የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የዮሐንስ ወንጌል ዋና ዋና ሐሳቦች



4ኛ ሩብ ዓመት 2024


መስከረም 25 - ጥቅምት 1

2ኛ ትምህርት

Oct 5 - 11




የመለኮት ምልክቶች



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚተከሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዮሐ. 6፡1-15፣ ኢሳ. 53:4-6፣ 1ኛ ቆሮ. 5:7፣ ዮሐ. 6:26-36፣ ዮሐ. 9:1-41፣ 1ኛ ቆሮ. 1:26-29፣ ዮሐ. 11።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ኢየሱስም፡- ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት” (ዮሐ. 11:25-26)።



የሱስ ክርስቶስ ከአብ ጋር አንድ የሆነ፣ ከሌላ ያልተገኘና ያልተፈጠረ ዘላለማዊ ልጅ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምራል። የተፈጠረውን ሁሉ የፈጠረው ኢየሱስ ነው (ዮሐ. 1፡1፣ 3)። ስለዚህም ኢየሱስ ሁልጊዜ አለ፤ እርሱ ያልነበረበት ጊዜ አልነበረም። ኢየሱስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ሰብዓዊ ማንነታችንን ቢለብስም፣ መለኮታዊነቱን ጠብቆአል፣ እናም አንዳንድ ጊዜ ኢየሱስ ይህን መለኮታዊነቱን የሚገልጡ ነገሮችን ተናግሮአል፣ አድርጓልም።

ይህ እውነት ለዮሐንስ አስፈላጊ ነበር፣ ለዚህም ነው፣ ዮሐንስ አንዳንድ የኢየሱስን ተአምራት ሲናገር፣ የክርስቶስን አምላክነት ለማመልከት የተጠቀመባቸው። ኢየሱስ መለኮታዊነቱን የሚገልጡ ነገሮችን ብቻ ሳይሆን የተናገረው ነገር ግን አምላክነቱን በመግለጥ የተናገራቸውን ንግግሮች የሚደግፉ ሥራዎችንም ሰርቷል።

የዚህ ሳምንት ትምህርት ሦስቱን የኢየሱስ መለኮታዊነት ምልክቶችን ይመለከታል።

በጣም የሚያስደንቀው ነገር በሁሉም ሁኔታዎች አንዳንድ ሰዎች ተአምሩን አላመኑም ወይም አስፈላጊነቱን አልተገነዘቡም ነበር። ለአንዳንዶች ከኢየሱስ የሚርቁበት፤ ለሌሎች ደግሞ ዓይናቸው የሚታወርበት፤ ለሌሎች ደግሞ የኢየሱስን ሞት የማሴር ጊዜ ነበር። እንደዚሁ ለሌሎች ደግሞ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚያምኑበት ጊዜ ነበር። የዚህን ሳምንት ትምህርት በማጥናት ለጥቅምት 2 ሰንበት ተዘጋጁ።

መስከረም 26
Oct 6

የአምስት ሺዎች መመገብ


በዮሐንስ 6፡4ና 5 ላይ፣ ሐዋርያው ከነበረበት ወጣ በማለት አምስት ሺህ ሰዎች የበሉበት ወቅት የፋሲካ በዓል መቃረቢያ እንደነበር ይናገራል። የፋሲካ በዓል እስራኤላዊያን ከግብፅ ነፃ የወጡበት መታሰቢያ በዓል ነበር። የፋሲካ በግ የበኩር ልጅ ሞትን ቦታ የተካ ነበር።

ይህ መስዋዕትነት የኢየሱስን በእኛ ምትክ መሞት ያመላክታል። በኃጢአታችን ምክንያት እኛ ልንቀበለው የሚገባን ቅጣት በኢየሱስ ላይ ወደቀ። በእርግጥ ፋሲካችን የሆነው ክርስቶስ ስለ እኛ ሲል ታርዶአል (1ኛ ቆሮ. 5፡7)።

“ልቡ እስኪሰነጠቅ፣ ሕይወቱም እስክትደቅ ድረስ የመተላለፍን ኩነኔና የአባቱን ፊት መሰወር ተሸከመ። ይህ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለው ኃጢአተኞች እንዲድኑ ነበር” (ኤለን ጂ ዋይት፣ ታላቁ ተጋድሎ፣ ገጽ 617)። ዮሐ. 6:1–14 ያንብቡ። እዚህ ላይ በኢየሱስና በሙሴ መካከል ምን ዓይነት ተመሳሳይነት ሊገኝ ይችላል? ማለትም ኢየሱስ ቅድመ አያቶቻቸው በሙሴ አገልግሎት አማካኝነት ያገኙትን ነፃ መውጣት ለሰዎች የሚያስታውስ ምን ነገር አደረገ?



የዚህ ታሪክ ብዙ ዝርዝር ነገሮች ኢየሱስን በዘፀአት ውስጥ ከሙሴ ጋር በንፅፅር የሚያቀርብ ነው። የፋሲካው ጊዜ (ዮሐ. 6፡4) ታላቁን ከግብፅ ነጻ መውጣትን ያመለክታል።

ሙሴ ወደ ሲና እንደወጣ፣ ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጣ (ዮሐ. 6፡3) ። እስራኤላውያን በምድረ በዳ እንደተፈተኑ፣ የሱስ ፊልጶስን ፈተነው (ዮሐ. 6:5፣ 6)። የእንጀራው መባዛት (ዮሐ. 6፡11) መናን ያስታውሳል። የተረፈውን ምግብ መሰብሰብ (ዮሐ. 6: 12) እስራኤላውያን መናውን ከመሰብሰባቸው ጋር ይስተያያል። የተረፈው እንጀራ በአሥራ ሁለት መሶብ መለቀሙ (ዮሐ. 6፡13) ከአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ቁጥሩ ጋር ተመሳሳይ ነው። በዘዳግም 18፡15 ከተተነበየው “እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ” ከሚለው ትይዩ፣ ኢየሱስ ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ እንደሆነ (ዮሐ. 6፡14) ሰዎቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ይህ ሁሉ የሚያመለክተው ኢየሱስን እንደ አዲሱ ሙሴ፣ ሕዝቡን ነፃ ለማውጣት መምጣቱን ነው።

ስለዚህ፣ ዮሐንስ ኢየሱስን እያሳየው ያለው ምልክቶችንና ድንቆችን ሲያደርግ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን በአውዳቸው ለአይሁዶች ልዩ ትርጉም ሊኖራቸው የሚገባቸውን ምልክቶችንና ድንቆችን እያደረገ እንደነበረ ነው። በመሠረታዊነት ሰዎችን ወደ እርሱ መለኮታዊነት እየጠቆመ ነበር። ኢሳያስ 53:4-7 እና 1ኛ ጴጥሮስ 2:24ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ስለ ኢየሱስ የእግዚአብሔር በግ መሆን እንዴት ያለ ታላቅ እውነት ያስተምራሉ? መለኮታዊነቱ ከዚህ እውነት ጋር እንዴት የተያያዘ ነው? ለምን ይህ እውነት ልናውቀው የምንችለው በጣም አስፈላጊ እውነት ሆነ?

መስከረም 27
Oct 7

“ይህ በእውነት ነቢይ ነው”


ዮሐንስ 6:14፣ 15፣ 26-36ን ያንብቡ። ሕዝቡ ለኢየሱስ ተአምራት ምን ምላሽ ሰጡ? ኢየሱስስ ማንነቱን ለማስተማር ይህንን የተጠቀመው እንዴት ነበር?



አይሁዳውያን ከሮም መንግሥት ጭቆና ነፃ የሚያወጣቸውን ምድራዊ መሲሕ ይጠባበቁ ነበር። በጦርነት ውስጥ ከሚያጋጥሙ በጣም አስቸጋሪ ነገሮች መካከል ሁለቱ፣ ወታደሮችን መመገብ እና የቆሰሉትንና የሞቱትን መንከባከብ ናቸው። ኢየሱስ በተአምራቱ ሁለቱንም ማድረግ እንደሚችል አሳይቷል።

ነገር ግን ኢየሱስ የመጣው ለዚህ አይደለም፣ እና የተአምራቱ ዓላማም ይህ አልነበረም።

ይልቁንም የአምስት ሺህ ሰዎች መመገብ ዘገባ፣ ኢየሱስ የሕይወት እንጀራ ስለመሆኑ፣ እግዚአብሔር ራሱ ከሰማይ እንደ ወረደ ለማስረዳት ዕድል ሰጥቷል። “‘የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ” ሲል ተናግሯል። “ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም” (ዮሐ. 6: 35)።

ይህ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ከሰባቱ “እኔ ነኝ” የእርሱ መግለጫ የመጀመሪያው ነው፣ “እኔ ነኝ” የሚለውም አንዳንድ አባባሎችን የሚያረጋግጥ ነበር (“የሕይወት እንጀራ” ዮሐ. 6፡35፤ “የዓለም ብርሃን” ዮሐ. 8፡ 12፤ “በር” ዮሐ. 10:7፣ 9፤ “መልካም እረኛ” ዮሐ. 10:11፣ 14፤ “ትንሣኤና ሕይወት” ዮሐ. 11:25፤ “መንገድ፣ እውነትና ሕይወት” ዮሐ. 14፡6፤ “እውነተኛ የወይን ግንድ” ዮሐንስ 15:1፣ 5)። እነዚህ እያንዳንዳቸው ስለ ኢየሱስ አንድ ጠቃሚ እውነት ያመለክታሉ። “እኔ ነኝ” የሚሉት መግለጫዎች፣ እግዚአብሔር ራሱን ለሙሴ ታላቁ “እኔ ነኝ” ብሎ ወዳቀረበው ወደ ዘጸአት 3 ያመላክታሉ (ከዮሐ. 8፡58 ጋር አነጻጽሩ)። የሱስ ታላቁ “እኔ ነኝ” ነው። ሕዝቡ ግን ይህን ሁሉ ሳይረዳ ቀርቷል።

“እነርሱ የዓይን ምስክር ሆነው እንዳዩት የሱስ ብዙ አስገራሚ ድርጊቶችን መሥራት ከቻለ ለሕዝቡ ጤንነትን፣ ጉልበትንና ሐብትን ለመስጠትና ከጨቋኞቻቸው አርነት አውጥቶ ኃይልና ክብር እንዲያገኙ ለማድረግ ለምን አይችልም የሚሉ ጥያቄዎች እርካታ ከማያውቁት ልቦቻቸው ተሰነዘሩ። የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ እያለ የእሥራኤል ንጉሥ ለመሆን አለመፈለጉ ሊረዱት የማይችሉት ምስጢር ሆነባቸው። እምቢታውን አጣመው ተረጎሙት። ብዙዎች ስለ ተልዕኮው መለኮታዊ ባሕርይ እርግጠኛ ስላልሆነ ነው መብቱን ለመቀበል ያልደፈረው ብለው ደመደሙ። ለጥርጣሬ የልባቸውን በር ስለከፈቱለት ሰይጣን የዘራው ዘር አምሳያውን ፍሬ፣ ማለትም አለመረዳትንና ክህደትን አፈራ” (ኤለን ጂ ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 389)።

እነርሱ ለዘላለም ሕይወት የሚጸናውን እውነት ሳይሆን ቁሳዊ ጥቅምን ይፈልጉ ነበር።

ይህ ካልተጠነቀቅን ሁላችንም ሊያጋጥመን የሚችል ወጥመድ ነው። በቁሳዊ ነገሮች በመጠመድ የመንፈሳዊ ነገሮች ኪሳራ ውስጥ ከመግባት መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

መስከረም 28
Oct 8

የዓይነ ስውሩ ፈውስ፡ ክፍል 1


ዮሐንስ 9:1-16ን ያንብቡ። ደቀ መዛሙርቱ የዚህ ሰው መታወር መንስኤ ምን እንደሆነ አስበው ነበር? ኢየሱስስ የሐሰት እምነታቸውን ያረመው እንዴት ነበር?



ደቀ መዛሙርቱ በበሽታና በኃጢአት መካከል ግንኙነት ፈጠሩ። በርካታ የብሉይ ኪዳን ምንባቦች ወደዚያ አቅጣጫ ያመለክታሉ (ከዘጸ. 20፡5፣ 2ኛ ነገ. 5፡15-27፣ 2ኛ ነገ. 15፡5፣ 2ኛ ዜና 26፡16-21 ጋር አነጻጽሩ)፤ ነገር ግን የኢዮብ ታሪክ እንዲህ ዓይነቱ ግንኙነት ሁልጊዜ መከሰቱን በተመለከተ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የሚያስተምር ነው።

ኢየሱስ ጉዳዩን መስመር አስያዘው፤ በኃጢአትና በሥቃይ መካከል ያለውን ግንኙነት ሳይክድ፣ ነገር ግን በዚህ ጉዳይ እግዚአብሔር በፈውስ እንደሚከብር በማሳየት ወደ ከፍተኛው ዓላማ አመላከተ። ዘገባው ከፍጥረት ታሪክ ጋር አንዳንድ ዝምድናዎችን ይዟል፤ እግዚአብሔር የመጀመሪያውን ሰው ከምድር አፈር እንደ ፈጠረ (ዘፍ. 2:7) ኢየሱስ ከማህፀን ጀምሮ ዓይነ ስውር የነበረው ሰው ያጣውን ለመስጠት ጭቃን አዘጋጀ።

በማቴዎስ፣ በማርቆስ እና በሉቃስ ውስጥ፣ ተአምራዊ ታሪኮች አንድ አይነት አቅጣጫን ይከተላሉ፤ የችግሩን ገለፃ፣ ግለሰቡን ወደ ኢየሱስ ማቅረቡ፣ ፈውሱ እና እግዚአብሔርን በማመስገን ለፈውሱ እውቅናን መስጠት ይገኙበታል።

በዮሐንስ 9 ውስጥ ባለው ታሪክ፣ ይህ ከላይ የተባለው ቅደም ተከተል በዮሐንስ 9፡ 7 ላይ ተጠናቋል። በዮሐንስ በተለየ መልኩ በቀረበው ዘገባ ግን የተአምሩ ጠቀሜታ በጣም ሰፊ የውይይት ነጥብ ሆነ፤ ይህም በተፈወሰው ሰው እና በኃይማኖት መሪዎች መካከል ረጅም ግንኙነት መፈጠሩ ነው። ይህ አስደናቂ ውይይት የሚያጠነጥነው በሁለት የተጠላለፉ ተቃራኒ ጥንድ ፅንሰ ሀሳቦች ላይ ነው፤ እነርሱም ኃጢአት ወይም ሥራ እና ዕውርነት ወይም ማየት ናቸው።

ተራኪው እስከ ዮሐንስ 9፡14 ድረስ፣ የሱስ በሰንበት ይህን ፈውስ እንዳደረገ ሳይናገር፣ ቀጥሎ ግን እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን እንደ ሰው ወግ ይህ ሰንበትን የጣሰ ተግባር ስለመባሉ ለአንባቢያን ይዘግባል። ስለዚህም እርሱ በፈሪሳውያን እንደ ሰንበት ተላላፊ ተቆጠረ። “ሰንበትን አያከብርም” በማለት ስለጸኑ፣ ድምዳሜያቸው እርሱ ከእግዚአብሔር አይደለም የሚል ነበር። ሌሎች ግን አንድ ኃጢአተኛ እነዚህን ምልክቶች ማድረግ መቻሉ የሚያስጨንቅ ሆኖ አግኝተውታል (ዮሐ. 9፡16)።

ውይይቱ ገና ሳይጠናቀቅ አስቀድሞ መለያያት ተፈጠረ። ዓይነ ስውሩ ስለ ኢየሱስ ማንነት ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጣለት፣ ነገር ግን የኃይማኖት መሪዎቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግራ ተጋቡ ወይም እውነተኛ ማንነቱን ባለማየት እየታወሩ መጡ። ይህ ታሪክ በራሳችን እምነት እና ትውፊት በመታወር በዓይናችን ፊት ለፊት ያሉትን አስፈላጊ የሆኑ እውነቶችን ሳናገኝ እንድንቀር ስለሚያደርገው አደጋ ምን ሊነግረን ይገባል?

መስከረም 29
Oct 9

የዓይነ ስውራኑ ፈውስ፡ ክፍል 2


ዮሐንስ 9:17-34ን ያንብቡ። መሪዎቹ ምን ዓይነት ጥያቄዎች ነው የጠየቁት? ዓይነ ስውሩስ ምን ምላሽ ሰጠ?





ምንም እንኳን እርሱ የመወያያ ርዕስ ቢሆንም፣ ይኽኛው የዮሐንስ ወንጌል 9 ረጅም ክፍል ኢየሱስ የመድረኩ ዋና ተዋናይ ያልሆነበት ብቸኛው የዮሐንስ ወንጌል ክፍል ነው።

የኃጢአት ጥያቄ ታሪኩን እንደጀመረው ሁሉ (ዮሐ. 9፡2) ፈሪሳውያኑ ኢየሱስ በሰንበት ስለፈወሰ ኃጢአተኛ ነው ብለው አስበዋል (ዮሐ. 9:16፣ 24) እናም የተፈወሰውን ሰው “ሁለንተናህ በኃጢአት ተወለድህ” በማለት ስሙን ሲያጠፉ ነበር (ዮሐ. 9:34)።

በተገላቢጦሽ ሁኔታ የማወቅ ጉጉት ተከሰተ። ስለ ኢየሱስ ያለው አድናቆት እያደገ በመምጣቱና በእርሱ በማመኑ፣ ዓይነ ስውሩ በአካል ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊውም በበለጠ እያየ መጣ። በአንጻሩ ፈሪሳውያን በኢየሱስ ላይ በነበራቸው መከፋፈል (ዮሐ. 9፡16)፣ ከዚያም እርሱ ከየት እንደመጣ ባለማወቃቸው (ዮሐ. 9፡29) ምክንያት የመረዳታቸው ዓይን እየታወረ መጥቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ይህ ተአምር ዮሐንስ ኢየሱስ ማን እንደሆነ እንዲነግረን አጋጣሚ ፈጥሮለታል። በዮሐንስ 9 ላይ ያሉት የምልክቶች ጭብጥ በወንጌል ውስጥ ካሉ ሌሎች በርካታ ጭብጦች ጋር ይገናኛል። ዮሐንስ ኢየሱስ የዓለም ብርሃን መሆኑን በድጋሚ አረጋግጧል (ዮሐ. 9፡ 5ን ከዮሐ. 8፡12 ጋር አነጻጽሩ)። ታሪኩ ስለ ኢየሱስ ምስጢራዊ አመጣጥም ይናገራል። እርሱ ማን ነው፣ ከወዴት መጣ፣ ተልዕኮውስ ምንድን ነው? (ዮሐ. 9:12፣ 29ን ከዮሐ. 1:14 ጋር አነጻጽሩ)።

በቀደሙት ተአምራዊ ዘገባዎች የተጠቀሰው የሙሴ ማንነት በዚህ ምዕራፍ ውስጥም ይታያል (ዮሐ. 9:28፣ 29፤ ዮሐ. 5:45፣ 46ን ከዮሐ. 6:32 ጋር አነጻጽሩ)። በመጨረሻም የሕዝቡ ምላሽ ጭብጥ አለ። አንዳንዶቹ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ይወዳሉ፣ ሌሎች ደግሞ በእምነት ምላሽ ይሰጣሉ (ዮሐ. 9፡16-18፣ 35-41ን ከዮሐ. 1፡9-16፣ ዮሐ. 3፡16-21፣ ዮሐ. 6፡60-71 ጋር አነጻጽሩ)።

እዚህ ላይ የሚታየው የኃይማኖት መሪዎች መንፈሳዊ እውርነት እጅግ አስፈሪ ነው።

በአንድ ጊዜ ዓይነ ስውር የነበረው “ዕውር ሆኖ የተወለደውን ዓይኖች ማንም እንደ ከፈተ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አልተሰማም፤ ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ምንም ሊያደርግ ባልቻለም ነበር” ብሎ ማወጅ ቻለ (ዮሐ. 9፡32፣ 33)። ምንም እንኳን ጠንካራ ማስረጃዎች ቢኖሩም፣ በቀዳሚነት ኢየሱስን ሊያውቁትና መሲሕ አድርገው ሊቀበሉት የተገባቸው የኃይማኖትና የአገሩ መንፈሳዊ መሪዎች ሊመለከቱ አልቻሉም። ወይም እነርሱ በእውነት ሊያዩት አልፈልጉም። ይህ የእኛም ልብ ሊያታልለን እንደሚችል እንዴት ያለ ኃይለኛ ማስጠንቀቂያ ነው! 1ኛ ቆሮንቶስ 1:26-29ን ያንብቡ። ጳውሎስ የጻፈው ነገር በዚህ ትዕይንት ውስጥ ከተፈጸመው ሁኔታ ጋር የሚስማማው እንዴት ነው? ይኸው መሠረታዊ መርሖ በአሁኑ ጊዜም እንኳ ተግባራዊ የሚሆነው እንዴት ነው?

መስከረም 30
Oct 10

የአልዓዛር መነሳት


ዮሐንስ 11 በሐዘን የተሞላ ነው፤ የአንድ ውድ ጓደኛ መታመም አሳዛኝ ዜና (ዮሐ. 11፡1-3)፤ ስለ ሞቱ ማልቀስ (ዮሐ. 11:19፣ 31፣ 33)፤ ኢየሱስ በቦታው ቢኖር ኖሮ አልዓዛር አይሞትም በማለት የሚሰማው የእህቱ ዋይታ (ዮሐ. 11:21፣ 32)፤ እና የገዛ የኢየሱስ እንባ (ዮሐ. 11፡35)።

ነገር ግን ኢየሱስ ወደ አልዓዛር የሚያደርገውን ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ሁለት ቀናት ዘግይቶ ነበር (ዮሐ. 11:6)፤ እንደው እርሱ ቀደም ብሎ ባለመሄዱ እንደተደሰተ አመላክቷል (ዮሐ. 11:14፣ 15)። ይህ ድርጊት ቀዝቀዝ ካለ ልብ የተነሳ የሆነ አልነበረም። ይልቁንም የእግዚአብሔርን ክብር ለመግለጥ እንጂ።

ወደ ዮሐንስ 11፡17-27 ስንደርስ፣ አልዓዛር ከሞተ አራት ቀን ሆኖት ነበር። ከአራት ቀናት በኋላ ሰውነቱ ይበሰብሳል እናም ማርታ “ጌታ ሆይ፥ ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል አለችው” (ዮሐ. 11፡39)። የኢየሱስ መዘግየት ከዚያ በኋላ የተፈጸመው ተአምራት ይበልጥ አስገራሚ እንዲሆን ብቻ ማስቻሉ ምንም ጥርጥር የለውም። የበሰበሰውን አስከሬን ማስነሳት? ኢየሱስ ራሱ እግዚአብሔር ለመሆኑ ከዚህ በላይ ምን ዓይነት ማረጋገጫ ሊሰጥ ይችላል?

እናም እንደ እግዚአብሔር፣ በመጀመሪያ ለመኖር ሕይወትን የፈጠረው ኢየሱስ በሞት ላይ ስልጣን ነበረው። ስለዚህ ኢየሱስ ይህን አጋጣሚ ማለትም የአልዓዛርን ሞት፣ ስለ ራሱ አንድ ወሳኝ እውነትን ለመግለጥ ተጠቅሞበታል። “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ። የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነ የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም” (ዮሐ. 11፡25-26)። ዮሐ. 11:38-44ን ያንብቡ። ኢየሱስ የተናገረውን ቃል የሚደግፍ ምን ነገር አደረገ?



ኢየሱስ የዓለም ብርሃን መሆኑን እንዳሳየ (ዮሐ. 8:12፣ ዮሐ. 9:5) ለዓይነ ስውሩ ማየትን እንደሰጠ ሁሉ (ዮሐ. 9:7)፣ በዚህም ስፍራ አልዓዛርን ከሞት አስነስቷል (ዮሐ. 11:43- 44)፤ ይህም እርሱ ትንሣኤና ሕይወት መሆኑን ያሳያል (ዮሐ. 11፡25)።

ይህ ተአምር ከሌሎቹ ሁሉ በላይ ኢየሱስን እንደ ሕይወት ሰጪ፣ እርሱን እግዚአብሔር እንደሆነ የሚያመላክት ነው። ይህ ኢየሱስ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ልጅ እንደሆነ እና በማመን በእርሱ በኩል ሕይወት ማግኘት እንደምንችል ለዮሐንስ ወንጌል ጭብጥ ሐሳብ ጠንካራ ድጋፍ ይሰጣል (ዮሐ. 20፡30፣ 31)። ሆኖም፣ ወደዚህ አስደናቂ ታሪክ መጨረሻ (ዮሐ. 11፡45-54)፣ ያዩት ብዙዎች ወዳመኑበት ስንደርስ (ዮሐ. 11፡45)፣ ኃይለኛ ግን አሳዛኝ ነገር ተገለጠ። ኢየሱስ ሙታንን ወደ ሕይወት ማምጣት እንደሚችል አሳይቷል፣ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች እርሱን በመግደል እርሱን ማስቆም እንደሚችሉ ያስባሉ? ይህ ከእግዚአብሔር ጥበብ እና ኃይል በተቃራኒ ለሚቆመው የሰው ልጅ ደካማ ባሕሪ እንዴት ያለ ምሳሌ ነው!

ጥቅምት 1
Oct 11


ተጨማሪ ሀሳብ


ከኤለን ጂ ዋይት የዘመናት ምኞት መፅሐፍ “አስጊ ሁኔታ በገሊላ” ገጽ 383-394፤ “አልዓዛር ና ውጣ” ገጽ 524-536፤ እና “የካህናት ሴራ” ገጽ 537-542 ያንብቡ።

“ለዓለም ሕይወትን የሚሰጠው የክርስቶስ ሕይወት የሚገኘው ከቃሉ ነው። የሱስ ሕሙማንን የፈወሰውና አጋንንትን ያስወጣው በቃሉ ነው። በቃሉም ባሕሩን ጸጥ እንዲል አደረገ፣ ሙታንንም አስነሳ። ቃሉ ኃይል እንዳለው ሕዝቡ የዓይን ምስክር ነበሩ። የሱስ በብሉይ ኪዳን ነቢያትና በመምህራን አማካይነት እንደተናገረው አሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ተናገረ።

መላው መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስ መግለጫ ነው፣ ስለሆነም አዳኛችን የተከታዮቹን እምነት በቃሉ ላይ ለመመሥረት ፈለገ። እርሱ በሥጋ በሚለያቸው ጊዜ የኃይላቸው ምንጭ የሚሆነው ቃሉ ነው። የሚኖሩት እንደ ጌታቸው “እግዚአብሔር በሚናገረው ቃሉ ሁሉ” ነው” (ማቴ. 4፡4)።

“ሥጋዊ ሕይወታችን የሚኖረው በምግብ ኃይል እንደሆነ ሁሉ መንፈሳዊ ሕይወታችንም የሚኖረው በእግዚአብሔር ቃል ነው። እያንዳንዱ ሰው በግሉ ሕይወትን ከእግዚአብሔር ቃል ማግኘት አለበት። ከምግብ የሚገኘውን ድጋፍ ለማግኘት እያንዳንዳችን በግል መመገብ እንዳለብን ሁሉ ልክ በዚያው ዓይነት የእግዚአብሔርን ቃል መመገብ አለብን። ቃሉን በሌላ ሰው አማካይነት ብቻ ማግኘት የለብንም። ቃሉን ለማስተዋል እንድንችል የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ለማግኘት እግዚአብሔርን እየጠየቅን መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ማጥናት ይገባናል” (የዘመናት ምኞት፣ ኤለን ጂ ዋይት፣ ገጽ 396)።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. በዚህ ሳምንት ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን ሲመግብ፣ ከመወለዱ ጀምሮ ዕውር የሆነውን ሰው ሲፈውስና አልዓዛርን ከሞት ሲያስነሳ አይተናል። በእያንዳንዱ ሁኔታ፣ ኢየሱስ ስለ መለኮታዊነቱ ጠንካራ ማስረጃዎችን ሰጥቷል። ሆኖም እነዚህ አስደናቂ ተአምራት፣ መለያየትን ፈጠሩ። አንዳንዶቹ በእምነት፣ ሌሎች ደግሞ በጥርጣሬ ምላሽ ሰጡ። ምንም እንኳን ኃይለኛ ማስረጃ ቢኖርም ሰዎች እግዚአብሔርን ላለመቀበል ሊወስኑ እንደሚችሉ ይህ ምን ያስተምረናል?

2. እነዚህ ታሪኮች ሁሉ ወደ ክርስቶስ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ልጅ መሆን ያመለክታሉ። በኢየሱስ አዳኝነት ለማመን የእርሱ መለኮታዊነት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው?

3. እንደገና 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡26-29 ተመልከቱ። በ 21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ይህ ተመሳሳይ መርሕ በምን ዓይነት መንገዶች ሲተገበር እንመለከታለን? “በሥጋ ጥበበኞች” የሆኑት የሚያፌዙባቸውና የሚቃወሟቸው ነገር ግን ክርስቲያኖች የሚያምኑባቸው አንዳንድ “ሞኝ ነገሮች” የትኞቹ ናቸው? “ብርቱ የሆነውን” የሚያሳፍረው ምንድን ነው ብለን እናምናለን?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL