የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት:የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት
መምሪያ
መደበኛ እትም
ጌታ እስኪመጣ ድረስ
የእርሱን ንብረት ማስተዳደር
በጂ ኤድዋርድ ሬይድ
ትርጉም፡ ታምሬ ሻዕማሎ
ይህ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ
የሚዘጋጀው በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ዋና መስሪያ ቤት
በሆነው በጀነራል ኮንፍረንስ ውስጥ ሆኖ፤ የጎልማሶች የመጽሐፍ ቅዱስ
ጥናት መምሪያን በሚያዘጋጀው ቢሮ ነው። መምሪያዎቹ የሚዘጋጁት
የጀነራል ኮንፈረንስ አስተዳደር ኮሚቴ ንዑስ ኮሚቴ በሆነውና የመጽሐፍ
ቅዱስ ጥናት መምሪያዎችን በሚያሳትመው የሰንበት ትምህርት ሕትመት
ቦርድ ነው። የታተመው መምሪያ በውስጡ ዓለም አቀፋዊ የሆነ የምዘና
ኮሚቴ ሀሳቦችንና የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድን ማረጋገጫ
ስለሚያንጸባርቅ የአዘጋጁን (የአዘጋጆችን) ሀሳብ ብቻ የሚወክል አይደለም።
በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ማተሚያ ቤት ታተመ
1ኛ ሩብ ዓመት
ከጥር እስከ መጋቢት 2015 ዓ.ም.
ጌታ እስኪመጣ ድረስ የእርሱን ንብረት ማስተዳደር
(በአግባብ መያዝ)
የዩኒቨርስ ፈጣሪ የሆነው አምላካችን ሰብአዊ ፍጡራን ከሆንን ከእኛ ጋር
እንዲኖረው ስለሚፈልገው ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ማስተዋል ይከብደናል
(ሀሳቡ ራሱ አስገራሚ ነው!) ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ
እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ! ›› ወይም ኤለን ኋይት እንደጻፈቸው፣
‹‹ማንኛውም ሰብዓዊ ክብር ከዚህ ጋር ሊስተካከል ይችላልን? የዘላለማዊ
አምላክ ልጆች ተብለን ከመጠራት የበለጠ ምን ከፍ ያለ ቦታ ልንይዝ
እንችላለን?...ማንኛውም ዓለማዊ ክብር ከዚህ ጋር ሊስተካከል ይችላልን?”—
ኤለን ጂ ኋይት፣ የእግዚአብሔር አስደናቂ ጸጋ፣ ገጽ 341። በኢየሱስ የተሰጠንን
ማዕረግ ሙሉ በሙሉ እንዳናደንቅ የሚያደርገን የዚህ ኃጢአት የተጫነው
ዓለም ጨለማ ብቻ ነው።
ስለዚህ ካልተጠነቀቅን የዓለም ማታለያና በዓለም ውስጥ ያሉ ነገሮች
ከክርስቶስ ይነጥሉናል (ያርቁናል)። ስለ ሰይጣን ፈተናዎችና ማታለያዎች
የእግዚአብሔር ቃል መረጃ ይሰጠናል። “ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ
በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ
ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ
ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ
ራሳቸውን ወጉ” (1 ጢሞ. 6:9፣ 10)።
ነገር ግን ጳውሎስ እንዳስጠነቀቀን ገንዘብ ‹‹ወደ ጥፋትና መፍረስ››
እንዲመራን ሳንፈቅድ ገንዘብን እንዴት ማግኘትና በጥበብ መጠቀም እንዳለብን
እግዚአብሔር መመሪያ ሰጥቶናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ገንዘብ፣ ስለ
ንብረት እና ስለ እነዚህ ነገሮች እኛ ስላለን አመለካከት በሚናገሩ ከ2000 በላይ
ጥቅሶች ውስጥ እንዴት ከሕይወት ጭንቀት በላይ መኖር እንደምንችልና
የተሰጠንን ነገር እንዴት በታማኝነት መያዝ እንዳለብን እግዚአብሔር ተግባራዊ
መመሪያ ሰጥቶናል።
በዚህ ሩብ ዓመት ትምህርት ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖረን
ግንኙነት እርሱ ምን እንድንሆንለት እንደሚጠብቅብን እንማራለን፤ መግዛትና
መሸጥ በማንችልበት ጊዜ እንኳን ለእርሱ ታማኝ ሆነን መቆየት የምንችልበትን
መታመን እንዴት ማሳደግ እንደምንችል በግልጽ እናያለን (ራዕይ 13፡
17ን ይመልከቱ) ። ነገር ግን የዚህ ዓይነት እምነት በአንድ ሌሊት ሊመጣ
አይችልም፤ እግዚአብሔር የሰጠንን ነገር በታማኝነት በመያዝ በመንገዳችን
ላይ ሊያጋጥመን ለሚችለው ለማንኛውም ነገር አሁኑኑ መዘጋጀት እንችላለን።
የሀብት ባለቤት እግዚአብሔር ስለሆነ ከእርሱ ጋር አብረን ስንሰራ
የእርሱን ንብረት በአግባቡ እንድንይዝለት ይፈቅዳል። የአዳኙ እቅድ ሰብአዊ
ፍጡራን ነጽተውና ተቀድሰው የእርሱ ረዳት እጆች እንዲሆኑ ነው። ለዚህ
ታላቅ እድል፣ “ከጨለማ ሥልጣን ላዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን
ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት ላፈለሰን” (ቆላ. 1:13፣ 14)
ለእርሱ ምሥጋና እንስጠው።
እግዚአብሔር በጠቢቡ ሰለሞን አማካይነት ልጆቹን እንዲህ በማለት
ይመክራል፡- “እግዚአብሔርን ከሀብትህ አክብር፥ ከፍሬህም ሁሉ በኵራት”
(ምሳሌ 3:9) ። ይህ ምክር ተገቢ የሆነው ምክሩን የሰጠው ሁሉን ነገር
ስለፈጠረ፣ በእርሱ ፈቃድ ስለተፈጠሩና ስለሚኖሩ፣ ክብር፣ ውዳሴና ኃይል
ሊቀበል የተገባው ስለሆነ ነው (ራዕይ 4፡11) ።
በዓለማዊ እይታ ስንመለከት የምንኖርባቸው ጊዜያቶች እጅግ
ግድድሮሽ የሞላባቸውና አስጨናቂ ናቸው። ነገር ግን የሰብአዊ ዘር ታሪክ ታላቁ
መደምደሚያ የሆነው የክርስቶስ ዳግም ምጻት እጅግ ቅርብና በደጅ መሆኑን
እንድናውቅ የሚያደርጉንን የጊዜውን ምልክቶች ስንመለከት ስለ ዓለም ያለን
የክርስትና አመለካከታችን መተማመንና ተስፋ ይሰጠናል። እነዚህ ተግባራዊ
ትምህርቶች በእግዚአብሔር ላይ ያላችሁን እምነት የጠለቀ እንዲያደርገውና
ለእርሱ ታማኝ አስተዳዳሪ እንድትሆኑ እንዲያደፋፍራችሁ እንጸልያለን።
ጂ ኤድዋርድ ሬይድ ከአንድሪውስ ዩኒቨርሲቲ በሥነመለኮት ትምህርት
የማስትሬት ድግሪ፣ ከሎማሊንዳ ዩኒቨርሲቲ በፐብሊክ ሄልዝ በማስተርስ
ድግሪ የተመረቁ ሲሆን የተቀቡ የወንጌል አገልጋይና ፈቃድ ያላቸው ጠበቃ
ሲሆኑ የሰሜን አሜሪካ ድቪዥን የመጋቢነት አገልግሎት ዳይሬክተር ሆነው
ለብዙ አመታት አገልግለዋል።