የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ዘፍጥረት


2ኛ ሩብ ዓመት 2022

ከመጋቢት 17 - ሰኔ 17 / 2014

መደበኛ እትም

Dec 25 - Mar 25




አዘጋጆች ዣክ ቢ. ዱካን

ዘላለም አስረስ እንደ ተረጎመው



ይህ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ የሚዘጋጀው በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ዋና መስሪያ ቤት በሆነው በጀነራል ኮንፍረንስ ውስጥ ሆኖ፤ የጎልማሶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያን በሚያዘጋጀው ቢሮ ነው። መምሪያዎቹ የሚዘጋጁት የጀነራል ኮንፈረንስ አስተዳደር ኮሚቴ ንዑስ ኮሚቴ በሆነውና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያዎችን በሚያሳትመው የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድ ነው። የታተመው መምሪያ በውስጡ ዓለም አቀፋዊ የሆነ የምዘና ኮሚቴ ሀሳቦችንና የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድን ማረጋገጫ ስለሚያንጸባርቅ የአዘጋጁን (የአዘጋጆችን) ሀሳብ ብቻ የሚወክል አይደለም። በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ማተሚያ ቤት ታተመ

የጅማሮው መጽሐፍ


የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ፡ ፈጣሪያችን ስለሆነው የሱስ፣ ደጋፊያችን ስለሆነው የሱስ፣ አዳኛችን ስለሆነው የሱስ ይናገራል። የዘፍጥረት መጽሐፍን ራሱ ሙሴ ከጻፈው በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ዮሐንስ፣ ከዚህ የኃይማኖት አባት የፍጥረት ዘገባ ተነስቶ የሱስን ይገልጸዋል፡ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። እርሱም በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ። ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሮአል፤ ከተፈጠረው ሁሉ ያለ እርሱ የተፈጠረ ምንም የለም። ሕይወት በእርሱ ነበረች፤ ይህች ሕይወት የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማውም አላሸነፈውም” (ዮሐ. 1፡1-4)።

ዮሐንስ እዚህ ላይ ምን ብሎ ነበር የጻፈው? “በመጀመሪያ” ሁሉም የተፈጠሩ ነገሮች እና በአንድ ወቅት ያልነበሩ ነገሮች ሁሉ ወደ መኖር መጡ፤ (በማን?)-በየሱስ! በግዙፉ ሕዋ ውስጥ ካሉ ጋላክሲዎች እና እንደ ርችት ከሚያበሩ አስገራሚ ተወርዋሪ ኮከቦች፣ ኢምንት እስከ ሆነው በታምራዊ ህዋስ የተሸመነ የዲ.ኤን.ኤ. ሞገድ--ሁሉም በየሱስ የተፈጠሩና በእርሱ የተደገፉ ናቸው። ኦሪት ዘፍጥረትም፣ የዚህ ፍጥረትም ሆነ የዚህ ፍጥረት መቤዠት--በቅዱሳን መጻሕፍት የመጀመሪያው ታሪክ ነው። በዚህ መጽሐፍ ስለ ጅማሮአችን የሚያወሳው ብቸኛ “ይፋዊ” ዘገባ ቀርቧል።

“በመጀመሪያ” የተሰኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ቀዳሚ ቃል የተወሰደው ከዕብራይስጡ ቤሬ’ሺት ነው። ዘፍጥረት ይህን መጽሐፍ ተከትለው የሚመጡ ሁሉም አምላካዊ መልእክቶች የሚያርፉበትን መሠረት ይሰጠናል። መጽሐፉ የመጀመሪያና በቀጣይ ለሚመጡ መሠረት እንደ መሆኑ፣ ከሌሎቹ ቅዱሳት መጻሕፍት ይልቅ በከፍተኛ ደረጃ በማመሳከሪያነት የሚጠቀስ ሳይሆን እንዳልቀረ ይታመናል።

የዘፍጥረት መጽሐፍ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ከየትኛውም ሥራ ይልቅ እንደ ሰው ማንነታችንን እንድናስተውል ይረዳናል። መጽሐፉ የያዘው እውነታ በተለይ ዛሬ እንደ ምናምንቴ ለተፈረጅንበት፣ በአጋጣሚና በዕድል ወደ መኖር መጣን ለሚለው ፍጹም የሆነ የዩኒቨርስ ቁሰ ሀሳባዊ እሳቤ በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ወይም አንድ የቁስ አካልና የኃይል ጥናት (ፊዚክስ) ባለሙያ እንዳሉት እኛ ሰዎች “የተደራጀ ጭቃ ነን” (ምንም እንኳ ለሰውየው፣ የተፈጥሮ ሕግጋት ብቻቸውን ያደራጁት ቢሆንም፣ ይህ በተወሰነ ደረጃ እውነትነት አለው)። ይሁን እንጂ የዘፍጥረት መጽሐፍ እኛ በዓላማና ፍጹም በሆነ አምላካዊ አምሳል፣ ፍጹም በሆነ ዓለም የተሠራን መሆናችንን በማውሳት እውነተኛ አመጣጣችንን ይገልጽልናል። በተጨማሪ ዘፍጥረት ስለ ሰው ውድቀት ይናገራል። ዓለማችን ፍጹም መሆኗ ያከተመውና የእኛ ሁኔታም ተመሳሳይ ችግር ውስጥ የወደቀው በዚሁ የተነሣ መሆኑን ያወሳናል። ይሁን እንጂ ዘፍጥረት፣ ውስጧም ሆነ ውጪዋ ከሞትና ሥቃይ ውጪ ምንም ልትሰጥ በማትችለው ዓለም፣ የአምላካዊውን የመዳን ተስፋ በመስጠት ያጽናናናል። በታምራዊ ታሪኮቹ (ፍጥረት፣ ውልደቶች፣ ቀስተ ደመና) እና ፍርዶቹ (የጥፋት ውሃ፣ ሰዶምና ጎሞራ) ቅዱስ ለሆነው አምላካዊ መገኘት ምስክርነቱን የሚሰጠው የዘፍጥረት መጽሐፍ በእጅጉ አስገራሚ ነው። ነገር ግን ዘፍጥረት ስለ ፍቅር (ያዕቆብ እና ራሔል)፣ ስለ ጥላቻ (ያዕቆብ እና ዔሳው)፣ ስለ ውልደት (ይስሐቅ፣ ያዕቆብ፣ የያዕቆብ ልጆች)፣ ስለ ሞት (ሣራ፣ ራሔል፣ ያዕቆብ፣ ዮሴፍ)፣ ስለ ግድያ (ቃየን፣ ስምዖን እና ሌዊ)፣ እንዲሁም ስለ ይቅርታ (ዔሳውና ያዕቆብ፣ ዮሴፍና ወንድሞቹ)--መሳጭ የሰው ልጅ ታሪኮች የቀረቡት መጽሐፍ ነው። በተጨማሪ መመሪያዎችን የያዘ ሲሆን--በሥነ ምግባር ትምህርት (ቃየን፣ ባቤል)፣ የእምነት ትምህርት (አብርሃም፣ ያዕቆብ) እንዲሁም ስለ ቤዛነት ተስፋ (የእባቡ መቀጥቀጥ፣ የተስፋይቱ ምድር) ተካተውበታል።

በዚህ ሩብ ዓመት፣ የዘፍጥረት መጽሐፍን ከማንበብና ከማጥናት ባለፈ-ውብ በሆኑ ታሪኮቹ ሐሴት እያደረግን የፍጥረት ጌታ ከሆነው የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ጋር በተሻለ ስለ መራመድ እንማራለን። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ከኤደን እስከ ባቤል፣ ከተስፋይቱ ምድር እስከ ግብፅ፣ ከግብፅ እስከ ተስፋይቱ ምድር የዘለቀው የመጽሐፉ መልክአ ምድራዊ ሽፋን-የዘላን ጉዞአችንን የሚያስታውሰን ከመሆኑም በላይ በእውነተኛዋ የተስፋይቱ ምድር--አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ያለን ተስፋ እንዲጠናከር ያደርጋል።

በመላው የዘፍጥረት ገጾች የቀረቡትን እነዚህን ገጸ ባሕርያት ስንከተል--ጊዜ፣ ቦታ፣ ባህል፣ እና ሁኔታዎች የቱንም ያህል ከለመድነው የተለዩ ቢሆኑም፣ ታሪኮቻቸው ግን በብዙ መንገዶች የእኛም እንደሆኑ እንገነዘባለን። ዣክ ቢ ዱካን (DHL, ThD.) በአንድሪውስ ዩኒቨርሲቲ፣ ነገረ መለኮት የትምህርት ክፍል የዕብራይስጥ እና ብሉይ ኪዳን የቀድሞ ፕሮፌሰር ናቸው።