የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ዘፍጥረት


የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2022

ከሰኔ 11 – 17

13ኛ ትምህርት

Jun 18 - Jun 24




እስራኤል በግብፅ ውስጥ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 4፣ ሮሜ 10:12-13፣ ዘፍ. 47፣ ዘፍ. 48፣ ዘፍ. 3:25-26 ዘፍ. 49፣ ፊልጵ. 2:10፣ ዘፍ. 49:29–50:21።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን በግብፅ አገር በጌሤም ይኖሩ ነበር፤ በዚያም ሀብት ንብረት አፈሩ፤ ቁጥራቸውም እጅግ እየበዛ ይሄድ ጀመር” (ዘፍ. 47፡27)።

የ ዘፍጥረት መጽሐፍ የያዕቆብና ዮሴፍን የመጨረሻ አብሮነት ዓመታት ይሸፍናል። ያዕቆብ (እስራኤል) ኑሮውን በግብፅ ለማድረግ ከነዓንን ትቶ (ዘፍ. 46) ወደዚያ እንደሚያመራና በግብፅ እንደሚሞት እንመለከታለን (ዘፍ. 49፡29-50፡21)። ምንም እንኳ ቤተሰቡ ኑሮውን በግብፅ ለማድረግ በአገሪቱ ምድር ቢሰፍርም፣ የተስፋይቱ ምድር ምናባዊ ሥዕል አሁንም በጉልህ ይታያል (ዘፍ. 50፡22-26)። የመጨረሻው ሀሳብ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የተቀዳጀው ድል ፋይዳ እንደገና በማረጋገጥ አማኞች በኢየሱስ ድል ውስጥ እንዲገቡ ይመራቸዋል። ጳውሎስ ከዳንኤል 7 ላይ ያለውን ምስል ለአንባቢያን በማስታወስ ኢየሱስ ከእግዚአብሔርን መንግስትና ፍርድን እንደተቀበለ ይነግረናል (ዳን. 7፡9-14)፤ ይህንን መንግስትም ከአማኞቹ “ከልዑሉ ቅዱሳን” ጋር ይጋራል (ዳን. 7፡18) ለዘላለምም ይኖሩበታል።

ያዕቆብ ፈርዖንን የባረከው ሲሆን (ዘፍ. 47፡7-10)፣ ይህም በምድር የሚኖሩ ሕዝቦች በአብርሃማዊው ኪዳን አማካይነት እንደሚባረኩ (በከፊል) የተገባው ቃል ፍጻሜ ነበር (ዘፍ. 12፡3)። ኋላ ላይ፣ ያዕቆብ ሊሞት አካባቢ የዮሴፍን ልጆች ባረካቸው (ዘፍ. 48)። ያዕቆብ የገዛ ልጆቹንም የባረካቸው ሲሆን (ዘፍ. 49፡1–28)፣ በወደፊቶቹ 12 የእስራኤል ነገዶች ዐውድ፣ ስለ እያንዳንዳቸው አስደናቂ ትንቢቶችን ተናግሯል (ዘፍ. 49፡1–27)።

እስራኤል በምድረ ግብፅ በመጻተኝነት “የመኖሩ” እውነታ የተስፋይቱን ምድር የተስፋ ቃል ከግምት ያስገባ ነበር። እንዲሁም ራሱ የዘፍጥረት መጽሐፍ የእስራኤል ልጆች በግብፅ እንዳሉ ቢያበቃም፣ ዮሴፍ የተናገራቸው የመጨረሻዎቹ ጥቂት ቃላት ሌላ ስፍራን ያመላከቱ ነበሩ፡ “እነሆ የመሞቻዬ ጊዜ ተቃርቦአል፤ እግዚአብሔርም በረድኤቱ ይጎበኛችሁና ከዚህ አገር ያወጣችኋል፤ ለአባቶቻችን ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ በመሐላ ተስፋ ወደ ሰጣቸው ምድር ያስገባችኋል’ ” (ዘፍ. 50፡24)።

ሰኔ 12
Jun 19

የያዕቆብ ወደ ዮሴፍ መሄድ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 46። ያዕቆብ ከነዓንን ለቅቆ የመሄዱ አንደምታ ምንድን ነው?



ያዕቆብ መኖሪያውን ከነዓን ለቅቆ በሄደበት ወቅት በተስፋ ተሞልቶ ነበር። ከዚህ በኋላ እንደማይራብ ያገኘው ማረጋገጫና የዮሴፍ በሕይወት መኖር የምሥራች፣ የተስፋይቱን ምድር ለቅቆ እንዲወጣ ጉልበት ሳይሆነው እንዳልቀረ ይታመናል።

የያዕቆብ ከነዓንን ለቅቆ መውጣት የአብርሃምን ተሞክሮ ያስተጋባል (ምንም እንኳ አብርሃም ወደ ተስፋይቱ ምድር እያመራ የነበረ ቢሆንም)። ያዕቆብ “ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ” (ያስተያዩ፡ ዘፍ. 46፡3 እና ዘፍ. 12፡2) የሚለውን አብርሃም ከእግዚአብሔር የሰማውን የተስፋ ቃል በተመሳሳይ ሰምቷል። ይህ አምላካዊ ጥሪ እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ይጠቁማል። በሁለቱም አጋጣሚዎች እግዚአብሔር “ ‘አትፍራ’ ” (ያስተያዩ፡ ዘፍ. 46፡3 እና ዘፍ. 15፡1) የሚለውን ተመሳሳይ የማጽናኛ ቃል የሚናገር ሲሆን፣ ይህ ደግሞ አስደሳች የሆነውን የወደፊት ተስፋ ይዟል።

ሴቶች ልጆችን ጨምሮ ወደ ግብፅ የወረዱት የእስራኤል ልጆች ስም በስፋት መዘርዘሩ (ዘፍ. 46፡7)፣ አብርሃም ገና ልጅ ሳይኖረው ዘሩ እንደሚበዛ እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃል ያስታውሳል። “ሰባ” የሚለው ቁጥር (ያዕቆብ፣ ዮሴፍና ሁለቱን ልጆቹን ጨምሮ) አጠቃላዩን ጽንሰ ሀሳብ ሃሳብ ይገልጻል። ወደ ግብፅ የወረደው “እስራኤል ሁሉ” ነው። በተጨማሪም 70 ቁጥር ከትውልዱ (ዘፍ. 10) አኻዝ ጋር ተያያዥነት እንዳለው መገንዘብ አስፈላጊ ሲሆን፣ በያዕቆብ ጉዞ የመላው ሕዝብ ዕጣ ፈንታ አደጋ ላይ እንደነበርም ይጠቁማል።

ይህ እውነት በይበልጥ ግልጽ የሚሆነው መስቀሉና የመዳን እቅድ ሙሉ በሙሉ ከተገለጠ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ሲሆን፣ ይህ በእርግጥ ለአብርሃም ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለመላው ሰብዓዊ ዘር ጭምር ነበር። በሌላ አነጋገር ስለ አብርሃም ዘር ብሎም ከዚያ ስለምናገኛቸው ማናቸውም ዓይነት መንፈሳዊ አስተምህሮዎች ቤተሰቡን አስመልክቶ የቀረቡ ታሪኮች የቱንም ያህል መሳጭ ቢሆኑም--እነዚህ ዘገባዎች የመዳን ታሪክ ክፍል ስለሆኑ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ይገኛሉ። በዚህች በወደቀች ምድር በተቻለ መጠን ለብዙዎች መቤዠት ማስገኘት የሚችሉ የአምላካዊው እቅድ አካል ናቸው። “በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ልዩነት የለም፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፤ የሚለምኑትንም አብዝቶ ይባርካል፤ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” (ሮሜ 10፡12-13)። ጳውሎስ የወንጌልን ዩኒቨርስ አቀፍ ባህሪ በሚያሳየው በዚህ መልእክቱ ምን አለ? ከሁሉም በላይ፣ እኛ እንደ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ለማስፋፋት ምን ማድረግ እንዳለብን አስመልክቶ እነዚህ ቃላት ምን ይነግሩናል?





ሰኔ 13
Jun 20

ያዕቆብ በግብፅ መኖር ጀመረ


ዮሴፍ በግብፅ በሕይወት እንዳለ ለያዕቆብ ቢነገረውም ነገር ግን ጌታ “ሌሊት በራእይ” (ዘፍ. 46፡2) ተገልጦ እንዴት እንዲሄድ እዳዘዘው መመልከት የሚገርም ነው። ያዕቆብ የተስፋይቱን ምድር ለቅቆ ወደ ግብፅ ያመራ ሲሆን-ኋላ ላይ የእግዚአብሔር ሕዝቦች እንዲሄዱ ከማይፈለጉባቸው ስፍራዎች መካከል፣ ግብፅ አንዷ ሆና ቀርባለች (ዘዳ. 17፡16)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. ምዕ. 47። በእነዚህ ዘገባዎቸ ውስጥ ምን ዓይነት መንፈሳዊ እውነቶችና መርኅዎች እናገኛለን እናገኛለን?



“ዮሴፍ አምስት ወንድሞቹን ፈርዖን ዘንድ አቀረባቸው። ፈርዖንም ቤት የሚሠሩበት ቦታ ሰጣቸው። ፈርዖን ለዮሴፍ ያለውን ምስጋና ለመግለጽ እነርሱን በሹመት ላይ ሊያስቀምጣቸው ይችል ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔርን ለማምለክ ታማኝ የሆነው ዮሴፍ ወንድሞቹ እግዚአብሔርን በማያምን ምድር ላይ ከሚፈጠርባቸው ፈተና እንዲጠበቁ ስለፈለገ ንጉሡ ሲጠይቃቸው ሥራቸውን በግልጽ እንዲናገሩ ለወንድሞቹ አሳሰበ። የያዕቆብ ልጆችም የእርሱን ምክር በመስማት በምድሪቱ ለመኖር እንደመጡ በመግለጽ ጭምር ቋሚ ነዋሪዎች እንደማይሆኑ አስረድተው ከአገሪቱ ለመውጣት ቢፈልጉ የመመለስ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ጠየቁ። ንጉሡም ምርጥ በሆነው ምድር ላይ በጌሤም ይኑሩ ሲል ፈቀደላቸው።”--ኤለን ጂ. ኋይት፡ የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ገጽ፡ 260።

ብልህ አስተሳሰብ የተንጸባረቀበት ፈርዖን እነዚህ የምድሪቱ እንግዶች የተመጽዋች ስሜት እንዲኖራቸው አላበረታታም። ይልቁንም ራሳቸውን ከአዲሱ መኖሪያ አካባቢያቸው ጋር በተሻለ ማስተካከል እንዲችሉ በማሰብ “ሥራችሁ ምንድን ነው?” (ዘፍ. 47፡3) ብሎ ይጠይቃቸዋል። ፈርዖን ዕውቀታቸውን ለመጠቀም ጉጉት ስለነበረው “የከብቶቹ ኃላፊዎች” (ዘፍ. 47፡ 6) ሆነው እንዲያገለግሉት ሐሳብ ያቀርባል።

ከዚያም፣ ምንም እንኳ ያዕቆብ ለአገሪቱ እንግዳና እጅግ ዝቅ ባለ ደረጃ የሚገኝ ቢሆንም፣ በቤተ መንግሥት የምድሪቱ ንጉሥ ፊት ለፊት ቆመ። ጥቅሱ እንደሚናገረው “ያዕቆብ ፈርዖንን መረቀው” (ዘፍ. 47፡7)። ለመሆኑ የኃያሏን ግብፅ ንጉሥ ፈርዖን የሚባርክ ይህ ምስኪን መጻተኛ ማን ነው? ይህ ስለምን ሆነ?

በፈርዖን “ፊት አቀረበው” (ዘፍ. 47፡7) የሚለው ግስ በመደበኛ ጥቅም ላይ የዋለው በክህነት ዐውድ ነው (ዘሌዋ. 14፡11)። በጥንቷ ግብፅ ፈርዖን የሊቀ ካህንነት ማዕረግ እንደነበረው አድርገን ስናስብ፣ ይህ ማለት ያዕቆብ ከግብፅ ሊቀ ካህን ብሎም ከራሱ ከፈርዖን ሳይቀር በላይ ነበር ማለት ነው። በሕይወታችን ውስጥ ያለን ቦታ ምንም ይሁን ምን ከሌሎች ጋር ባለን መስተጋብር እኛ “የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ለራሱ” የለየን ሕዝብ መሆናችን ለእኛ ምን ትርጉም ሊኖረው ይገባል (1ጴጥ. 2፡9)? እምነታችን ምን ዓይነት ግዴታዎች ይጥልብናል?





፡ ሰኔ 14
Jun 21

ያዕቆብ የዮሴፍን ልጆች ባረከ


ያዕቆብ የመሞቻው ጊዜ ሲቃረብ፣ ወደ ቤተል የተመለሰበትን ቀደም ያለ ጊዜ ማለትም (ዘፍ. 35፡1-5) ለአብርሃም ተሰጥቶት የነበረውን (ዘፍ. 17፡8) የታደሰ “የዘላለም ርስት” (ዘፍ. 48፡4) ከእግዚአብሔር ሲቀበል የነበረውን ሁናቴ አስታወሰ። ስለዚህ እንደሚሞት ቢሰማውም፣ ስለ ተስፋይቱ ምድር የተሰጠው የተስፋ ቃል ተስፋውን የሚያለመልምና አጽናኝ ሆነለት። ከዚያም ያዕቆብ በግብፅ ወደ ተወለዱት የዮሴፍ ሁለት ልጆች ዘወር ብሎ የመረቃቸው ሲሆን፣ ነገር ግን ይህን ያደረገው በገዛ ዘሩ ላይ በሚሆነው የወደፊት ተስፋ ዐውድ ነው።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. ምዕ. 48። እዚህ ላይ ያዕቆብ ሌሎቹን የልጅ ልጆቹን ሳይጨምር የዮሴፍን ሁለቱን ልጆች ብቻ የመረቀው ለምንድነው?





ያዕቆብ የመረቃቸው ሁለቱ የዮሴፍ ልጆች ምናሴ እና ኤፍሬም፣ በብቸኝነት የባረካቸው የልጅ ልጆቹ ናቸው። ስለዚህ ከነበራቸው የልጅ ልጅነት ደረጃ ወደ ልጅነት ማዕረግ ከፍ አሉ (ዘፍ. 48፡5)። ምንም እንኳ የያዕቆብ ምርቃት ታናሹን (ኤፍሬም) ከታላቁ (ምናሴ) ያስበለጠ ቢሆንም፣ ነገር ግን የያዕቆብ መባረክ በዋነኝነት ዮሴፍን ይመለከታል (ዘፍ. 18፡15)።

እዚህ ላይ የምንመለከተው እግዚአብሔር ባለፉት ጊዜያቶች ለእነርሱ ያሳየውን ታማኝነት እና ለወደፊት የተሰጣቸውን ተስፋ የሚያመለክት የግል ምስክርነት ነው። ያዕቆብ ምግብ የሰጣቸውንና ከለላ የሆናቸውን የአብርሃም እና የይስሐቅ አምላክ በመጥቀስ (ዘፍ. 48፡15) “ከጉዳት ሁሉ የታደገኝ” (ዘፍ. 48፡16) ነው ይላል። በተጨማሪ ያዕቆብ ከእርሱ ጋር ትግል የገጠመውን (ዘፍ. 32፡29) እና ስሙን ከያዕቆብ ወደ “እስራኤል” (ዘፍ. 31፡13) የለወጠውን “የቤቴል አምላክ” (ዘፍ. 31፡13) በአእምሮው ይዞ ነበር።

እግዚአብሔር ክፉውን ወደ መልካም የቀየረባቸውን እነዚህን ሁሉ ክስተቶች በመጥቀስ፣ ለእርሱና ለዮሴፍ እንዳደረገው ሁሉ፣ የልጅ ልጆቹን ሕይወት መንከባከብ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ዘሮቹ ወደ ከነዓን ስለሚመለሱባቸው የወደፊት ጊዜያቶች እንደሚያስብም ያዕቆብ ተስፋውን ገልጿል። ይህ ተስፋ ስለ ሴኬም (ዘፍ. 48፡22) ባቀረበው ማጣቀሻ በግልጽ ተወስቷል። ይኸውም መሬቱ በግዢ የራሱ ያደረገው ብቻ ሳይሆን (ዘፍ. 33፡19) ነገር ግን የዮሴፍ ዐጥንቶችም የሚቀበሩበትና (ዘፍ. 24፡32) ለእስራኤል ነገድ በእኩል የሚከፋፈል ርስት ይሆናል (ዘፍ. 24፡1)። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ቢከሰቱም፣ “ ‘በምድር የሚኖሩ ሕዝቦች በአንተ አማካይነት ይባረካሉ’ ” (ዘፍ. 12፡3) ሲል እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ በአእምሮው ይዞ ነበር። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐዋ. 3፡25-26። ጴጥሮስ እንደ ተናገረው እግዚአብሔር በዘፍ. 12፡3 የሰጠው የተስፋ ቃል ፍጻሜ ያገኘው እንዴት ነበር? እኛ ራሳችን ይህን በረከት የተቀበልነው እንዴት ነው?





ሰኔ 15
Jun 22

ያዕቆብ ወንዶች ልጆቹን ባረከ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 49፡1-28። ያዕቆብ ልጆቹን የባረከበት መንፈሳዊ ትርጉሙ ምንድን ነው?



ያዕቆብ ብዙም ሳይቆይ ዕውን ስለሚሆነው የእስራኤል ነገዶች ታሪክ ከተናገረው ትንቢት ባሻገር፣ መሲሑንና የመጨረሻውን የመዳን ተስፋ ተመልክቷል። ይህ ተስፋ “በኋለኛው ዘመን” (ዘፍ. 49፡1) በሚሉ ቃላት በያዕቆብ ንግግር መግቢያ ላይ የተመለከተ ሲሆን፣ ወደፊት የሚመጣውን መሲሕ ንጉሥ (ኢሳ. 2፡2፣ ዳን. 10፡14) በተጨባጭ የሚያመለክት አነጋገር ነው።

ከዚያም ጥቅሱ በእያንዳንዱ ልጅ የወደፊት ህይወት መስመር ላይ ዳሰሳ ያደርጋል። እነዚህ በእያንዳንዱ ልጅ እንዲደርሱ በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተወሰኑ ዕጣ ፈንታዎች አልነበሩም። ይልቁንም የእነርሱና የልጆቻቸው ባህሪ የሚያስከትለውን ውጤት የሚገልጹ ናቸው። ለምሳሌ አንድ ሰው ንጹህ የሆነውን ግለሰብ እንደሚገድል እግዚአብሔር ማወቁ፣ ገዳይ ግድያውን እንዲፈጽም ከመፍቀዱ ጋር ፈጽሞ ሊገናኝ አይችልም። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 49፡8-12። እዚህ ላይ የተሰጠው ትንቢት ምንድን ነው? ለምን አስፈላጊ ሆነ?



ከሰብዓዊው ፍጡር የመምረጥ ነጻነት በላይና ከዚያ በላቀ እግዚአብሔር የወደፊቱን የሚያውቅ አምላክ እንደመሆኑ፣ መሲሕ በይሁዳ በኩል የሚመጣበትን መስመር አዘጋጀ። ይሁዳ (ዘፍ. 49፡8-12) በአንበሳ የተመሰለ ሲሆን (ዘፍ. 49፡8-12) ንግሥና እና ምስጋና የእርሱ ናቸው። ከይሁዳ ዘር የሚወጣው ንጉሥ ዳዊት ብቻ ሳይሆን፣ ሻሎም “ሰላም” (ኢሳ. 9፡6-7) የሚያመጣውና “ሕዝቦች ሁሉ ይታዘዙታል” (ዘፍ. 49፡10) የተባለው እርሱ-ሴሎ ነው። አይሁዳውያን ይህን ጥቅስ ወደፊት የሚመጣውን መሲሕ እንደሚያመላክት ትንቢት አድርገው ከረጅም ጊዜ አንስቶ ሲመለከቱት ኖረዋል። በተመሳሳይ ክርስቲያኖችም ይህን ጥቅስ የሱስን እንደሚያመላክት አድርገው ወስደውታል። “ሕዝቦች ሁሉ ይታዘዙታል” (ዘፍ. 49፡10) የሚለው ሃረግ ምናልባት ለአዲስ ኪዳኑ “ጉልበት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ” (ፊልጵ. 2፡10)--ፈር ቀዳጅ ሊሆን ይችላል።

“የዱር አራዊት ንጉሥ የሆነው አንበሳ ለዚህ ነገድ የሚስማማ ምልክት ነው። ዳዊት እና የዳዊት ልጅ የሆነው እውነተኛ ‘የይሁዳ ነገድ አንበሳ’ ከዚህ ነገድ የመጣ ሲሆን፤ ሁሉም ሥልጣን ለእርሱ የሚገባ፣ መንግሥታትም ለእርሱ የሚሠግዱ ናቸው”--ኤለን ጂ. ኋይት፡ የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፤ ገጽ፡ 236።

ሕዝቦች ሁሉ ይህን ከማድረጋቸው በፊት፣ እኛ አሁን ለየሱስ ክብር መስጠት ያለብን ለምንድን ነው?





ሰኔ 16
Jun 23

የተስፋይቱ ምድር የተስፋ ቃል


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 49፡29-50፡21። በዘፍጥረት መጽሐፍ መደምደሚያ ላይ ምን ዓይነት ታላላቅ የተስፋ ጭብጦች ይገኛሉ?



የዘፍጥረት መጽሐፍ መደምደሚያ ሦስት በተስፋ የተሞሉ ክስተቶችን ይዞአል፡ የመጀመሪያው፡ እስራኤል ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደምትመለስ የተሰጠው ተስፋ ነው። የዘፍጥረት መጽሐፍ ጸሐፊ የሆነው ሙሴ፣ የያዕቆብና የዮሴፍ ሞት እና የቀብር ሥነ ሥርዓት የተስፋይቱን ምድር የሚያመላክቱ ድርጊቶች መሆናቸውን ገልጾአል። ያዕቆብ ስለ “ዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች” (ዘፍ. 49፡28) ትንቢት ተናግሮ እንዳበቃ ከባረካቸው በኋላ፣ ስለ ሞቱ በማሰብ ልጆቹ በከነዓን ሣራ በተቀበረችበት ማክፌላ ዋሻ እንዲቀብሩት አዘዛቸው (ዘፍ. 49፡29-31)። በከነዓን የተደረገውን የቀብር ሥነ ሥርዓት የሚገልጸው ትረካ፣ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ከግብፅ ለመውጣታቸው መነሻ ሆኗል። ሁለተኛው፡ እግዚአብሔር ክፉውን ወደ በጎ የሚለውጥበት ተስፋ ነው። ያዕቆብ ከሞተና ከተቀበረ በኋላ የዮሴፍ ወንድሞች ስለ ወደፊት ሕይወታቸው ተጨንቀው ነበር። ዮሴፍ አሁን የበቀል እርምጃ ሊወስድብን ይችላል ብለው ፈርተዋል። ስለዚህ የዮሴፍን ትንቢታዊ ሕልሞች በሚያስታውስ መልኩ በዮሴፍ ፊት ተደፍተው ባሮቹ መሆናቸውን ገለጹለት (ዘፍ. 50፡18)። ዮሴፍ ግን “አትፍሩ” (ዘፍ. 50፡19) ሲል የሰጠው የማረጋረጫ ቃል የወደፊቱን የሚያመላክት ነበር (ዘፍ. 15፡1)። እርሱን “ለመጉዳት” አድርገውት የነበረውን ነገር እግዚአብሔር ግን “ለበጎ” (ዘፍ. 50፡20) በማዋል ሕይወት ታደገበት (ያስተያዩ፡ ዘፍ. 50፡19-20 እና ዘፍ. 45፡5፣ 7-9)። ይህ ማለት አያሌ ሰብዓዊ ውድቀቶች ቢኖሩም እንኳ፣ አምላካዊው መግቦት ያን ሽሮ ወደ መልካም በመቀየር ይሠራል።

ሦስተኛው፡ እግዚአብሔር የወደቀውን ሰብዓዊ ዘር የማዳኑ ተስፋ ነው። በዚህ የዘፍጥረት መጽሐፍ መጨረሻ ቁጥር ላይ ስለ ዮሴፍ ሞት የሚናገረው ታሪክ ከዮሴፍ ሞትም የገዘፈ ነው። የሚገርመው ዮሴፍ ዐጥንቶቹ እንዲቀበሩ ትእዛዝ አይሰጥም። ይልቁንም “እግዚአብሔር በረድኤቱ ያስባችኋል፤ በዚያን ጊዜ ዐፅሜን ከዚህ አገር ይዛችሁ እንድትወጡ” (ዘፍ. 50፡25) በማለት የተናገረውን የኑዛዜ ቃል ከብዙ ዓመታት በኋላ በመታዘዝ ፈጽመውታል (ዘፀ. 13፡19)። የተስፋይቱ ምድር የተስፋ ቃል የሆነችው ከነዓን፣ የሁላችንም መዳን የመጨረሻ ተስፋ የሆነችውና በእርሱ--ሴሎ ሞት የተረጋገጠችው የአዲሲቱ የሩሳሌም ምሳሌት ናት።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 21፡1-4። ጥቅሶቹ የተሰጠንን ከሁሉ የላቀ ተስፋ እንዴት ይወክላሉ? ይህ ተስፋ ባይኖር ኖሮ የችግሮቻችን ሁሉ ፍጻሜ ከሞት በቀር ሌላ ምን ሊሆን ይችል ነበር?

ሰኔ 17
Jun 24


ተጨማሪ ሀሳብ


ኤለን ጂ. ኋይት፡ “ዮሴፍና ወንድሞቹ”፡ የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፤ ገጽ፡ 248-270። “የዮሴፍ ሕይወት የክርስቶስን ሕይወት ያንጸባርቃል። የዮሴፍ ወንድሞች ወንድማቸውን እንዲሸጡ የገፋፋቸው ቅናት ነበር። እርሱ ከእነርሱ የበለጠ እንዳይሆን ለመከላከል ተስፋ አድርገው ነበር። ወደ ግብፅ በተወሰደ ጊዜ በእርሱ ምኞት እንደማይረበሹ በማመንና የእርሱ ምኞት የሚሳካበትን መንገድ በሙሉ እንደዘጉ በማሰብ ተደስተው ነበር። ነገር ግን እነርሱ የተከተሉት መንገድ ሊከላከሉት የፈለጉትን ክስተት ይፈጥር ዘንድ በእግዚአብሔር ተሻረ። የአይሁድ ቀሳውስትና ካኅናት በየሱስ የቀኑት የሕዝቡን ትኩረት ከእነርሱ መንጥቆ ወደ ራሱ ይወስድብናል በሚል ፍርሃት ነበር። እንዲሞት ያደረጉት ንጉሥ እንዳይሆን ለመከላከል አስበው ቢሆንም ያስገኙት ውጤት ግን የጠሉትን ነበር።

“ዮሴፍ ግብፅ ውስጥ በነበረው ሥልጣን ምክንያት ለአባቱ ቤተሰብ አዳኝ ሆነ። ነገር ግን ይህ እውነታ የወንድሞቹን የጥፋተኝነት ስሜት አልቀነሰውም። የሱስ በጠላቶቹ መሰቀሉ ሰብዓዊውን ፍጡር የሚዋጅ፣ በኃጢአት የወደቀውን ዘር የሚያድንና የዓለም ሁሉ ገዥ አደረገው። ነገር ግን ገዳዮቹ የፈጸሙት ወንጀል የሚታደገው የእግዚአብሔር እጅ ሁናቴውን ለራሱ ክብርና ለሰዎች መልካም ሲል ሊቆጣጠረው ያልቻለው ክፉ ድርጊት ይመስል ነበር።

“ዮሴፍ በገዛ ወንድሞቹ ለባርነት የተሸጠው ኃይማኖት ለሌላቸው ሰዎች ሲሆን ክርስቶስም ከደቀመዛሙርቱ በአንዱ አማካኝነት ለመራር ጠላቶቹ ተላልፎ ተሸጠ። ዮሴፍ ለመርኅ በመገዛቱ ምክንያት የሐሰት ውንጀላ ቀርቦበት ወደ እስር ቤት ተጥሎ ነበር። ክርስቶስ የተናቀውና ነቀፌታ የደረሰበት ጻድቅና እራስን የሚክድ ሕይወቱ ኃጢአትን በመገሰጹ ነበር። ምንም ዓይነት ስህተት ባይገኝበትም ነገር ግን በሐሰት ተመስክሮበት ጥፋተኛ ተባለ። ዮሴፍ በፍትህ ማጣትና ጭቆና ስር ሆኖ ያሳየው ታጋሽነት፣ ታዛዥነት፣ ይቅር ባይነትና በጨካኝ ወንድሞቹ ላይ ያሳየው ርኅራኄ--ክፉዎች አዳኙ ላይ ጭካኔና በደል ሲያደርሱበት ያሳየው ይቅርታ ለገዳዮቹ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ወደ እርሱ በመቅረብ ኃጢአታቸውን በመናዘዝ ይቅርታን ለሚለምኑት ሁሉ የሚሰጠውን ምህረት ያንጸባረቃል።”--ኤለን ጂ. ኋይት፤ የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፤ ገጽ፡ 268-269።


የመወያያ ጥያቄዎች



1.ያዕቆብ ከሞተ በኋላ የዮሴፍ ወንድሞች አሁን ሊበቀለን ይችላል የሚል ስጋት አድሮባቸው ነበር። ይህ እስከዚህ ወቅት ድረስ ጠብቀው የያዙት ጉዳይ ስለ ጥፋተኝነት ስሜት ምን ያስተምረናል? የዮሴፍ ምላሽ ስለ በደል ይቅርታ ምን ያስተምረናል?

2.በዮሴፍና በየሱስ ሕይወት መካከል ምን ሌላ ተመሳሳይ ነጥቦች ማግኘት ይችላሉ?

3.ምንም እንኳ እግዚአብሔር የወደፊቱን በቅርብ የሚያውቅ ቢሆንም፣ ምርጫዎቻችንን አስመልክቶ አሁንም ነጻ ነን። እነዚህን ሁለት ጽንሰ ሀሳቦች እንዴት እናስታርቃቸዋለን?




መግቦት- የእግዚአብሔርን የፍጥረት መጋቢነት (Providence) ለመግለጽ ከ1993 አዲሱ መደበኛ ትርጉም መግቢያ ላይ የተወሰደ

የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት መምሪያ የትንቢት መንፈስ መጻሕፍትን ተርጉሞና አሳትሞ ማሰራጨት ለሚፈልጉ የተደራጁ ቤተክርስቲያናት ሆነ ፈቃድ ያላቸው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች የተሠጠ ማሳሰቢያ

የትንቢት መንፈስ ( Spirit of Prophecy - SOP) መጻሕፍት በሙሉ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት አለም አቀፍ ቤተክርስቲያን ንብረት ናቸው፡፡ እነዚህን ጽሁፎች በከፊልም ሆነ በሙሉ ወደ አማርኛም ሆነ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች በማስተርጎምና በማሳተም ለማዳረስ የሚፈልግ የተደራጀ ቤተክርስቲያንም ሆነ በዋናው መስሪያ ቤት ፈቃድ ያለው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች ሥራውን ከመጀመሩ በፊት የኢትዮጵያ ዩኒየን ሚሽን በበላይነት በሚያስተዳድራቸው ሰበካዎችና ኮንፍራንስ የጽሁፍ ክፍል ጥያቄውን በጽሑፍ በማቅረብና በአካልም ቀርቦ በመወያየት ወደ ሰምምነት ከተደረሰ በኋላ እንዲያስተረጉም ፈቃድ ይሰጠዋል ትርጉሙም ሲጠናቀቅ የመጽሐፉን የመጀመሪያ ገጽ በታተመ ወረቀትና ሙሉውን መጽሐፍ በሲዲ ካስረከበ በኋላ ህትመቱና ስርጭቱ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ተከናውኖ ሥራውን መፈፀም ይቻላል፡፡

በዚሁ መሠረት የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን በማሳተም ወንጌልን ለማዳረስ የሚጥሩ የተደራጁ ቤተክርስቲያናት ሆነ ፈቃድ ያላቸው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች በእጅጉ ይበረታታሉ፡፡

ሆኖም ግን ይህንን በመተላለፍ ያለ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ፈቃድ በቤተክርስቲያኗ ስም የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን አሳትሞ ማስራጨት፣ በአገሪቱም ሆነ በዓለም ዓቀፍ የሥነ ጽሁፍ ህግ ያስጠይቃል፡፡ በተጨማሪም ድርጅቱ እያስተረጎመ ያለውን መጽሐፍ ሌላ አካል ተመሳሳዩን መጽሐፍ በመተርጎም ላልተፈለገ የጊዜ፣ የጉልበትና የገንዘብ ወጪም ይዳርጋል፡፡ ሰለሆነም የቤተክርስቲያኗ ህግና መተዳደሪያ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት ሁላችንም ጽሁፎችን በማሳተምም ሆነ በማሰራጨት የሶስቱን መላዕክት መልዕክት ለማዳረስ እንድንችል ጌታ ይርዳን፡፡

ድርጅቱ




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL