የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የዮሐንስ ወንጌል ዋና ዋና ሐሳቦች



4ኛ ሩብ ዓመት 2024


ጥቅምት 23 - 29

6ኛ ትምህርት

Nov 2 - 8




ስለ ኢየሱስ የተሰጡ ተጨማሪ ምስክርነቶች



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚተከሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዮሐ. 3፡25-36፣ ዮሐ. 1፡32-36፣ ዳን. 7፡18፣ ዮሐ. 6፡51-71፣ ዮሐ. 5፡36-38፣ ዮሐ. 7፡37-53።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ” (ዮሐ. 12፡32)።



የሱስ ስለ ራሱ፣ ስለ ማንነቱ፣ ማን እንደላከው፣ ወይም ከየት እንደመጣ ብቻ አስገራሚ ነገሮችን አልተናገረም። ባደረጋቸው ተአምራትና ምልክቶችም ማንነቱን አሳይቷል። አንዳንዶች ስለ ኢየሱስ በግልጽ እንደሚመሰክሩት፡- “ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ይህ ካደረጋቸው ምልክቶች ይልቅ ያደርጋልን? አሉ” (ዮሐ. 7፡ 31)።

እርሱ የቃሉን እውነት በሚያረጋግጡ ተግባራት ቃላቱን ደግፏል። ድራማው ሲቀጥል ግን በህዝቡ መካከል መለያየት ይጀምራል። በቤተሳይዳ መጠመቂያ አጠገብ ያለው ሰው ፈውስ የአንዳንድ መሪዎችን ቁጣ ቀስቅሷል። 5,000 ሰዎችን መመገቡን ተከትሎ በቅፍርናሆም የተደረገው ውይይት ኢየሱስን ብዙ ሰዎች እንዳይቀበሉ አድርጓል። የአልዓዛር ትንሣኤ በአንዳንዶች ላይ እምነት ቢፈጥርም በሌሎች ላይ ግን የኢየሱስን ፍርድ እና ሞት የሚያስከትል ጠላትነት እንዲፈጠር አድርጓል።

የዚህ ሳምንት ትምህርት ስለ ኢየሱስ ከተሰጡ ምስክርነቶች የተወሰኑትን ይመለከታል። በእነዚህ በእያንዳንዳቸው ክንውኖች ውስጥ፣ የኢየሱስ እውነተኛ ማንነት አንዳንድ ገጽታዎች የተገለጡ ሲሆን፣ በአንድ ላይ ሆነው ስለ መሲሑ ኢየሱስ ጥልቅ ራእይ ፈጥረዋል። የዚህን ሳምንት ትምህርት በማጥናት ለጥቅምት 30 ሰንበት ይዘጋጁ።

ጥቅምት 24
Nov 3

የነፍስ ትሕትና፡- መጥምቁ ዮሐንስ


እንደገና ይመሰክራል

ሁለተኛው ትምህርት የመጥምቁ ዮሐንስ ምስክር የመጀመሪያዎቹን ደቀ መዛሙርት ማለትም እንድሪያስንና ዮሐንስን፣ ጴጥሮስ፣ ፊሊጶስንና ናትናኤልን ወደ ኢየሱስ እንዴት እንዳመጣቸው ይገልጻል። አንድ ሰው መጥምቁ ምስክርነቱን ከሰጠ በኋላ ከአከባቢው ይሄዳል ብሎ ይጠብቅ ይሆናል። ነገር ግን በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ በተደጋጋሚ ይመጣል። ዮሐንስ 3:25-36ን ያንብቡ። መጥምቁ ዮሐንስ ራሱን ከኢየሱስ ጋር የሚያነጻጽረው እንዴት ነው?



በመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት እና ስሙ ባልተገለጸ አንድ አይሁዳዊ መካከል ስለ መንጻት አለመግባባት ተፈጠረ፤ ይህም ደግሞ የጥምቀትን ውጤታማነት የሚመለከት ጥያቄ ሊሆን ይችላል (ከማር. 1:4፣ 5 ጋር አነጻጽሩ)። ያለ ጥርጥር ጥያቄውን ለመፍታት ደቀ መዛሙርቱ ወደ ዮሐንስ ሲመጡ፣ በሚገርም ሁኔታ “እነሆ፥ እርሱ ያጠምቃል ሁሉም ወደ እርሱ ይመጣሉ’’ ብለው ስለ ኢየሱስ አነሱለት። በጥቅሶቹ መካከል ለማንበብ አስቸጋሪ አይደለም፡ በኢየሱስ ቀንተዋል፤ እንዲሁም ለመምህራቸው እና ለራሳቸውም ቀናተኞች ነበሩ።

ለዮሐንስ በቅናት ውስጥ ለመግባት በጣም ቀላል ይሆን ነበር፤ ነገር ግን አላደረገውም፣ ምክንያቱም ተልዕኮው ምን እንደሆነ ያውቅ ነበርና። ከዚህ ይልቅ ደቀ መዛሙርቱን እርሱ ክርስቶስ ነኝ ብሎ ፈጽሞ እንዳልተናገረ አሳስቧቸዋል። በተቃራኒው ወደ እርሱ ሊያመለክት፣ መንገዱን ሊጠርግለት፣ ስለ እርሱ ሊመሰክር ነበር የመጣው (ዮሐንስ 1፡6-8)።

የሠርግ ምሳሌን በመጠቀም ራሱን የሙሽራው ወዳጅ ኢየሱስን ደግሞ ሙሽራው ብሎ ጠራ። ሙሽራይቱ የእግዚአብሔር ሕዝብ መሆኑ ነው (ከሆሴዕ 2፡16-23፣ ኢሳ. 62፡1-5 ጋር አነጻጽሩ)። ከዚያም የዮሐንስን እውነተኛ ታላቅነት በሚያሳዩ ቃላት “እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል” አለ (ዮሐ. 3፡30)።

ዮሐንስ 3፡31–36 በኢየሱስ እና በዮሐንስ መካከል ያለውን ንጽጽር ይቀጥላል፣ ይህም የመሲሑን ከመንገድ ጠራጊው በላይ መሆን ያሳያል። ወደ ኢየሱስ በማመላከት የተሰጠው የዮሐንስ ምስክርነት፣ የምስክርነትን ሐሳብ እንደገና አጽንዖት እንዲሰጠው አድርጓል። ያንን ምስክር የተቀበሉ እና በኢየሱስ የሚያምኑ የዘላለም ሕይወት አላቸው። እርሱን ያልተቀበሉት በእግዚአብሔር ቁጣ ሥር ይቀራሉ። ጽሑፉ የሚለው ይህንን ነው። እግዚአብሔር ዓለምን ስለሚወድ ዓለምን ለመቤዠት ልጁን ላከ (ዮሐ. 3፡16፣17)። ነገር ግን የተሰጣቸውን ስጦታ እምቢ ያሉ ሰዎች ለኃጢአታቸው ቅጣቱን ማለትም የዘላለም ሞትን መክፈል ይኖርባቸዋል። በእግዚአብሔርም ሆነ በሰው ፊት የትሕትናን ትምህርት እንዴት ልንማር እንችላለን? ስለ ነፍስ ትሕትና ከዮሐንስ ምሳሌ ምን ልንማር እንችላለን?

ጥቅምት 25
Nov 4

ስለ መሲሑ አዲስ ግንዛቤ


ዮሐንስ 1:32-36ን ያንብቡ። እዚህ ላይ መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ፣ ሕዝቡ በጣም ሲጠበቅ ስለነበረው መሲሕ፣ ነገር ግን ስላልተዘጋጀበት ሁኔታ ምን አለ?



አይሁዶች ከሮም አገዛዝ ነፃ የሚያወጣቸውን መሲሕ ይጠባበቁ ነበር። በጭቆና ውስጥ ለረዥም ጊዜ የቆዩት አይሁዳውያን መሲሑ ሮምን እንደሚያስወግድ ብቻ ሳይሆን ታላቅና ኃያል ሕዝብ አድርጎ እንደሚያቋቁማቸው ያምኑ ነበር። ይሁን እንጂ ዮሐንስ ኢየሱስን “የእግዚአብሔር በግ” ብሎ መጥራቱ፣ ምንም እንኳን በቀጥታ ወደ ቤዛ መስዋዕቱ ቢያመላክትም፣ አብዛኛዎቹ ሰዎች ሳይረዱት ቀርተው ሊሆን ይችላል። የሚናገረውን ሁሉ ጨርሶ ላያውቁም ይችላሉ።

በመሆኑም ዮሐንስ በወንጌሉ ስለ መሲሑ ያላቸውን ግንዛቤ በመቀየር፣ ስለሚመጣው ንጉሥ የሚናገሩት ትንቢቶች በኢየሱስ ፍጻሜ እንዳገኙና እርሱ ስለሚያደርጋቸው ነገሮች እንዲገነዘቡ ለማድረግ ፈልጎ ነበር። እርሱ የሚመጣው እንደ ፖለቲካ እና ወታደራዊ መሪ ሆኖ ሳይሆን ነገር ግን ራሱን ለዓለም ኃጢአት መስዋዕት አድርጎ በማቅረብ ነበር። አላማውም ያ ነበር። ከዚያ በኋላ ብቻ፣ ሁሉም ነገር ሲፈጸም ነው የመጨረሻው መንግሥት የሚመጣው (ዳን. 7፡18ን ይመልከቱ)።

“የሱስ በተጠመቀ ጊዜ፣ ዮሐንስ የሱስ የእግዚአብሔር በግ እንደሆነ ሲናገር ስለ መሲሑ ሥራ አዲስ ብርሃን መከሰቱ ነበር። የነቢዩ አእምሮ “ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም” ወደሚለው ወደ ኢሳያስ ትንቢት አመራ (ኢሳ. 53፡7)።” (ኤለን ጂ ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 121)

ዮሐንስ በዮሐንስ 1፡31 ላይ “እኔም አላውቀውም ነበር” ይላል። ታዲያ ዮሐንስ ኢየሱስን መሲሕ መሆኑን ያወቀው እንዴት ነው? መልሱ ዮሐንስን የላከው ጌታ አስቀድሞ፡- “መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ። እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ” (ዮሐ. 1:33፣ 34) በሚለው ውስጥ ነው። በሌላ አነጋገር፣ እግዚአብሔር ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለዮሐንስ ገለጠለት። “የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው” (1ኛ ቆሮ. 1:24)።

ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ማወቅ፣ በመንፈሱ የማሳመን ኃይል አማካኝነት ከእግዚአብሔር ከራሱ የሚመጣ ነው። ይህ ጭብጥ በዮሐንስ ውስጥ በተደጋጋሚ ይታያል። መዳን ከዓለማዊ ፍልስፍና፣ ሳይንስ ወይም ከፍተኛ ትምህርት አይመጣም። በእምነት እና በመታዘዝ ለኢየሱስ ወደተሰጠ ልብ ከእግዚአብሔር ብቻ ይመጣል። ለእኛ ካልተገለጠልን በቀር ኢየሱስ የስርየታችን መስዋዕት የመሆኑን እውነት እንዴት እናውቃለን? ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስንና ስለ ኢየሱስ የሚያስተምረውን ነገር ማወቅ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ጥቅምት 26
Nov 5

ተቀባይነት እና ተቃውሞ


ሁለተኛው የሰንበት ትምህርት በዮሐንስ 6 ላይ ስለ 5,000 ሰዎች አመጋገብ ገልጿል፤ ነገር ግን የዚያ ታሪክ የመጨረሻውን ክፍል አልዳሰሰም ነበር፤ ይህም አሁን የምናጠናው ይሆናል። ዮሐንስ 6:51-71ን ያንብቡ። ኢየሱስ ሰዎች ለመቀበል ችግር እንዳለባቸው በተመለከተ ምን አለ?



በኢየሱስ አማካኝነት በተአምር ከተመገቡ በኋላ፣ ሰዎቹ ኢየሱስን ንጉሥ አድረገው ዘውድ ሊጭኑበት ተዘጋጅተው ነበር (ዮሐ. 6፡1-15)። በኋላ ግን በቅፍርናሆም ምኵራብ ከእነርሱ ጋር ሲነጋገር፣ የተአምራቱን መንፈሳዊ ትርጉም ገለጸ፤ “እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ” በማለት ተናግሯል (ዮሐ. 6፡35)። ይህ እንጀራ ለዓለም ሕይወት ሲል የሚሰጠው ሥጋው እንደሆነ በሰፊው ገልጿል (ዮሐ. 6፡51)።

ይህ አባባል ኢየሱስ ምድራዊ ንጉሣቸው እንደማይሆን የሕዝቡን ዓይን የከፈተ እውነታ ነበር። ምድራዊ አስተሳሰብ ከፈጠረው አቋም ጋር ሳይገጥም ቀረ። እነርሱ ሲያስቡ የነበረውን መንገድ በመቀየር እንዲለወጡ የሚያደርገውን ኢየሱስን እንደ መሲሕ እንዲያውቁና እንዲቀበሉት የሚያደርገውን መንገድ ሳይቀበሉ ቀሩ። በዚህ ጊዜ ብዙዎቹ ደቀ መዛሙርቱ ትተውት ሄዱ (ዮሐ. 6፡66)።

ከሰብዓዊነት አንፃር ይህ ለኢየሱስ ከባድ ሊሆን ይችላል። የሕዝቡ ተቀባይነት ደስ ይላል። መወደድን የማይፈልግ ማነው? ነገር ግን ብዙ ሰዎች ወደ ኋላ ሲመለሱ እና የአንድን ሰው መርሖዎች ጥያቄ ውስጥ ሲያስገቡ ማየት ተስፋ አስቆራጭ ተፈጥሮ አለው። ሕዝቡ ሲሄድ አይቶ፣ ኢየሱስ የእርሱ የቅርብ የሆኑትን አስራ ሁለቱን፣ እነሱም መሄድ ይፈልጉ እንደሆነ ጠየቃቸው።

በዚህ ጊዜ ነበር ጴጥሮስ አስደናቂ የሆነውን ምስክርነት የገለጸው፤ ይህ ኢየሱስ ምን እንዳለው እና ስለ ማንነቱ የተሰጠ ሌላ ምስክርነት ነው። “አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤ እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምነናል አውቀናልም ብሎ መለሰለት” (ዮሐ. 6:68፣ 69)።

ደቀ መዛሙርቱ ከኢየሱስ ጋር ለተወሰኑ ዓመታት አብረው ሲጓዙ፣ ተአምራቱን ሲያዩ፣ ስብከቱን ሲሰሙ ነበር። ከእርሱ ጋር የሚወዳደር ማንም እንደሌለ ከልምድ አውቀዋል። ምንም እንኳን አንዳንድ ሁኔታዎች ያልተለመዱ ቢሆኑም፣ ይህ ሰው የመምጣቱን ዓላማ የቱንም ያህል ባይረዱም መሲሕ መሆኑን በማመን ጸንተው ነበር። ኢየሱስ ለምን እንደ መጣ መረዳት የጀመሩት ከሞቱና ከትንሳኤው በኋላ ነው። ብዙሃኑ ብዙውን ጊዜ ስህተት ስለመሆኑ ከዚህ ታሪክ ምን እንማራለን? በተለይም በብዙዎች ክርስቲያኖች ዘንድ እንኳ ተቀባይነት ከሌላቸው የእምነታችን ገጽታዎች አንጻር፣ ይህንን ማስታወስ ያለብን ለምንድን ነው?

ጥቅምት 27
Nov 6

የአብ ምስክርነት


የዮሐንስ ወንጌል የሚጀምረው ስለ ቃሉ (ሎጎስ) ከእግዚአብሔር ጋር እንዳለ በመናገር ነው፤ ይህም ከእግዚአብሔር አብ ጋር ማለት ነው (ዮሐ. 1፡1)። ቃል ሥጋ ሲሆን መንፈስ በጥምቀቱ ጊዜ በእርሱ ላይ በማረፍ ስለ ኢየሱስ መሰከረ (ዮሐ. 1፡32-34)። ነገር ግን አብም በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ስለ ኢየሱስ ይመሰክራል። ዮሐንስ 5:36-38ን ያንብቡ። እዚህ ላይ ኢየሱስ ስለ አብ ምን አለ?



ኢየሱስ አብን ካደረጋቸው ሥራዎችና ተአምራቶች ጋር ያያይዛል። አብ እንደላከው እና ስለ እርሱም እንደመሰከረ በጣም በግልጽ ተናግሯል። ማቴዎስ 3:17፣ ማቴዎስ 17:5፣ ማርቆስ 1:11፣ እና ሉቃስ 3:22ን ያንብቡ (በተጨማሪም 2ኛ ጴጥ. 1:17፣ 18 ተመልከቱ)። አብ ስለ የሱስ ምን ይላል?



በኢየሱስ ጥምቀት ጊዜ፣ አብ እና መንፈስ ቅዱስ ከልጁ ጋር በመሆን ይህን አስፈላጊ አጋጣሚ ማለትም የኢየሱስን አገልግሎት መጀመርን አመልክተዋል። አብ ኢየሱስ በእርሱ ደስ የሚሰኝበት የሚወደው ልጁ እንደሆነ ይናገራል። ነገር ግን በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ እንደተዘገበው በክርስቶስ ወሳኝ በሆነ የአገልግሎት ወቅት፣ አብ በድጋሚ ይናገራል።

በዚያ አገልግሎት የመጨረሻዎቹ ቀናት ነገሮች ከፍተኛ ደረጃ ላይ እየደረሱ ነበር።

የኃይማኖት መሪዎቹ እሱን ሊያስቆሙት አልቻሉም (ዮሐ. 12፡19ን ይመልከቱ)። አሁን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ እንዲሞት ይፈልጉ ነበር። አልዓዛርን ከሞት እንዳስነሳው የሰሙ ሰዎች፣ የሕዝቡ ቁጥሩ እየጨመረ በመጣ ጊዜ እጅግ ደስ ብሏቸው (ዮሐ. 12: 17፣ 18) ኢየሱስን መከተል ጀመሩ። ለበዓሉ እዚያ የነበሩት ግሪኮች እንኳ ኢየሱስን ለማየት ይፈልጉ ነበር።

በዚህ ጊዜ፣ በዮሐ. 12፡28 ላይ “አባት ሆይ ስምህን አክብረው” ብሎ ለተናገረው ለኢየሱስ ቃል ምላሽ አብ ከሰማይ ሆኖ “አከበርሁት ደግሞም አከብረዋለሁ” በማለት በድጋሚ ተናግሯል (ዮሐ. 12:28)።

ቀደም ሲል እንዳየነው የኢየሱስ የክብር ሰዓት መስቀሉ ነው። ስለዚህ፣ ስለ ኢየሱስ የሚሰጠውን የአብ ምስክርነት፣ የእግዚአብሔር በግ ለዓለም ኃጢአት ሲል የሚሰዋውን ታላቅ መስዋዕት ያመለክታል። ይህ የምድራዊ አገልግሎቱ ፍጻሜ ነው። የእርሱ ሞት የኃጢአታችንን ቅጣት በሙላት ከፍሏል፣ እናም በእርሱ በማመን መዳን እንጂ ያንን ቅጣት ራሳችን ልንጋፈጠው አይገባንም።

ጥቅምት 28
Nov 7

የሕዝቡ ምስክርነት


“ከበዓሉም በታላቁ በኋለኛው ቀን ኢየሱስ ቆሞ። ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ” (ዮሐ. 7:37-38)።

ኢየሱስ ስለ ራሱ፣ ስለ ማንነቱና ምን ሊያደርግ እንደመጣ በድፍረት የተናገረውን ዮሐንስ ብዙ ጊዜ መዝግቦ ነበር። ከላይ በዮሐንስ 7፡37-38 ድረስ የተጠቀሱት ቃላቶች ኢየሱስ ስለ ራሱ እና ወደ እርሱ ለሚመጡት ሁሉ ምን እንደሚያደርግ የተናገረውን የሚገልጽ ሌላ ምሳሌ ነው። እነዚህም አስገራሚ የይገባኛል ጥያቄዎች ነበሩ። ኢየሱስ በዳስ በዓል ላይ ለነበሩት አይሁዳውያን ሲናገር የብዙ ሰዎች ምላሽ ምን ነበር? ዮሐንስ 7፡37-53።



አንዳንዶች እርሱ እንደ ሙሴ ከረጅም ጊዜ በፊት የተተነበየለት ነቢይ ነው ብለው ነበር (ዘዳ. 18፡15-19 ይመልከቱ)። ሌሎች ደግሞ ኢየሱስን ክርስቶስ ነው ብለው አስበዋል።

ነገር ግን ይህ መሲሑ ከገሊላ ስለማይመጣ፣ ከዳዊት ዘር ሆኖ በቤተልሔም መወለድ አለበት የሚለውን ክርክር አስነሳ፤ ምንም እንኳን ብዙዎች ይህንን ያወቁ ባይመስልም፣ ስለ ኢየሱስ የተባሉት እነዚህ ሁሉ እውነት ነበሩ! (ከማቴዎስ 1-2 ጋር አነጻጽሩ) ሊያስሩት የመጡ ወታደሮች እንኳን በእሱ እና በንግግሮቹ አንደበተ ርቱዕነት ተቸገሩ። ፈሪሳውያን ለወታደሮቹ ሌላ ጥያቄ በመጠየቅ መልስ ሰጡ “ከአለቆች ወይስ ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለን?” (ዮሐ. 7፡ 48)። ይህ የፈሪሳውያን ጥያቄ ዮሐንስ ከኢየሱስ ጋር ከተገናኘ በኋላ ኢየሱስን ከፈሪሳዊያን ተንኮል ለመጠበቅ ሲፈልግ ስለነበረው ስለኒቆዲሞስ ለመናገር እንደገና እድል ሰጠው።

“ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን? አላቸው” (ዮሐ. 7፡51)።

ኒቆዲሞስ ኢየሱስን መሲሕ አድርጎ ተቀብሎት ይሆን? ምንም እንኳን ይህ ትዕይንት እርሱን እንደ መሲሕ እንደተቀበለው ባያረጋግጥም፣ በዚህና ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ባደረገው ድርጊት መካከል (ዮሐ. 19:39፣ 40ን ተመልከቱ) መጽሐፍ ቅዱስ ኒቆዲሞስ በእርሱ እንዳመነ ጠንካራ ማስረጃ ይሰጠናል።

እናም ለጥያቄያቸው ትክክለኛው መልስ የሚሆነው፣ አዎን እንደውም ከፈሪሳውያን አንዱ በእርሱ አምኗል የሚል ነው። ዮሐንስ 7:49ን ያንብቡ። መሪዎቹ ኢየሱስን ተከትለው ለመጣው ሕዝብ ያላቸውን ንቀት በሚያሳይ መልኩ የተናገሩት ምን ነበር? ከዚህ ላይ ምን ትምህርት ልንወስድ እንችላለን?

ጥቅምት 29
Nov 8


ተጨማሪ ሀሳብ


ከኤለን ጂ ዋይት፣ የዘመናት ምኞት ከሚለው መፅሐፍ “አስጊ ሁኔታ በገሊላ” ገጽ 383-394፤ “በቤተ መቅደስ የውጭ አደባባይ” ገጽ 621፣ 626 ያንብቡ።

“ወደ ማን እንሄዳለን?” የእስራኤል መምህራን የስግደት ሥርዓትና ሕግጋት ባሮች ነበሩ። ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ዘወትር እንደተነታረኩ ናቸው። ከየሱስ መለየት ማለት በስግደት ሥርዓት አምላኪዎችና በሕልማቸውና በእውናቸው የራሳቸውን ክብር ብቻ በሚያስቡ ሰዎች እጅ መውደቅ ማለት ነው። ደቀ መዛሙርት ክርስቶስን ከተቀበሉ ወዲህ ከዚያ በፊት አግኝተውት የማያውቁትን ሰላምና ደስታ አግኝተዋል። እንዴት የኃጥአንን ወዳጅ ወደናቁትና ወደአሳደዱት ሰዎች ይሔዳሉ? ለብዙ ዘመን ሲጠብቁት የነበረው መሲህ መጥቶላቸዋል። ስለሆነም እርሱን ትተው ሕይወቱን ለማጥፋት ወደሚፈልጉትና እነርሱም የመሲሑ ተከታይ በመሆናቸው ወደሚያሳድዱዋቸው ሰዎች መሔድ አይችሉም።

“ወደ ማን እንሄዳለን?” የክርስቶስን የፍቅርና የምሕረት ትምህርት ትቶ ወደ አለማመንና ወደ አመጽ የጨለማ ዓለም መሔድ የማይታሰብ ነገር ነው። የየሱስን አስደናቂ ሥራ ያዩ ብዙ ሰዎች ትተውት ሲሔዱ ጴጥሮስ “አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ” አውቀናል በማለት የደቀ መዛሙርቱን እምነት ገለጸ። የነፍሳቸውን መልህቅ የማጣት ሐሳብ ፍርሃትና ጭንቀት ለቀቀባቸው። አዳኛቸውን ማጣት ማለት በጨለማ በባሕር ላይ በማዕበል መነዳት ማለት ነው” (ኤለን ጂ ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 393)።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ መሲሕ ስለመሆኑ እና ስለ ክርስትና እውነት ማስረጃ ሲሰጣቸው በደስታ የሚቀበሉት እና ሌሎች ደግሞ ተመሳሳይ ማስረጃ ቢሰጣቸውም የማይቀበሉት ለምን እንደሆነ፣ ስለዚህ ከባድ ጥያቄ በቡድናችሁ ውስጥ ተነጋገሩ?

2. ኢየሱስ ክርስቶስ ለኃጢአታችን ሞቷል ከሚለው የበለጠ ምን እውነት አለ? ሆኖም፣ ይህን ወሳኝ እውነት ማወቅ የቻልነው እንዴት ነው? በሳይንስ፣ በተፈጥሮ ህግ፣ በተፈጥሮ ነገረ-መለኮት፣ በሎጂክ ወይም በምክንያት ነው? ምንም እንኳን እነዚህ ነገሮች ፈጣሪ በሆነው እግዚአብሔር እንድናምን ሊመሩን ቢችሉም፣ ነገር ግን የመጀመሪያው ምክንያት፣ የማይንቀሳቀሰው አንቀሳቃሽ፣ እነዚህ የጥናት መስኮች ምንም ይሁኑ ምንም፣ ለብቻቸው ወይም በጋራ ሆነው፣ ማወቅ ያለብንን በጣም አስፈላጊ እውነት ሊያስተምሩን አይችሉም። ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ። እነዚህ ሁሉ የትምህርት ዓይነቶች፣ በመርሕ ደረጃም ቢሆን እንኳን፣ በእርግጥ ማወቅ ወደሚገባን አንድ ነገር ሊመሩን አለመቻላቸውና መጽሐፍ ቅዱስን በእምነት ጉዳዮች ላይ የመጨረሻው ባለስልጣን ማድረግ ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑ ሊያስተምረን የሚገባው እውነታ ምንድን ነው?

3. አምላክ በአንድ ሰው የግል ሕይወት ውስጥ ያደረጋቸውን ነገሮች መናገሩ በራሱ ለእምነት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL