኢንስቲትዩት ተባባሪ ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል። በኤለን ጂ ዋይት እስቴት ቦርድ ምክትል ሊቀመንበርነትና የአድቬንቲስት ሪቪው አገልግሎቶች ከፍተኛ አማካሪነትን ጨምሮ፣ በበርካታ የቤተ ክርስቲያን ተግባራት እና ቦርዶች ውስጥ ይሳተፋሉ።

ከሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ዩኒቨርሲቲዎች ሶስት የክብር ዶክትሬት ዲግሪ አግኝተዋል። በአሁን ሰዓት በአሜሪካ በሜሪላንድ ግዛት ውስጥ ይኖራሉ ቶማስ ሼፐርድ (ፒ.ኤች.ዲ፣ ዲአር. ፒኤች) እ.አ.አ. ከ 2008 ዓ.ም ጀምሮ ባስተማሩበት በአንድሪውስ ዩኒቨርስቲ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት ውስጥ የአዲስ ኪዳን ከፍተኛ የምርምር ፕሮፌሰር ናቸው። እሳቸውና ባለቤታቸው ሼሪ ሼፈርድ (ኤም.ዲ) አፍሪካ ውስጥ በምትገኘው በማላዊ እና ብራዚል ውስጥ ሚስዮናውያን ሆነው አገልግለዋል። ሁለት ልጆች እና ስድስት የልጅ ልጆች አሏቸው።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL