የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ
ይህ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ የሚዘጋጀው
በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ዋና መስሪያ ቤት በሆነው በጀነራል
ኮንፍረንስ ውስጥ ሆኖ፤ የጎልማሶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያን በሚያዘጋጀው
ቢሮ ነው። መምሪያዎቹ የሚዘጋጁት የጀነራል ኮንፈረንስ አስተዳደር ኮሚቴ ንዑስ ኮሚቴ
በሆነውና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያዎችን በሚያሳትመው የሰንበት ትምህርት
ሕትመት ቦርድ ነው። የታተመው መምሪያ በውስጡ ዓለም አቀፋዊ የሆነ የምዘና
ኮሚቴ ሀሳቦችንና የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድን ማረጋገጫ ስለሚያንጸባርቅ
የአዘጋጁን (የአዘጋጆችን) ሀሳብ ብቻ የሚወክል አይደለም። በተለየ ካልተጠቀሰ
በቀር በዚህ ሰንበት ትምህርት ጥቅም ላይ የዋሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በሙሉ
የተወሰዱት ከአዲሱ መደበኛ ትርጉም ነው።
1ኛ ሩብ ዓመት
ከታህሳስ 20 - መጋቢት 20 2016 ዓ.ም.
በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ማተሚያ ቤት ታተመ
መግቢያ፡ መጽሐፈ መዝሙረ ዳዊት
መዝሙረ ዳዊት፡- ሰውና እግዚአብሔር ልብ ለልብ
የሚገናኙበት ቦታ
በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ ያሉ መዝሙሮች ተወዳዳሪ የሌላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ
ጸሎቶችና መንፈሳዊ መዝሙሮች ናቸው። በውዳሴ፤ በደስታ፤ በሀዘን እና በተስፋ መቁረጥ
ውስጥ የተነገሩ፤ በተራ ሰዎች፤ በነገስታት እና በካህናት በግልና በህብረት የተነገሩ ወይም
የተዘመሩ፤ መዝሙሮቹ ከጻድቃንና ከተናዛዥ ኃጢአተኞች በመምጣት እንደ የጸሎት
መጽሐፍ እንዲሁም እንደ መዝሙር ደብተር አማኞችን ለዘመናት ሲያገለግሉ የኖሩ ናቸው።
አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለእኛ የሚናገረን ሲሆን በመዝሙረ ዳዊት
ውስጥ ያሉ መዝሙሮች ደግሞ ለእኛ እና ከእኛ ጋር መናገራቸው ልዩ ሚና እንዲኖራቸው
አድርጓቸዋል። መዝሙረ ዳዊት የበረከት፤ የተስፋ እና የመነቃቃት ምንጭ ነው፤
እንዲሁም ስለ ራሳችን ባህሪይ በጥንቃቄ ወደማሰብ እና በእግዚአብሔር ታላቅነት፣፣ አንድ
ግለሰብ በጥልቅ ሆኖ ሲጮህ ነጻ በማውጣቱና ግለሰቡ ራሱን እንደገና ለእግዚአብሔር
እንዲሰጥ በማድረጉ ላይ በጥልቀት ወደማሰብ የሚመራ ነው። ስለዚህ ብዙ ሰዎች የዳዊት
መዝሙሮች በስሜቶቻቸውና በልምምዶቻቸው ውስጥ ሲያስተጋቡ ማግኘታቸውና እንደ
ራሳቸው ጸሎቶች አድርገው መውሰዳቸው የሚያስገርም አይደለም። ሉተር በአሳዛኝ
ሁኔታ ስለ መዝሙረ ዳዊት እንዲህ ይላል፡- “አንድ ሰው ደስታውን ለመግለጽ የሚረዱ
የከበሩ ቃላትን በመዝሙረ ዳዊት ውዳሴ ወይም ምስጋና ውስጥ ካልሆነ በቀር የት
ማግኘት ይችላል? በእነሱ ውስጥ አስደሳች የሆነ የአትክልት ስፍራን እንደምትመለከት
ወይም ሰማይን ትኩር ብለህ እንደምትመለከት የሁሉንም ቅዱሳን ልብ ትመለከታለህ።
ወይም አንድ ሰው ሀዘኑን ለመግለጽ እጅግ ሥር ነቀል የሆኑ የኑዛዜና የሀዘን ቃላትን
በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ ባሉ የለቅሶ ዝማሬዎች ውስጥ ካልሆነ በቀር የት ማግኘት ይችላል?
በእነዚህ ዝማሬዎች ሞትን ወይም ገሃነምን እንደምትመለከት የቅዱሳንን ሁሉ ልብ ብትመለከት
በሚለዋወጡ የእግዚአብሔር ቁጣ ጥላዎች የሚቀርበው ትዕይንት እጅግ ጨለማና ለመረዳት
እጅግ የሚከብድ ይሆናል። ስለዚህ የመዝሙራት መጽሐፍ የሁሉም ቅዱሳን ተመራጭ
መጽሐፍ ሆኖ ማግኘት ቀላል ነው። እያንዳንዱ ሰው በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ለፍላጎቱ
የሚስማማ፤ ለራሱ ተብሎ የተጻፈ በሚመስል ሁኔታ ገጣሚ የሆነ መዝሙር ያገኛል። አንድ
ግለሰብ በሌሎች መጻሕፍት ውስጥ ከእነዚህ ቃላት ጋር የሚስተካከሉ ወይም የተሻሉ ቃላትን
ማግኘት አይችልም።“ Martin Luther, Martin Luther: Selections From His Writings,
ed. John Dillenberger (New York: Anchor Books, 1962), pp. 39, 40.
የመዝሙራትን ሕይወት ለዋጭ ኃይል ለመለማመድ ውዳሴዎቻቸውን፣
ልመናዎቻቸውን፣ ኑዛዜዎቻቸውን፣ ለቅሶዎቻቸውንና ምሥጋናዎቻቸውን ሉአላዊ
በሆነው የጸጋና የፍትህ አምላክ ፊት ለማፍሰስ እነዚህን ዝማሬዎች እንደተጠቀሙ
የአማኞች ትውልዶች እኛም እንድንዘምራቸውና እንድንጸልይ ተጠርተናል።
ታዲያ የዳዊትን መዝሙራት መማር አለብን? እንደ ሌሎቹ ቅዱሳት መጻህፍት
ሁሉ የዳዊት መዝሙሮችም ልዩ በሆኑ ታሪካዊ፤ ስነ-መለኮታዊና ስነ-ጽሑፋዊ አውዶች
ተጽፈዋል። የመዝሙር መጽሐፍን የማጥናት ዓላማ የመዝሙራትን ዓለም ወደ ዘመናዊው
አንባቢ/አድማጭ ማቅረብ ነው። መዝሙረ ዳዊት የእግዚአብሔር ሕዝቦች ጸሎቶች እና
ኢየሱስ ሥጋ የለበሰው መለኮታዊ አምላክ ሆኖ የጸለየው ፀሎት ሆኖ ሳለ ስለ ኢየሱስ
የተጸለዩ ጸሎቶችም ናቸው። መዝሙራት ለሰብአዊ ፍጡራን የመለኮት መገለጥ ናቸው።
መዝሙራትን የማጥናት ሌላኛው ዓለማ እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ውስጥ እና
በእርሱ አማካይነት ለዓለም ያደረገውን ፤ እያደረገ ያለውንና ወደ ፊት ሊያደርግ ያለውን
ሁሉ ለማወቅ ነው።
መዝሙረ ዳዊት የ150 ግጥሞች ስብስብ ቢሆንም ስብስቡ አሁን እንደሚታየው
በዘፈቀደ የተደረገ ላይሆን ይችላል። መዝሙረ ዳዊት ለብዙ የእግዚአብሔር ሕዝቦች
የተለመደውን የመንፈሳዊ ጉዞ ምስክርነትን ያዘለ ነው። ጉዞው መልካም የሆኑ
በሚሸለሙበትና ክፉ የሆኑ በሚቀጡበት በእግዚአብሔር ሉአላዊ ሕግ ላይ በጽኑ
በተመሰረተና በተደላደለ እምነት ይጀምራል። ጥናታችንን ስንቀጥል በሥርዓት ይመራ
የነበረው የእምነት ዓለም ተግዳሮት ሲገጥመውና ክፉ ሲያስፈራራው ምን እንደሚሆን
እንመለከታለን። እግዚአብሔር አሁንም በዙፋኑ ላይ አለ? የእግዚአብሔር ሕዝቦች በባእድ
ምድር እንዴት የእግዚአብሔርን መዝሙር መዘመር ይችላሉ?
ምኞታችንና ጸሎታችን እነዚህ መዝሙራት በህይወት ጉዞአችን እንዲያበረቱንና
አንድ ቀን ኢየሱስ ክርስቶስን ፊት ለፊት እስከምንገናኝ ድረስ በእነርሱ አማካይነት በየእለቱ
ከእግዚአብሔር ጋር ልብ ለልብ እንድንገናኝ ነው።
ድራጎስላቫ ሳንትራክ በብሉይ ኪዳን PhD ያላቸው ሲሆኑ በጀነራል ኮንፍራንስ
ዋና መስሪያ ቤት የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ኢንሳይክሎፒዲያ ዋና አርታኢ በመሆን
ያገለግላሉ። በመዝሙር 76-150 ላይ ለሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ
ቅዱስ ሀተታዊ የጥናት መመሪያ አንድ ቅጽ ጽፈዋል።